ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የሕዳሴ ግድብ ሙሌት በዓመታዊ የውሃ ፍሰት ላይ ምንም ተጽእኖ እነዳማያመጣ የቀድሞው የሱዳን የውኃ እና መስኖ ሚኒስትር ምስክርነት ሰጡ!!

የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ጌዲዮን የግብጹን ተከራካሪ –  የግብጽ ተከራካሪ አገራቸውን የፈረመችውን ስምምነት እንኳን በቅጡ የማያውቁ መሆናቸውን በማመልከት እርጋታ በተሞላው አንደበት መሳቂያ አደረጓቸው!! 
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵ፣ የሱዳን እና የግብጽ ተወካዮች ትናንት በአልጀዚራ ቴሌቪዥን ተከራክረዋል፡፡ በክርከሩ የግብጽ ተወካይ እብሪት የተሞላበት የወይይቱን መርህ የለቀቀ አስተያየት በኢትዮጵያው ወኪል አግባብ ያለው ምላሽ የተሰጠበት ሲሆን፣ የሱዳኑ ወኪል ታላቅ ምስክርነት ሰጥተዋል።
በክርክሩ የተሳተፉትም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የቴክኒክ ኮሚቴ ተወካይ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው፣ የቀድሞው የሱዳን የውኃ እና መስኖ ሚኒስትር ኦስማን ኢል ቶም እና የግብጽ የፖለቲካ ተንታኝ እና ተመራማሪ ማክ ሻርካዊ ናቸው፡፡ አልጀዚራ በዘገባ መነሻው ግድቡ ሚሊዮኖችን ከጨለማ ሕይወት እንደሚያወጣ እና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር እንደሚቀይረው ስለመታመኑ አሳይቷል፡፡
ኢንጂነር ጌዲዮን ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ውጥን ሀሳብ ካነሳችበት ጊዜ ጀምሮ ለተፋሰሱ ሀገራት እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጸኝነት እየሠራች መሆኑን አንስተዋል፡፡ በተለይም ለሦስቱ ሀገራት ከአጠቃላይ የግድቡ ዲዛይን ጀምሮ የግንባታ ሂደቱ ምን እንደሚመስል ግልጽነትን መፍጠሯን አስገንዝበዋል፡፡ የግድቡን የውኃ አሞላል እና አለቃቀቅ በተመለከተም በቀጣናው ባልተለመደ መልኩ መተማመን ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያ ከበቂ በላይ መሥራቷን ነው ኢንጂነር ጌዲዮን ያስረዱት፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ግድቡን በሁለት እና በሦስት ዓመታት ሞልታ ማጠናቀቅ ብትችልም ሌሎች የተፋሰሱን ሀገራት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሙሌቱን ጊዜ ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ማራዘሟንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን የምታደርገውም ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ካላት ተቆርቋሪነት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ሙሌቱን የምታከናውነው ደግሞ ከወንዙ ዓመታዊ የፍሰት መጠን ላይ 10 በመቶውን ብቻ በመጠቀም መሆነቡንም አስታውቀዋል፡፡ የሀገራቱ ስጋት መሠረት የሌለው መሆኑን ያስረዱት ኢንጂነር ጌዲዮን በተለይ ግብጽ ቀደም ባሉት ጊዜያት ግድቦችን ስትሠራ ኢትዮጵያ እንዳከበረች ሁሉ ሀገራቱ የኢትዮጵያን ፍላጎት ሊያከብሩላት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የግብጹ የፖለቲካ ተንታኝ እና ተመራማሪ ማክ ሻርካዊ በበኩላቸው ሀገራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በሚሠራው ሥራ እምነት እንደሌላት ተናግረዋል፡፡ ግብጽ በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች እና ህጎች እንደምታምን የተናገሩት ተንታኙ ግብጽ የችግሮችን 90 በመቶ ይፈታል ብላ ያመነችበትን የዋሽንግተኑን ስምምነት ኢትዮጵያ ማቋረጧ ተገቢ እንዳልነበረ አንስተዋል፡፡ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን ኢትዮጵያ አልተቀበለችም የሚል መከራከሪያም አንስተዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የመርህ ስምምነቱን በመጣስ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት የምታደርስ አስመስለውም ተናግረዋል፡፡ ከአጀንዳው በመውጣትም ሌሎች የተፋሰሱን ሀገራት ስም በመጥራት ተቆርቋሪ ለመምሰል ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡
የሱዳኑ ወካይ በበኩላቸው ውሃው ለኤሌክትሪክ ማመንጫ የተሠራ እስከሆነ ድረስ በዓመታዊ የውሃ ፍሰት መጠን ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡ እንዲያውም የግድቡ መገንባት በየዓመቱ በሱዳን ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመቆጣጠር እና በዘላቂነት የኤሌክትሪክ እጥረቷን ለመቅረፍ እንደሚጠቅማትም አረጋግጠዋል፡፡ የውኃ ሙሌቱ አጀማመር መከራከሪያ ሊሆን እንደማይገባው የተናገሩት የሱዳኑ ተከራካሪ ሁለቱ ሀገራት ጉዳዩን ከሚገባው በላይ እያከረሩት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይቶች ከ 90 እስከ95 በመቶ ሚሆኑ የቴክኒካዊ ጉዳዮች ስምምነት እንደተደረሰባቸው አመላክተዋል፡፡ ቀጣይ የተለያዩ ውይይቶች በማድረግ ልዩነቶችን ማጥበብ እንደሚቻል ያነሱት የሱዳን የቀድሞ የውኃ እና መስኖ ሚኒስትሩ ለዚህም ወደሌላ ርቆ መሄድ አስፈላጊ እንዳልሆነ መክረዋል፡፡ ከግድቡ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት እና በአፍሪካ ኅብረት፣ እንዲሁም በሦስቱ ሀገራት የቴከኒክ ቡድን አማካኝነት መፍታት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
ኢንጂነር ጌዲዮን በሰጡት ማብራሪያ በግብጽ በኩል የቀረቡት ግለሰብ በጉዳዩ በቂ እውቀት የሌላቸው፣ በምክንያት የማያምኑ እና ያነሱት የመወያያ ሀሳብም ውኃ የማያነሳ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ምእራፍ የውኃ ሙሌት ሥራ ትጀምራለች፡፡ በአንድ ዓመት የመጀመሪያዎቹን ሁለት ተርባይኖች ትሞክራለች፡፡ በቀጣዮቹ አምስት እና ስድስት ዓመታት ደግሞ ቀሪ ተርባይኖች እንደሚሞከሩ ኢንጂነር ጌዲዮን አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብቷል መባሉ ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመግለጽም ይህን እያደረጉ ያሉት የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ በ2015 (እ.አ.አ) የመርህ ስምምነት መሠረት እንዲፈታ ግልጽ አቋም እንዳላትም ኢንጂነር ጌዲዮን አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ መንገዶች በኢትዮጵያ በኩል አስፈላጊ እንዳልሆኑም አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵ ግድቡን በሰባት ዓመታት ውስጥ ሞልታ እንደምታጠናቅቅም ነው ያስረዱት፡፡
በደጀኔ በቀለ
Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ