ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ፖሊስ ሰላሳ አምስት ሰዎችን መያዙን ይፋ አደረገ

የአርቲስት ሃጫሉን አስከሬን ወዳጅ ዘመዶች አጅበው ወደ አምቦ በሚወስዱበት ወቅት ቡራዩ ላይ ጠብቀው በሃይል በመንጠቅና በራሳቸው ተሽከርካሪ ባማጓጓዝ በኦሮሚያ የብልጽግና ፓርቲ ቢሮ አሳርፈዋል፣ በጥበቃ ላይ ያለ የኦሮሚያ ፖሊስ አባል ገድለዋል በሚል የተወነጀሉ ሰላሳ አምስት ሰዎች መታሰራቸውን ፖሊስ አስታወቀ። ድርጊቱን የፈጸሙት አካላት በአቶ ጃዋር መሀመድ የሚመሩ እንደሆነም ተጠቆመ። እስሩ አቶ ጁሃርና አቶ በቀለ ገርባን ያካተተ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

Related stories   የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲራዘም ያቀረቡት ጥሪ ብልህነት የጎደለው እጅግ አደገኛ ነው - ሎረንስ ፍሪማን

በሌላ ተመሳሳይ ዜና በአዳማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ አምስት ሰዎች በጥይት ተመትተው መሞታቸው ይፋ ሆኗል።  75 ሰዎች ቆስለው በሆስፒታሉ እንደሚገኙና  በእሳት ቃጠሎ የተጎዱና የቆሰሉ አስራ ዘጠኝ ሰዎች ከአርሲ ለህክምና ሆስፒታል መድረሳቸውም ታውቋል። በዚሁ ተቃውሞ የመንግሥት ህንጻዎች መቃጠላውን መንግስት አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ሶስት ስፍራዎች ፈንጂ የፈነዳ ሲሆን የጉዳቱ መተን ይፋ አልሆነም። ይሁን እንጂ ከተማዋ አንጻራዊ ስለም ማሳየቷን ነዋሪዎች በስጋት መንፈስ ሆነው አመልክተዋል። የተለያዩ የኦሮሞ አክቲቪስት በትግራይ ሚዲያ ሃውስና በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች የበቀል ጥሪ እያቀረቡ ሲሆን በሌላ በኩል ” ድራማውን እንረዳና እንረጋጋ” በሚል እየወተወቱ ያሉም አሉ።

Related stories   አየር ሃይል " ትዕግስትም ልክ አለው" ሲል ለሱዳን ምክረ ሃሳብ ሰጠ

ሲፒጄ ለምን ኢንተርኔት ተዘጋ ሲል ቁጣውን አሰምቷል። የአምነስቲ በበኩሉ ለማረጋጋት የሚወሰዱ እርምጃዎች ጉዳታቸው የከፋ እንዳይሆን ምክር ለግሰዋል። የሲፒጄ መግለጫ በርካቶችን አስገርሟል። ከስር [ፖሊስ የሰጠውን መግለጫ ቢቢሲ እንደወረደ ያቀረበው ነው።

ጃዋር መሐመድ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል የሆነው ጃዋር መሐመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ የፌደራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሸን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽንር ጀነራል እንደሻው ጣሰው በዛሬው ዕለት ማክሰኞ ምሽት በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በሰጡት መግለጫ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 35 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በሰጡት በዚህ መግለጫ ላይ የጃዋር ጠባቂዎች ይዘውት የነበረው የጦር መሳሪያዎች እና መገናኛ ሬዲዮችም መያዛቸውን አመልክተዋል።

በዚህም መሰረት 8 ክላሽ፣ 5 ሽጉጥ እና 9 የሬዲዮ መገናኛዎች ከጃዋር ጠባቂዎች ላይ ፖሊስ መያዙን ተገልጿል።

ቀን ላይ ቀደም ሲል በጃዋር መሐመድ ዋና ዳይሬክተርነት ይመራ የነበረው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጃዋርና ሌሎች ሰዎች በፖሊስ መያዛቸውን የዘገበ ቢሆንም ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ ሳይሰጥ ቆይቶ ነበር።

ነገር ግን ምሽት ላይ የኦሮሚያና የፌደራል ፖሊስ እንዳስታወቁት ጃዋር መሐመድ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ተገልጿል።

በመግለጫው ላይ “ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም” ያሉት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራሉ “ሕግ ለማስከበር የጸጥታ አካል በሚወስደው እርምጃ ሁሉም ሰው ተባባሪ መሆን አለበት” ብለዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም “አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍል በተሳሳተ አረዳድ እነዚህ ሰዎች የታሰሩበት ሁኔታ ትክክል አይደለም ብሎ በተለያየ መንገድ ተሰልፎ ዳግም ጥፋት እንዳያጠፋ አስፈላጊውን ማሳሰቢያ ፖሊስ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ስለጉዳዩ ፖሊስ በየጊዜው የሚደርስበትን መረጃ በደንብ አጠናክሮና አደራጅቶ ለኅብረተሰቡ የሚያሳውቅ መሆኑን ኮሚሽነር ጄነራሉ እንደሻው ጣሰው ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አራርሳ መርዳሳ በበኩላቸው “በጃዋር መሐመድ የሚመራው ቡድን የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ወደ አምቦ እንዳይሄድ አድርጓል” ብለዋል።

ኮሚሽነሩ “በጃዋር መሐመድ የሚመራው ቡድን አስክሬኑ በቤተሰቡ ጥያቄ መሰረት ከጳውሎስ ሆስፒታል ወጥቶ ወደ አምቦ እየተሸኘ ሳለ፤ ከቤተሰቡ ፍቃድ ውጪ ቡራዩ ሲደርስ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ አደርጓል” ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም አስክሬኑ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽህፈት ቤት ውስጥ እንዲገባ እንደተደረገ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላም “በኃይል ሰብረው በመግባት በጥበቃ ላይ የነበረ የኦሮሚያ ፖሊስ በጥይት በመምታት ገድለዋል። አስክሬኑን ካስገቡ በኋላም አስክሬኑን ይዞ ለማቆየት ጥረት ተደርጓል” ሲሉ ገልጸዋል።

በጸጥታ ኃይሉ ግድያ እና አስክሬኑ ወደ ቤተሰብ እንዳይሄድ በመከልከል አቶ ጃዋርን ጨምሮ በዚህ ውስጥ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ወደ 35 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አመልክተዋል።

የፖሊስ ኃላፊዎቹ በአጠቃላይ 35 ሰዎች መያዛቸውን ይግለጹ እንጂ ከጃዋር መሐመድ ውጪ የሌሎቹን ማንነት እንዲሁም ቀጣይ ዝርዝር ሁኔታዎች አልገለጹም።