በአገሪቱ ከተቋረጠ ቀናት የተቆጠሩት የኢንትርኔት አገልግሎት በቀጣይ ሳምንት ሊመለስ እንደሚችል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የሆኑት ቢልለኔ ስዩም ለቢቢሲ ኒውስዴይ ተናገሩ።

ቢልለኔ እንዳሉት የኢንተርኔት አገልግሎት የብሔር ጥላቻን ለማስፋፋት ጥቅም ላይ በመዋሉ መንግሥት አገሪቱንና ሕዝቡን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ለማቋረጥ መገደዱን ተናግረዋል።

ኢንተርኔት መቼ ይለቀቃል ተብለው ሲጠየቁ ነገሮች ወደ ቀደመው ሁኔታ እየተመለሱ መሆኑን ገልጸው በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል።

ቃል አቀባይዋ ለኒውስዴይ እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባም ሆነ በኦሮሚያ ውስጥ ሁኔታዎች ወደ ቀደሞው መረጋጋታቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ቢልለኔ ስዩም የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ግጭት 80 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋው፤ አንዳንድ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በማስተጓጎል ችግር ለመፍጠር ቢሞክሩም ፖሊስ ግን በሰዎች ላይ አልተኮሰም ብለዋል።

ጨምረውም ካለመረጋጋት ታሪክ ውስጥ እየወጣች ያለችውን አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ዲሞክራሲ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጽ ከጥቂት ዓመታት በፊት የማይቻል የነበረው በአሁኑ ሰዓት በርካታ ወገኖች ድምጻቸውን ማሰማት ችለዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ከሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ ሰሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት ቃል አቀባይዋ፤ ነገር ግን ጉዳዩ በምርመራ ላይ ያለ በመሆኑ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዲስ አበባ ቢሯቸውን ከፍተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታወቋል።

እነዚህም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አስራት፣ ድምጺ ወያኔ እንዲሁም ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ሲሆኑ ኦኤምኤን የአዲስ አበባ ቢሮው መዘጋቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እንዳለው ለድምጺ ወያኔ እና ለትግራይ ቲቪ ጠንከር ያለ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን ገልጿል።

ቢቢሲ ስማቸው ከተጠቀሱት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከእራሳቸው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እየሞከረ ቢሆንም እስካሁን አልተሳካም። ምላሻቸውን ለማግኘት ጥረታችን ይቀጥላል።

የድምጺ ወያኔ ዋና ቢሮ መቀሌ የሚገኝ ሲሆን አስራትና ኦኤምኤን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ ዋና ስቱዲዮዋቸው በአሜሪካ መሆኑ ይታወቃል።

በትናንትናው ዕለት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በሰጡት መግለጫ የከተማ አስተዳደሩ ከጥምር የፀጥታ ኃይል ጋር በመሆን የከተማዋን ሰላምና ሥርዓት ማስከበር መጀመሩንም ተናግረው ነበር።

“ማናችንም ብንሆን ከአገር በታች ነን፣ ከሕግ በታች ነን” በማለት አገርንና ትውልድን ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ጠቅሰው፤ አገር የማስተዳደር ሂደትን ለማደናቀፍ የሚሞክር የትኛውም አካልን “ትዕግስት ልክ አለው” በማለት “ከዚህ በኋላ በየትኛውም ሚዲያ፤ በየትኛውም ጽሁፍ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ፤ ግለሰብን ማዕከል ያደረገ፤ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የጥላቻ፤ የፕሮፖጋንዳ ሥራ አንታገስም” ማለታቸው ይታወሳል።

ሲፒጄ በበኩሉ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ መዘጋቱ ከተሰማ በኋላ ባወጣው መግለጫ “የመንግሥት ባለስልጣናት በአስቸኳይ ኢንተርኔቱን እንዲመልሱት” ጠይቆ ነበር።

@BBC Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *