“Our true nationality is mankind.”H.G.

አንድነታችን፣ ሰላማችን እና ሉዓላዊነታችን ላይ የተቃጣውን ጥቃት ስክነት በተሞላበት የኃላፊነት መንፈስ በአንድነት ቆመን እንመክት !- ኢዜማ

የኢዜማ መግለጫ !
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባላት እና አመራሮች በታዋቂው እና ተወዳጁ የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ እና የሙዚቃ ደራሲ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል። ሃጫሉ የጥበብ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን ችሎታውን ተጠቅሞ ብዙዎችን ለእኩልነት ትግል ያነሳሳ፤ እራሱም አምባገነናዊ ሥርዓትን በድፍረት ፊት ለፊት የተጋፈጠ ጀግና የሀገራችን ልጅ ነበር። ሃጫሉ ለወገኑ እና ለሀገሩ ብዙ መሥራት በሚችልበት የወጣትነት ዕድሜው በእኩይ ኃይሎች ሕይወቱን መነጠቁ ሀዘናችንን እጅግ የከፋ አድርጎታል።
በዚህ ጀግና ወንድማችን ሞት ሀዘን ውስጥ እንደሆንን በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ሆን ብለው ረብሻ ባስነሱ ኃይሎች የዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ አውቀናል። እስካሁን ድረስ ቢያንስ 91 ዜጎች ረብሻ ባስነሱ ኃይሎች ሕይወታቸውን እንደተነጠቁ እና ብዙ ዜጎች በተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተረጋግጧል። ይህ ሀዘናችንን እጥፍ ድርብ እና መራር አድርጎታል። ረብሻ ያስነሱት ኃይሎች በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ (የአዳማ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ)፣ የፖለቲካ ፓርቲ ጽሕፈት ቤቶች፣ የዕምነት ተቋማት፣ የንግድ ቤቶች እና የግል መኖሪያ ቤቶች ላይ ውድመት አድርሰዋል።
በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ እና ሌሎች ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያ ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ፈጽሞ የምናወግዘው እና ከዚህ በኋላ በፍጹም እንደማይደገም ማረጋገጥ ያለብን የጭካኔ ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባላት እና አመራሮች ሕይወታቸውን ላጡ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ቤተሰቦች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልባዊ መጽናናትን እንመኛለን።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እጅግ ተደራራቢ ጫና ውስጥ ትገኛለች። በዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ የሚያዙ እና ሕይወታቸውን የሚያጡ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መጥቷል።
የሉዓላዊነታችን እና ከእኛም አልፎ የአካባቢያችን ሀገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን ካዘለው ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እየተፈጠረብን ይገኛል። ከግድቡ ግንባታ ሂደት ጋር ተያይዞ የግብጽ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥ በመፍጠር ከግድቡ ግንባታ ሥራ እንዴት ሊያደናቅፉን እንደሚችሉ በአደባባይ ሲዝቱ እንደነበር የሚታወስ ነው። ባለፉት ሦስት ቀናት በሀገራች የታየው ሁኔታ ድንገት የተከሰተ ሳይሆን ሆን ተብሎ ታቅዶበት እና በጥፋት ኃይሎች የተቀነባበረ እንደሆነ በቂ ምልክቶች አሉ።
ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን አጠናክረን የሁላችንንም ደህንነት እና የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር መቆም በሚገባን በዚህ ሰዓት የኢትዮጵያን መረጋጋት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ማየት የማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎች ወጥመድ ውስጥ ላለመግባት ሁላችንም ከፍተኛ መረጋጋት ያስፈልገናል። ይህን አንድነታችን፣ ሰላማችን እና ሉዓላዊነታችን ላይ የተቃጣ ጥቃት በተረጋጋ እና ስክነት በተሞላበት የኃላፊነት መንፈስ በአንድነት በመቆም እንድንመክት የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የምንገኝበትን ዘመን እና ያጋጠሙንን ችግሮች የሚመጥኑ የመፍትሄ ሀሳቦችን አመንጭተን በውይይት ልዩነቶቻችንን መፍታት እንጂ በጉልበት ፍላጎትን ለመጫን መሞከር ከዚህ በፊት ደጋግመን ሞክረን ደጋግመን ወደወደቅንበት የግጭት አዙሪት ከመክተት ያለፈ ውጤት እንደማይኖረው በቂ ማስረጃዎች አይተናል። የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሀገራችን መረጋጋት እና የአንድነታችን ቀጣይነትን ማረጋገጫ ብቸኛ የማዕዘን ድንጋይ እንደሆኑ ልንረዳ ይገባል።
ይህንን በመረዳት ሁላችንም በደረሰው የዜጎች ሕይወት መጥፋት መሪር ሀዘን ቢሰማንም ከዚህ በላይ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ የሚፈጥሩ አደጋዎችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት እና ማንኛውም ዓይነት ግጭቶችን ለማስወገድ ማድረግ ያለብንን ሁሉ እንድናደርግ፤ እንዲሁም ሁኔታዎች ከአቅም በላይ ሊሆኑ የሚችሉ ከሆነ ከፖሊስ እና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ከተሰማሩ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ለሀገር መረጋጋት የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ እንጠይቃለን።
መንግሥት ሕግ እና ሥርዓትን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እና ከምንም ነገር ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስከብር እና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ እንዲሁም ከዚህ በፊት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እና የዜጎች ሕይወትን የቀጠፉ እና አሁንም ተመሣሣይ ጥፋት የፈጸሙ ኃይሎችን በአፋጣኝ ለሕግ በማቅረብ ከአሁን በኋላ በሀገር አንድነት እና በዜጎች ደህንነት ላይ አደጋ የሚደቅኑ ኃይሎችን በፍፁም እንደማይታገስ እንዲያረጋግጥ እናሳስባለን።
የሀገር አንድነት እና የዜጎች ደህንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የማይተው የሁላችንም የጋራ ኃላፊነታችን እንደሆነ በመገንዘብ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚጠበቅብንን ገንቢ ሚና እንድንጫወት እየጠየቅን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባላት እና አመራሮች የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ እንደሆንን ለማስገንዘብ እንወዳለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ሰኔ 26 ቀን 2012 ዓ.ም

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣
0Shares
0