ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ኢትዮጵያ፣ የሠላም ዋጋዉ ምንድነዉ? ስንትስ ነዉ?

የተወዳጁ ድምፃዊ መገደልና መዘዙ ጋጠወጦችን ለፌስ ቡክ ስድብ-ዉግዘት እርግማን «ሻምፒዮንነት» ሲያሽቀዳድም፣ አዉሮጳና አሜሪካ ተሻግሮ ለንደን፣ ፍራንክፈርት፣ ዋሽግተንና  ሚኒያፖሊስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን እያጋጨ፣ በአደባባይ  ሲያስጮኽ፣ሳምንቱ ሔዶ ሌላ ሳምንት፣ ምናልባትም የሌላ ግድያ፣ ሁከት፣ ዉዝግብ ሳምንት መጣ።

ሐጫሉ ሁንዴሳ ተገደለ።ሰኞ።እንደ ሐጫሉ ሁሉ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ሲታገሉ በአሸባሪነት ተከሰዉ የታሰሩ፣ በአሸባሪነት ተወንጅለዉ በሌሉበት ተፈርዶባቸዉ የነበሩም ፖለቲከኞችም እንደገና ታሰሩ።አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ እንደ ብዙዉ የቅርብ ዘመን ታሪኩ ሁሉ ሟቹን ቀብሮ፣ ቁስለኛዉን አክሞ፣ የጠፋ ሐብት ንብረቱን አስልቶ ከሐዘን፣ትካዜዉ ሳይላቀቅ የሐጫሉ አጎትን ጨምሮ በትንሽ ግምት 166 ሰዎች ተገደሉ።ብዙ መቶዎች ቆሰሉ።ታሰሩም።ኢትዮጵያ ሰላም እየተዘመረባት ጦርነት ሲወርድባት፣ ምርጫ እያስተናገደች ሁከት  ሲያናጥርባት፣ ለዉጥ እየታወጀባት ሽብር ሲነዉጣት፣ዘመን ሸኝታ ዘመን ተቀበለች።የሰላም ግብሩ ምድነዉ? ስንትስ ነዉ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል፣ የዜጎችዋ መገደል፣መፈናቀል፣ መራብ፣ መቸገር ዉድመት ጥፋቷ የዓመት ዑደት መርገምት የመሰላቸዉ አንድ አድማጭ «ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ሲባል እስማለሁ» አሉ ሰሞኑን ።«መቼ ነዉ የምትዘረጋዉ—-ዘርግታ ከሆነስ—-» እያሉ ጠየቁም።

እኔም አልገባኝም።የኢትዮጵያ እዉነታ ከአብዛኛ ዜጎችዋ ተስፋ፣ የአብዛኛ ፖለቲከኞችዋ እርምጃ እንመራሐለን ከሚሉት ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት መቃረኑን ለማወቅ ግን ጠያቂም-መላሽም ተንታኝም- አያስፈልግም።
ግራ-የገባቸዉ አድማጭ መልስ አልባ ጥያቄ በደረሰን ሳምንት ድምፃዊ ሐጫሉ በሰዉ እጅ ተገደለ።ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣የፖለቲካ ቀንቃኞች፣ ጋዜጠኞች ታሰሩ።ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ መንገዶች፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ሁሉም ተዘጋ።ከአንቦ እስከ ሮቤ፣ ከድሬዳዋ እስከ ነገሌ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ሐረር፣ ከጭሮ እስከ ጊምቢ ሰዎች ይገደሉ፣ ሐብት ንብረታቸዉ ይዘረፍ፣ ይጋይ ገባ።የሰብአዊ መብት አጥኚዉ ያሬድ ኃይለ ማርያም እንደሚሉት አንዳድ ስፍራ የተፈፀመዉ ግድያ የተጠና የሚመስል ነዉ።

የተወዳጁ ድምፃዊ መገደልና መዘዙ ጋጠወጦችን ለፌስ ቡክ ስድብ-ዉግዘት እርግማን «ሻምፒዮንነት» ሲያሽቀዳድም፣ አዉሮጳና አሜሪካ ተሻግሮ ለንደን፣ ፍራንክፈርት፣ ዋሽግተንና  ሚኒያፖሊስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን እያጋጨ፣ በአደባባይ  ሲያስጮኽ፣ሳምንቱ ሔዶ ሌላ ሳምንት፣ ምናልባትም የሌላ ግድያ፣ ሁከት፣ ዉዝግብ ሳምንት መጣ።
ኢትዮጵያ-ባጠቃላይ ሰሞኑን ደግሞ ኦሮሚያ-በተለይ ከጠብ፣ ግድያ፣ግጭት፣ እስራት ስደት ሌላ-ሌላ እንዳያዉቁ የመገደዳቸዉ ሰበብ ምክንያት በርካታ ወቅታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣  ምጣኔ ሐብታዊ ከሁሉም በላይ ፖለቲካዊ እዉነታዎችን የሚያማዝዝ፣ ብዙ አነጋጋሪም ነዉ።ዶክተር ሐዩ ቱለማ በየነ ሰንበቱ ሮሚ ግን አንድ ነገር ይላሉ «ሰሚ ጠፋ»

ዝነኛዉ ደቡብ አፍሪቃዊዉ የጥቁሮች መብት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ «ሰላም ማንኛዉም ሰዉ ሊኖረዉ የሚገባዉ የዕድገት ወይም የልማት መሳሪያ ነዉ» ማለታቸዉን የሚያዉቋቸዉ ደጋግመዉ ይጠቅሱታል። ማንዴላ ለሕዝባቸዉ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዉ መብት መከበር ያደረጉትን ትግልና አስተምሕሮቱን ለመዘከር የዓለም መሪዎች ከጎርጎሪያኑ 2019 እስከ 2018 ያለዉን 10 ዓመት «የኔልሰን ማንዴላ የሰላም አስርት» ብለዉ ሰይመዉታል።
ማንዴላና የአስተምሕሮታቸዉ እንዲዘከር የወሰኑት እንደ ጎርጎርጎሪያኑ አቆጣጠር መስከረም 24 2018 በተሰየመዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ  ጉባኤ ላይ የተካፈሉ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሐገራት መሪዎችና ተወካዮች ናቸዉ።
ማንዴላ ለሰላምና ለሰብአዊነት ያበረከቱት  አስተዋፅዖ ኒዮርክ ላይ ከመዘከሩ ከአራት ወር በፊት የአዲስ አበባና ያካባቢዉ ሕዝብ አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር ለማመስገን አደባባይ ወጥቶ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ አመስጋኝ ሕዝባቸዉን ለማመስገን አደባባይ ሲወጡ የማንዴላ ምስል የተለጠፈበት ቲ ሸርት ለብሰዉ ነበር።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የቲ ሸርት መልዕክት፣ ዓለም ማንዴላን በሚወነጅልበት በዚያ በሩቁ የመከራ ዘመን፣ ማንዴላን የረዳችና ያስተማረችዉ ኢትዮጵያ፣የማንዴላን የሰላም፣የሰብአዊነትና የእኩልነት ተጋድሎ ለመዘከርም ዓለም አቀፉ ድርጅት እስኪወስን አለመጠበቋን የሚያረጋግጥ በሆነ ነበር።ለኢትዮጵያዉያን ታሪካዊ ኩራት።የአዲስ አበባና አካባቢዉ  ሕዝብ ምናልባት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈቃዱና ፍላጎቱ መሪዉን ባደባባይ ሰልፍ አመስግኖ፣ አድንቆ፣ አወድሶ ሳያበቃ ግን ሕዝቡም-መሪዉም በቦምብ ፍንዳታ መሸበራቸዉ ነዉ አሳዛኙ ቁጭት-ቅጭት።
ዶክተር ሐዩ ቱለማ በየነ ሰንበቱ ሮሚ እንደ ሐገር ሽማግሌ ዛሬም ይመክራሉ።

ባለፉት 40ና ሐምሳ ዓመታት የተፈራረቁት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ አቀንቃኞች እና ደጋፊዎቻቸዉ ሰላም፣ አንድነት፣ብልፅግናና ዕድገትን የሚሰብኩትን ያክል ተከታያቸዉን ለማገዳደል፣

Äthiopien Militär Pick-up Truck in Addis Abeba (Reuters/T. Negen)

ለማነጣጠል፣ ለማቂያቂያም፣ የሚያጣድፉበት፣ እንዲደመጡ የሚሽቱን ያክል ሌሎችን የማያደምጡበት ምክንያት በርግጥ ሊጠና-ሊተነተን ሊከለስ ይገባዋል።
በ1985 የኤርትራን ሕዝበ-ዉሳኔ ለመታዘብ (ከፈለጋችሁ ለማስፈፀም በሉት) አስመራ የነበሩ አንድ የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናንን የኤርትራን መገንጠል በግላቸዉ የሚደግፉበትን ምክንያት ጠይቄያቸዉ ነበር።
የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት (ደርግ) ባጭሩ ቀይ ኮኮብ ያለዉን ዘመቻ በከፈተበት በ1974 ግድም የሕወሓትን ጦር ይዘዉ ኤርትራ ዘምተዉ እንደነበር ነገሩኝ።«ተራራ ስንወጣ ከታች አስከሬን እየረገጥን—ካላይ አስከሬን ላይ እየተንጠላጠልል—ሲተኮስብን በአስከሬን እየተከለልን—እያሉ ቀጠሉ፣ ዘግናኛ ትዝታቸዉን ይከፍልላቸዉ ይመስል ሲጋራቸዉን በላይ በላዩ እየለኮሱ—የኤርትራን ነፃነት ከፓርቲያቸዉ አቋም እኩል  በግላቸዉ የደገፉት የጦርነትን ዘግናኝ እልቂት ስለተሳተፉበት፣እልቂቱን ለማስቀረት ነዉ።ሰዉዬዉ እንዳሉት።ዛሬም በሕይወት አሉ።
ኤርትራ «ለሰላም ሲባል» በይፋ ነፃ በወጣች በ5ኛ ዓመቱ ሁለቱ ሐገራት  በገጠሙት ጦርነት መቶ ሺ ወጣቶች መርገፋቸዉ እንጂ የሰላም ቃል፣ተስፋ፣የእምነት-ስብከታቸዉ ከንቱነት።
በ1997 የተደረገዉ ምርጫ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ለኢትዮጵያ የአስተማማኝ ሰላም መሠረት፣  የዴሞክራሲ ሥርዓት ጅምርም መስሎ ነበር።ሌላ ተስፋ። የዉጤቱ ዉዝግብ የመቶዎችን ሕይወት አጥፍቶ፣ የሺዎችን ደም አራጭቶ፣ ሺዎችን ወሕኒ ሲያስዶል ግን ተስፋዉ በንኖ ስቃይ ሰቆቃዉ  ነገሰ።
ከ1998 ጀምሮ የስቃይ፣ ሰቆቃ፣ አፈና ጭቆናዉን ልክ እያሰላ 2008 የደረሰዉ ሕዝብ ካመፅ ሌላ ምርጫ አልነበረዉ።አመፁ መጋቢት በ2010 በተስፋ ሰጪ ለዉጥ እስኪያሳርግ ድረስ ሺዎች፣ የኦሮሞ ፖለቲካ አቀንቃኞች እንደሚሉት ደግሞ፣ አምስት ሺሕ ወጣቶች ሕይወታቸዉን ገብረዋል።
በተስፋ ሰጪዉ ለዉጥ ስልጣን በያዙት በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ላይ በተቃጣ የግድያ ሙከራ የመጀመሪያዎቹ የለዉጥ ማግስት ሰለቦች አብዮት አደባባይ ወደቁ።

የዓለም መሪዎች፣ የማንዴላን ትግል ለመዝከር  ኒዮርክ ላይ ጉባኤ በተቀመጡበት ዕለት መስከረም 14 2011፣ ከብዙዎች ቀድማ ማንዴላን የደገፈችዉ፣ ከብዙዎች በላይ ሰላም የተጠማችዉ ኢትዮጵያ ቡራዩ ላይ በደም አበላ ትለቃለቅ ነበር።
ከቡራዩ ጭፍጫ፣ ሐጫሉ እስከተገደለበት ድረስ ለጎሰኞች፣ ለፅንፈኞች፣ ለጥቅም አጋባሾች፣ ለፖለቲከኞች የበላይነት ጥማት ርካታ፣ ከቅማንት እስከ ነገሌ ቦረና፣ ከጂጂጋ እስከ ራያ፣ ከናዝሬት እስከ ጌዲኦ፣ ከሐዋሳ እስከ ደምቢ ዶሎ፣ ከጉሙዝ እስከ አዲስ አበባ ብዙ ሺዎች ረግፋዋል።ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።በቢሊዮን የሚቆጠር ሐብት ንብረት ወድሟል።
ከአንድድ ሥፍራ የሚዘገበዉ ግድያ፣ዘረፋ፣ ቃጠሎ ዉድመት  በርግጥ የሰዉ ልጅ በሰዉ ልጅ ላይ ይፈፅመዋል ብሎ ለማሰብ የሚዘግነነን ነዉ።እንደገና ያሬድ ኃይለማርያም።

ለኢትጵያዉን የሰላም ዋጋዉ ምን  ይሆን? ግዛት? ሕይወት? ንብረት ስደት? አመፅ? የሥርዓት ለዉጥ? ኖቤል? ሐብት ንብረት? ደግሞስ ስንትና እስከ መቼስ ይሆን?
ኢትዮጵያዉያን ከ30 ዓመት ጦርነት በኋላ ትልቅ ግዛት ሰጥተዉ፣ በትንሽ ቀበሌ ሰበብ ከ60ሺ የሚበልጡወጣቶቻቸዉን ሕይወት ገብረዋል።

እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ በሰላም መርጠዉ፣ ለዉጤቱ ዉዝግብ መቶዎችን ሰዉተዋል። ከጆርጂያ እስከ ቱኒዚያ፣ ከግብፅ እስከ ዩክሬን እንደሆነዉ ለሥርዓት ለዉጥ ሲታገሉ ብዙ ሺዎች ወሕኒ ተወርዉረዉ፣ የሺዎችን ሕይወት ሰጥተዉ ከሚሹት ደርሰዋል።ከሚሽት በመድረሳቸዉ ሐሴት ፈንድቀዉ ሳያበቁ፣ ከጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እስከ ተራ ወታደር፣ ከብርጌድየር ጄኔራል እስከ ሚሊሺያ፣ ከርዕሰ መስተዳድር እስከ ወረዳ አስተዳዳሪ፣ ከታላቅ መሐንዲስ እስከ ዩኒቨርስቲ ተማሪ፣ ከገበሬ እስከ ከብት አርቢ ብዙ ሺዎችን ጭዳ አርገዋል።ሴቶ ወጣቶ ታግተዋል።
መሳጂዶች፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ ፋብሪካዎች፣ ሱቆች፣ ትምሕርት ቤቶች፣ መኪኖች አግይተዋል። ሐዉልቶች፣ ድልድዮች፣ መንገዶች ፈርሰዋል።የዚያኑ ያሕል መሪያቸዉን ለሰላም ኖቤል አብቅተዋልም።ኢትዮጵያ ግን ሰላም የለም።
ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድሕን በ1983 በተዘጋጀ አንድ የሐዘን ሥርዓት ላይ «ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ሰዉ ትወልዳለች፣ ግን አታሳዳግም ታቀጭጫለች።ትቀጫለች።» ብለዉም ነበር። ኢትዮጵያ በዘር ፖለቲካ ቀዉስ ስትዳክር ወጣቱ ድምፃዊ ሐጫሉ ሑንዴሳ ዘፍኖ፣ ጨፍሮ፣ ተናግሮ ሳይጠግብ-ሳይጠግብ ተቀጨ። ሁለት መቶ ያክል ሰዎችም ተገደሉ።ፖለቲከኞች ታሰሩ።መገናኛ ዘዴዎች ተዘጉ።እና የሰላም ዋጋዉ ስንት ይቀረዉ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ