አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የታቀደ ግድያ እንደተፈጸመበት የሚያመለክቱ ማስረጃዎች መገኘታቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
በአርቲስቱ ግድያ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ የነበሩ ሦስቱም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል።
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የአርቲስቱን ግድያና ግድያውን ተከትሎ በተፈጠረው ብጥብጥና ሁከት የተፈፀሙ ወንጀሎችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የድንበር ተሻጋሪና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ፀጋ በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ሰኔ 22 ቀን 2012 ምሽት ላይ በአርቲስቱ ላይ የተፈፀመውን የግድያ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ በፀጥታ መዋቅሩና በሕብረተሰቡ ትብብር በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተጠርጣሪዎች ላይ በተደረገ ምርመራም አርቲስቱ ሆን ተብሎ ግድያ እንደተፈጸመበት የሚያመላክቱ ማስረጃዎች መገኝታቸውን ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም በደረሰበት ምርመራ አርቲስቱ በተራ የእርስ በእርስ ፀብ አማካኝነት እንዳልተገደለ የሚያረጋግጥ ማስረጃ መገኝቱን ተናግረዋል።
“በተለይም አርቲስቱ ኦ.ኤም.ኤን ለተሰኝው መገናኛ ብዙሃን ቃለምልልስ ከሰጠ በኋላ በግልጽ ማስፈራሪያዎች ይደርስቱ እንደነበረም ለማረጋገጥ ተችሏል” ብለዋል ዳይሬክተሩ።
አርቲስት ሃጫሉ ከኦ.ኤም.ኤን ጋር በቅርቡ አድርጎት በነበረው ቃለምልልስ ከኦነግ ሸኔ በየጊዜው ማስፈራሪያዎች እየደረሱት መሆኑን የገለፀበት ክፍል ተቆርጦ እንዲወጣ መደረጉም ሌላ ጥርጣሬ መጫሩን ጠቁመዋል።
በእዚሁ የግድያ ወንጀል ላይ በቀጥታ ተጠርጣሪ የሆነው ግለሰብ ተልእኮውን ከሰጡት ሰዎች ጋር በገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ለሦስት ጊዜ እንደተገናኘና አርቲስቱን ለመገድል ገንዘብ መቀበሉን አቶ ፈቃዱ አመልክተዋል።
ተጠርጣሪው ወይም በአርቲስት ሃጫሉ ላይ ሽጉጡን የተኮሰው ግለሰብ ተልእኮውን መቀበሉን እንጂ ማንን እንደሚገድል በግልጽ እንዳልነገሩትም ነው ያስረዱት።
በአጠቃላይ እስካሁን የተካሄደው የምርመራ ሂደት የሚያሳየው ግለሰቡ ግድያ የተፈፀመበት ድንገት ሳይሆን በዓላማና በተልኮ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እየተገኙ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል።
“በተጨማሪም ግድያውን ተከትሎ የአርቲስቱ አስከሬን ከቤተሰቦቹ ፍላጎት ውጭ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ሲባል የተፈጠረውን ብጥብጥ የመሩ አቶ ጃዋር መሃመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ላይ አስፈላጊ መረጃዎች ተሰብስበዋል፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል።” ብለዋል።
የአቶ ጃዋር መሀመድ መኪና ውስጥ የነበረ ታጣቂ የአርቲስት ሃጫሉን አስከሬን ይዞ ሲጓዝ የነበረ መኪኒ አሽከርካሪ እንዲቆም ማስገደዱንና በኃይልና በጦር መሳሪያ ታግዞ አስክሬኑ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ማድረጉን ማስርጃዎች ተሰብስበዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ ሁከትና ግርግር ሲያስነሱ በነበሩ በነ አቶ እስክንድር ነጋ ላይም እንዲሁ ምርመራ መቀጠሉን አቶ ፈቃዱ ጠቁመዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ ” በበኩላቸው የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ ወንጀለኞትን ለመያዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል” ብለዋል።
“በቀጣይም መንግስት ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል” ያሉት ኮሚሽነሩ፣ አገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትንም ለሕግ የማቅረብ ተግባር እንደሚከናወን አስረድተዋል።
 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *