ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ስለ አስከሬን …

በባህላችን አስከሬን ይከበራል። የማያውቁት ሰው ቢሆን እንኳን፣ አስከሬን ሲያልፍ ኮፍያ ተወልቆ፣ በክብር ተቁሞ ነው የሚሸኘው። ሰውዬው ማን ሆነ፣ ከማን ነገድ ሆነ፣ ምን ዓይነት ታሪክ ኖረው፣ በምን ሞተ፣ በማን ተገደለ፣ ምን ዓይነት በደሎች ፈጸመ፣ ምን ዓይነት ገድሎች ነበሩት፣ ከእነ ማን ጋር ተቀያየመ… ወዘተ ቦታ የላቸውም። ሲሞት ሁሉም ሰው እኩል ነው።
እንግዲህ የራሱ እንዳይሆን ሞቷልና፣ በክብር ይሸኛል። “ካባ ልበስ ምንድን ነው? ሰርግ እና ሞት አንድ ነው” የሚል ዘፈን እየሰማን ያደግን፣ በዚያም እያበድን የኖርን ብንሆንም፥ ሰርገኛ እና ለቀስተኛ በአንድ መስመር የተገናኙ ቀን ግን፣ ሰርግ እና ሞት አንድ አለመሆኑ ይለያል። ሰርግ እና ሞት ይለያያሉ። የሟች አስከሬን የበለጠ ክብር ያገኛል። “ነግ በእኔ”ም ነው። ለዚህም ሰርገኞች ቆመው፣ አስከሬንን በክብር ዝቅ ብለው ያሳልፋሉ።
አሁንም ማንነቱ አይገዳቸውም። የትነቱ አያሳስባቸውም። የ1 ዓመት ጨቅላም ቢሆን፣ የመቶ ዓመት ዕድሜ ጠገብ፥ አስከሬን አስከሬን ነው። የተቀያየሙ ሰዎች ቢሆኑ እንኳን ለቅሶ ይደራረሳሉ። ያቃብራሉ። ያላቅሳሉ። ያራግዳሉ። ያመራግዳሉ። ያሟሻሉ። ያጽናናሉ። እንዲህ ነው የኖርነው። አስከሬን አይንገላታም። አገናነዙ እንኳን በክብር እና በፍጥነት ነው። የሞተበት ሰው ኀዘኑን ዋጥ አድርጎ ላረፈው ሰውነት ክብር ይሰጥ ዘንድ በአግባቡ ይገንዛል። አስከሬን እንዳይበላሽበት፣ ድረሱልኝ ብሎ ሰው ይጠራል።
እስኪ የአስከሬንን ትርጉም ምንጭ እንይ።
በአማርኛ ትርጓሜው፥ በልማድ “የሬሳ መቅበሪያ ሳጥን፣ መሸከሚያ ቃሬዛ፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው አፅም፣ የሞተ ሰው ስጋ” ብለን ብንፈታውም፣ “ሣጥን፣ ሙዳይ፣ የገንዘብ መክተቻ” የሚል ትርጓሜም አለው።
ግዕዙ አስከሬንን “የገንዘብ መያዣ፣ ማፋዳ፣ ኰረጆ፣ ቍናማት፣ ከረጢት፣ ኪስ፣ ሙዳይ፣ ተረንተራ፡፡ የወርቅ የብር የገንዘብ ሣጥን፣ የልብስ የጌጥ የሽልማት መዝገብ፣ ግምጃ ቤት፣ ቤተ መዛግብት” ብሎ ይፈታዋል። (የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፪: ፮፣ “እለ ይረፍቁ በእንተ ምንት ይቤሎ ዘንተ። ወቦ እለ መሰሎሙ ከመ በእንተ አስክሬን ቀምጠራ ዘሙዳየ ምጽዋት ዘሀሎ በኅበ ይሁዳ ዘይቤሎ ኢየሱስ ተሣየጥ ዘንፈቅድ ለበዓል አው ዘንሁብ ለነድያን።” ~ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፫: ፳፱)
እንዲሁም “መቃብር፣ የሬሳ ርጥብ ሬሳ ወይም ደረቁ የፈረሰው የበሰበሰው፡፡ ይህ ደግሞ የነፍስ ሣጥን ማለት ነው፡፡ ምሥጢሩ ከዚያው አይወጣም፡፡” ይለዋል። ከዚህ በተጨማሪም እጅግ ውድ ነገር፣ የሕይወት፣ የከበረ ነገር መቀመጫ መሆኑን በተለያዩ ንባቦች በዐውድ ፍቺ መረዳት እንችላለን።
Kumar International, Noida - Dead Body Freezer Box On Hire in ...
መልክአ: ሥዕል: ላይ
“ኦርኅርኅተ፡ ሕሊና፡ ለእግዚአብሔር፡ አስከሬኑ።
ዘሐነፀኪ፡ እደ፡ የማኑ።
(እንተ: ኢያውዓየኪ: እሳተ: ርስኑ።)
ኰናኔ ሥጋ ወነፍስ ወልድኪ አኮኑ
መሐርኒ፡ ድንግል፡ ወተሣሃልኒ፡ በበዘመኑ።
ለእመ፡ መሐርክኒ፡ አንቲ (እግዝእትየ)፡ ዘይኳንነኒ፡ መኑ።
ኮናኔ፡ ሥጋ፡ ወነፍስ፡ ወልድኪ፡ አኮኑ፨”
የሚል ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የቀረበ ውዳሴና ልመና ዐርኬ አለ። የመጀመሪያ መስመር ላይ ብንመለከት “ለእግዚአብሔር: አስከሬኑ” ይለል። ይኽም የእግዚአብሔር ማደሪያ ስለሆነች፣ ጌታችንን ስለወለደችልን ‘የከበረ ሳጥን ነሽ፣ የሀብት የዕንቁ ማደሪያ ነሽ፣ ግምጃ ማኅደራችን ነሽ’ ሲላት ነው። (ከሳትኩ እታረማለሁ)
በላቲን ተመጣጣኙ ቃል Scrinium ይባላል። (ማን ከማን ወረሰ ወደሚለው ኣንገባም። በፈረንሳይኛም ቀራቢ ቃል አለ።) ትርጓሜውም የሲሊንደር ቅርጽ ያለው ውድ ሳጥን፣ መያዣ፣ በጥንታዊት ሮም ፓፒረስ እና የተለያዩ መጻሕፍትን ለመያዝ ይጠቅሙበት የነበረ ነው። እንግዲህ ይኽንን ብንወስደውም የጥንት ሮማውያን እና ጽሑፍ ያላቸውን ቁርኝት ማየቱ ብቻውን ምን ያህል የከበረ ነገር መገለጫ መሆኑን እንረዳለን። ግዕዙም ቤተ መዛግብት ይለዋል።
ውስጡ የሞተ ሰው ስጋ ሲቀመጥበት ብቻ ነው በአማርኛ አስክሬን የምንለው። ለምሳሌ፣ መርካቶ ያለውን መሸጫ ሰፈር “ሳጥን ተራ” እንለዋለን እንጂ፣ አስከሬን ተራ አንለውም። ሳጥኑ ልብስ ቢቀመጥበትም ያው ሳጥን ነው እንጂ አስከሬን አይባልም። ወርቅ እና አልማዝ ቢቀመጥበትም ያው ሳጥን ነው። አስከሬን ወደሚል ክቡር መጠሪያ የሚሸጋጋረው ውስጡ በሚቀመጥበት ክቡር ነገር ነው። ስላደረበት ነገር ይከብራል። ያ ክቡር ነገር ደግሞ ሰው ነው!!
የሰው ልጅ ክቡርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ተገልጿል። “ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ።” (መዝሙረ ዳዊት 49፥12) ትንቢታዊ በመሰለ መልኩ ዛሬ እስከደረስንበት ድረስ ተነግሮናል። በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትም ተነግሮናል። እጅጋየሁ ሽባባውም አድዋ የተሰኘው ሙዚቃዋ ላይ
“የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆን ክቡር
ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን
ሰውን ሲያከብር” ብላ የሰው ልጆችን ክቡርነት በጥዑም ዜማዋ አውስታለች።
ይኽንን ማንሳቴ ከሀጫሉ ሁንዴሳ ቀብር መስተጓጎልና ከአስከሬኑ መንገላታት ጋር ተያይዞ ነው። ባስበው ባስበው ሊገባኝ አልቻለም!
ቤተሰብ ባልፈለገበት ሁኔታ መሆኑ እንኳን ቢቀር፥ ሰው እንዴት በዚህ ልክ ርህራሄ ያጣል? ቢያንስ፥ ወዳጄ ወገኔ ነው፣ በግፍ ተገድሎብኛል፣ ፍትህ እፈልጋለሁ ለሚልለት ቀርቶ፣ የማንንም ክቡር የሰው ስጋ ማደሪያ እናንገላታ ዘንድ ድፍረቱን ከየት ቀዳነው? ጭካኔውንስ ማን ጨመረብን? ቤተሰቡንስ ማክበር ማስተዛዘን ለምን አልተፈለገም? “አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ።” (መዝሙረ ዳዊት 49፥20) እንደተባለው ሆኖብን ይኾን!?
የሀጫሉን ነፍስና የእሱን መገደል ተከትሎ፥ በግርግር፣ በማንነታቸው ምክንያት ለተገደሉ ሁሉ ነፍስ ይማር። ለቤተሰብ መጽናናት ይሁን።
Via – yohanes Molla
Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?