ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ጥቂት የማይባሉ ፖለቲከኞች ተይዘው መታሰራቸው ተሰምቷል።

በዚህም መሰረት ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አቶ ደጀኔ ጣፋ እና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ደግሞ ኮሎኔል ገመቹ አያና በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል።

የኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ ማክሰኞ ዕለት ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ ተይዘው መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ አሰለፈች ሙላቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለቤታቸው እንዳሉት ፖሊሶች አቶ ደጀኔ ጣፋን አሸዋ ሜዳ አካባቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸውና ተመልሰው ይዘዋቸው በመምጣት ቤታቸውን ፈትሸው እንደሄዱ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኦነግ ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑት አቶ ቶሌራ አደባ የፓርቲያቸው አባል የሆኑት ኮሎኔል ገመቹ አያና በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከዚህ ባሻገር ከሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል በኋላ ባሉት ቀናት በመጀመሪያ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ እና የፓርቲው አባላት አቶ ጃዋር መሐመድ እንዲሁም ሐምዛ ቦረና በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

በተከታይነትም የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ እስክንድር ነጋና የፓርቲው አመራር አባላት አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ወ/ሮ አስቴር ስዩም ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ተይዘው በእስር ላይ እንደሚገኙ ፓርቲው አስታውቀወል።

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው የተነገረው ባለፈው ሳምንት ነው። የፓርቲው አባላት እንደተናገሩት ሊቀመንበራቸው ለእስር የተዳረጉበትን ምክንያት እንዳላወቁ ገልጸዋል።

ኦነግ ትናንት ታስረውብኛል ካላቸው አባላቱ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንትም ሌሎች የግንባሩ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

እነሱም የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቶ ሚካኤል ቦረን እና አቶ ኬነሳ አያና እንዲሁም የፓርቲው አማካሪ ዶክተር ሽጉጥ ገለታ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ባለፈው ሳምንት ለእስር ከተዳረጉ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል የተወሰኑት ፍርድ ቤት ቀርበው ቀጣይ ቀጠሮ የተሰጣቸው ሲሆን ቀሪዎቹም ዛሬ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦችና የፓርቲ አባላት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

BBC Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *