ሰሞኑንን በአገሪቱ በተለይም በኦሮሚያ በተከሰተው የተደራጀ ነውጥ ከ175 በማይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። መረጃዎች፣ ተጠቂዎችና መንግስት ይህንኑ የሚያረጋግጥ መረጃ እየሰጡ ቢሆንም፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዳነች አቤቤ አብዛኞች ህይወታቸው ያለፈው አስቀድመው በተደራጁ ሃይሎች መሆኑንን ይፋ አድረገዋል። በግፍ በመንጋ ጥቃት የደረሰባቸው ወገኖች በደላቸውን እየዘረዘሩ የፍትህ ያለህ ሲሉ እየተሰሙ ነው። ቢቢሲ የሚከተለውን ዘግቧል።

ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ከተገደሉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረጉት ረብሻ ለመፍጠር ቀደም ብለው ሲዘጋጁ በነበሩ ኃይሎች መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ እንደተናገሩት ባለፈው ሳምንት ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ለበርካቶች ሞትና ለከፍተኛ የንብረት መውደም ጋር ተያይዞ በቁጥጥር የዋሉት ሰዎች ቁጥር ከ2700 በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወ/ሮ አዳነች እንዳሉት ተቋማቸው እስካሁን ባለው መረጃ “በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ረብሻ የመፈጸም ቀድመው ዝግጅት አድርገው ሲጠባበቁ በነበሩ ኃይሎች ነው” በድንገት የተፈጸመ ወንጀል አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

ከግድያው በፊት ዝግጅት ስለመደረጉ ዐቃቤ ሕጓ እንደማስረጃ የጠቀሱት የአርቲስት የመገደል ዜና እንደተሰማ፤ የጦር መሳሪያ እና የግንኙነት ሬዲዮ ታጥቀው፣ ሚዲያ አዘጋጅተው ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል ብለዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በግድያው ማግስት በተከሰተው ውጥረት ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ከአቶ ጃዋር እና ከአቶ በቀለ ጋር የጦር መሳሪያ እና ከመንግሥት አካላት ውጪ መያዝ የማይፈቀድ የሬዲዮ መገናኛ ከመያዙ በተጨማሪ ሚዲያውም በፍጥነት የተለያየ ነገር ሲያውጅ እንደነበር ገልጸዋል።

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

ባልደራስ በተመለከተ ደግሞ “ቄሮን የሚሳደቡ፣ ኦሮሞ አያስተዳደረንም የሚሉና የሚረብሹ ወጣቶች በከተማዋ አሰማርቷል” በማለት ለዚህም ሰው ተመልምልሎ፣ ሞተር እና ታክሲ ተመድቦ፣ ገንዘብ ተከፍሎ ስለት እና ብረት ይዘው እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል። “እነዚህ አካላት ይህን ቀድመው ባያዘጋጁ ኖሮ እንዲህ አይነት ነገር በዚያ ደቂቃ፣ በዚያ ሰዓት አይፈጸምም ነበር።”

ዐቃቤ ሕግ አዳነች ከዚህ ባሻገርም “በኦሮሚያ ውስጥ በጣም በሚያሳፍር እና በአሰቃቂ ሁኔታ ከሃጫሉ ግድያ ጋር ግነኙነት የሌላቸው፣ በየትኛውም ወገን የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች በቤታቸው ውስጥ እንዲገደሉ ተደርጓል” ሲሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙትን ድርጊቶች አውግዘዋል።

የጸጥታ ኃይሉ አባላት መስዋዕት ሆነው ይህን ረብሻ ለማስቆም ጥረት ባያደርጉ ኖሮ፤ ይህ አሰቃቂ ድርጊት ከቁጥጥር ውጪ ይወጣና ይደርስ የነበረው ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን ይችል እንደነበር “እውነት ለመናገር በቁጥጥር ሥር ባይውል ኖሮ ሊደርስ የሚችለውን ማሰብ እንኳን በጣም ከባድ ነው” ብለዋል።

በሁከቱ ውስጥ ተሳትፎ አላቸው ተብለው ከተጠረጠሩት በተጨማሪ ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ እንደተናገሩት በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች ቁጥር ከ2700 በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኦሮሚያ 1714 ሰዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ወደ 1ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በፖሊስ መያዛቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ አለመረጋጋቱን ተከትሎ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች “ዋነኛው ትኩረት አገርን መታደግ ነው። ሕዝቡ በብሔር እና በሐይማኖት እንዲጋጭ የሚደረገው ሙከራ አስከፊ ስለሆነ ይህ እንዲቆም እንሰራለን” ሲሉ ግጭቶችን ለመቀስቀስና ለማባባስ የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አመልክተዋል።

በዚህም መንገዶች እንዲዘጉና ሕዝቡ ወደ ገበያ እንዳይወጣ በአካል፣ በበራሪ ወረቀት፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ሲቀሰቀሰ እንደነበር አስታውሰው፤ “ፖሊስ ይህን ተከታትሎ አክሽፎታል። አሁንም ይህን ማን እየፈጸመ እንደሆነ እናጣራለን። በቁጥጥር ሥር እናውላለን። አስፈላጊውን ማጣራት አድርገን ነጻ የሆኑ ሰዎች ይለቀቃሉ።”

የአገሪቱን መረጋጋት ክፉኛ ካናጋውና ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ከአስር በላይ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ሰሞኑን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገልጾ የነበረ ሲሆን ከዚህ በፊት ከተከሰቱ ግድያዎች አንጻር የታየው የፍትህ ሂደት አዝጋሚ መሆኑ የሰሞኑ የግድያ ወንጀል ፍጻሜም ሊዘገይ ይችላል የሚል ስጋት በበርካቶች ዘንድ አለ።

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አዳነች ከዚህ አንጻር የሰኔ 15ቱን እና የሰኔ 16ቱን ጉዳዮችን አንስተው ለቢቢሲ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት የሰኔ 15ቱ ጉዳይ የፍርድ ውሳኔ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

Related stories   የትህነግ "ውሮ ወሸባዬ" - የመንግስት ሩጫ - የሃላኑ የኢትዮጵያን ቋንጃ የመበጠስ የእባብ አካሄድና ባንዳዎች!

ለዚህ ጉዳይ መጓተት እንደምክንያት የጠቀሱት አንደኛ ተከሳሽ የቀድሞው የደኅንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ተይዘው እንዲቀርቡ ውሳኔ ተሰጥቶ የነበረ መሆኑን አስታውሰው “ነገር ግን በሕዝብ መካከል ተደብቆ ስላለ ኃይል ወደዚያ በመላክ አንድን ሰው ለመያዝ በሚረደረገው ጥረት ሌሎች ይጎዳሉ የሚል ስጋት በመመጣቱ፤ ግለሰቡ በሌለበት የፍርድ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ተወስኗል።”

በዚህም በጉዳዩ የተከሰሱት ሌሎች አምሰት ሰዎች ላይ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ተደምጦ ተከሳሾቹም መከላከያ በማቅረባቸው በክሱ ላይ ጉዳዩን የሚመለከተው ችሎት የፍርድ ውሳኔ ከሚሰጥበት ደረጃ ላይ እንደተደረሰ ገልጸዋል።

የሰኔ 16ቱ ጉዳይን በተመለከተ በጀነራል ሰዓረ መኮንን ግድያ ተሳትፎ የነበረው ተጠርጣሪም እራሱን ሳያውቅ በመቆየቱ መዘግየት እንደነበር አስታውሰው ከዚያ በኋላ ግን ችሎት ሲካሄድ ቆይቶ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለሁለት ወራት በመቋረጡ ምክንያት ሊዘገይ እንደቻለ ተናግረዋል።

በእነዚህ ጉዳዮች በኩል የታየው መዘግየት በፍትህ ሥርዓቱ በኩል በነበረ ቸልተኝነት ሳይሆን ከጉዳዮቹ ጋር ባጋጠሙ ችግሮችና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፍርድ ቤት ሥራ በመስተጓጎሉ ነው ብለዋል።

ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው በተያዙ ሰዎች ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ በተገቢው ፍጥነት ውሳኔ ለመስጠት መስሪያ ቤታቸው እንደሚሰራ አመልክተዋል።

BBC Amharic

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *