አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 16 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ከሰአት በፌደራል የመጀመርያ ፍርድቤት ልደታ ችሎት የአረዳ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ቦታውን ቀይሮ የመርማሪ ፖሊስ የምርመራ ሂደትን እና የተጠርጣሪዎች አቤቱታና መቃወሚያን አዳምጧል። ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር ዛሬ ፍርድቤት ከቀረቡት ውሰጥ ከ10 የአቶ ጀዋር መሐመድ አጃቢዎች ዘጠኙና የአቶ በቀለ ገርባ ሁለት ልጆች ይገኙበታል ።
አንዱ የአቶ ጀዋር አጃቢ በኮረና ቫይረስ በመጠርጠሩ በለይቶ ማቆያ እንዲገባ መደረጉን ፖሊስ አስታውቋል። ፖሊስ በእስካሁን የምርመራ ሂደት አስር ክላሽ ዘጠኝ ሽጉጥና ዘጠኝ የመገናኛ ሬዲዮኖችን መያዙንና በእነዚህም ላይ የፎረንሲክ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ፖሊስ በአቶ በቀለ ገርባ ቤትም ሁለት ሽጉጦች ማግኘቱን እና ፍቃድ ይኑረው አይኑረው እያጣራ መሆኑንም አስታውቋል። በሁከቱም 140 ሚሊየን የሚገመት ንብረት የወደመባቸው ሁለት ተቋማትን የሰነድ ማስረጃ መያዙንም አስታውቋል። በመሆኑም የሚቀሩ የማጣራት ስራዎችን ለመስራት ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በሚል መቃወሚያቸውን አቅርበዋል። የሁለቱንም ወገኖች የቀረቡ ጉዳዮችን ያዳመጣው ፍርድቤቱ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄው ላይ ለመወሰን ለሐምሌ ዘጠኝ ተለዋጭ ቀጠሮ ስጥቷል።
በብሩክ ተስፋዬ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *