የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው ተቃውሞ በባቱ ከተማ (በዝዋይ) ከ125 በላይ የመኖሪያ ቤቶችና ሆቴሎች መውደማቸውን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ተያይዞ 83 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተጠቁሟል።
የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለሙ ደዋና ሰኔ 22 ምሽት የተፈጸመው የአርቲስት ሐጫሉ ግድያን ተከትሎ ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ላይ ከየአቅጣጫው እሳት በመለኮስና በጩኸት ታጅቦ ወደ ከተማው የገባው ሕዝብ መጠነ ሰፊ ጥቃት አድርሷል።በድርጊቱም የንግድ ቤቶች፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ በሆቴሎችና በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፤ የአንድ ሰው ሕይወትም አልፏል።
እንደ አቶ አለሙ ገለጻ ክስተቱ እኩለ ሌሊት ላይ የተፈጸመና ወደከተማው የገባው ሕዝብም እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የከተማው የጸጥታ ኃይልም ሆነ የአስተዳደሩ አመራር ሊገታው አልቻለም፤ በእዚህም 100 የመኖሪያ ቤቶች፣ 24 ሆቴሎችና በርካታ የንግድ ቤቶች ሲቃጠሉና ሲፈርሱ፤ 34 የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል።
እንዲህ ዓይነት የተደራጀና በሁሉም አቅጣጫ ለጥፋት ወደ ከተማው የገባን ብዛት ያለው ሕዝብ አይተው የማያውቁ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አለሙ፤ በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት በከተማው ብቻ ሳይሆን በአገር ኢኮኖሚ ላይም ኪሳራ የሚያደርስ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በከተማዋ አሉ በተባሉ ሆቴሎችና ንግድ ተቋማት ላይ የተፈጸመው ውድመት የከተማዋን ዕድገት ለ20 እና 30 ዓመታት ወደኋላ የሚጎትት፤ ከኦሮሞ ባህል ያፈነገጠና ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን ጠቅሰው፤ በወቅቱ ንብረት ማትረፍ እንደማይቻል በመገንዘብም ከአገር ሽማግሌዎችና ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት የሰው ሕይወት ወደማትረፍ መግባታቸውን ተናግረዋል።
የጠፋውን ንብረት ለመተካት፤ የሰዎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ሰዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም አምስት ኮሚቴዎች ተዋቅሮ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ከንቲባው፤ የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ የተፈጸመው ጥቃት አንድም ሃይማኖታዊ ሌላም ደግሞ ብሄርን መሠረት ያደረገ ገጽታ እንዲላበስ አድርገው ያካሄዱት መሆኑንም አስረድተዋል።
ጥቃት የደረሰባቸው የንግድ ቤት ባለንብረቶች በከተማው ተወልደው ያደጉና የኖሩ፣ በከተማው ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ያላቸው፣ ማሕበራዊ መስተጋብራቸውም ጠንካራ የሆነና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች መሆናቸውንም የተናገሩት ከንቲባው፤ ተግባሩ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክል፣ ድርጊቱ በጉራጌ፣ በስልጤ፣ በአማራ፣ በወላይታና በተለያዩ ብሔረሰቦች ላይ ያረፈ እንጂ የተለየ ብሔርን ለማጥቃት ታስቦ የተፈጸመ ሳይሆን በተጠና እና በተናበበ መልኩ የተፈጸመ የአፍራሽ ኃይሎች ሴራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜናም በቡልቡላ ከተማ በዕለቱ በተፈጸመ ጥቃት የተለያዩ ንግድ ቤቶችና መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት እና ፖሊስ ጣቢያ፣ የወጣት ማዕከል ቤተ መጽሐፍትና የወጣቶች መዝናኛ እንዲሁም በማዘጋጃ ቤት ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ሰነዶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ወይሳ ሞርኬ ገልጸዋል።
ድርጊቱ ብሔርን ከብሔርና ሰዎችን ሃይማኖታዊ በሆነ ሰበብ በማነሳሳት እርስ በእርስ እንዲጋጩ ለማድረግ ታስቦ ስለመፈጸሙ የጠቀሱት ከንቲባው፤ ተግባሩ የኦሮሞ ባህልና እሴትን ያላከበሩ በመሆናቸው የሚወገዙ መሆናቸውን ከንቲባው ገልጸው፤ በማዘጋጃ ቤቱም ሆነ በፖሊስ ጣቢያው የተፈጸመው ጥቃት የከተማ አስተዳደሩ ተግቶ እንዲሰራ የሚያነቃው እንጂ፤ እንደታሰበው የመንግሥት መዋቅሩን በማዳከም መንግሥትን ለመጣል የሚደረግ ክስተትን አያሳካም ሲሉ አስረድተዋል።
በወንድወሰን ሽመልስ
       
ፎቶ ዳኜ አበራ
(ኢ.ፕ .ድ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *