ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

“እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ” የዘረኝነት ጥግ “ሁለቱን ልጆች ባድናቸውም በሁለት ሰዎች ግድያ ተሳትፌያለሁ”

“እናት ነኝ። የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ” ብላለች። ከጥቂት ቀናትም በኋላ ወላጆቻቸው በቆንጨራ የተገደሉባቸው ሁለት የቱትሲ ህፃናት እየተንቀጠቀጡ ቤቷ መጡ። የሚደበቁበት የጠፋቸው፤ የሚሄዱበት የጨነቃቸው ልጆች መጠለያን ፈልገው ነበር ደጃፏ የደረሱት። ከምትጠላው ጎሳ ቢሆኑም የእናትነት አንጀቷ አላስቻላትም። አስገብታ ደበቀቻቸው። ከጭፍጨፋውም ሊተርፉ ቻሉ። “ሁለቱን ልጆች ባድናቸውም በሁለት ሰዎች ግድያ ተሳትፌያለሁ። ምንም ቢሆን ካደረስኩት ጥፋት ነፃ ሊያወጣኝ አይችልም”

በአሰቃቂው የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል። በርካቶች ተደፍረዋል፣ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል።

የማያቋርጥ ዋይታ፣ ለቅሶ የተሰሙባቸው መራር መቶ ቀናት።

የዘር እልቂቱ ሁለት አስርት ዓመታትን ቢያስቆጥርም ከመራር ሃዘን ጋር ለመኖር የተገደዱ፣ ከማይሽር ጠባሳ ጋር እየተጋፈጡ የሚኖሩ ጥቂት አይደሉም።

ያው ህይወት መቀጠል አለባት።

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት በሩዋንዳው የዘር እልቂት ተሳትፈዋል የሚባሉት ታዋቂ ስሞች በተደጋጋሚ ይነሳሉ። ብዙዎቹም ወንዶች ናቸው።

ከእልቂቱ ጀርባ ግን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ቢሳተፉም ታሪክ ዘንግቷቸዋል። ጋዜጠኛዋ ናታሊያ ኦጄውስካ በጭፍጨፋው ተሳታፊ ከነበሩት መካከል በእስር ላይ የሚገኙትን የተወሰኑትን አናግራቸዋለች።

ቀኑ ምንም የተለየ ነገር አልነበረውም። ፎርቹኔት ሙካንኩራንጋ ሌላ ጊዜ እንደምታደርገው ከቤቷ የወጣችው ቁርስ ለማዘጋጀት በሚል ውሃ ልትቀዳ ነበር።

ነገር ግን በዚያኑ ዕለት ውሃ ብቻ አይደለም የቀዳችው፤ የሰው ህይወትም ነበር ያጠፋችው። እንዴት?

የእስር ቤቱን ብርቱካናማ ቀለም ያለው መለያ ልብስ ለብሳ፣ ረጋ ባለ ድምጿ ከሃያ ስድስት ዓመት በፊት የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ታስታውሰዋለች።

ጊዜው ሚያዝያ 2/1986 ዓ.ም (በጎርጎሳውያኑ ሚያዝያ 10/1994)፤ እለቱም እሁድ ነበር።

ቁርስ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጋትን ውሃ ልትቀዳ ከቤቷ ወጣች። በመንገዷ ላይም በርካታ ሰዎች ተሰባስበው ሁለት ወንዶችን ክፉኛ ሲደበድቧቸው አየች።

በጥላቻ የተሞላ ጊዜ፤ ርህራሄም ሆነ ሃዘን በመጀመሪያ አልተሰማትም።

“ግለሰቦቹ ድብደባው ሲበዛባቸው መሬት ላይ ተዝለፍልፈው ሲወድቁ እንጨት አነሳሁና ቱትሲዎች መሞት አለባቸው እያልኩ አብሬ መደብደብ ጀመርኩ . . . ሰዎቹ በድብደባውም ሞቱ። ከገዳዮቻቸውም መካከል አንዷ እኔ ነኝ” ትላለች የ70 ዓመቷ እስረኛ።

የሞቱት ድምፅ ይጣራል

እነዚህ በጭካኔ መንገድ ላይ የተገደሉት ሁለቱ ሰዎች በመቶ ቀናት ውስጥ ከተገደሉት 800 ሺህ ቱትሲዎችና፣ ለዘብተኛ ከተባሉ ሁቱዎች መካከል ናቸው።

Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?

ከሁቱ ጎሳ የሆነችው ፎርቹኔት በግድያው ከተሳተፈች በኋላ ለሰባት ልጆቿ ቁርስ ልትሰራ ወደቤቷ፣ ወደኑሮዋ ተመለሰች።

ወደ ቤቷ ስትመለስ ግን ሌላ ሰው ሆና ነው የተመለሰችው። ቤት ስትደርስ ተሸማቀቀች። ውስጧ ተፀፀተ።

የተገደሉት ሁለት ሰዎች ተማፅኖ፣ አሰቃቂ ድብደባም ፊቷ ላይ ድቅን ይልባታል። እረፍትም ነሳት።

“እናት ነኝ። የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ” ብላለች።

ከጥቂት ቀናትም በኋላ ወላጆቻቸው በቆንጨራ የተገደሉባቸው ሁለት የቱትሲ ህፃናት እየተንቀጠቀጡ ቤቷ መጡ።

የሚደበቁበት የጠፋቸው፤ የሚሄዱበት የጨነቃቸው ልጆች መጠለያን ፈልገው ነበር ደጃፏ የደረሱት።

ከምትጠላው ጎሳ ቢሆኑም የእናትነት አንጀቷ አላስቻላትም። አስገብታ ደበቀቻቸው። ከጭፍጨፋውም ሊተርፉ ቻሉ።

“ሁለቱን ልጆች ባድናቸውም በሁለት ሰዎች ግድያ ተሳትፌያለሁ። ምንም ቢሆን ካደረስኩት ጥፋት ነፃ ሊያወጣኝ አይችልም” ብላለች ፎርቹኔት።

በዘር ጭፍጨፋው ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ክስ ከተመሰረተባቸው 96 ሺህ ሴቶች መካከል ፎርቹኔት አንዷ ናት። እንደ ፎርቹኔት በርካታ ሰዎችን በመግደል እስር ቤት የገቡ እንዳሉ፤ ብዙዎችም ቱትሲ ሴት ህፃናትን ጨፍጭፈዋል እንዲሁም ቱትሲ ሴቶች እንዲደፈሩ ተባብረዋል።

ከምሽቱ ሚያዝያ 2/ 1986 ዓ.ም በጊዜው ፕሬዚዳንት የነበሩት ጁቬናል ሃብያሪማና ተሳፍረውበት የነበረው አውሮፕላን መዲናዋ ኪጋሊ በሚገኘው አየር ማረፊያ አካባቢ ተመትቶ ወደቀ። ከሁቱ ጎሳ የሆኑት ፕሬዚዳንት ጁቬናልም ህይወታቸው አለፈ።

ፕሬዚዳንቱን የገደላቸው ማን እንደሆነ ባይታወቅም የሁቱ ፅንፈኞች ግን የቱትሲ አማፂ ቡድን ነው ጥቃቱን የፈፀመው በሚል ወሬ መንዛት ጀመሩ።

ምንም እንኳን ይሄ የፕሬዚዳንቱ ሞት የቅርብ መንስኤ ቢሆንም ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲዘራ የነበረው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ፍሬ አፍርቶ ለበርካታ ቱትሲዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነ።

ደም የጠማቸው በጥላቻ የናወዙ ጽንፈኛ ሁቱዎች ተደራጅተው ወጡ፤ ያገኙትንም በአሰቃቂ ሁኔታም ጨፈጨፉ።

ምንም እንኳን በዚህ ጭፍጨፋ ላይ ብዙ ጊዜ ስማቸው የሚነሳው ወንዶች ቢሆኑም በርካታ ሴቶች ተሳትፈዋል። ልክ እንደ ሌሎቹ አገራት በሩዋንዳም ሴቶች እንደ አዛኝ፣ ጠባቂና ርህራሄ የተሞሉ ናቸው ተብለው የተሳሉ ከመሆናቸው አንፃር ሴቶች በግድያዎቹ ተሳትፈዋል የሚለው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ፎርቹኔት ትናገራለች።

“ልጆቿን የምትወድ እናት እንዴት የጎረቤቶቿን ልጆች ትገድላለች የሚለውን እሳቤ መቀበል አስቸጋሪ ነው” በማለት የምትናገረው በሰላምና እርቅ ላይ የሚሰራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሠራተኛዋ ሬጂን አባንዩዙ ናት።

Related stories   የበልግ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

ጭፍጨፋዎቹ ከተቀጣጠሉ በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶቸ ከወንዶች ጋር አብረው ተሳትፈዋል።

በእስር ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ሲሰፉ

ፓውሊን ኒይራማሹኮ በወቅቱ የቤተሰብ ደኅንነትና የሴቶች ልማት ሚኒስትር ነበሩ። በወንድ ፖለቲከኞች ተሞልቶ በነበረው የሩዋንዳ መንግሥት ውስጥ የመሪነት ቦታን ከተቆናጠጡ ሚኒስትሮች መካከል አንዷ ናቸው። በዘር እልቂቱም ከፍተኛ ሚናን እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል።

በጎርጎሳውያኑ 2011ም የሩዋንዳን ጭፍጨፋ ሲያይ የነበረው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትም ጥፋተኛ ብሏቸዋል። በታሪክም ውስጥ በሰብአዊነት ላይ በሚፈፀም ወንጀል በመድፈር የተከሰሱ ብቸኛዋ ሴት ናቸው።

የቀድሞ ሚኒስትሯ ቡታሬ በተሰኘ የመንግሥት ቢሮ ውስጥ የቱትሲ ሴቶች በታጣቂዎች እንዲደፈሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ተብሏል። ሚኒስትሯ በኃላፊነት ቦታ ላይ ሆነው ትዕዛዝ በማስተላለፍ ሲሳተፉ በርካቶች ደግሞ ባገኙት መሳሪያ ጎረቤቶቻቸውን ከመጨፍጨፍ ወደ ኋላ አላሉም። ከሩዋንዳ እርቅ ጋር ተያይዞ በእልቂቱ እጃቸው ያለበት ወንዶች በተሃድሶ ፕሮግራም ቢሳተፉም ሴቶች በማኅበረሰቡ በሚሰጣቸው ሚና ከእርቅ ፕሮግራሞቹ ተገለዋል፤ እንዲሁም ተገፍተዋል።

ማርታ ሙካሙሺንዚማና

የጭፍጨፋው ሁለት ወግ

የአምስት ልጆች እናት ማርታ ሙካሙሺንዚማና ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል ወንጀሏን ደብቃ ነበር። ሸክሙን ጫንቃዋ መቻል ሲከብደው፣ ከህሊናዋ ጋር መኖር ሲያዳግታት በእራሷ ጊዜ ወንጀሏን ለመናዘዝ ወሰነች።

በርካቶቹ ካላቸው የእናትነት ሚናም ጋር ተያይዞ በጭፍጨፋዎቹ ላይ መሳተፋቸውን ለቅርብ ወዳጅ ዘመዶች ለመንገርም ያሳፍራቸዋል። ልጆች ያሏት እናት እንዴት ልጆችን ትገላለች?

“በጊዜ ሂደት ብዙ ህመሞች ያገግማሉ። የተሃድሶውም ዋነኛ ትኩረት ጊዜን መስጠት ነው። የተቻለውን ያህል ጊዜ እንሰጣቸዋለን፤ እናደምጣቸዋለን። በራሳቸው ጊዜም የፈጸሙትን ጥፋት እንዲናዘዙ እናደርጋቸዋለን” ይላሉ ንጎማ የተባለው የሴቶች ማረሚያ ቤት ዳይሬክተር ግሬስ ንዳዋንይ።

“ቤቴ መንገድ ዳር ነበር። ፉጭት ይሰማኛል፤ እሱንም ተከትሎ በርካታ ጎረቤቴ የሆኑ ቱትሲዎችም ወደ ቤተክርስቲያን ሲወሰዱ ትዝ ይለኛል” ትላለች ፓውሊን ሳግ በሚቆራርጠው ድምጿ።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ቱትሲዎች በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሳምንት ያህልም ተደብቀው ነበር። የሃምሳ ሦስት ዓመቱ ስታኒስለስ ካይቴራ በህይወት ከተረፉት እድለኞች መካከል አንዱ ነው።

በክርኑ ላይ የሚታየው ትልቅ ጠባሳ ያንን የጨለማ ጊዜ ማስታወሻ ነው። ቦምቡ ባያገኘውም፤ ፍንጣሪው አቁስሎታል።

“ሴቶቹ ድንጋይ ለወንዶች ሲያቀብሉ ትዝ ይለኛል። ወንዶቹም ድንጋይ እየወረወሩብን ነበር። ከዚያም አለፍ ሲል ወንዶቹ ሽጉጥ ይተኩሳሉ፤ ቦምብ ይወረውራሉ። በእሳትም ለማቃጠል ሞክረዋል” ይላል ።

Related stories   የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ

“ቤተ ክርስቲያኑንም በርግደው ገብተው በቆንጨራ ጨፈጨፉን” የሚለው ስታኒስለስ የተረፈውም ከተደራረቡ አስከሬኖች በታች ሆኖ ነው፤ የሞተ መስሏቸው ዳነ።

ፓውሊን አሁን ብትፀፀትም በወቅቱ ግን “ትዕዛዝ ተቀባይ ነበርኩ” ትላለች።

“ልጄን አዝዬ በቤተክርስቲያኑ ተደብቀው የነበሩት ላይ ድንጋይ የሚወረውሩትን ተቀላቀልኩ። ብዙዎችንም ገድለናል” የምትለው ፓውሊን በወቅቱ ከወለደች ሁለት ሳምንቷ ነበር።

ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ የፈፀመችውን ወንጀል ለመናዘዝ ስትወስንም ዘመዶቿ ልጆቿን ለመያዝ ፈቃደኛ አልነበሩም።

በማረሚያ ቤት የምትገኝ ታራሚ ስትሰፋ

“የዘር ጭፍጨፋ እልቂት ብቻ አይደለም የሚያስከትለው። ማኅበረሰቡን ሽባ ያደርገዋል። ተጠቂዎችን ብቻ ሳይሆን የአጥቂዎቹንም ቀሪ ህይወት ይነጥቃል። አጥቂዎቹም ቢሆኑ ካደረሱት ጉዳትና ፀፀት ሊድኑ ይገባል” በማለት የሩዋንዳ ብሔራዊ ትብብር የእርቅ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ፊደሌ ንዳይሳባ ይናገራሉ።

ወንጀላቸውን የተናዘዙ ሴት ጥቃት አድራሾች ለገደሏቸው ሰዎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ደብዳቤ እንዲፅፉ ይበረታታሉ።

ከእስር ሲለቀቁ ማኅበረሰቡን ለመቀላቀልና ቀሪ ህይወታቸውንም በሰላም እንዲኖሩ ያለመ ቢሆንም ለበርካታ ሴቶች ቀላል አይደለም።

የቀድሞ ባለቤቶቻቸው ሌላ ሴት አግብተው ከውርሳቸውም እንዲሁ ይነጠቃሉ። ከወንዶቹ ጥቃት አድራሾች ጋር ሲነፃፀር በዘር ጭፍጨፋ የተሳተፉ ሴቶች ማኅበረሰቡ አይቀበላቸውም። ቤተሰቦቻቸውም እንዲሁ አይናቸውን ማየት አይፈልጉም።

ምንም እንኳን በርካቶች በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው ይቅርታ ቢጠይቁም አሁንም ቢሆን የጎሳ ጥላቻ ውስጣቸው የዘለቀና ዝንብ የገደሉ የማይመስላቸውም አሉ።

“ምንም ወንጀል እንዳልፈፀሙ የሚሰማቸው አንዳንዶች አሉ። ቁጥራቸው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው” ይላሉ ፊደሌ።

እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም

ፎርቹኔትም ቢሆን ከታሰረች ከአራት ዓመታት በኋላ ነው ወንጀሏን የተናዘዘችው። በግድያው ከተሳተፈችበት የአንደኛውን ልጅ ይቅርታ ስትጠይቅም ልቧ እንዴት እንደተሸበረ ታስታውሳለች።

ከምትጠብቀውም ውጪ ልጁ ተረጋግቶና በሰላም ነው ያናገራት “ደስ ብሎት አናገረኝ፤ እምባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። አቅፌው አለቅስ ነበር” ብላለች።

ፎርቹኔትም እሱ ይቅር ካላት በኋላም የወደፊቱ ህይወቷ ብሩህ ሆኖ ታይቷታል። ምናልባትም ቀሪ ህይወቷን ከቤተሰቧ ጋር በሰላም ልትኖር እንደምትችል ተስፋ ሰንቃለች።

“ከእስር ቤት ወጥቼ ቤቱ ስመለስ ከቤተሰቦቼ ጋር በሰላም እኖራለሁ። የበለጠ ሰው ወዳጅና በደንብ ተንከባካቢ እሆናለሁ። ለፈፀምኩት ወንጀል እየከፈልኩ ቢሆንም እናት እንደ መሆኔ መጠን እስር ቤት መቆየት አልነበረብኝም” በማለት ሃሳቧን አጠናቃለች።

ቢቢሲ አማርኛን ለዚህ ዘገባው አመሰግናለሁ