ባለፉት 24 ሰዓታት 5 ሺህ186 ናሙናዎች የኮቪድ-19 ምርመራ እንደተደረገላቸው ተገለፀ። ከእነዚህም መካከል 294 ሰዎች ላይ ኮሮናቫይረስ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴርና የህብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ 209፣ ኦሮሚያ 13፣ ትግራይ 31፣ ጋምቤላ 20፣ አማራ 9፣ አፋር 6፣ ድሬዳዋ፣ 4፣ ሶማሊ 2፣ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎችን አስመዝግበዋል።
በአሁኑ ሰዓት በጽኑ ሕሙማን የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 36 ሲሆን ከሕመሙ ሙሉ በሙሉ ያገገሙ ደግሞ 51 መሆናቸው በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ሁለት ሰዎች ሲሞቱ አንዱ ግለሰብ በአፋር ህክምና ክትትል እየተደረገለት የነበረ መሆኑ ሲነገር ቀሪው ግለሰብ ደግሞ በአዲስ አበባ ከአስክሬን ላይ በተወሰደ ናሙና መገኘቱ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 4768 ሰዎች ከኮቪድ-19 ሲያገግሙ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 148 ደርሷል።
በመላው ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ300 ሺህ በላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 8 ሺህ 475 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ታውቋል።
ቢቢሲ

ኢራን 140 ጤና ባለሙያዎችን በኮቪድ-19 ምክንያት አጣች

ኢራን 140 የጤና ባለሙያዎችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በቫይረሱ ምከንያት በሞት መነጠቋን አስታወቀች።
የኢራን ጤና ሚኒስቴር ባለስልጣን ሲማሳዳት ላሪ፣ የሕክምና ባለሙያዎቹ የዜጎችን ህይወት ለማዳን ሕይወታቸውን መክፈላቸውናና ክብር እንደሚገባቸው ጠቅሰው “. . . ሁላችንም የተደነገጉ የጤና መመሪያዎችን መከተል አለብን” ብለዋል።
አገሪቷ ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ከሚያዚያ ወር አጋማሽ ጀምሮ ካላላች በኋላ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ መጥቷል።
እስካሁን ድረስ በኢራን 264 ሺህ 561 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ 13 ሺህ 410 ደግሞ መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያሳያል።
የጤና ባለስልጣናት አሁን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙት በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎችን አገሪቷ የመመርመር አቅም በማደጉ የተገኘ ሊሆን እንደሚችል ገልፀው፣ ዜጎች የአካላዊ ርቀት መጠበቅ ላይ ቸልተኝነት ማሳየታቸውን ገልፀዋል።
ረቡዕ እለት የኢራን ፕሬዝዳንት ሃሰን ሮሃኒ፣ ዜጎች የጤና መመሪያዎችን እንዲያከብሩ በይበልጥ ደግሞ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
“ ሰዎች ምንም አይነት መሰባሰብን ማስወገድ እና ከወቅታዊ ሁናቴ ጋር አኗኗራቸውን እንዲያስተካክሉ እንጠይቃለን” ብለዋል በሚኒስትሮች ካቢኔ ስብሰባ ወቅት።
BBC Amharic