በአንድ ወር ውስጥ ሁለት ወንዶችን እንድታገባ የተገደደችው የ12 ዓመት ታዳጊ የኬንያ ባለስልጣናት ጣልቃ ገብተው እንዳስጣሏት ተዘገበ።

ከኬንያ ዋና ከተማ በስተምዕራብ በምትገኘው ናሮክ በተባለችው ግዛት ውስጥ ነዋሪ የሆነችው ታዳጊ አባት ልጁን መጀመሪያ የ51 ዓመት አዛውንት ለሆኑ ግለሰብ ድሯት ነበር።

ከዚያም በኋላ ከመጀመሪያው ‘ጋብቻ’ ማምለጥ ብትችልም ተመልሳ ከሌላ የ35 ዓመት ጎልማሳ ጋር ለመኮብለል መገደዷ ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ ጉዳዩ በአካባቢው ወዳሉ የህጻናት መብት ተከራካሪዎችና የመንግሥት ባለስልጣናት ዘንድ በመድረሱ ታዳጊዋ ያለዕድሜዋ እንድትገባበት ከተደረገው ጋብቻ እንድትወጣ ተደርጓል።

ታዳጊዋ ከገባችበት ያለዕድሜ ጋብቻ እንድትወጣ የተደረገችው አንድ የህጻናት መብት ተከራካሪ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበረች ሌላ ታዳጊን ጉዳይ እየተከታተለ ባለበት ጊዜ ባገኘው መረጃ መሰረት ነው።

“አባቷ መጀመሪያ ለአንድ አዛውንት ድሯታል። ከዚያም ምንም አማራጭ ስላልነበራት በድጋሚ ከሌላ ጎልማሳ ጋር ለመሆን ተገደደች” ሲል በናሮክ ግዛት ውስጥ ያለው የህጻናትን ጉዳይ የሚከታተለው ማኅበር ባልደረባ ጆሽዋ ካፑታህ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ስታንዳርድ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው የመጀመሪያው ግለሰብ አራት ላሞችን በጥሎሽ ያቀረበ ሲሆን፣ ታዳጊዋ ጋብቻውን በብትቃወምም በአጎቷ ልጆች መመታቷ ተገልጿል።

“ከመጀመሪያው ጋብቻ አምልጬ ወደ አባቴ ቤት ብመለስ መልሰው ሊሰጡኝ ይችላሉ ብዬ ስለፈራሁ፤ ከ35 ዓመቱ ሰው ጋር አብሬ ኮበለልኩ” ስትል ከሌላ ባለትዳር ሰው ጋር እንደጠፋች መናገሯን ጋዜጣው ጠቅሷል።

Related stories   እኛ የምንመርጠው አባትና አያቶቻችን የመረጡትን ነው።

ነገር ግን መኮብለሏን ያወቀው አባት ታዳጊዋን አግኝቶ መጀመሪያ ለተዳረችለት ሰው መልሶ እንደሰጣት የህጻናት መብት ተከራካሪው ካፑታህ ተናግሯል።

ካፖታህ ጨምሮም በአካባቢው ያለው ድህነትና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ህጻናት ያለዕድሜያቸው እንዲዳሩ የማድረጉን ሁኔታ እንዳባባሰው ገልጿል።

“አንዳንድ ቤተሰቦች ይራባሉ፤ በዚህም ለሴት ልጆች ወላጆች በጥሎሽ መልክ የሚሰጡት ሁለት ወይም ሦስት ላሞች ስለሚያጓጓቸው በችግር ምክንያት ታዳጊ ልጆቻቸውን ያለዕድሜያቸው እንዲዳሩ ያደርጋሉ” ብሏል።

በናሮክ ግዛት ውስጥ በሚገኙት በማሳይ ማኅበረሰቦች ዘንድ ሴት ልጆች በቤት ውስጥ እንደ ሃብት የሚታዩ ሲሆን፣ ሲያገቡም በሚያመጡት የከብቶች ጥሎሽ ምክንያት በአካባቢው ታዳጊ ህጻናትን ያለዕድሜያቸው እንዲዳሩ ይደረጋል።

Related stories   የመረጃ መንታፊዎች ዋትሳፕን እንደ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ተገለጸ

የመንግሥት ባለስልጣናትና የህጻናት መብት ተከራካሪዎች ታዳጊዋን ከገባችበት ሕገወጥ ጋብቻ ለማስጣል ወዳለችበት ሄደው ቢያገኟትም ግለሰቦቹ ግን መሰወራቸው ተገልጿል።

የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ታዳጊዋ ከተገኘች በኋላ ፖሊስ ተደብቀዋል የተባሉትን አባቷንና ሁለቱን ግለሰቦች ለመያዝ ፍለጋ ላይ ነው።

ተፈላጊዎቹ ተይዘው ጥፋተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ በአገሪቱ ሕግ መሰረት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ወይም አንድ ሚሊዮን ሽልንግ ማለትም 10 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

BBC Amharic

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *