ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ከሁለት ሳምንት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የአቶ ጃዋር መሐመድን ጉዳይ የተመለከተው ፍርድ ቤት ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቀደ።

አቶ ጃዋር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ የጀመረውን ምርመራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

በፖሊስ ከቀረቡት ክሶች መካከል ለአንድ ፖሊስ ህይወት መጥፋት ምክንያት በመሆንና በኦኤምኤን ቴሌቪዥን ላይ በቀረቡ ጥሪዎች አማካይነት ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም መንስኤ በመሆን ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የሁለት ሳምንት ጊዜ እንዲሰጠው በመጠየቁ ነው ተጨማሪ ቀናት የተፈቀዱለት።

ይህንንም ተከትሎ የጃዋር ጠበቃ ደንበኛቸው በዋስ ከእሰር ቤት ውጪ ሆኖ ጉዳዩን መከታተል እንዲችል እንዲፈቀድለት ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጥያቄ ተቀብሎታል።

በዚህ ጊዜ የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኛቸው ምግብ ከቤተሰቡ የሚቀርብለት ቢሆንም ግንኙነታቸው በርቀት በመሆኑ ባለበት ከርቀት አይቶ የመለየት ችግር ቤተሰቦቹን በቅርበት እንዲያገኝ እንዳልተፈቀደለት ለችሎቱ አቤት ብለዋል።

Related stories   የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ እስክንድር ነጋ ጉዳይ የተፋጠነ ፍትሕ መስጠት እንዲቻል ከቀጠሮ ቀን በፊት ችሎት ሰየመ

ፖሊስም ይህንን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ታሳሪዎችና ጠያቂዎች መካከል መቀራረብ እንዳይኖር የተደረገው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር በወጣው ደንብ መሰረት መሆኑን ጠቅሶ ምላሽ ሰጥቷል።

በተጨማሪም አቶ ጃዋር ታስረው የሚገኙበት ክፍል በቂ ብርሃን የሌለው መሆኑና መጸዳጃ ቤት የመጠቀም ችግርን በማንሳት አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም ደንበኛቸው ጥፋተኝነታቸው ገና ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ምስላቸው እየቀረበ ዘገባዎች እንደሚቀርቡና ፍርድ ቤቱም ይህንን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ለእስረኞች መጸዳጃ ቤትን በተመለከተና በማረፊያ ክፍሎች ውስጥ ያለውን ብርሃን በተመለከተ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ያዘዘ ሲሆን፤ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ስለቀረበው አቤቱታም ጠበቆች ያሏቸውን ተቋማት በስም ለይተው እንዲያቀርቡ አዟል።

በዚህም መሰረት ፖሊስ ለምርመራ የጠየቀውን የ14 ቀናት ጊዜ ፈቅዶ ጉዳዩን ለመመልከት ሐምሌ 22/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ አብቅቷል።

በተጨማሪም ፖሊስ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ የሚያደርገውን ምርመራ ለመቀጠል በተመሳሳይ ተጨማሪ ቀናትን ከፍርድ ቤት ተሰጥቶታል።

ከአቶ ጃዋር መሐመድ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ ከችሎቱ ቀደም ብሎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አቶ ጃዋርን ባለፈው ማክሰኞ አግኝተዋቸው እንደነበር ገልፀው፤ ታስረው የሚገኙት ምድር ቤት ውስጥ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በማረፊያ ክፍሉ ውስጥም አነስተኛ ተፈጥሯዊ ብርሃን እያገኙ እንደሆነና ብርሃኑም በትንሽ መስኮት በኩል የሚገባ ብቻ መሆኑን እንደነገሯቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ነገር ግን አቶ ጀዋርና አቶ በቀለ ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረዋል ስለመባሉ ሲያብራሩም የኤሌትሪክ መብራት በክፍሉ ውስጥ መኖሩንና ችግሩ የተፈጥሮ ብርሃን አለማግኘታቸው መሆኑን ገልፀዋል።

የጃዋር ቤተሰብ ምግብ ሲያደርሱላቸው የቤተሰባቸውን አባላት መለየት አለመቻላቸውን ከቤተሰቡ አባል ማረጋገጣቸውን አቶ ቱሊ ተናግረዋል።

“ጃዋርን በምን ምክንያት መለየት እንዳልቻለ ጠይቄው፤ ከቤተሰቡ አባል ጋር የሚገናኙት ከርቀት ቆመ እንደሆነና ድምጻችንን ከፍ አድርገን ነው ጮኸን የምንነጋገረው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ከክፍሌ የፀሐይ ብርሃን ወዳለበት ስወጣ አይኔ አጥርቶ ማየት አልቻለም ነበር ብሎኛል” ሲሉ ጠበቃው ገልጸዋል።

አቶ ጃዋር መሀመድ እና አቶ በቀለ ገርባ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አቶ ሀምዛ ቦረና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ በሌላ ክፍል በጋራ ታስረው እንደሚገኙ አቶ ቱሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Related stories   የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ እስክንድር ነጋ ጉዳይ የተፋጠነ ፍትሕ መስጠት እንዲቻል ከቀጠሮ ቀን በፊት ችሎት ሰየመ

አቶ ሸምሰዲን ጠሃ አቶ ጃዋር በቁጥጥር ስር በዋለ በማግስቱ ቦሌ ሚካኤል ከሚገኘው የጓደኛቸው ቤት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በወቅቱ በፀጥታ ኃይሎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው አቶ ቱሊ አረጋግጠዋል።

የሕክምና እርዳታ ለማግኘት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም እንዳልተፈቀደለት እነደነገራቸው አቶ ቱሊ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ቱሊ ሸምሰዲንን ሲያገኙት አካሉ ላይ የደረሰበትን ጉዳት እንዳሳያቸው ተናግረው ደረቱ፣ ጎኑ ላይና እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የጃዋር ጠባቂዎች የጤና ሁኔታ

የጃዋር የግል ጠባቂዎች ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ አቶ ቱሊ አረጋግጠዋል።

በእስር ቤቱ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዙ የተጠረጠረ ሰው መገኘቱን ተከትሎ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤት እየጠበቁ እንደሆነ ከጠባቂዎቹ አስተባባሪ መስማታቸውን አቶ ቱሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን እስካሁ ግን በቫይረሱ የተያዘ ሰው ስለመኖር የተረጋገጠ እንደሌለ ጠበቃ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ሲል ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *