የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን ተከትሎ አስክሬን በመቀማት እና ሁከት በመፍጠር ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ጃዋር መሃመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
አቶ ጃዋር መሃመድ እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎችም ተጠርጣሪዎች በዛሬው እለት ነው ልደታ ምድብ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እና አራዳ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት።
ከእነ አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ባሳለፍነው ሰኞ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል አይገባም በሚለው ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ ሐምሌ 9 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ በሰጠው መሰረት ነው ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት።
ባሳለፍነው ሰኞ ሐምሌ 6 2012 ዓ.ም ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር በተያያዘ መርማሪ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል ወደ ተለያዩ አካበቢዎች ስልክ በመደወል ሁከት እንዲቀሰቀስና ነዋሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የመንግስት ደጋፊዎች ላይም ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ያስተላለፉበት የስልክ ልውውጥ በማስረጃ መልክ ማግኘቱን አስታውቋል።
ከዛም ባለፈ በአቶ በቀለ ገርባ ቤት ባደረገው ብረበራ ሁለት ሽጉጦች መገኘታቸውን እና ፍቃድ ይኑራቸው አይኑራቸው ገና እያጣራ መሆኑን መርማሪ ፖሊስ ማስታወቁም ይታወሳል።
አቶ በቀለ ገርባ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የለኝም ለቅሶ ለመድረስ በአሸዋ ሜዳ ስሄድ መንገድ በመዘጋቱ ነው የተመለስኩት እና ወደ ኦሮሞ ባህል ማዕከል ያቀናሁት ቢሉም፤ መርማሪ ፖሊስ ግን አስክሬን በሃይል ቀምተው መስቀል አደባባይ ለ10 ቀናት አቆይተው ህዝብን በማስለቀስና ብጥብጥ ለመፍጠር አቅደው የፈጸሙት መሆኑን በምላሹ ጠቅሷል።
ከአቶ በቀለ ገርባ ሁለት ልጆች ጋር በተያያዘ መርማሪ ፖሊስ የአባታቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ሁከት ሲያነሳሱ ነው በቁጥጥር ስር ያዋልኳቸው ያለ ሲሆን፥ ጠበቆቻቸው ደግሞ ልጆቹ ለቅሶ ለመድረስ ከአባታቸው ጋር አብረው ስለተገኙ ብቻ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት ብሏል።
በኤግዚቢትነት ከተያዙት እቃዎች ውስጥ ወደማስረጃነት የሚቀየሩ ጉዳዮችን ለመመርመር ጊዜ እንደሚያስፈልገው ፖሊስ አስታውቋል።
ሰባት መርማሪዎች በተለያዩ የአሮሚያ ክልል አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸው የሰውና የንብረት ጉዳት መጠንን ለመመርመርና ማስረጃ ለመሰብሰብ በማቅናታቸው እነርሱ ይዘው የሚመለሱትንና ሌሎች ማስረጃዎችን ለማሰባሰበ 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል መርማሪ ፖሊስ መጠየቁም ይታወሳል።
ጉዳዮን የተመለከተው ችሎትም የተጠርጣሪዎችን መቃወሚያ አድምጦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል አይገባም በሚለው ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሐምሌ 9 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ አይዘነጋም።
በታሪከ አዱኛ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *