ለኮሮናቫይረስ የሚሆን መድኃኒት ማግኘቷን በፕሬዝዳንቷ አማካይነት ለዓለም ስታስተዋውቅ የቆየችው ማዳጋስካር ሁለት የምክር ቤት እንደራሴዎቿ በወረርሽኙ መሞታቸው ተገለጸ።

አንድ የአገሪቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልና ሌላ የሕዝብ እንደራሴ ናቸው በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ የተገለጸው።

የምክር ቤት አባላቱ በበሽታው መሞትን በተመለከተ ትናንት ዕሁድ ይፋ ያደረጉት የአገሪቱ ፕሬዝደንት አንድሬይ ራጆሊን ናቸው። ፕሬዝደንቱ ከአርቲ የተቀመመ ነው የተባለውን የኮሮናቫይረስ ‘መድኃኒት’ በመገናኛ ብዙሃን ወጥተው በማስተዋወቅ ቀዳሚው እንደሆኑ ይታወቃል።

Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን

ፕሬዝደን ራጆሊን ይፋ ካደረጉት የሁለት የምክር ቤት አባላት ሞት በተጨማሪ 11 የአገሪቱ ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴዎችና 14 የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት በተደረገላቸው የኮሮናቫይረስ ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው መናገራቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የማዳጋስካር መንግሥት ዋና ከተማዋ አንታናናሪቮ በምትገኝበት ዋነኛ ግዛቱ ውስጥ የኮሮናቫይረስ በከፍተኛ መጠን መስፋፋቱን ተከትሎ ቀደም ሲል አንስቶት የነበረውን ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ባለፈው ሳምንት ተመልሶ ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል።

ባለስልጣናት እንዳሉት ጥብቅ የሆነው የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለው በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለውን ወረርሽኝ ለመግታት ነው ብለዋል።

Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ማዳጋስካር ኮቪድ-19ን ሊፈውስ የሚችል መድኃኒት ማግኘቷን በመግለጽ በልበ ሙሉነት በመገናኛ ብዙሃን ላይ እየወጡ ሲያስተዋውቁ እንደነበር ይታወሳል።

አንዳንድ የአፍሪካ አገራትም በእርግጥ መድኃኒቱ ፈዋሽ እንደሆነ ለማወቅ ወደ ሃገራቸው ማስገባታቸው የሚታወቅ ሲሆን እስካሁን ግን ስለመድኃኒቱ ውጤት ያሉት ነገር የለም።

ከአሪቲ የተቀመመው “መድኃኒት” ስላለው ጠቀሜታ በህክምና ባለሙያዎች በኩል የተሰጠ ምንም ማረጋገጫ የሌለ ሲሆን ባለሙያዎችና የጤና ተቋማት ግን ስለመድኃኒቱ ፋዋሽነት የታወቀ ነገር ስለሌለ ሰዉ እንዳይዘናጋ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን

አሁን ደግሞ በሽታው በአገሪቱ ከመስፋፋት አልፎ በወረርሽኙ ሰበብ ሁለት የምክር ቤት አባላት መሞታቸው የመድኃኒቱን ነገር ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል ተብሏል።

በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት ወረርሽኙ በመጀመሪያ በማዳጋስካር መኖሩ ከታወቀ ጀምሮ እስካሁን 4,578 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 34 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሰበብ ህይወታቸውን አጥተዋል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *