“Our true nationality is mankind.”H.G.

በፖለቲካ ወገንተኛነትና ከወደቁ ሃይሎች ጋር ባለ ግንኙነት ለቀረበው ሪፖርት አምነስቲ ግልጽ ውይይትን አሻፈረኝ አለ

በፖለቲካ ወገንተኛነትና ከወደቁ ሃይሎች ጋር ባለ ግንኙነት ለቀረበው ሪፖርት አምነስቲ ግልጽ ውይይትን አሻፈረኝ ማለቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አመለከተ። በቀረበው ሚዛን አልባና የአንድ ወገን ምስክርነት ያካተተ ሪፖርት አምነስቲ በተደጋጋሚ መወቀሱ አይዘነጋም። አምነስቲ ዛሬ በንጹሃን ላይ እነማን በደልና ግፍ እየፈጸሙ እንደሆነ እያወቀ እስካሁን ዝም ማለቱም አነጋጋሪ ሆኗል። ዛሬ ይፋ የሆነው የጠቅላይ አቃቤ ህግ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል። አምነስቲ ግልጽ ምክክርና ውይይት ሊቀበል ያልቻለበትን ምክንያት እስካሁን ይፋ አላደውረገም። የአምነስቲ የምስራቅ አፍሪካ ወኪል አቶ ተክሌ እንደተለመደው በቪኦኤ ያስተባብላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይህን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል
በግንቦት 2012 ዓም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ድርጅት “Beyond Law Enforcement: Human Rights Violations by Ethiopian Security Forces in Amhara and Oromia”. በሚል ርዕስ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት አውጥቷል። የሪፖርቱን መውጣት ተከትሎ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ከራሱ፣ ከሁለቱ ክልሎች ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ መስሪያ ቤቶች እና የፖሊስ መርማሪዎች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጣ አጣሪ ቡድን በማደራጀት የሪፖርቱ ይዘት የተዘረዘሩ የመብት ጥሰቶችን እውነተኛነት እንዲጣራ አድርጓል።
የአጣሪ ቡድኑን ግኝቶች እና የሪፖርቱን ይዘት በተመለከተ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ምክክር ለማድረግ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ እና ይህ ጥያቄም ለተቋሙ የደረሰ መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም እስካሁን በቂ ምላሽ ለማግኘት አልተቻለም። በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ መሪነት በተከናወነው የማጣራት ተግባራት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መንግስት ሕግ ለማስከበር የሚወስደውን እርምጃዎች ሁሉ የሰብዐዊ መብት ጥሰት አድርጎ የማጠልሸት ዝንባሌ የሚስተዋልበት፣ በአብዛኛው ገለልተኘነት የጎደለው፣ የማስረጃ ምዘና ችግር ያለበት፣ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና ዐውድ ያላገናዘበ እና ሌሎችም መሰርታዊ ግድፈቶች ያሉበት ቢሆንም በዘገባው ውስጥ ከተካተቱት የመብት ጥሰት ወቀሳዎች የተወሰኑት በከፊልም ቢሆን ተዓማኒነት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል።
ከነዚህ በከፊል ተዐማኒነት ካላቸው ጉዳዮች መካከል በርካቶቹ ጉዳዮች ሪፖርቱ በአምነስቲ ከመውጣቱም በፊት በመንግስት ታውቀው ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የምርመራ ስራ ሲከናወንባቸው የነበሩ ናቸው። ሆኖም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከዚህ ቀደም ከሚታወቅባቸው ጥራታቸውን የጠበቁ እና ተዓማኒነት ካላቸው ሪፖርቶቹ በተለየ ይህ የአሁኑ ሪፖርት የራሱን የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን እንኳን ሰብዓዊ መብት ሪፖርት አዘገጃጀት መመሪያዎች እና መስፈርቶችን የማያሟላ ነው። ሪፖርቱ ገለልተኛነት የጎደለው፣ ጥቂት እና ተዓማኒነት የጎደላቸውን ወይም ወገንተኛ የሆኑ ምስክርነቶችን በመያዝ እጅግ ውስብስብ በሆኑ ግጭቶችና የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ የተሳሳቱ መደምደሚያዎች ላይ የሚደርስ ነው።
ሪፖርቱ በህግ ማስከበር ሂደት በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ሁሉ የመብት ጥሰት አድርጎ ለማቅረብ ባደረገው ጥረት መሬት ላይ የሌሉ ጉዳዮችን እንዳሉ በማስመሰል የሚያቀርብ መሆኑ እንዲሁም አውድን ሳያሳይ ማለፉ በሪፖርት አዘጋጆቹ ዘንድ ያለውን የፖለቲካ ወገንተኛነት የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም የመብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ያላቸው ጉዳዮች ዙሪያ በወቅቱ የነበረውን አውድ ሳያቀርብ ማለፉ፣ ለምሳሌ የታጠቁ እና በሕቡዕ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በተለይም በጉጂ ዞን በህዝብ እና በመንግስት ላይ እየፈፀሙ የነበውን ወንጀል እና ጥቃት አለመግለፁ፤ በተቃርኖዎች የተሞላ መሆኑ ለአብነት ያህል መንግስት የዜጎቹን ደህንነት የማስከበር ሃላፊነቱን አልተወጣም የሚል ወቀሳ እያቀረበ መንግስት ይህን ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ደግሞ የሰብዐዊ መብት ጥሰት አድርጎ መተቸቱ እና እውነት ያልሆኑ መረጃዎችን ማካተቱ እንዲሁም በገሃዱ ዓለም የሌሉ ምስክሮችን ስም እና ሃላፊነት እየጠቀሰ መቅረቡ ታይቷል። ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የነዚህ ግድፈቶች መፈጠር የአጋጣሚ ስህተት ሳይሆን አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የሪፖርቱ ጸሃፊዎች ከዚህ ቀደም በስልጣን ላይ የነበሩና አሁን ለውጡን ለማደናቀፍ እየሰሩ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የነበራቸው የሚታወቅ ንቁ ተሳትፎ ጋር ተያይዞ ሆን ተብሎ የተፈጸመ እንደሆነ ያምናል። ስለሆነም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቀጣይ ከመንግስት ጋር ለሚኖረው በጎ ትብብር እና የስራ ግንኙነት ሲባል የዚህን ሪፖርት አዘገጃጀት በተመለከተ የውስጥ ምርመራ እንዲያከናውን እና እንዲፈትሽ ጥሪ እናቀርባለን። በሪፖርቱ ላይ እነዚህ ጉልህ ስህተቶች የተስተዋሉ ቢሆንም መንግስት በሪፖርቱ ከተጠቀሱት የመብት ጥሰት ወቀሳዎች መካከል ተዓማኒነት ባላቸው ጥቂት ጉዳዮች ላይ ቀደም ብሎ የጀመረውን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች ይበልጥ እንዲከበሩ ከሃገራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ትብብር ይቀጥላል።
ሃገራችን ኢትዮጵያ የዜጎች መብት በሚገባ የሚከበርባት እንድትሆን የሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት በተለይም የሕጎች እና ተቋማት ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉ፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው የተሰደዱ እና የታሰሩ ዜጎች ነጻ እንዲወጡ እና ወደሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ፣ በሲቪል ማህብረሰብ የመደራጀት መብት፣ በሚድያ እና በፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻነት አንጻር ተጨባጭ እና አበረታች ውጤት የተገኘበት ቢሆንም፣ ስር ከሰደዱ እና እጅግ ውስብስብ ከሆኑ የተለያዩ ተግዳሮቶች የተነሳ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል የሚደርገው እንቅስቃሴ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ነው ለማለት አይቻልም። ማሰብ፣ ሃሳብን መግለጽ፣ መናገር፣ መከራከር፣ መደራጀት፣ መቃውም እና መተቸት፣ ብሎም መፎካከር የሚቻልበት ዲሞክራሲያዊ መድረክ እየሰፋ ቢሄድም ይህንን መድረክ ትቶ በግጭት እና በግርግር፣ ሰላማዊ ዜጎችን በማጥቃት እና ዘግኛኝ የሆኑ ኢሰብዓዊ ተግባራትን እየፈጸሙ ህዝብ በማሸበር የተሰማሩ አንዳንድ ቡድኖች ባለፉት ሁለት አመታተ ውስጥ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል ተስተውለዋል። እነዚህ ተግዳሮቶች ያሉ ቢሆንም የኢፌድሪ መንግስት በሙሉ አቅሙ እና በህዝብ ተሳትፎ በሃገሪቱ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እና የዜጎች መብቶች እንዲከበሩ አበክሮ እየሰራ እያደረገ ይገኛል፣ ይህንንም ጥረቱን አጠንክሮ ይቀጥላል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያሰማራው አጣሪ ቡድን ግኝቶች እና ምልከታዎች የተጠናቀሩበት ዘገባ በመጪው ሳምንት በተቋሙ ድህረ ገጽ እና የማህበራዊ ሚድያ ገጾች ለህዝብ ይፋ የሚደረግ ስለሆነ፣ ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ዘገባውን እንዲያነቡ እንጋብዛለን።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
ሐምሌ 11 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው
0Shares
0