“Our true nationality is mankind.”H.G.

የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አግተው ለኦነግ ሸኔ አመራሮች ሰጥተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሠረተ

NtJDO

ሪፖርተር – በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተፈጠረውን ግጭት በመፍራት ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ እያሉ ኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ቄሌም ወለጋ ዞን ሰዮ ወረዳ ሜንኮ ቀበሌ ቧንቧ በተባለው አካባቢ  ታፍነው የተወሰዱ የአማራ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎችን፣ ለኦነግ ሸኔ አመራሮች አስረክበዋል የተባሉ 17 ተጠርጣሪዎች ላይ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ተከሳሾች 17 ቢሆኑም፣ በቁጥጥር ሥር ውለው በክስ ላይ የሚገኙት ግን ዘጠኝ ናቸው፡፡ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በኮሮና ቫይረስ በመጠርጠራቸው ባይቀርቡም ሰባቱ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

ብጥብጥ በመፍራት ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ኦብሳ ፉፋ በተባለው ተከሳሽ በኮድ-3 34629 ኦሮ ዶልፊን ተሽከርካሪ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩትን ተማሪዎች ሞንሞን በላይ፣ ጤና ዓለም ሙላቴ፣ ሳምራዊት ቀሬ፣ አሳቤ አያልና የአካባቢው ነዋሪ የሆነችውን ትዕግሥት መሳይን ጨምሮ ለጊዜው ስማቸው ያልታወቁ ተማሪዎችን ተከሳሾቹ አፍነው ወስደዋቸዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

ከሊፋ አብዱራህማን፣ ሬድዋን ተማም፣ አብዲ ኢብራሂም፣ ናስር መሐመድ፣ ዮሴፍ ጅራታ፣ አውሉ ጅብሪል፣ ነብዩ ባባከርና ጋዲሳ የተባሉት ተከሳሾች ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ተሽከርካሪውን በዱላና በጦር መሣሪያ አስገድደው በማስቆምና ቁልፉን በመንቀል፣ የኦሮሚኛ ቋንቋ የማይናገሩትን ብቻ በመለየት እየደበደቡ ከመኪናው አስወርደው በአካባቢው ወደሚገኘው ጫካ ይዘው በመሄድ ለኦነግ ሸኔ የበላይ አመራሮች ማስረከባቸውን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ኅዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ቄሌም ወለጋ ዞን አንፊሎ ወረዳ ሱዲ ቀበሌም አካባቢ የዩኒቨርሲቲውን ግጭት በመፍራት ወደ ቤተሰቦቸው በጋምቤላ ከተማ አቅጣጫ በሰሌዳ ቁጥር 3- 35136 ኦሮ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተሳፍረው የነበሩ የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑትን ተማሪዎች በላይነሽ መኮንን፣ ስርጉት ጌጤ፣ ውዴ ግርማ፣ ግርማሽ የኔነህ፣ አስካሉ (የማታ) ቸኮል፣ ግርማው ሀብቴና ለጊዜው ያልተለዩ ተማሪዎችን ለኦነግ ሸኔ አመራሮች እንዳስረከቧቸው በክሱ ተብራርቷል፡፡ አጋቾቹ ደበላ ቀንአ፣ ኩሌሼ ባይሳ፣ ኦቦ አስፋው ገመዳ፣ ዳዊት ታዬ ምሬሳና ሌሎችም ተሽከርካሪውን በመንገድ ላይ በማስቆምና ኦሮሚኛ ቋንቋ የማይችሉትን ለይቶ በማስወረድ ደብድበው በመጥለፍ፣ ዳዊት ታዬና ኦብሳ ፉፋ ከሌሎች የኦነግ ሸኔ አባላት ጋር በመውሰድ ለአመራሮቹ ማስረከባቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ)፣ 35፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(3) ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ኅዳር 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በቄሌም ወለጋ ዞን ሰዮ ወረዳና አንፊሎ ወረዳ ሞንሞን በላይ፣ ጤና ዓለም ሙላቴ፣ ሳምራዊት ቀሬ፣ አሳቤ አያል፣ ትዕግሥት መሳይ፣ በላይነሽ መኳንንት፣ ስርጉት ጌጤ፣ ውዴ ግርማ፣ ግርማሽ የኔነህ፣ አስካሉ (የማታ) ቸኮል፣ ግርማው ሀብቴ፣ ቢተውልኝ አጥናፍ፣ ገብረ ሥላሴ ሞላ፣ ገደባ ገነት፣ መሰለች ከፍያለውና ዘመድ ብርሃን የተባሉ 18 ተማሪዎችን በትግል ስማቸው ጃል መሮ፣ ጃል ሮባ፣ ጃል ጉራራ፣ ጃል ኡርጂና ጃል ፈንድሼ ለተባሉና ለጊዜው ላልታወቁ የሸኔ አመራሮች አሳልፈው መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ደበላ ቀንአ፣ ኩለሴ ባይሳ፣ አቦ አስፋው ገመዳ፣ ዳዊትና ሌሎች ለጊዜው ያልታወቁ በርካታ የኦነግ ሸኔ አባላት በዱላና በጦር መሣሪያ ተማሪዎቹን ጠልፈውና አግተው፣ ከሱዲ ቀበሌ ወደ ኤሾ ከተማ ኅዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ተፈራ ሂካ የተባለው የአካባቢው የኦነግ ሸኔ አስተባባሪ የታገቱትን ተማሪዎች የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (12)ን በመተላለፍ በቤቱ ማሳደሩን ክሱ ያስረዳል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ተማሪዎቹን ለኦነግ ሸኔ አመራሮች አሳልፈው በመስጠትና ያሉበትን ባለማሳወቅ የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ሰባት ተከሳሾች ዓርብ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት የቀረቡና የክስ ቻርጅ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ጠበቃቸውን አማክረው እንደሚመጡ በመግለጻቸው በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩትም ክሱ በፖሊስ በኩል ከመጥሪያ ጋር ደርሷቸው እስከሚቀርቡ ለመጠበቅና ክስ ለማንበብ ለሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

FacebookTwitterLinkedInShare

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0