“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጃዋር “ጉዳዩ ፖለቲካዊ ነው፤ የሚበጀው ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው” ሲል ፍርድ ቤት ተናገረ፤ ከቴሌ ዕውቅና ውጪ የሚሠራ የሳተላይት መቀበያ ተገኘበት

NtJDO

በወንጀል ተጠርጥሮ በህግ ጥላ ስር የሚገኘው ጃዋር መሐመድ ቴሌኮም የማያውቀው የሳተላይት መሳሪያ ቤቱ መገኘቱን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት አስታወቀ። ይህ የተገለጸው ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ባስቻለው ችሎት ነው።  ቀደም ባለው ችሎት አቶ ጃዋር ቤታቸው በፍርድ ቤት ፈቃድ ሲበረበር በአካል ተገኝተውና አይናቸው እያየ በቪዲዮ  እየተቀረጹ መሆኑን ፖሊስ አስታውቆ ነበር። በሐምሌ 9 ችሎት ጉዳዩ ፖለቲካዊ በመሆኑ በንግግር ሊቋጭ እንደሚገባው ሲገልጹ ፖሊስ ተገኘባቸው ስላላቸው መሳሪያዎች ማስተባበያ አልሰጡም።

ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኘው ጃዋር ሲራጅ መሃመድ የተከሰሰበት ጉዳይ “ፖለቲካዊ ነው፤ ይህ ችግር የሚፈታው ቁጭ ብሎ በመወያየት ነው” በማለት ለፍርድ ቤቱ ተናገረ።

የወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ፖሊስ የጀመረውን ምርመራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ከጃዋር ጋር አብሮ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎችም ተጠርጣሪዎች ሐሙስ ዕለት ነው ልደታ ምድብ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እና አራዳ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት።

ይህንንም ተከትሎ የጃዋር ጠበቃ ደንበኛቸው በዋስ ከእስር ቤት ውጪ ሆኖ ጉዳዩን መከታተል እንዲችል እንዲፈቀድለት ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጥያቄ ተቀብሎታል።

በዚህ ጊዜ የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኛቸው ምግብ ከቤተሰቡ የሚቀርብለት ቢሆንም፤ ግንኙነታቸው በርቀት በመሆኑ ባለበት ከርቀት አይቶ የመለየት ችግር ቤተሰቦቹን በቅርበት እንዲያገኝ እንዳልተፈቀደለት ለችሎቱ አቤት ብለዋል።

ፖሊስም ይህንን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ታሳሪዎችና ጠያቂዎች መካከል መቀራረብ እንዳይኖር የተደረገው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር በወጣው ደንብ መሰረት መሆኑን ጠቅሶ ምላሽ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ጃዋር ታስሮ የሚገኝበት ክፍል በቂ ብርሃን የሌለው መሆኑና መጸዳጃ ቤት የመጠቀም ችግርን በማንሳት ጠበቃው አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም ደንበኛቸው ጥፋተኝነታቸው ገና ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ምስላቸው እየቀረበ ዘገባዎች እንደሚቀርቡና ፍርድ ቤቱም ይህንን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ለእስረኞች መጸዳጃ ቤትን በተመለከተና በማረፊያ ክፍሎች ውስጥ ያለውን ብርሃን በተመለከተ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ያዘዘ ሲሆን፤ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ስለቀረበው አቤቱታም ጠበቆች ያሏቸውን ተቋማት በስም ለይተው ስላላቀረቡ አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል።

በዚህም መሰረት ፖሊስ ለምርመራ የጠየቀውን የ14 ቀናት ጊዜ ፈቅዶ ጉዳዩን ለመመልከት ሐምሌ 23/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ቢቢሲ አማርኛ ሳይዘግበው ያለፈው ቁልፍ መረጃ ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያው ችሎት ለፖሊስ በሰጠው ቀናት ምን ምርመራ እንዳደረገ የጠየቀው ነበር። የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የምርመራ ቡድንም የሚከተለውን መረጃ ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል፤

  • የድምጻዊ ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ ተጠርጣሪው ጃዋር በአዲስ አበባና በኦሮሚያ የብሔርና የሃይማኖት የግጭት መቀስቀሱን ያስረዱ የ34 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፤
  • የወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር የሃጫሉን አስከሬን ከቡራዩ ኬላ በመቀማት በከተማዋ ከነበሩት የጸጥታ ኃይላት ጋር የእርሱ የታጠቀ ቡድን ተኩስ መክፈቱን የመሰከሩ መኖራቸውና ቃላቸውን መቀበሉን፤
  • አስከሬኑ የምኒልክ ሃውልት ፈርሶ መቀበር አለበት በማለት ወደ ኦሮሚያ ብልጽግና ጽ/ቤት ያመራው የወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር የሚመራው የታጠቀ ቡድን በከፈተው ተኩስ አንድ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባል መገደሉን፣ ሦስት ደግሞ መቁሰላቸውን፤ ይህም በሰው 10 ምስክርና በፎረንሲክ ምርመራ ማረጋገጡን፤
  • በኦኤምኤን ሚዲያ በወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር የተጠራውን የዓመጽ ጥሪ ከብሮድካስት ሚዲያ ባለሥልጣን መቀበሉን፤
  • ከወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር እና ከቡድኑ 10 ክላሽ፣ 1 ቺቺ፣ 10 የተለያዩ ሽጉጦች፣ 9 የሬዲዮ መገናኛ፣ ሕጋዊ አለመሆናቸውን በሚመለከተው አካል ማረጋገጡን፤
  • የወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር የሚያስተላልፋቸውን የወንጀል መልዕክቶችን ተከትሎ በአዲስ አበባ 14 ሰዎች እንዲሁም በኦሮሚ ክልል 167 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ምርመራው ማረጋገጡን፤
  • በኦሮሚያ ክልል የወደመው ንብረት ለጊዜው ያልታወቀ ቢሆንም በአዲስ አበባ ግን ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን በምርመራው ማረጋገጡን፤
  • የወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር የስልክ ልውውጡ ከግጭቱ ጋር የሚያሳየውን ተሳትፎ ምርመራው ማመላከቱን፤
  • ከወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር ቤት የተገኘው የሳተላይት መቀበያ ጨምሮ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች በባለሙያ ማስመርመርና የወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር ከኦኤምኤን ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ ብጥብጥ እንዲፈጠር ከሚሹ ኃይሎች ጋር ያለውን ግንኙነት በቀጣይ የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን፤
  • ግጭት በተከሰተባቸው ቦታዎች የተላኩት 14 ቡድኖች የሚያመጡትን መረጃ ውጤት በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ቡድኑ ጠቅሶ ሌሎች ግብረአበሮችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መሆኑን

በመጥቀስ የምርመራ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የጽሁፍ ሪፖርት አስታውቋል።

ፍርድቤቱ ይህንን ከፖሊስ ከሰማ በኋላ የወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር ሲራጅ መሐመድ እንዲናገር ተፈቅዶለት የተናገረው “የተተኮሰ ጥይትም ሆነ የሞተ ሰው የለም፤ ጉዳዩ ድራማ ነው፤ የሚበጀው ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው፤ የአርቲስቱን አስከሬን ወደ አምቦ ለመውሰድ መንገድ ስለተዘጋጋ ወደኋላ ተመለስን እንጂ ሌላ ተልዕኮ አልነበረንም፤ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ነው፤ ይህ ችግር የሚፈተታው በፖለቲካዊ ውይይት ነው” ብሏል።

በሌላ በኩል ከእነ በቀለ ገርባ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል አይገባም በሚለው ላይ ፍርድ ቤቱ ሐሙስ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ባሳለፍነው ሰኞ ሐምሌ 6፣ 2012 ዓ.ም ከወንጀል ተጠርጣሪው በቀለ ገርባ ጋር በተያያዘ መርማሪ ፖሊስ በቀለ በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት በኦሮሚያ ክልል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ስልክ በመደወል ሁከት እንዲቀሰቀስና ነዋሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የመንግሥት ደጋፊዎች ላይም ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ያስተላለፈበት የስልክ ልውውጥ በማስረጃ መልክ ማግኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።

ከዚያም ባለፈ በወንጀል ተጠርጣሪው በቀለ ገርባ ቤት ባደረገው ብረበራ ሁለት ሽጉጦች መገኘታቸውን እና ፍቃድ ይኑራቸው አይኑራቸው ገና እያጣራ መሆኑን መርማሪ ፖሊስ ማስታወቁም ይታወሳል።

የወንጀል ተጠርጣሪው በቀለ ገርባ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የለኝም ለቅሶ ለመድረስ በአሸዋ ሜዳ ስሄድ መንገድ በመዘጋቱ ነው የተመለስኩት እና ወደ ኦሮሞ ባህል ማዕከል ያቀናሁት ቢልም፤ መርማሪ ፖሊስ ግን አስክሬን በኃይል ቀምቶ መስቀል አደባባይ ለ10 ቀናት አቆይቶ ህዝብን በማስለቀስና ብጥብጥ ለመፍጠር አቅዶ የፈጸው መሆኑን በምላሹ ጠቅሷል።

የወንጀል ተጠርጣሪው በቀለ ገርባ ሁለት ልጆች ጋር በተያያዘ መርማሪ ፖሊስ የአባታቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ሁከት ሲያነሳሱ ነው በቁጥጥር ሥር ያዋልኳቸው ያለ ሲሆን፥ ጠበቆቻቸው ደግሞ ልጆቹ ለቅሶ ለመድረስ ከአባታቸው ጋር አብረው ስለተገኙ ብቻ ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ብሏል።

በኤግዚቢትነት ከተያዙት እቃዎች ውስጥ ወደማስረጃነት የሚቀየሩ ጉዳዮችን ለመመርመር ጊዜ እንደሚያስፈልገው ፖሊስ አስታውቋል።

ሰባት መርማሪዎች በተለያዩ የአሮሚያ ክልል አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸው የሰውና የንብረት ጉዳት መጠንን ለመመርመርና ማስረጃ ለመሰብሰብ በማቅናታቸው እነርሱ ይዘው የሚመለሱትንና ሌሎች ማስረጃዎችን ለማሰባሰበ 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል መርማሪ ፖሊስ መጠየቁም ይታወሳል።

ጉዳዮን የተመለከተው ችሎትም የወንጀል ተጠርጣሪው በቀለ ገርባ ላይ 11 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሰጥቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላኛው የወንጀል ተጠርጣሪው እስክንድር ነጋ አዲስ አበባ ውስጥ ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ በማድረግ፣ ሰዎችን በማሰማራት፣ ገንዘብ በማሰራጨት፣ የዓመጽ ቅስቀሳ በማድረግና ይህንንም ተከትሎ ለሞቱን 14 ሰዎች ተጠያቂ መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።

የወንጀል ተጠርጣሪው ጃዋር ሲራጅ መሃመድ ከፍርድ ሥርዓቱ ይልቅ “መፍትሔው ቁጭ ብሎ መወያየት ነው” በማለት ያቀረበውን የመፍትሔ ሃሳብ ፍርድቤቱ ምላሽም እንኳ ሳይሰጥበት ወደ ማረፊያ ክፍሉ እንዲወሰዱ በማድረግ ችሎቱ አጠናቅቋል።

ከአገር ውስጥ ሚዲያዎች በዘገቡት ቪዲዮ ላይ የወንጀል ተጠርጣሪዎቹ በቀለ ገርባ እና ጃዋር ሲራጅ መሃመድ በብረት ለበስ ወታደራዊ መኪና ተጭነው ተወስደዋል።

(ዜናውን ያጠናቀርነው ከኢቲቪ፣ ከአዲስ ሚዲያ፣ ከቢቢበሲ አማርኛ ነበር)

ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0