በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሐረማያ ከተማ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከ5 ሺህ በላይ ህገ ወጥ የሞባይል ሲም ካርድ ፣ መድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶች መያዙን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ተጠባባቂ ኃላፊ ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ለኢዜአ እንደገለፁት ህገ ወጥ ቁሳቁሶቹ ሐምሌ 12 ቀን 2012 ዓም የተያዙት በሐረማያ ከተማ 02 ቀበሌ በተለምዶ ፍልስጤም ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው ።

ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው የተቀናጀ ብርበራ ከአንድ ተከራይ ግለሰብ መኖሪያ ቤት  ከ5 ሺህ በላይ የተከፈተና ያልተከፈተ የሞባይል ሲም ካርድ ተይዟል ።

እንዲሁም የተለያዩ ህገ ወጥ መድሃኒቶች ፣ ላፕቶፖች ፣ ዲጂታል ካሜራዎች ፣ ቤንዚን የመሳሰሉ ቁሳቁሶች በብርበራው ወቅት ተይዟል ።

ተጠርጣሪው ተከራይና የቤት አከራዮቹ ለጊዜው መሰወራቸውን ኢንስፔክተሩ ገልፀው፤ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በፊትም ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ህገ ወጥ የሞባይል ሲም ካርድ በዞኑ ባቢሌ ከተማ ከአንድ ግለሰብ ቤት መያዙን ገልፀው፤ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በፍርድ ሒደት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል ።

በኢትዮ ቴሌኮም የማእከላዊ ምስራቅ ሪጅን ኦፕሬሽናል ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሰይድ እንደገለፁት ድርጊቱ በአገር ፣ በህዝብና በድርጅቱ ላይ ጉዳትና ኪሳራ የሚያስከትል ተግባር በመሆኑ ህገ ወጥ የሲም ካርድ ዝውውር ወንጀልን ለመቆጣጠር ከፖሊስና ከህብረተሰቡ ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በሀረማያ ከተማ የተያዘው ህገ ወጥ ሲም ካርድ ከየትኛው የሽያጭ ማእከል እንደወጣ ማወቅ ስለሚቻል አስፈላጊውን መረጃ በማጣራት ለፖሊስ እንዲደርስ እናደርጋለን ብለዋል ።

(ኢዜአ)

Related stories   የአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛት መርዝ የሚያፋጃቸው ካሜሮናውያን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *