ተጠርጣሪዎቹ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው ተናገሩ

ከሰኔ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በሞቱ ሰዎችና በወደመ የመንግሥትና የግል ንብረት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ ይልቃል ጌትነት ላይ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆ ተፈቀደ፡፡

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በተለይ በአዲስ አበባ ከአምስት በላይ በሚሆኑ ክፍላተ ከተሞች በተፈጠረ የግድያና የንብረት ውድመት የተጠረጠሩት የኢትዮጵያውያን አገራዊ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀመንበር ይልቃል (ኢንጂነር)፣ የምክር ቤት አባል ናቸው የተባሉት አቶ ወንድአለ አስናቀና በወንጀሉ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩት አቶ ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ ከሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠበቃቸው አቶ አዲሱ ጌታነህ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ሦስቱም ተጠርጣሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ ሐምሌ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ መርማሪ ቡድን በጋራ ባቀረቡት የ14 ቀናት የምርመራ ሪፖርት፣ ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች በተሳተፉበት የአመፅና የረብሻ ድርጊቱ የአሥር ሰዎች ሕይወት አልፏል ማለቱን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የመንግሥትና የግል ንብረት መውደሙን፣ ይኼንንም በሰው ምስክር እንዳረጋገጠ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ጠበቃው ገልጸዋል፡፡

የይልቃል (ኢንጂነር) ቤት ሲበረበር ሲዲዎች፣ ፍላሾችና ስልኮች (ሞባይሎች) ማግኘቱን መርማሪ ቡድኑ ገልጾ፣ የቴክኒክ ምርመራ ለማድረግ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ለፌዴራል ፎረንሲክ ወንጀል ምርመራና ለኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ለምርመራ ልኮ ውጤት እየጠበቀ መሆኑን፣ ግብረ አበሮችን ለመያዝና ቀሪ ምርመራዎችን ለማድረግ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት መጠየቁን ጠበቃው ተናግረዋል፡፡

እነ ይልቃል (ኢንጂነር) ባቀረቡት የመቃወሚያ ምላሽ መርማሪ ቡድኑ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ በመቀስቀስና በመሳተፍ›› ከማለት ውጪ፣ ምን አድርገው እንደተጠረጠሩ የገለጸው ነገር ስለሌለ በደፈናው በመግለጽ እንዲታሰሩ ማድረግና ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ  ተገቢ አለመሆኑን በማስረዳት ቡድኑ በግልጽ እንዲያስረዳ ጠይቀዋል፡፡ እነ ይልቃል (ኢንጂነር) በታሰሩበት ሥፍራ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሁለት እስረኞችን ስም በመጥቀስ ሥጋት እንደገባቸው ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውንም ጠበቃው ገልጸዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፣ መርማሪ ቡድኑ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር አብረው ያልተካተቱ የሌሎች ተጠርጣሪዎችን የምርመራ መዝገብ እንደ ማስረጃ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁሞ፣ በሦስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ብቻ የሠሩትን ወይም የተጠረጠሩበትን የወንጀል ድርጊት የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ከተጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ 11 ቀናት በመፍቀድ ለሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሪፖርተር ታምሩ ጽጌ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “በተለምዶ ‘ሸኔ’ የሚባለው ራሱን ‘የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት’ ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *