ራሳቸውን ቀይረው የተመረጡ ቦታዎችን ለማጥቃት፣ ባለስልጣናትን ለመገደልና ክልሉን ለማተራመስ ሰልጥነውና ተልዕኮ ተቀብለው ወደ አማራ ክልል የገቡ የጥፋት ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የመንግስት መገናኛዎች የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጠቅሰው ዘገቡ። በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ማን እንደለካቸው ፍንጭ ተሰጥቷል።
በአማራ ክልል ውስጥ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ተልእኮ ተቀብለው ወደ ክልሉ ሰርገው የገቡ 85 የጥፋት ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ያስታወቁት በማእከላዊና በሰሜን ጎንደር ዞኖች የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን ትናንት በመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው።
የጥፋት ሃይሎቹ የክልሉን ሰላም በማደፍረስ ክልሉን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ተልእኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡
እነዚህ ጸረ-ሰላም ሃይሎች በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሰርገው የገቡት ጸበልተኛ፣ መነኩሴና የአዕምሮ ህሙማን በመምሰል እንደሆነ የጠቆሙት ርእሰ መስተዳድሩ እኩይ አላማቸውን ሳያሳኩ በህብረተሰቡ ትብብርና ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
የጥፋት ተልእኮ በመቀበል ወደ ክልሉ ገብተው የነበሩት እነዚህ ጸጉረ ልውጥ ግለሰቦች ታዋቂ ሰዎችንና ከፍተኛ አመራሮችን የመግደል፤ በሃይማኖት ተቋማትና በታሪካዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት ለማድረስ እቅድ ይዘው የገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ለውጡ የገፋቸው የህወሓት ቡድን ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ዳግም ወደ ስልጣናቸው ለመመለስ ሌት ተቀን እየሰሩ ናቸው ያሉት አቶ ተመስገን እኩይ ሴራቸውን በማክሸፍ ህዝቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
የስልጣን ተስፈኛው ቡድን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል አማራና ኦሮሞን እርስ በእርስ በማጋጨት ሀገር አፈራርሶ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሸረበው ሴራ ከሽፎበታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የፌደራሉ መንግሰት በሌሎች አካባቢዎች የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ አሁንም በቀሩት አካባቢዎች መውሰድ ይገባዋል ሲሉም ርእሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
ትጥቃችንን ሳንፈታ ወደ ማንም ጣታችንን ሳንቀስር ውስጣችን አጥርተንና አንድነታችንን ጠብቀን የሚመጡ ስጋቶች ካሉም በጋራ እየመከትን ልማታችንን ማስቀጠል ለነገ የማይባል ተግባራችን መሆን አለበትም ብለዋል፡፡
የአማራና የትግራይ ህዝብ ለዘመናት ተዋልዶና ተጋብቶ በታሪክ ሂደትም ተጋምዶ የኖረ ህዝብ መሆኑን የጠቆሙት ርእሰ መስተዳድሩ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት ለማስነሳት የሚጥሩ ሃይሎችን እረፉ ሊላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
መጪው ጊዜ የአማራ ህዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር አብሮና ተባብሮ የሚኖርበት ዘመን መሆኑን ጠቅሰው ብልጽግና ፓርቲም ይህን ተልእኮ ከዳር ለማድረስ ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ህዝብ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን የማንነትና የድንበር ጉዳዮችም በስርዓት መመለስ አለባቸው በሚል የድሮው ብአዴን የአሁኑ ብልፅግና አቋም ይዞ ችግሩ እንዲፈታ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
እነዚህን ጥያቄዎች አድበስብሶ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የተፈፀመው ጥፋት በማስተካከል ብልፅግና ፓርቲ በህግ አግባብ እንዲፈታ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
ፋኖነት በአማራ ህዝብ ልብ ውስጥ የታተመ የክብር ስም ነው ያሉት አቶ ተመስገን ይህን የጀግንነት መለያ ስም ህዝቡ በክብር እንዲጠብቀውም አሳስበዋል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በሁለቱ ዞኖች ስር ባሉ ሁለት ወረዳዎች ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን መመረቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *