ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የዛሬዋ ትግራይ የትናንቷ አይደለችም – Animut Abraham

መነሻ አንድ: ከሻዕቢያ የስሌት ስህተት መማር
ከዚህ ቀደም እንዳነሳሁት ሕወሓትና ሻዕቢያ የአፍሪካ ቀንድን የመቆጣጠር ተፎካካሪዎች ሲሆኑ ሁለቱም የየራሳቸውን ብሔረ-መንግስት ለመገንባት የተሰለፉ ናቸው።
በሕወሓትና ሻዕቢያ መካከል ያለው ልዩነት : ሻዕቢያ ብሔረ-ኤርትራን ከኢትዮጵያ ተነጥሎ ለመገንባት ሲወስን : ሕወሓት ግን ብሔረ-ትግራይን በኢትዮጵያ ፌደሬሽን ውስጥ ለመገንባት መወሰናቸው ነው።
በሕወሓት እምነት የትግራይ ነፃ ሪፐብሊክነት ሲያስፈልግ የሚደረስበት ብቻ ሳይሆን በቀላል ህጋዊ ሒደት ለማሳካት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ በሕገመንግስቱና የቋንቋን መስመር በተከተለ ፌደራሊዝም አመቻችቶ አስቀምጧል።
መነሻ ሁለት :- Economic Humiliation የፈጠረው ቁጭት
ሕወሓታውያን በትግላቸው ወቅት የትግራይ ኢኮኖሚ ከጦርነት ታሪካዊ ጫና እና ነባራዊ ይዞታ የሚነሳ ቁጭት በግልፅ አስቀምጦ ብሔረ-ትግራይን አልሟል።
“..ሕዝባችን ስደትና ሽር**ና መለያው የሆነ Dehumanization መገለጫው ሆኗል” በሚል በ69ኙ ማኒፌስቶ እስከማስቀመጥ ሔዷል።
ከዚያም በላይ በደርግ ሹማምንትና ተቃዋሚዎቻቸው ትግራይን በተመለከተ የሚቀርበው ፍረጃና Humiliation የፈጠረው ቁጭት አለ። ‘ከአንበጣና በለስ እስከ ድንጋያማና ጠመኔ እንኳ የማታማርተዋ ትግራይ’ ብዙ ተብሏል።
መንግስቱ ኃ/ማርያም ደግሞ “ርሃብተኞች ችጋራሞች የምንባለው ከዚሁ አካባቢ በሚመጣ ችግር ነው : በተቀረው የኢትዮጵያ ክልል ርሃብ የለም” በማለት ቁጭቱን የሕዝብና አካባቢ ገፅታ እንዲላበስ አርጎታል።
ስለሆነም ሕወሓት ብሔረ-ትግራይን ለመገንባት ሲነሳ ይህንን ቁጭት ይዞ ነውና በሻዕቢያ መንገድ ሊያሳካው እንደማይችል ያውቅ ነበር።
👉 ያለኢኮኖሚ እና ገበያ የሚታሰብ ብሔረ-መንግስት ግንባታ የለም።
የ1983ቷ ትግራይ “ምንም” ነበረች። ምናልባት ሶስት highschool : አንድ ፋብሪካ: እዚህ ግባ የማይባል መሠረተ ልማት እና ጦርነት ያስመረረው ድሃ ማህበረሰብ ነበር። ይህን ይዘህ ነፃ ሪፐብሊክ እብደት ነበርና ከሻዕቢያ ብዙ ርቀት የተሻለ ውሳኔ ወሰኑ።
የብሔረ-ትግራይ ግንባታ የሠመረ ይሆን ዘንድ የት ምን እንደሚሠራ በረሃ እያለ አስቦ የተነሳ ነው። እናም ድህረ-83 ዋናውን ትግል ወደኢኮኖሚ አዞረው።
አሁን ከሩብ ክፍዘ የፌደራል ስርዓት ቁጥጥር በኋላ ግን ትግራይ በብዙ ለመለወጧ ማሳያዎች ብዙ ናቸው። እርግጥ ነው የዛሬዋ ኢትዮጵያም የተለየች ነች።
❶ የብሔር ግንባታው ቁልፍ : ‘መሠረተ ልማት’ ተቀምጧል።
ይሔ በዋናነት መሠረተ ልማትን ታሳቢ አድርጎ የተሠራ ‘ድል’ ነው። የማላስታውሰው ፀሐፊ “Roads created Nations” ይላል። ሕወሓታውያን ይህን ቀድመው አውቀው ገና ከ20 አመት በፊት “ትግራይን በመንገድ እንደጠፍር አልጋ እናደርጋታለን!” የሚል መፈክር በየአካባቢው ይለጠፍ እንደነበር ያወጋኝ ወዳጅ ነበር።
እናም ታንክ ይመላለስባቸው የነበሩ የትግራይ መንደሮች ከዳርዳር ከፍተኛ ጥራት ባለው የመንገድ ግንባታ ተሳስረዋል።
👉 ያለመንገድ የሚመጣ ብሔር-ግንባታ የለም!
ሳይገናኙ ጠንካራ መስተጋብር የለም ÷ መስተጋብር በሌለበት ማህበራዊ ትስስር የለም: የኢኮኖሚ ትስስር የለም: አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ትስስር የለም።
“ብሔር” ደግሞ በግራ ዘመሙ ብያኔ መሠረት እንኳ አንድ ቋንቋና ተቀራራቢ ባህል ያለው ብቻ ሳይሆን በገበያ የተሳሰረ: የጋራ ፍላጎት የገነባ: የጋራ ግብ ያለውና የጋራ ጥረት የሚያደርግ ነው።
[ ብሔረ-ኢትዮጵያም ብትሆን የሕዝቦቿ ግንኙነትና መስተጋብሮች ቀላል: ፈጣን: አመቺ ሲሆን ልትፈጠር የምትችል ነች። ያ ሳይሆን የልማት አጥሮች በፀኑበት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ብሎ ነገር የለም።]
እናም በአገሪቱ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ ሀብት በፈሰሰበት የመንገድ ልማት ዘርፍ የትግራይ መንደሮች መተሳሰር ብቻ ሳይሆን ሕወሓት እና በርካታ የትግራይ ተወላጆች የደረጃ አንድ የግንባታ ተቋራጭነት ንቁ ተሳታፊ በመሆን ከፍተኛ ሀብት መፍጠር ችለዋል። 2 ወይም 3 Highschool የነበራት ትግራይ : 1 ዩኒቨርሲቲን ከ1 ሚሊዮን ለሚያንስ ሕዝብ ማዳረስ ያስቻሏትን 4 መደበኛና 1 የፓንአፍሪካ በድምሩ 5 ዩኒቨርሲቲዎች ባለቤት ሆናለች። በጤና ዘርፍም እንዲሁ።
ወደኢትዮጵያ የገባ የNGO ኢንሼቲቭና ካፒታል ትግራይ ላይ ከ”ትልማ” እና “ማረት” ጋር ሰፊ ስራ ሠርቷል።
❷ ትግራይን ያሸጋገረ “የኢንዶውመንት” ልማት
ትግራይ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማዕከል ከሆነው መሐል አገር መራቋ እንደሌሎቹ ክልሎች comparative disadvantage ቢኖራትም ÷ ሰፊ ቁጥር ያለው የአማራ: ኦሮሞ: ጉራጌ ወይም ሌላ የአገሪቱ ባለሀብት ሔዶ ኢንቨስት ባያደርግባትም ይሔን ያካካሰ ልማት በሕወሓት ኢንዶውመንት ድርጅቶች በኩል ፈፅሟል። የአገር ውስጥ ባለሀብት ትግራይን ባይመርጣትም የውጭ ባለሀብቶች መዳረሻ ሆና ሔደው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሕወሓት ዲፕሎማቶች ሚና የላቀ ነው።
#ድንጋያማ ነች : #ለጠመኔ አትሆንም የተባለችው ትግራይ ÷ በ80ዎቹ ጋምቤላና ቤሻጉ ተብለው ከተካለሉት የማይሻል ቁሳዊ ሀብት የነበራት ትግራይ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን አስችለዋል።
ሀብት #አንፃራዊ ቢሆንም እንደትግራይ የአገር ውስጥ ባለሀብት መዳረሻ ያልሆኑ እንደጋምቤላና ቤኒሻጉ ያሉ ክልሎች ዛሬም ድረስ አንድ ማምረቻ ፋብሪካ እንደሌላቸው ሲታይ የኢንዶውመንት ኢንቨስትመንትን የላቀ ሚና ያሳያል። እንመልከታቸው።
➨ በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ
ከጠመኔና ድንጋያማነት ጋር ትመሰል የነበረችው ትግራይ ዛሬ ዓለማቀፍ የአውቶሞቲቭ ብራንዶች የሚገጣጠሙባት ሆናለች። ከተራ ጋራዥነት የተነሳው MIE ዛሬ የፈረንሳዩን #Peugeot የቤት መኪና ÷ የጀርመኑን #Man ገልባጭ መኪና ÷ የህንዱን የእርሻ #ትራክተር እና #ሞተርሳይክል ይገጣጥማል። #Saba እና #Addis_Geely የሚባሉ መኪኖች በየመስራያ ቤቶች ካየህም የዚሁ ፋብሪካ ውጤቶች ናቸው። በነክንፈ ዳኜው ሜቴክ በኩልም ውቅሮ ላይ #የመኪና_ሞተር ይመረታል።
➨ በኮንስትራክሽን
በኢት/ያ ከተካሔዱ የመንገድ : የግድብ : የቤት ልማትና ሌላም ኮንስትራክሽን ስራዎች ጀርባ #Sur_Construction እና #ሞሶቦ_ሲሚንቶ አሉ። ብዙ ቢሊዮኖች ከፈሰሱበት የግንባታ ዘርፍ ብዙ ቢሊዮኖችን መስራት ችለዋል። ከላይ የጠቀስኳቸውና ሌሎች አንዳንድ ክልሎች ከፌደራል መንግስቱ ከተሰጣቸው የድጎማ በጀት ይልቅ ከፌደራል መንግስቱ ለነዚህ ኩባንያዎች የተሰጠ የፕሮጀክት ካፒታል እንደሚበልጥ መገመት ይቻላል። ሻዕቢያ ከኢትዮጵያ ተነጥሎ ሊሠራ ያቀደው የተሳሳተ ስሌት እንዲህ ነበር።
➨ በግብርና
በግብርና መስክ ትግራይን ‘ድንጋያማ’ ነች ቢባልም ሕወሓት ገና ከጥንት የቱን አካባቢ ይዞ እንዴት እንደሚያለማ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። አመታዊ የግብርና ምርቱ ከአማራና ኦሮሚያ አንድ ወረዳ ያነሰ ይሁን እንጂ ሊለማ የሚችለው ቀድሞ ይታወቅ ነበርና አወዛጋቢዎቹ ወልቃይት ሑመራና ራያ ድንቅ የግብርና መስክ ተደርገው የታሰቡ ናቸው። ያም ሆኖ የሰሊጥና ማሽላ እርሻ ልማት ÷ የጥጥ እርሻ ልማት: የአገው ልጆች የማንነት ጥያቄ የሚያነሱበት #የአበርገሌ አካባቢ ከብት ልማት ለትግራይ ትልቅ ትርጉም አላቸው። መንግስቱ ኃ/ማርያም #ወልቃይት_ስኳርን ቢያይ ምን ይላል? “ማን የትግራይ አደረገው? ወይስ ተሳስቼ ” ነበር?
➨ በማዕድን ልማት
እዚህም “የጠመኔና ድንጋይ” ወግ ትዝ ቢልህም ትግራይ ዛሬ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፋሪካ ቀንድ ብቸኛ #የወርቅ ፋብሪካ ባለቤት ነች። #ኢዛና_ማይኒንግ ወርቅም : #እምነበረድም በስፋት የሚያመርት ነው።
➨ ኬሚካልና ፋርማሲውቲካልስ
የሻዕቢያ ከንቱ ህልም የተገለጠው እዚህ ግድም ነው። ትእምት ገና ድሮ በሰላሙ ጊዜ #አዲስ መድኃኒት ፋብሪካን ሲከፍት ቅሬታ ገባው አሉ። ምክንያቱም የሻዕቢያ ህልም ከኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃ ማጓጓዝና የኢንዱስትሪ ምርቱን ኤርትራ ላይ ሠርቶ ለአለምና ለኢት/ያ ማቅረብ ነበር። የምርጫ መለያየት ከሕወሓት ያሳነሰው እዚህ ነው። ሕወሓት ግን በትእምት በኩል #የአዲግራት_መድኃኒት ፋብሪካን ጨምሮ በመክፈት በአገሪቱ መድኃኒት አቅርቦትና ግብይት ትልቅ ሚና መያዝ ችሏል። ከፍተኛ ካፒታል የወጣበት ፎቶ ላይ የምታየው የደጀና #የኬሚካል_ኢንዱስትሪም ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነው።
➨ በኢምፖርት-ኤክስፖርት
#ጉና_ትሬዲንግ እና #ሉና_ኤክስፖርት የዚህ ባለሚና ናቸው። ጉና በአመት ከ40ሚሊዮን ዶላር በላይ ምርት ሲልክ ሰሊጥና መሰል የቅባት እህል ብቻ ሳይሆን በቡና ሊኪነትም ሚና አለው። በደጉ ዘመን ሻዕቢያ ኤርትራን ቡና ላኪ ሲያደርግ መገንጠሉ ትክክል መስሎት ነበር። የሕወሓት ምርጫ ግን ትእምት ብቻ ሳይሆን በርካታ ትግራውያን በቡና ንግድ ትልቅ ሚና እንዲይዙ ያስቻለ ነው።
➨ በሌሎች
እነ #ማይጨው_ችቡድ ፋብሪካ እንደወትሮው የጎጃምን እንጨት እየጫነ ባይገፋበትም የትግራይ acacia ለመጠቀም እየሠራ ነው። #ሰላም_ባስ እንደወትሮው በመላ አገሪቱ እየሔደ ባይነግድም አቅሙ እንዳለ ነው። እነ #ትራንስ እንደበፊቱ ከጅቡቲ-ጉባ ባይጭኑም ለሕወሓት አቅም የፈጠሩ ናቸው። #አፋሪካ_ኢንሹራንስ እነ ጀነራል ተ/ብርሃን በኢንሳ በኩል በከፈሉት ብዙ ሚሊዮን የህንፃ ኪራይ ብር አዲስ ህንፃ ቦሌ ላይ እያጠናቀቀ ነው።
ሕወሓት ይህንን ሲሠራ ለክልሉ ኢኮኖሚ ትልቅ አቅም ቢቆጣጠርም: የፓርቲውን ልሒቃን ከድህነት ቢያወጣም: ቀላል የማይባሉ ትግራውያን ካፒታሊስቶችን ቢፈጥርም: የትግራይን ሕዝብ ድህነት ጨርሶ አልቀረፈም።
ለሕዝቡ ከቀረፈለት ድህነት ይልቅ ጠላት ያበጀበት የመድሎ ፖለቲካ ጉልህ ነው።
በአጠቃላይ ይሔ ሲደማመር የሻዕቢያን ስሌት ኪሳራ ቢመሠክርም: ዛሬም ድረስ ክልል ከሆኑ ወዲህ የማምረቻ ተቋማትና የመሠረተ ልማት አንፃራዊ ለውጥ ላይ ከቅሬታ ባይወጡም : የዛሬዋ ትግራይ በብዙ የተለየች ሆናለች።
በአገራዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከፍተኛ የሰው ኃይል አቅም ለመፍጠር ያስቻለ ትምህርት መወሰዱ እንዳለ ሆኖ የክልሉን ኢኮኖሚ ከኢንዱስትሪ ወደ እውቀት ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ዲያስፖራውን በማንቀሳቀስ ከ12 በላይ የልዩ ተሰጥኦ ትምህርት ቤቶችንና በየወረዳው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት እየተገነቡ ነው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ላለችው ትግራይ ዛሬ እነደብረፅዮን “የመገንጠል ስሜት ውስጥ ነን” ቢሉ ÷ እነ ጀነራል ተ/ብርሃን “ለኢትዮጵያ ዋጋ ከፈልን” ባሉበት : “የታገልነው ለትግራይ ብቻ ነው ” ቢሉ ÷ የትግራይን ነፃነት አነስተኛ ዋጋ ከፍለን እናረጋግጣለን” ቢሉ አሳማኝ ምክንያትና ምቹ ሁኔታ ስላላቸው ነው።
Animut Abraham face book