በሻሸመኔ ከተማና በምእራብ አርሲ በ10 ወረዳዎች በሁከትና አመጽ ወንጀል የተጠርጣሩ 1 ሺህ 523 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ። ፍርድ ቤት የቀረቡት 1 ሺህ 523  ግለሰቦች  የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ÷ በሻሸመኔ ከተማ እና በምእራብ አርሲ 10 ወረዳዎች በተፈጠረ ሁከትና አመጽ፣ በሰው ህይወት ላይ ለደረሰው ጥፋት ፣በንብረት ላይ ለደረሰው ውድመትና በዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው።

በሻሸመኔ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና በምዕራብ አርሲ 10 ወረዳዎች በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በቀረቡ ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ  የተጠረጠሩበትን ወንጀል ድርጊት ገልጿል።

የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል የጥምረት መርማሪ ፖሊሶች በሻሸመኔ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት  በአጠቃላይ 553 ተጠርጣሪዎችን ያቀረቡ ሲሆን ÷ከዚህ ውስጥ 97ቱ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል  በምእራብ አርሲ ዞን በ10 ወረዳ ፍርድ ቤቶች 970 ተጠርጣሪዎች  የቀረቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 54ቱ ሴቶች ናቸው ተብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ በተጠቀሱት  አካባቢዎች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ÷ በሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ለደረሰ የሰው ህይወት መጥፋት ፣ የግልና የመንግስት ንብረት ፣ መውደም እና ዘረፋ  ተጠርጥረው ምርመራ እየተከናወነባቸው መሆኑን መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል። የአስከሬን ምርመራ እና የወደመው ንብረትን በባለሙያ ለማስገመት እየሰራ መሆኑን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ የሰውና የተጠርጣሪ ቃል መቀበሉን ተናግሯል።

ከዚያም ባለፈ  የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለመሰብሰብ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው በዋስ እንዲፈቱ የጠየቁ ሲሆን÷ የሻሸመኔ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የምዕራብ አርሲ ወረዳ ፍርድ ቤቶች የተጠርጣሪዎችን  የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜን ፈቅደዋል።

የምርመራ ውጤቱን ለመጠባበቅ ከሃምሌ 28 እስከ ሃምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

#FBC

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *