ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

አይሁዶች ለምን ይጠላሉ? Namrud RasTeferi

አይሁድን በጥላቻ ዐይኑ ያላየ ሕዝብ ከቶ አልተገኘም። ከፈርዖን እስከ ሂትለር፥ ከአረማዊ እስከ አማኒ፥ ከማኅበር እስከ ሀገር ድረስ ሊያጠፋቸው ድንጋይ ያልፈነቀለ አልነበረም። እግዚአብሔር ለመኖሩ ማሳያ የሚኾኑት ይሁዲዎች ናቸው። አልጠፉምና!
ታሪክ ዐዋቂዎች አይሁዶች የተጠሉበትን ምክንያት በስድስት ይከፍሉታል።
– በሀብት ባለጸጋ ስለኾኑና የኢኮኖሚ የበላይነት ስላላቸው
– የተመረጥን ሕዝብ የሚለው ትርክት
– ለችግር ኹሉ መንሥኤ ተደርገው በመታየታቸው
– ክርስቶስን በመስቀል ስለተወነጀሉና ክርስትናን እስከዛሬ ድረስ ያልተቀበሉ ስለኾኑ
– ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ልማድ የተለየ ባህል ስላላቸው
– የዘር ንድፈ ሐሳብ (አነሳና ብቁ የሰው ዘር አይደሉም የሚል)
ነገር ግን እነዚህ ምክንያቶች አጥጋቢ አይደሉም። ከክርስትና በፊትም የአይሁድ ዘር ከፈርዖን እስከ ሐማ ድረስ ዕልቂት ሲደገስለት ቈይቷል። እንደ ራባዮች አገላለጽ አይሁዶች የተጠሉት ሕግ ስላላቸው ነው። ሕግ ደግሞ የሥነ ምግባር መርሕ ነው። መላው አሕዛብ ሕግ ምን እንደኾነ በማያውቅበትና በሕገ አራዊት ጠባይ ሲተዳደር በሚኖርበት ጊዜ አይሁዶች ከእግዚአብሔር ሕግን ተቀብለው ነበር። ራባዮች የአይሁድ መጠላት ምክንያቱን ከታልሙድ (ትራክቴት ሻቦስ 89) ጠቅሰው እንዲህ ያስረዳሉ። የሲና ተራራ סיני እና ሢና (שנאה) ተመሳሳይ ድምፅ አላቸው። ሢንኣህ (ሢና) ማለት ጥላቻ ማለት ሲኾን ሲናይ ማለት ደግሞ ሙሴ ሕገ ኦሪትን የተቀበለበት ተራራ ስም ነው። ስለዚህ አሕዛብ አይሁድን የሚጠሉት የሞራልም ኾነ መለኮታዊ ሕግ ስለሌላቸው ነው። አይሁድ የተጠላው መጥፎ ስለኾነ ሳይኾን ደግነት ምን እንደኾነ ለዓለም ሕዝብ በማሳየታቸው ነው። የአይሁድ ባህልና የሥነ ልቦና ልህቀት ምንም ለሌለው አሕዛብ የመናቅን ስሜት ፈጥሮበታል።
አይሁድ ስለሚበላው፥ ስለሚጠጣው፥ ስለሚለብሰው ስለ ኹሉ ነገር ሕግ አለው። በአንጻሩ ደግሞ አሕዛብ ይህ የለውም ነበር። የዐረቡ ዓለምም ኾነ አውሮጳ በሕግና በአንድ አምላክ መተዳደር ፥ የጸሎት መጽሐፍ ማዘጋጀት የዠመረው ከአይሁድ እምነት በመቅሠም ነው። ይህም ሌላው ከባዱ የጥላቻ ምክንያት ነው።
ሌላው አይሁድ ከሚጠላበት ምክንያቶች መኻል አንዱ ጠንካራ የሞራል ሰብእናና ኅሊና ስላለው ነው። ለዚህ እንደ ማሳያ የሚጠቀሰው ሂትለር ነው። በ1980ዎቹ መጨረሻ ጀርመን እንደ ዐዲስ እየተገነባች ባለችበት ሰዓት የሂትለር ጨካኝ ዐይኖች በአይሁዳውያኑ ላይ ይንከራተቱ ነበር። ሂትለር ብሔራዊ ሶሻሊዝም የዐዲሱ ዓለም ሥርዐት መርሕ ነው ብሎ የሰውን ልጅ በዐዲስ መንገድ የመፍጠር ዕቅዱን ያሰላስል በነበረበት ወቅት ለዓላማው መሰናክል የኾኑበት አይሁዳውያን ነበሩ።
አይሁድን ጨርሶ ማጥፋት የሂትለር ተምኔት ኾኖ ዘልቋል።ምንም እንኳ ሂትለር ክርስቲያን ቢኾንም ዓላማው ግን ዓለምን ከግብረ ገብነትና ከኅሊና ማላቀቅ፥ በአንድ አምላክ ማመንንም ማስቀረት እንደነበረ ከንግግሮቹና ከጻፈው መጽሐፍ መረዳት ይቻላል። በዚህ ኺደት ውስጥ በአንድ አምላክ ብቻ የሚያምነው፥ “ኹሉም ፍጥረት እኩል ነው” ፥ “ባልንጀራኽን እንደ ራስኽ ውደድ” የሚለው ጠንካራው የአይሁድ ማኅበረ ሰብና ዕሴቱ ለሂትለር ስጋት ስለኾነ መንቋሸሹ፥ ተነጥሎ መመታቱም አልቀረም። ለአኹኑ የአውሮፓ ግብረ ገብነት መላሸቅና ለጀርመን የጠባይ ልቅነት መሠረቱ ሂትለር ለመኾኑ ጥርጥር የለውም። የሂትለር ትውልድም እንዲህ እያለ ያዜም ነበር፡–
“እኛ ለክርስቲያን ምግባር ፍላጎት የለንም
መሪያችን አዳኛችን ነው፤
ጳጳስና ራባይ ያልፋሉ
እኛም ላንዴ እንደገና
አረማዊ እንኾናለን።”
ሂትለርም በአደባባይ ይህን መናገሩ አይረሳም፡–
“ዐሥርቱ ትእዛዛት ጕልበታቸውን ዐጥተዋል። ኅሊና የአይሁድ ፈጠራ ነው።…”
ከዚህ ሌላ ሂትለር የአንደኛውን የዓለም ጦርነት ሽንፈት አምኖ ከመቀበል ይልቅ በአይሁድ ላይ ማላከክና “አይሁድ ከዠርባ ወጉን” በሚለው የሤራ ፖለቲካ በመነዳት ከሀገሩ መመንጠር እንዳለበት አበክሮ ያምን ነበር። ከርሱ በፊት የተነሡ የክርስትና እምነት መሥራቾች በአይሁድ ላይ የጻፉትን ጽሑፎች በማንበብ የተጠመደው ሂትለር ጽንፍ እየያዘ ለመኼዱ ዋነኛ ምክንያት ነው። ከዚህም ዐልፎ ሂትለር የሰውን ዘር በመደብ ከፍሎ ላዕላይና ታሕታይ በማለት አይሁድን ከሰውነት ጎዳና በማውጣት ለኅሊና የሚሰቀጥጥ የጅምላ ግድያ በአይሁድ ላይ ፈጽሟል።
በነዚህ ኹሉ ማዕበላት የአይሁድ ዘር አለመጥፋቱን ያስተዋለው ታላቁ ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ በመደመም እንዲህ ብሎ ነበር፡–
“ይሁዲ ምንድነው? የዓለም ኹሉ ሕዝቦች መሪዎች ኹሉ አዋርደውትና ጨፍልቀውት፥ ነቅለውትና አጥፍተውት፥ አሠቃይተውትና አቃጥለውት፥ አስጥመውት ርሱም ከቍጣቸውና ንዴታቸው ዐልፎ መኖርና ማበብ የሚቀጥል ይህ ምን ዐይነት ፍጥረት ነው? … ይሁዲ የሕያውነት ምልክት ነው። ለረዥም ጊዜ የነቢያንን መልእክት ጠብቆና ለሰው ፍጡር ዅሉ ያን አስተላልፎ የነበረ ቀዳሚው ርሱ ነው። እንደዚህ ያለ ሕዝብ ከቶ ሊጠፋ አይችልም። ይሁዲ ሕያው ነው። ርሱ የሕያውነት ተምሳሌት ነው።”
ምንም እንኳ አይሁድ አእምሮን የታደለ ቢኾንም፥ እንደ አልበርት አንስታይን፥ ሲግመንድ ፍሩድና ካርል ማርክስ የመሰሉ አንድ መስለው ብዙ የኾኑ ዓለምን በሥራቸው የጠቀሙ ምሁራን ያሉት ቢኾንም፥ ይህ ግን ከመሳደድ አላዳነውም። አይሁድ የተጠላው እግዚአብሔርን አስቀድመው በሚጠሉ ሕዝቦች ነው። ይህ ኹሉ ጥላቻ ግን ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። ወደፊት በእሥራኤል ላይ ለሚደረገው ጦርነት መነሻ ስለኾነ ጭምር እንጂ…
(ናምሩድ
ወዳጃችን አያሌው ሊንኩን አያይዞ እንድናትመው በላከልን መሰረት አትመነዋል። ሃስቡ የጸሃፊው ብቻ ነው