የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ህልፈት ተከትሎ በተፈጸመ ሴራ የወደሙ ኢንቨስትመንቶች መልሰው እንደሚገነቡ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዘዳንት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ዛሬ በአዳማ ከተማ ኦሮሚያ ሥራ አመራር አካዳሚ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ህልፈት ምክንያት በማድረግ በተፈጸመ ሴራ የወደሙ ኢንቨስትመንቶች መልሰው ይገነባሉ ብለዋል፡፡
የጥፋት ሃይሎች የኦሮሞን ህዝብ ስሜት ቀስቅሰው ክልሉን የጦርነት አውድማ ለማድረግ መሞከራቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ጫልቱ፣ ያደረሱት ጥፋት ቀላል ነው ባይባልም ከውጥናቸው አንፃር ሲታይ ግን ጥቂት ነው ብላዋል፡፡
በተለይም ኢንቨስትመንት ለክልሉና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ምን ያህል አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳለ የተረዱት እነዚህ ሃይሎች ሆን ብለው ባለሃብቱን ለማስበርገግና ዜጎችን ከስራ ለማፈናቀል አልመው መስራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ የንግድና የኢንቨስትመንት ተቋማት እንደወደሙ የገለጹት ምክትል ፕሬዘዳንቷ እነዚህን የኢንቨስትመንት ተቋማት ለመገንባት የፌደራል መንግስት ፣ የክልሉ መንግስትና ባለሃብቶች ተረባርበው ወደ ነበረቡት ይመልሷቸዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ አቃፊ ፣ ስራ ወዳድና መልካም ሰብዕና እንዳለው የተናገሩት ምክትል ፕሬዘዳንቷ የተፈጠረውን ክስተት እንደጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በሰዎች አዕምሮ ውስጥ መጥፎ ስዕል የሚስሉ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ባለሀብቱ ይህ ክስተት ለውጡን ለማደናቀፍና በአቋራጭ ወደ ስልጣን መምጣት በሚፈልጉ አካላት የተፈጸመ ድራማ መሆኑን ተረድቶ ያለምንም የስነ ልቦናና የጸጥታ ችግር ስራውን ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመትም በርካታ የኢንቨስትመንት ማሻሻያዎች፣ መመሪያና ደንቦች ጸድቀው ወደ ስራ እንደተገባ የገለጹት ፕሬዘዳንቷ በመጪው አመት በክልሉ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልግ ባለሃብት ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ለነዋሪውና ለባለሃብቱ ዋስትና እንደሚሰጥና አሁን የተጀመረው ህግን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ፕሬዘዳንቷ ገልጸዋል፡፡
ኢንቨስትመንት ኢኮኖሚን ለማሳደግና የስራ እድልን በመፍጠር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የጠቀሱት ወይዘሮ ጫልቱ አሁን የግል ባለሃብቱን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ እንዳለ አስረድተዋል፡፡
ባለሃቱም በሚሰራበት አካባቢ ካለው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበትና ህዝቡ የፈሠሠው መዋዕለ ነዋይ የእኔነው ብሎ እንዲያምን ምድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡
የሥራ ዕድል በመፍጠርም ይሁን ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ህዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በክልሉ ለሚገኙ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች ልዩ ጥበቃ የማድረግ ስራ ለመተግበር እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ፕሬዘዳንቷ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በጥፋት ላይ የተሰማሩ አካላትን እና ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አካላትን ተከታትሎ ለፍርድ በማቅረብ ህጋዊ እርምጃ የማስወሰዱ ስራ እንደተጀመረ ጠቅሰዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ በርካታ ባለሃቶች የተሳተፉ ሲሆን አብዛኛዎቹ ባንጸባረቁት ሃሳብም መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲስጠብቅና ላፈሰሱት መዋዕለ ነዋይም ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በክልሉ ምክትል ፕሬዘዳንት ማዕረግ የግብርና ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እና የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ተማሳሳይ ሀሳቦችን አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ኢንቨስትምት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ ጀልዴም የዓመቱን የኢንቨስትመንት ሥራ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አሳይተዋል፡፡
ኦቢኤን ዜና

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በኢትዮጵያ የትግራይ ጉዳይ ላይ የጸጥታው ምክር ቤት ሳይስማማ ተበተነ፤ አማራ ትህነግን በህግ ሊጠይቅ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *