ሀገራት በዋናነት የአሜሪካ ዶላርን በመጠቀም ግብይትና የንግድ ልውውጥ ያካሂዳሉ፡፡ የአሜሪካ ዶላር ከየን፣ ከሊሬ፣ ከዲርሃምና ሌሎች መገበያያ ገንዘቦች ጋር ያለው ምንዛሬም ከፍተኛና ዝቅተኛ ልዩነት የሚስተዋልበት ነው፡፡
በኢትዮጵያም የአሜሪካ ዶላር ከብር ጋር ያለው ምንዛሬ በፍጥነት ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ በ1990ዎቹ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ10 ብር ይመነዘር የነበረ ሲሆን ከ2000 ዓ.ም በኋላ ግን በፍጥነት እያሻቀበ በመሄዱ አሁን ላይ መሸጫ ዋጋውን 35 ብር አልፏል፡፡
ይህ ግን ለምጣኔ ሀብት ውድቀት መንስኤ በመሆን የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ በኋላ በእጅጉ ያዳክመው ይሆን? የብር የመግዛት አቅም ተዳክሟል የሚባለውስ መቼ ነው? የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ትርጓሜ ምን ይመስላል? በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አርጋ ሹመቴ (ዶክተር) የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም በሁለት ዓይነት መንገድ እንደሚታይ አስታውቀዋል፡፡ አንደኛው ገንዘብን በገንዘብ የመግዛት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ገንዘብ ዕቃን የመግዛት የሚሉ ናቸው፡፡
ገንዘብ ዕቃን የመግዛት አቅሙ ሲደክም በዋጋ ግሽበት ምክንያት የሚከሰት እንደሆነ ዶክተር አረጋ አመላክተዋል፡፡ ገንዘብ ሌላን ገንዘብ የመግዛት አቅሙ የውጭ ምንዛሪ ይባላል፡፡ በውጭ ምንዛሬ ምክንያት የሚመጣው የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም በመንግሥት ሆን ተብሎ ዋጋው እንዲወርድ ሊደረግ እንደሚችልም ዶክተር አረጋ ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል በገበያው ሁኔታ ወይም ከፍላጎትና ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ችግሩ ሊፈጠር እንደሚችል ምሁሩ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የዶላር ምንዛሬው እየጨመረ ሄዶ 35 ብር ደረሰ ማለት ገንዘብ ገንዘብን የመግዛት አቅሙ ተዳከመ ማለት ነውም ብለዋል፡፡
ሦስት ዓይነት የገንዘብ ለገንዘብ ግብይት እንዳለ የጠቀሱት ዶክተር አረጋ ቋሚ (ፊክስድ)፣ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ በተወሰነ መጠን ግን ለቀቅ የሚያደርገው (ማኔጅድ ብሎኪንግ) እና በገንዘብ አቅርቦትና ፍላጎት በገበያው ሥርዓት የሚወሰንበት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ የገንዘብ ግብይት ሥርዓት እንዳላት ዶክተር አረጋ አንስተዋል፡፡ ከጎረቤት ምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የብር የመግዛት አቅም ከፍ ያለ ነውም ብለዋል፡፡ ይህም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ የገንዘብ ግብይት ሥርዓት በመኖሩ ምክንያት የመጣ መሆኑን ዶክተር አረጋ አስገንዝበዋል፡፡
መንግሥት ግን ሆን ብሎ ዋጋውን እያወረደ ከተጓዘ ትልቅ ስጋት እንደሚፈጥር ዶክተር አረጋ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም እዳው ያድግና ከውጭ የሚገቡ ቁሳቁስ በጣም እየተወደዱ በመሄድ የሀገር ውስጥ ዕቃዎች ዋጋቸው በጣም ይቀንሳል፡፡ በግብርና ምርቶች ላይ በተንጠለጠለው ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ምንም ጭማሪ አይኖርም፤ የሚለወጥ ምርት ከሌለ የሀገር ውስጥ ዋጋ መውረዱ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ዶክተር አረጋ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ምንዛሬው ባለበት እንዲረጋ የቁጥጥር ሥርዓቱን ጠበቅ አድርጎ መጓዝ፣ የውጭ ምንዛሬን መጨመር፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማስፋፋት፣ የውጭ ሀገራት ጥሬ ገንዘብ ለማግኘት መሞከር፣ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ወዘተ ማድረግ ቢቻል ሲሉ ዶክተር አረጋ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደለ ፈረደ የብር የመግዛት አቅምን በኢትዮጵያ ተጀምረው ከተቋረጡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጋር በማያያዝ ማብራሪያ ሰጠውበታል፡፡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚጠይቁ ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደለ ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በታሰበው ጊዜ ያልተጠናቀቁት የፕሮጀክት አስተዳደር አቅም ማነስ ምክንያት እንደሆነም አንስተዋል፡፡ በቅድሚያ ፕሮጀክቶቹ የአዋጪነት ጥናት ቢካሄድላቸው መልካም ነበር ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ሁሎችንም በአንዴ (በተቀራራቢ ጊዜ) መጀመሩና ማጠናቀቅ ስለመቻሉ ጥናት መደረግ እንደነበረበት ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውጭ በውጭ ሀገር የብድር ገንዘብ የተጀመሩ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ቢገቡ ግን የውጭ ምንዛሬ መቆጠብ ይቻል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን ተጨማሪ የውጭ እዳ ጫና መፍጠራቸውን አመላክተዋል፡፡
ምንዛሬው በጊዜ ሂደት በመጨመሩ መንግሥት ብድሩን ለመክፈል ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጣ ያስገድደዋል፡፡ በውጤቱም የመንግሥት በጀት ይናጋል፤ የመክፈል አቅም በመፈታተን አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡
የብር የመግዛት አቅም በፍጥነት እየተዳከመ መጥቷል ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ወደ ውጭ ለምንልካቸው ምርቶች ጠቀሜታ ቢኖረውም ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ምርቶች ግን የቁሳቁስ መወደድን በማስከተል የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
ምንዛሬው በፍጥነት እየጨመረ ስለሆነም ብሔራዊ ባንክ አሁን በደረሰበት ደረጃ ማስቆም እንዲችል መክረዋል፡፡ መንግሥት በጥሩ ደረጃ ላይ ያሉትን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ ሰጥቶ በማገባደድ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ፣ ተጠያቂነትን ያቀፈ ጥሩ የፕሮጀክት አስተዳደር መዘርጋት እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል፡፡ ለባከነው የውጭ ምንዛሬ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡
አንድ ኩባንያ ምንም አፈፃፀም ሳያሳይ ወይም የሆነ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ገንዘብ አስቀድሞ መክፈል ተገቢ እንዳልሆነም ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደለ አስረድተዋል፡፡ አዘግይቶ መክፈልም ጎጂ ነው ብለዋል፡፡ በስምምነት መሠረት ሥራዎቹ በየጊዜው እየተፈተሹ ገንዘብ መከፈል ቢኖርበትም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ እንዳልተተገበረ አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *