አገራት እንደ አገር ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ጫናዎችን ተቋቁመው ለመቀጠል፤ የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ፤ ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው ለመዝለቅ በሚያደርጉት ትግል ውስጥ መከላከያ ግንባር ቀደም ተቋም ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም በዚህ ልክ ሚናውን ሲወጣ የቆየ፤ ከምንም በላይ ህይወቱን እየገበረ አገርና ህዝብን አጽንቶ ያኖረ፤ አሁንም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ብሎም በኢትዮጵያውያን ደህንነት ላይ ከውስጥም ከውጭም የሚቃጡ ማናቸውንም ጥቃቶች በብቃት እየመከተና እያከሸፈ ያለ ነው።

 

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የመከላከያ ሠራዊት እንደ ተቋም ፖለቲካና ፖለቲከኞች በተለዋወጡ ቁጥር አብሮ የሚለዋወጥ ሳይሆን፤ ሕገ መንግሥታዊ መሠረቱ ፀንቶና ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮዎቹን ጠብቆ እንዲሠራ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከዚህ አንፃር አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሪፎርም ከተካሄደባቸው ተቋማት አንዱና ቀዳሚው የመከላከያ ተቋም ነው። ሪፎርሙ ሠራዊቱ ቀደም ሲል በብቃት ሲወጣ የነበረውን ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮዎቹን በበለጠ አቅም ፈጥሮ መወጣት የሚችልበትን የላቀ አቅም የሚፈጥርለት ስለመሆኑም ይነገራል። እኛም በዛሬው እትማችን በመከላከያ የተከናወነውን ሪፎርም፣ የለውጡ ጉዞና አገራዊ ፈተናዎቹን፣ ወቅታዊ የአገራችን ችግሮችና የተቋሙ ቀጣይ አቅጣጫዎችን መነሻ በማድረግ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።

አዲስ አመን፡- በኢትዮጵያ ብዙ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል፤ የቅርቡን አገራዊ ለውጥ ብናይ እንኳን አገራዊ ለውጡን ያቀጣጠሉ የህዝብ ጥያቄዎች ተነስተው አሁን የደረስንበትን አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል። በእርስዎ ምልከታ የሕዝቡን የዴሞክራሲ ጥያቄ እርስዎ ከሚመሩት ተቋም የቀደመ ቁመና ጋር እንዴት ይገልፁታል?

ጄኔራል አደም፡- እንደሚታወቀው አገራችን ሰፊ የሆነ የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች። እንዳልከው ባለፉት ዓመታት የህዝብ የለውጥ ንቅናቄዎች እንደነበሩ ይታወቃል። እነዚህ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ሁላችንም እንደምናውቀው ገዢው ፓርቲም በሚገባ ረዘም ያለ ጊዜ ገምግሞ ለህዝብ ይፋ እንዳደረገው መነሻቸው፤ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፤ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች፣ የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄዎች፣ የሙስና ጥያቄዎች፣ እና መሰል ጥያቄዎች ናቸው ።

ምንም እንኳን ባለፉት 27 እና 28 ዓመታት በርካታ ለውጥ በአገራችን የተመዘገበ ቢሆንም፤ ከህዝብ ፍላጎት አንፃር በርካታ ፍላጎቶች፣ በርካታ ተግዳሮቶች ስለነበሩ፤ ህዝቡ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሷል። በዚህ ምክንያትም ገዢ ፓርቲው እነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ ናቸው፤ ትክክልም ናቸው ብሎ፤ ፍትሃዊ ጥያቄዎች መሆናቸውንም ተቀብሎ ወደ ለውጡ ገብቷል።

ዞሮ ዞሮ የመከላከያ ሠራዊት ደሴት አይደለም። ከህብረተሰቡ የወጣ፣ ህብረተሰቡን የሚያገለግል፣ አገሩን የሚያገለግልና እያገለገለ የመጣም ተቋም ነው። ስለዚህ ሠራዊቱም በሌላ መንገድ ከህብረተሰቡ የተለየ ፍላጎት፣ የተለየ ጥያቄም ሊኖረው አይችልም። ጉዳዩ ህዝቡ ወይም ወጣቱ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎች ሲያነሳ፤ የሰላም ጥያቄ ሲያነሳ፤ ወይም የኢኮኖሚ ጥያቄ ሲያነሳ በተደራጀም ባልተደራጀም መንገድ ጥያቄ ሊጠይቅ ይችላል። ጥያቄዎቹንም ህጋዊና ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲመልስም ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው።

ሠራዊቱ ግን ሠራዊት ስለሆነ፣ በሕግና በአሰራር የሚንቀሳቀስ ስለሆነ፤ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችም ምንም እንኳን የሠራዊቱም ጥያቄዎች ቢሆኑም የተደራጀበት አደረጃጀትና በሕግ አግባብ የሚንቀሳቀስ ተቋም ስለሆነ፤ ሠራዊቱ ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ አትኩሮ ሲሰራ ቆይቷል።

ሠራዊቱም ሕግ በማስከበር ሥራ ላይ ከለውጡ በፊትም ይሰራ ነበር። ከለውጡ በኋላም እየሰራ ነው። ስለዚህ ሠራዊቱ ከለውጡ በፊት በነበሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ሥርዓት አልበኝነት እንዳይከሰት፤ ወይም የአገሪቷ ኢኮኖሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፤ የአገር ዳር ድንበር አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ጥረቶችን ሲያደርግ ነበር። በዛም ወቅት ቢሆን ሠራዊቱን ከህብረተሰቡ የለውጥ እንቅስቃሴ ውጭ አድርጎ መመልከት ስህተት ነው። ሁከት እንዳይኖር ይከላከል ነበር፤ የሰው ህይወትም ሆነ ንብረት እንዳይጠፋ ይንቀሳቀስ ነበር። ከዚህ ባለፈ ግን ያንን ሠራዊት ደሴት አድርጎ ከህብረተሰቡ ጥያቄ ውጭ አድርጎ መመልከት ተገቢ አይደለም ።

አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ተከትሎ ሪፎርም ከተካሄደባቸው ተቋማት አንዱና ቀዳሚው የመከላከያ ተቋም ነው። የሪፎርሙ ዋና ዓላማ እና መሠረታዊ መርሆዎች ምንድን ናቸው?

ጄኔራል አደም፡- በመከላከያ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የሪፎርም ሥራ አሁን አገሪቱ እያካሄደችው ያለችው የለውጥ እንቅስቃሴዎች አካል አድርጎ መመልከት ተገቢ ነው። ህዝቡ እየጠየቀ ያለው የዴሞክራሲ ጥያቄ፣ የልማት ጥያቄ፣ የፍትሃዊነት ጥያቄ ጉዳይ ነው። እነዚህን ጥያቄዎች መንግሥት ለመመለስ በሚያደርጋቸው ጥረቶች ውስጥ የሠራዊቱ የሪፎርም ወይም የግንባታ ጥያቄ ወይም የአገሪቱ የሪፎርም አጀንዳ ጥያቄ ሠራዊቱንም አብሮ የሚቀይርና የሚለውጥ መሆን መቻል አለበት። አገሪቷ በአሁን ወቅት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ የለውጥ አጀንዳዎችን ቀርፃ ተግባራዊ እያደረገች ነው። እነዚህም እጅግ መልከ ብዙ የለውጥ አጀንዳዎችን የያዙ ናቸው። ከእነዚህ አገራዊ የለውጥ አጀንዳዎች አንዱ መከላከያን በተገቢው መንገድ ማደራጀት ነው፤ ይሄም አሁን አገሪቷ እየፈለገች ካለችው የለውጥ መንገድ፣ አስተሳሰብና አመለካከት፤ በአካባቢያችን እየተለወጡ ካሉ ጂኦ ፖለቲካል ሁኔታዎች እና አገሪቷ ከምትፈልገው የለውጥ አስተሳሰብና አመለካከት አንፃር የሠራዊታችን አጠቃላይ ቁመና ሊቃኝ ይገባል።

ከዛም ባሻገር የሠራዊታችን ወታደራዊ ቁመና የአገራችንን ሉዓላዊነት እና የህዝባችንን ደህንነት በሚገባ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ሊሰነዘር ከሚችል ማንኛውም አይነት ጥቃት ሊከላከል የሚያስችል ሊሆን ይገባል። ይሄ በወታደራዊ ክህሎቱ፣ በወታደራዊ ሳይንስ አስተሳሰቡ፣ በሚታጠቀው ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ጭምር አገራችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ማንኛውም አይነት አደጋዎች መከላከል የሚችል ብቃት ያለው ተቋም ሆኖ ሊገነባ ይገባል። የሪፎርሙ አንዱ ዓላማ ይኸው ነው ።

ሌላው ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው። ጠንካራ አገር ያለ ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት ወይም ያለ ጠንካራ የፀጥታ ተቋማት የሕግ የበላይነት ሊከበር አይችልም። እንደ ኢትዮጵያ በመሰሉ የተለያየ አመለካከትና አስተሳሰብ ባሏዋቸው ማህበረሰቦች ጉዳይ ሰፊ ትኩረት የሚጠይቅ ነው።

ቀደም ሲል በገዢው ፓርቲ በስፋት ተገምግሞ፣ የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት አለብን ተብሎ የተቀመጠውም ትልቁ አጀንዳ የዴሞክራሲ ተቋማትን ሊገነቡ ወይም ሊደግፉ የሚችሉ ተቋማትን ላይ ሪፎርም ማድረግ ነው።

ይሄ ማለት የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፤ ስለዚህ እነዚህን በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች ሕግና ሥርዓት ተከትለው ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ዓላማቸውን ለህዝብ አስተዋውቀው ወደ ስልጣን መምጣት እስከቻሉ ድረስ፤ በዚህ አገር ለዚህ አገር አለኝ የሚሉትን አማራጭ ማቅረብ ይችላሉ፤ መብታቸውም ነው።

ከዚህ አንፃር የመከላከያ ሠራዊት አገነባብና አቀራረጽ ሁሉንም ኢትዮጵያውያኖችን እኩል ሊያገለግል የሚችል ተቋም ሆኖ መገንባት አለበት ማለት ነው። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል፣ ሁሉም የተፎካካሪ ፓርቲ ይሄ ሠራዊት የእኔ ነው፤ የአገሬንም የእኔንም ደህንነት የሚጠብቅ ተቋም ነው ብሎ መከላከያን፣ ደህንነቱን፣ ፖሊሱን፣ የፍትህ አካላቱን ሆነ ሌሎችም ከፓርቲ ፖለቲካ ገለልተኛ ሆነው መቀረጽ ያለባቸውን ተቋማት ገለልተኛ አድርጎ የመቅረጽና የመገንባት የሪፎርም ሥራ የመንግሥት የመጀመሪያው ሥራ ነው። ምናልባት የምናስታውስ ከሆነ ጠቅላይ ሚንስትራችን በመጀመሪያው የፓርላማ ንግግራቸው ያስቀመጡት ነገር ቢኖር የፀጥታ ተቋማት ሪፎርም ጉዳይ ነው። ጉዳን በከፍተኛ ደረጃ በተደጋጋሚ ሲያነሱት የነበረ ነው።

እነዚህ የፀጥታ ተቋማት የማንም ፓርቲ አሴት ወይም ሀብት አይደሉም። የኢትዮጵያ ሀብት ናቸው። መከላከያ የኢትዮጵያ ሀብት ነው። በአንድ ፓርቲ ፕሮግራም ሊቀረጽና ሊገነባ የማይገባው ነው። በኢትዮጵያውያን እሴቶች፣ በአገር ሉዓላዊነት፣ ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ተመስርቶ መገንባት ያለበት ተቋም ነው። እዚህ ጋ ይሄ ሠራዊት ይሄን ያደርጋል፣ የገዢው ፓርቲ ብቻ ነው፤ ብለው የሚያስቡ ተቋማት ወይም የማህበረሰብ ክፍሎች ወይም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ባሉበት አገር፤ ሠራዊታችን ምን ጊዜም ወርቃማ ሥራ ቢሰራ ይሄ ሠራዊት የእኔ ነው ስለማይባል፤ ወይም ገዢው ፓርቲ ስልጣኑን ለማራዘም መጠቀሚያ ያደርገዋል ብለው ስለሚታሰብ ሁል ጊዜ ይሄን ተቋም የማጠልሸት ሥራ ይኖራል ማለት ነው።

የፖለቲካ ምህዳር የማስፋት /የዴሞክራሲ/ ጥያቄ ለመመለስ በነዚህ የፀጥታ ተቋማት ላይ የሚደረግ የሪፎርም ሥራ ቁልፍና መሠረታዊ ነው። በዚህ ረገድ የሌሎች አገሮችን ልምዶች ወስዶ ማየት ጥሩ ነው። ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተለይም በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመን አሁንም የምናያቸው የአውሮፓ ጠንካራ አገራት ያለፉበት መንገድ ይታወቃል። እነዚህ አገራት ብዙ ተግዳሮቶችን አልፈው ነው ወደ ጠንካራ አገርነት የመጡት። የነዚህ አገራት የፖሊስ፣ የመከላከያ፣ የደህንነትና፣ የፍትህ አካላት አሁን ያላቸውን ቁመና የያዙት በየወቅቱ በተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ተገንብተው ነው።

በፀጥታ ተቋማቱ ላይ የሚደረጉ የለውጥ ሥራዎች መልሰው የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ያጠናክራሉ። የዴሞክራሲው ሥርዓቱም መልሶ እነዚህን ተቋማት ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያጠናክራቸዋል። ስለዚህ አንዱ የመከላከያ ሪፎርም አጀንዳ አገሪቱ ከጀመረችው የለውጥና የዴሞክራሲ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ሪፎርሙ እነዚህ ተቋማት ፍፁም ገለልተኛ፣ ፍፁም በአንድ ፓርቲ አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይም ርዕዮተ ዓለምና ፕሮግራም የማይመሩ፤ የማይቀረፁና የማይገነቡ መሆን አለባቸው ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። ከዚህ ይልቅ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚያገለግሉ፤ በአገር ደህንነትና በህዝብ ደህንነት ላይ ብቻ አትኩረው የሚሰሩ ተቋሟት እንዲሆኑ ለማስቻል ነው ።

አገራችንን ሊያጋጥማት ከሚችል ማንኛውም አይነት የደህንነትና፤ የሉዓላዊነት አደጋ መከላከል፣ መቀልበስና መግታት የሚችል ተቋም ሆኖ እንዲገነባ ነው። ከዛም በላይ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የሆኑ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ሰዓት ሠራዊታችን ከማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ቀድሞ አደጋን የሚታደግ አቅም ያለው ተቋም እንዲሆን ጭምር ነው መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጦ በሪፎርም ፕሮግራሙ እየሠራ ያለው።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ሪፎርም መከላከያ ሠራዊቱ አገራዊ ተልዕኮውን እና ተልዕኮውን ለመፈፀም የሚያስችለውን ምን መሠረታዊ ለውጥ አምጥቶለታል ማለት ይቻላል?

ጄኔራል አደም፡- ይሄን ሠራዊት ወይም ተቋሙን በተመለከተ ሁላችንም ማወቅ ያለብን ሠራዊቱ ወይም ተቋሙ ከለውጡ በፊትም ሆነ በኋላ የልማት እና የሰላም ጀግና ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይሄ የሚካድ ነገር አይደለም። በዚህ በኩል ትልቅ ዝናና ስም ያለው ሠራዊት ነው። አሁንም በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ማንኛውንም የሀገር እና የህዝብ ስጋቶችን በመከላከል ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ነው። ከለውጡ በፊትም ባሉ እንቅስቃሴዎች በተመሳሳይ በአገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥና በማስከበር የሠራዊቱ ሚና ቀላል አልነበረም።

እንደ ሠራዊትም እንደ ተቋም ከታየ ህዝብን ያገለገለ፤ እየሞተ ህዝብን ያዳነ ሠራዊትና ተቋም ነው። በለውጡ መሃልም ሆነ ከለውጡ በኋላም በነበረው ሂደት ይሄ ሠራዊት ይሄ ለውጥ አይስማማኝም፤ ይሄ ለውጥ የእኔ ለውጥ አይደለም ወደሚል የሄደ ተቋም አይደለም። እንዳልኩህ በሕግና በሥርዓት የሚመራ ተቋም ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ በህብረተሰቡ የሚነሱ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የኢኮኖሚ የመሳሰሉ የህዝብ ጥያቄዎች በሌላ መንገድ የሠራዊቱም ጥያቄዎች ነበሩ። ዋናው ጉዳይ እንደ ህዝቡ ቀጥታ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረገ መንግሥትን ሊጠይቅና ሊያስገድድ አይችልም። ሥርዓትና ሕግ ባለው መንገድ ሁከትንና ጥፋጥን እየተከላከለ፣ ሕግን እያስከበረ የህብረተሰቡ ጥያቄ ሲመለስ የእርሱም ጥያቄዎች እንደሚመለሱ አምኖ፤ ከዚህ በፊት በነበሩ የህዝብ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራ የመጣ ሠራዊት ነው።

አሁንም በሪፎርም ፕሮግራሙ የተሰሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። ከሥራዎቹ አንዱ በተቻለ መጠን ሠራዊቱ የአገሪቷን የፖለቲካ የለውጥ አስተሳሰብና አመለካከት እንዲረዳ ማድረግ ነው። የሠራዊቱ ተልዕኮ ከሕገ መንግሥቱ ነው የሚመነጭ ነው። ዛሬም የሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮዎቹ እንዳሉ ናቸው። ሕገ መንግሥቱ አልተቀየረም ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩት ተልዕኮዎች ላይ ምንም የሚያጠራጥሩ የተቀየሩ፣ የተለወጡ አጀንዳዎች የሉም። ግን ደግሞ ሠራዊቱ የህብረተሰቡን ጥያቄና የለውጡን እንቅስቃሴ በሚገባ መረዳት አለበት፤ ይሄ ሠራዊት ገለልተኛ መሆን አለበት ብሎ መንግሥት ሲያስቀምጥ፤ እጅግ ቁርጠኛ በሆነ አቋምና መንገድ ነው። አደጋውንም በማሳየት ነው።

ሠራዊቱ ገለልተኛ ካልሆነ፤ 108 ፓርቲዎች ሲነታረኩ አብሮ የሚነታረክ፣ አብሮ የሚፈርስና አብሮ እየወደቅ የሚነሳ ተቋም ይሆናል ማለት ነው። የሠራዊታችንን ጥንካሬ ግን በግልጽ ማየት እንችላለን፤ ሌሎቹን ትተን እንኳን በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ንትርኮች በአንድ በኩል የነበረውን ጥንካሬ ማሳያ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይሄ ለውጥ እኔን አይመለከተኝም ብሎ መሣሪያ ቢያነሳ፤ አመጽ ቢያነሳ፣ ወይ ሌላ ነገር ቢያደርግ ወይም የሌላ ኃይል መሣሪያ ቢሆን፤ የታጠቀ ኃይል እንደመሆኑ አገራችን ለተያያዘችው ለውጥ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥር ይችል ነበር። ይህ አለመሆኑ የሠራዊቱን ጠንካራ ዲስፕሊን የሚያሳይ ነው።

በአስተሳሰብና በአመለካከት ደረጃ ሠራዊቱ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ብቻ ሳይሆን፤ ተጽዕኖ ውስጥ እንዳይገባ፣ ጫና እንዳያድርስበት የማድረግ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል። ይሄ ገለልተኛ አቋምና ሀሳብ እንዲይዝ መደረጉ በተልዕኮ አፈፃፀሙ ላይ በየትኛውም አካባቢ፣ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች በሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች፣ የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች፣ የሃይማኖት ጥያቄና መሰል ጥያቄዎች በሚነሱ ወቅት ሠራዊታችን እንደ ዳኛ ነው የሚታየው። በሁሉም የሚከበር፣ ሁሉን የሚመክር፣ ህይወቱን ሰጥቶ ሰላሙን የሚያረጋግጥ፣ ሰላም የሚያወርድና ሰላም የሚጠብቅ፤ በሁሉም ህዝቦቻችንም ትልቅ ተቀባይነት የሚያገኝበትን ሁኔታ ነው የምናየው።

አሁን ሠራዊቱ ትኩረቱ የአገሩ ሉዓላዊነትና የህዝብ ደህንነት ላይ ብቻ ሆኗል። ይሄኛው ፓርቲ እንደዚህ ሆነ፤ ያኛው እንደዛ ሆነ በሚሉ አስተሳሰቦችና የፓርቲ ንትርኮች አጀንዳው ያልሆነ ሠራዊት ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በተለይ ይሄንን ከማገዝ አኳያ በመንግሥት ደረጃ ቀደም ሲል የነበረውን “የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለውን የግንባታ መጽሐፍ ወቅቱን በሚመጥን ሰነድ ለመተካት የተሠራው ሥራ ትልቅ ነው። ምክንያቱም ይሄ የግንባታ መጽሐፍ ከሕገ መንግሥቱ እጅግ የተቃረነና የተፃረረ ነበር።

ሕገ መንግሥቱ ሠራዊቱ ገለልተኛ መሆን አለበት ይላል። ከየትኛውም ፓርቲ ወገንተኛ መሆን የለበትም ይላል፤ በፖለቲካ ጉዳዮች እጁን አያስገባም ይላል፤ የፖለቲካ አዋላጅም መሆን የለበትም ይላል። እነዚህ ነገሮች ግልጽ በሆነ መንገድ በሕገ መንግሥቱ ተቀምጠዋል። በሀገሪቱ የሚኖረው የፖለቲካ ሥርዓት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንደሆነም በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ በተቀመጠበት ሁኔታ፤ ሠራዊቱ የሚገነባበት የፖለቲካ ኢንዶክትሪኔሽን ግን ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው ከሠራዊቱ ዓላማና የግንባታ መርሆዎች አንፃር በተፃራሪው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ፤ በአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ላይ የሚያተኩርና የሚያጠነጥን ነበር ።

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

የተለያዩ ርዕዮተ ዓለም እና አመለካከቶች ያላቸው ፓርቲዎች ሕገ መንግሥታዊ እውቅና አግኝተው እየተንቀሳቀሱ ባሉበት አገር፤ ሠራዊቱን በአንድ ፓርቲ ፕሮግራም ላይ፣ በአንድ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ላይ መቅረጽና መገንባት ተገቢ አልነበረም ። ከሕገ መንግሥቱም የሚቃረን፤ ፀረ ሕገ መንግሥት ነበር። በሪፎርሙ ከተከናወኑ ሥራዎች አንዱ እና ትልቁ ሥራ ሠራዊቱን እንድንገነባ ያስቀመጥነው ዓላማ እና የሠራዊቱ ተልዕኮ ከየትኛውም የፓርቲ ፕሮግራም ወይም ርዕዮተ ዓለም በላይ እንዲሆን ማድረግ ነው።

በሪፎርሙ ሠራዊቱ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በግልጽ አውቆ ለሱና ለሱ ብቻ ታማኝ እንዲሆን በሚያስች አስተሳሰብ እንዲገነባ ተደርጓል፤ ይሄ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ሕገ መንግሥቱ የሁላችንም የኢትዮጵያኖች ሕገ መንግሥት ነው። ፓርቲዎች ከሕገ መንግሥቱ በመለስ ናቸው። የሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ እጅጉን የገዘፈ ተልዕኮና ዓላማ ነው። ከአንድ ፓርቲ ፕሮግራምና ዓላማ በላይ ነው፤ የተከበረ፤ የአገርን ሉዓላዊነት፤ የህዝብ ደህንነት ላይ መሰረት ያደረገ ተልዕኮና ዓላማ ያለው ነው። ሠራዊቱ ይህንን ቁመና እንዲይዝ ነው እየተሠራ ያለው። ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ብሔር፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች የጋራ እሴቶች ላይ ተመስርቶ የሚገነባ ሠራዊት መሆን አለበት። ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የእኛ ነው ብለው የሚያምኑበት፣ በአስተሳሰባቸው እና በአብሮነት እሴቶቻቸው መገንባት አለበት።

ከዚህ አንፃር ከዚህ በፊት የነበሩት የግንባታ አካሄዶች በአዲስ መንገድ ተስተካክለው “የሠራዊት ግንባታ ስትራቴጂ” በሚል ማዕቀፍ በተዘጋጀ የመንግሥት ሰነድ መሠረት አመራራችንንም ሆነ ሠራዊታችንን እየቀረጽን፣ እያሰለጠንንና እየገነባን ነው። ልዩነቱንም በትክክል ማየት ይቻላል። ከዚህ በፊት ሕገ መንግሥቱ የሚለው እና የሠራዊት ግንባታ ሰነዱ የሚለው የተለያየ እንዲያውም የተፃረሩ ነበር። ይሄ ደግሞ በፍፁም መታረቅ ነበረበት። ምክንያቱም ሠራዊታችን የሁሉም ኢትዮጵያውያን፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያንም የእኔ ብለው የሚኮሩበት እና እነርሱን የሚያገለግል ተቋም መሆን የሚያስገድደው ሕገ መንግሥታዊ ሃላፊነትና ተልዕኮ የተሰጠው ነው።

ይሄንን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት፣ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይሄ ደግሞ ህጋዊ በሆኑ ዶክመንቶች ተደግፎ፣ ሰነዶችም ተዘጋጅተው እየተሠራ ነው። ጠቅላይ ሚንስትራችንም እንደገለፁት፣ ይህ ሰነድ ሚስጢራዊ ሰነድ አይደለም። ማንም ህዝብ ሊያገኘውና ሊያነበው የሚችል ነው። በሕገ መንግሥቱ ሠራዊቱ ለተሰጠው ተልዕኮና ሠራዊቱን በምንገነባበት ኢንዶክትሬኔሽን መሃል በጣም ከፍተኛ የሆነ መጣጣምና መመጋገብ እንዲሁም አንድነት የፈጠረ ነው።

በሪፎርሙ ትልቁ የተሠራው ሥራ ይሄ ነው ማለት ይቻላል። ይሄ ሰነድ በአንድ በኩል ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ሠራዊቱ እንዴት ገለልተኛ መሆን አለበት? የሚለው ነገር ከሕገ መንግሥቱ ጋር አጣጥሞ በግልጽ አስቀምጧል። ሁለተኛው ደግሞ ሠራዊቱ በውስጥም በውጭም አገራችን ሊገጥሟት በሚችሉ ማንኛውም አይነት የአውደ ውጊያ መስኮች፤ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ማንኛውም አይነት ስጋቶችን መከላከል የሚችል፤ ተዋግቶ ማሸነፍ የሚችል ሙያዊ የሆነ ተቋም እንዲገነባ በርካታ ስትራቴጂዎች ወይም አቅጣጫዎች የተቀመጡበት ሰነድ ነው። ሠራዊቱ ሥራው ላይና ሥራው ላይ ብቻ አተኩሮ እንዲሠራ፤ እንዲሰለጥን፤ እንዲማር፤ የሚያደርጉ ሥራዎች ናቸው የተሠሩት።

ከዚህ ጎን ለጎንም ሠራዊቱን በሁለንተናዊ መልኩ የማዘመን ሥራዎች ተሠርተዋል። የሰው ሀብት አጠቃቀሙ፣ የሰው ሀብት ግንባታው፤ የሀብት አጠቃቀሙን ዘመናዊ ማድረግ፤ ያሉትን ስጋቶች ሊቋቋም እና ሊመክት የሚያስችለው፣ አደረጃጀቶች እንዲኖሩት፤ ቀጣይ የአገራችን ዕድገት እና የአገራችን ስጋት በሚገባ እያነበበ የሚሄድ፤ ራሱን ሁል ጊዜ በለውጥ ውስጥ ያደረገ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ በርካታ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። ለዛም ነው አሁን እየሠራናቸው ያሉ ሥራዎች ከዚህ በፊት ከነበሩት ጋር ሲነፃፀር የሠራዊታችን ውጤታማነት እየጨመረ መጥቷል፤ ውጤታማ የሆነ ተግባቦት እየፈፀመ የመጣበት ሁኔታ እየተመዘገበ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከአመለካከትና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲልም ፓርቲና መከላከያ መርፌና ክር ሆነው ስለመኖራቸው ነው የሚነገረው። በሪፎርሙ በተጨባጭ ምን ያክል ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጠራን ነን ትላላችሁ? የቀዩን መጽሐፍ ወይም የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲን ስህተቶች ከማረም አንፃርስ ምን ተጨባጭ ነገሮች ተሠርተዋል?

ጄኔራል አደም፡- ከዚህ በፊት የነበሩት አካሄዶች እንዳልኩህ የመከላከያ ሠራዊት አመጣጡም ያው የምታውቀው ነው፤ ቀደም ብሎ ይሄ ሪፎርም ተሠርቶ ቢሆን ምናልባት እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችም ባልመጡ ነበር። የሠራዊቱ ግንባታ አቅጣጫ እና ሕገ መንግሥቱ መካከል ያሉ ክፍተቶች ታርቀው ቢሆን ኖሮ በርካታ ነገሮችን ማስተካከል ይችሉ ነበር።

ሪፎርሙም ቀደም ብሎ ቢጀመር ኖሮ አሁን የሚባሉና ዛሬ የሚነሱ አጀንዳዎች አይኖሩም ነበር። ሆኖም ለውጥ ሁል ጊዜ ይኖራል፤ የለውጥ አጀንዳም ሁል ጊዜ ይኖራል። እናም ራስህን እየለወጥህ መኖር አለብህ። ከዚህ አንፃር ሲታይ ሠራዊታችን በዋነኛነት እየገነባን የመጣነውም፤ በመሰረታዊነትም ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጡ ዋና ዋና የሕገ መንግሥቱ ምሰሶዎች ተብለው በሚታወቁት መርሆዎች፣ አቅጣጫዎችና በሠራዊቱ ተልዕኮዎች ላይ ነው። በመሆኑም ሠራዊታችን የነበረው መልካም ሥራ ከዚህ የሚመነጭ ነው ።

ቀደም ብዬ ለማንሳት እንደሞከርኩት የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለው ከሕገ መንግሥቱ ጋር በግልጽ የተቃረነ ነበር። በተቃራኒ የሄደ ሰነድ ነው። መታረም ነበረበት። በመሰረታዊነት ይሄ የሚመለከተው ደግሞ አመራሩ አካባቢ ያለውን እንጂ ታች ያለውን የሠራቱን አባል ብዙ የሚመለከተው ጉዳይ አይደለም። የሚያውቀውም ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ እንደ አስተሳሰብህ ነው የምትወስደው። እናም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለምን እንደ ብቸኛ ርዕዮተ ዓለም የሚወስድ ግለሰብ ሊኖር ይችላል፤ ላይኖርም ይችላል። በዛ አይነት ጫና ውስጥ የሚኖር አመራር መከላከያ ውስጥ አልነበረም ሊባል አይቻልም ነበር።

የፈለግከውን ርዕዮተ ዓለም መከተል ትችላለህ፣ እንደ ግለሰብ የሚከለክለህ የለም። ሶሻል ዴሞክራሲን ልታምን ይችላል፤ ወይም አብዮታዊ ዴሞክራሲን ልታምን ትችላለህ፤ ወይም ሌላ ልታምን ትችላለህ። ይህ እንደ ግለሰብ ያለህን እምነት ይዘህ ምርጫ ላይ ልትመርጥ ትችላለህ። ነገር ግን መከላከያ ላይ የተሰጠህን ኃላፊነት ግን ባልተገባ መንገድ ልትጠቀምበት አትችልም። ሠራዊቱን ልታነሳሳበት፤ ወታደራዊ ስምሪት ልትሰጥበት አትችልም፤ በግል የፖለቲካ አስተሳሰብህ ሠራዊቱን ልትገነባ እና ልትቀርጽ አትችልም።

የቀደመው የሠራዊት ግንባታ በሠራዊቱ ውስጥ ለነበሩ በርካታ የሠራዊት የግንባታ ጥያቄዎች ላይ እንቅፋት አልነበረውም ማለት አይደለም። ብዙ ኪሳራዎችም ነበሩት። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተቋም ግንባታ ላይ የተቀመጡ አስተሳሰቦችን በግለሰብ ደረጃ አለመቀበል እንደ ሐጢያት ይቆጠር ነበር። በዚህም የከሰርናቸው ኪሳራዎች አልነበሩም ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ወደ አስተሳሰብ ትሄዳለህ ማለት ነው። ወይ አንዱን ጠባብ ብለህ ታባርራለህ፤ ወይ ትከስሳለህ። ወይ አንዱን ትምክህተኛ ብለህ ትጠረጥራልህ፤ ታባርራለህ፤ ወይ ትከስሳለህ።

እንዲህ አይነት ነገሮች በምንም ተዓምር ቢሆን የሠራዊቱን አንድነት ማፋለሳቸው አይቀርም፤ ዴሞክራሲያዊ አንድነቱንም አያስጠብቁም። እናም በአንዳንድ ጉዳይ የፓርቲ ፖለቲካ አጀንዳ በተነሳ ቁጥር ቀጥታ ወደ ሠራዊቱም እየመጡ ችግር የሚፈጥሩበት ጊዜ ነበር። ይሄንን በትክክል መረዳት ያስፈልጋል። ፖለቲከኞችም ቢሆን በአግባቡ መረዳት ያለባቸው ይመስለኛል። ሌላውን ትተን በአደባባይ የሆነውን እውነታ ማየት እንችላለን፤ ሠራቱን የኢህአዴግ ሠራዊት የሚለው አካል እንደነበረ ትተን፤ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው አመራርም ወይም ኢህአዴግ በውስጡ በነበረ ትርምስና ንትርክ ወይም የፖለቲካ ክርክርና ውይይት እርስ በእርሳቸው ወደ አለመግባባት በሄዱበት ጊዜ ይሄን ሠራዊት የእኛ አይደለም ብሎ እስከመጠራጠር የተሄደበት እውነታ ነበር።

ይሄ ለእኔ ትልቅ ትምህርት ነው። ለፖለቲከኞቹም ትልቅ ትምህርት ነው። ዛሬ በስልጣን ላይ ያለ ገዢ ፓርቲ ነገ ሊደክም ይችላል። በምርጫም ሊሸነፍ ይችላል። በምርጫው ተሸንፎ በቀጣይነት ሊወዳደር ከሆነ ሕጋዊ ዋስትና የሚሰጠው ሕገ መንግሥቱ ነው፤ ሕገ መንግሥቱን የሚያስከብሩት የፀጥታ አካላት ደግሞ ከየትኛውም ፓርቲ አስተሳሰብ ነፃ ሆነው ሲገነቡ ሁሉም ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዚህ ተቋም ያለአግባብ ችግር አይደርስባቸውም፤ ህልውናቸውም እንደተጠበቀ ይቀጥላል ማለት ነው። ደከሙም ጠነከሩም ይሄ ይሆናል። እናም ይሄ ተቋም እንደ አገር ነው መኖር ያለበት። ለአገርና ለህዝብ ነው መኖር ያለበት እንጂ ለፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር የለበትም። እነሱ አንድ የማህበረሰብ ክፍል ናቸው፤ በዛ ማዕቀፍ መታየት አለባቸው።

የሠራዊቱም ጥንካሬ ከአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ጥንካሬ የሚነሳ መሆን የለበትም። ከአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ጥንካሬ የሚነሳ ከሆነ፤ ፓርቲው ሲጠነክር አብሮ የሚጠነክር ይሆናል። ሌላውን እያዳከመ የሚኖርም ይሆናል። ያ ፓርቲ ሲደክም፣ ነገ በሌላ መንገድ ወደ ሥልጣን የሚመጣ ሃይል ደግሞ የሚንደውና የሚያፈርሰው ተቋም ይሆናል። ስለዚህ ይሄ ተቋም የአገር እና የህዝብ ተቋም ሆኖ በትውልዶች መገንባት መቻል አለበት። ፓርቲዎች በራሳቸው በሚያደርጉት ጭቅጭቅና ንትርክ ይሄንን ተቋም መጠቀሚያ የሚያደርጉበት ሁኔታ ከተፈጠረ የሆነ ፓርቲ ወደሥልጣን በመጣ ቁጥር እየወደቀና እየፈረሰ እንደገና የሚገነባ ይሆናል። እየፈረሰ እየተገነባ የሚሄድ ተቋም ደግሞ ይህችን ታላቅ አገር አይመጥንም።

ኢትዮጵያ ገናና ታሪክ ያላት አገር ናት። ይህችን አገር እና ገናና ታሪኳን ለማስቀጠል፤ ከዚህም በላይ ገናና ታሪክ ለመሥራት፤ ወደ አለመችው ከፍታ ለማውጣት ካስፈለገ ይሄ ተቋም ጠንክሮ የህዝብና የአገር መሆን አለበት። አንድ የብሔራዊ አቅም አካል ሆኖ መገንባትና መቀረፅ አለበት። የሚቀረፀው ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮው ሊወጣ በሚችል መልኩ መሆን አለበት። የሚቀረፀው በአንድ ፓርቲ ፕሮግራም ወይም ርዕዮተ ዓለም ከሆነ ግን ዕጣ ፈንታው አሁን ያልኩት ነው። ስለዚህ የሠራዊታችን ሪፎርም እኔ መናገር የምችለው ቢያንስ ማንም ሰው ሊያነበው የሚችለው፤ ሠራዊታችንንም ከእንደዛ አይነት የፖለቲካ ጨዋታና ዘመምተኛነት ሊያወጣው የሚችል፤ አገሩንና ህዝቡን ብቻ እንዲያይ የሚያደርገው አቅጣጫ በግልጽ የተከተለ እና በሰነድ የተደገፈ ነው ።

ይህ ሰነድ ምንም አይነት የፓርቲ (ለምሳሌ፣ አሁን ያለው ገዢ ፓርቲ ብልጽግና ከሆነ) እሱን የሚመለከት የቃላት ሽታ እንኳን የለውም። እንኳንስ በግልጽ ብልጽግና ወይም ሌላ ፓርቲ የሚያራምደውን ርዕዮተ ዓለም ከሕገ መንግሥቱ ተቃርኖ ማስቀመጥ ይቅርና ቃል እንኳን ማግኘት አትችልም። ይሄ ትልቅ የመንግሥት ቁርጠኝነት ነው። እኛ የምንዳኘው በዚህ ነው ማለት ነው። እኛ የምንገነባው በዚህ ነው፤ በዚህ ነው ሠራዊታችንንም የምንገነባው። መንግሥት የሚጠይቀንም በዚህ አቅጣጫ ነው። መንግሥት የሚመራንም በዚህ በሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጡ የሕግ አግባቦች ብቻ ይሆናል ማለት ነው።

ስለዚህ መንግሥትም ሕግን ተከትሎ ሠራዊቱን ያዛል፤ ይመራል፤ ይገነባል፤ ይቀርፃል። ሲገነባና ሲቀርፅ ግን በፓርቲው ፕሮግራምና ርዕዮተ ዓለም አይሆንም። በአገሪቱ በተቀመጡ ብሔራዊ ፍላጎቶች፣ ብሔራዊ አቅም ግንባታ ላይ ተመስርቶ ነው። አገራችን ወደፊት በተጓዘች ቁጥር ሊያጋጥሟት በሚችሉ ማንኛውም አይነት ስጋቶች ሊከላከል፣ ሊያመክንና ሊቀለብስ የሚችል ተቋም አድርጎ መቅረጽ ነው። የሠራዊት ግንባታው ዓላማም፤ ትኩረትም ይኸው ነው። ሠራዊታችንንም ይሄንን ነው እያስተማርነው ያለነው። አመራሩንም ይሄንኑ ነው እያስተማርን ያለነው። ከአንድ ፓርቲ ፕሮግራም ጋር ሙት አይደለም እያልነው ያለነው። ከብልጽግና ወይም ከህወሓት ወይም ከኢዜማ ወይም ከሌላ ፓርቲ ጋር ሙት አይደለም እያልነው ያለነው።

እንደውም እነዚህ ሁሉ ተቋማት፤ እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች፤ እነዚህ ሁሉ አካላት ይሄን ሠራዊት ሳይነካኩት ወደየራሳቸው ፍላጎት ሳያመጡት፤ ለአገርና ለህዝብ ብቻ የሚተጋና የሚቆም ተቋም እንዲሆን አግዙን ነው የተባሉት። መንግሥትም ይሄን ነው እየጠየቀ ያለው። ከዚህ አንፃር መንግሥት የሠራዊቱን የግንባታ ሰነዱ በማዘጋጀት እና ተግባራዊ እንዲሆን ያሳየው ቁርጠኝነት ትልቅ ነው። በሰነዱ ሠራዊታችን ስልጠናም እየወሰደበት ነው።

በተግባርም አሁን እያየን ያለነው ሠራዊታችን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ገለልተኛ ሆኖ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ /ግዳጁን/ በሚገባ እየተወጣ ነው። የሚያኮራ ሠራዊት ሆኖም ነው እየተገነባ ያለው። በዚህ አጋጣሚ ምናልባት በርካታ ኢትዮጵያውያንም ወጣቶችም ይሄን ሠራዊት ሊቀላቀሉ የሚችሉበት ጊዜም አሁን ነው ብዬ አምናለሁ ።

አዲስ ዘመን፡- ከመከላከያ ሪፎርም ሥራው በተጓዳኝ ከለውጥ ማግስት መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የወሰዳቸው እርምጃዎችን አሁን ካለንበት ሁኔታ አንፃር እንዴት ይገልፁታል?

ጄኔራል አደም፡- ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በመንግሥት የተወሰዱ በርካታ እርምጃዎች አሉ። እነዛ እርምጃዎች በትጥቅ ትግል ጭምር ታግዘው ፀረ መንግሥት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ አገር ውጭ ሆነው ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ አገር ውስጥም እንዲሁ ሰላማዊ የሆነ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ፓርቲዎች፤ ከዛም በላይ በርካታ እስረኞችን የተፈቱበት ሁኔታ ነበር። በርካታ አክቲቪስቶች ወደአገራችን የገቡበት፣ በአንዴ ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ያለው ህዝብም እየወጣ እንኳን ደህና መጣችሁ እያለ የተቀበላቸው፤ ብቻ በአገራችን ታይቶ የማይታወቁ ኩነቶች የተከሰቱበት ነው።

የፖለቲካ ምህዳርን ከማስፋት ጋር ተያይዞ እውነትም ይህችን አገር ለአንዴና ለመጨረሻ ከነበርንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ወይም ችግር ሊያስወነጭፋት በሚችል መልኩ የመንግሥት ሆደ ሰፊነት የታየበት ነበር። ይህም አንዱ የለውጡ ትሩፋት ነበር። ለውጥ ደግሞ በአንድ ጀምበር ተጀምሮ የሚጨረስ ጉዳይ አይደለም። ብዙ ዋጋ መክፈል የሚጠይቅ፤ በየጊዜው የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች እየተሻገርክ፣ እየተለወጥክ፣ እየለወጥክና እያስተካከልክ ወደምትፈልገው መንገድ በቁርጠኝነት መሄድን የሚጠይቅ ነው። ይህን ማድረግ ሳንችል ከተዘናጋህ ለውጡ ወደኋላ ሊመለስ ይችላል።

ምንም እንኳን ዋጋ ያስከፈሉ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም፤ እስካሁንም መንግሥት የገባባቸው የለውጥ ቁርጠኝነቶች ተጠናክረው እየቀጠሉ እንዳሉ መናገር ይቻላል። አሁንም በርካታ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን ሠራዊታችን በሚገባ ይረዳቸዋል። በየቀኑ እነዚህን ጥያቄዎች ስለሚሰማ ብቻም ሳይሆን፤ በእነዚህ ጥያቄዎች ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችንም ለማብረድ ወይም ለመከላከል የሚያስችሉ ግዳጆችን ስለሚቀበል ያውቃቸዋል። መንግሥታችን እነዚህን ጥያቄዎች በተለያዩ መንገዶች ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው። ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን ለመቀልበስም አቅም መፍጠር ያስቻለ ነው ብዬ አስባለሁ።

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

ለውጥ ስለተፈለገ ብቻ በአንድ ወቅት የሚመጣና ለነገሮች ሁሉ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። አሁንም ብዙ ትግሎች የሚጠይቀን ነው። እየጠየቀንም እያየነው ነው። እነዚህን ሁሉ ማለፍና መራመድ ያስፈልጋል። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ጠንካራ የህዝብ ሥራ መሥራት ይጠይቃል። የፀጥታ ተቋማትን ማጠናከር ይጠይቃል። ፖሊስ መጠናከር አለበት፤ ደህንነቱ መጠናከር አለበት፤ መከላከያ መጠናከር አለበት፤ የፍትህ አካሉና ሌላውም መጠናከር አለበት። እነዚህ ተቋማት ሲጠነክሩ ቀደም ብለው ያመለጡንን ቀዳዳዎች ቶሎ ብለን እየዘጋን እንሄዳለን። ምክንያቱም ህዝባችን አሁንም ምንጊዜም ከመንግሥት ጋር ለሰላም የሚቆም ነው። ለመልካም አስተዳደር የሚቆም ነው። ለልማቱ የሚቆም ነው።

ችግሮች በየዘርፉ እየተፈቱ የመጡ ቢሆንም፤ ተግዳሮቶቹ ሊቀጥሉ ይችላሉ። በመሰረቱ እየተፈቱበት ያለው አካሄድ ግን መንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ በጣም ብዙ ዋጋ እየከፈለ የሄደባቸው ናቸው። ህዝቡን ለማስተማር፣ ከተግባሩ እየተማረ እንዲሄድ ለማድረግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠንነት በተጨባጭ ያሳየ ነው። ምናልባት በአንዳንድ ወገኖች የመንግሥትን አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ወይም የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት እንደአለመቻል፣ ወዘተ አድርገው ሲያዩት ይታያል። ይሄ ትልቅ ስህተት ነው። ዞሮ ዞሮ እነዚህ ጥያቄዎች የህዝቡ ጥያቄዎችም ያሉበት በመሆኑ አፈታቱ፣ አያያዙና አካሄዱ እጅግ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፤ ህዝብን በሚያስተምር፣ ህዝብን በሚያሳትፍ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ ደረጃ በደረጃ እርምጃ እየተወሰደ መሄድ ስላለበት ካልሆነ በስተቀር፤ መንግሥት አሁንም በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ከፀጥታ ተቋማቱ በላይ የሚሆን ነገር በሀገሪቱ የለም ።

በተግባርም ካየን ብዙ በትጥቅ ትግል መንግሥትን ሲቃወሙና ሲታገሉ የነበሩ በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ ያሉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። የሚቀሩ ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም፤ ከኤርትራ ጋር ሠላማዊ ሁኔታ ተፈጥሯል። አሁን እኛ በአገራችን ደህንነት ከውስጥም ከውጭም ሊመጡ የሚችሉ ሌሎች ስጋቶች ላይ አትኩረን እንድንሠራ እንጂ በፓርቲ ፖለቲካ ንትርክ ላይ አትኩረን እንድንሰራ እዛ ላይ አጀንዳውን ያደረገ ተቋም እንድንገነባ እየተደረግን አይደለም። እናም ከዚህ በፊት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እየሄዱ ነው ያሉት ብዬ ነው የማስበው።

አዲስ ዘመን፡- የውስጥ በርካታ ችግሮች ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ በተለያየ ጊዜ ከሚፈጠሩ የውስጥ አለመረጋጋቶች፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ካለችበት ጅኦ ፖለቲካ አንፃር በሕዝቦች ዘንድ ሥጋት አለ። አንዳንዶችም ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው፤ እየፈረሰችም ነው፤ ሲሉ የሚደመጡም አሉ። ለመሆኑ መከላከያው እነዚህን ከውስጥም ከጆኦ ፖለቲካም አንፃር ተያይዘው የሚነሱ ሥጋቶችን መሠረት ያደረገ ዝግጁነቱ ምን ይመስላል?

ጄኔራል አደም፡- ይቺ አገር ትፈርሳለች የሚለውን ነገር ብዙ ጊዜ የምንሰማው ጉዳይ ነው። አገርን የሚያፈርስ ችግር የለው ወይም አደጋ የለም ማለት አልችልም። ምክንያቱም በዓለማችን የፈረሱ አገሮች አሉ። ሊቢያን ማየት ይቻላል፤ የመንን ማየት ይቻላል፤ ሶሪያን ማየት ይቻላል፤ ሶማሌንም ማየት ይቻላል። እናም በርካታ አገሮች በተለያየ ምክንያት (በውስጥም በውጭም ባሉ የተለያዩ ተጽዕኖዎች) ፈርሰዋል፤ አንድ አገርም የነበረውን ጥንካሬ ይዞ እንዳይሄድ ተላላኪም ሊሆን ይችላል ወይም እንዲፈርስ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎች የሉም ማለት አልችልም።

በአገራችን ሁኔታም ይሄንን የሚያቀነቅኑ ሃይሎችም ሊኖሩ ይችላሉ። የእኔ ጥቅም ካልቀደመ ወይም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚል ፍላጎት ያለው ቡድን የለም እያልኩህ አይደለም። ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ ያቆማት ነገር ደግሞ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች ወይም አካላት አይደሉም። ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ነበረች። ኢትዮጵያ የምትኖረው በሕዝቦቿ አንድነት፤ በሕዝቦቿ የመተሳሰብ የጋራ እሴቶችና ኢትዮጵያውያን አሁን ላለችው ኢትዮጵያ በከፈሉት መስዋዕትነት ነው። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የከፈሉት መስዋዕትነት፣ የከፈሉት ዋጋ አሁንም ኢትዮጵያን የሚያስቀጥላት አስተሳሰብና አመለካከት አለ ብዬ አምናለሁ። ከዛ በላይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የቆሙ ሃይሎችም ቀላል ናቸው ብዬ አላስብም።

ስለዚህ ኢትዮጵያን እኔ ከሌለሁ ትፈርሳለች ወይም እኔ ካልተጠቀምኩ እናፍርሳት የሚለው አካል ሁል ጊዜ ቢናገርም፤ በእኔ በኩል ኢትዮጵያ የምትፈርሰው መጀመሪያ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ላይ የሚያምኑት ሕዝቦቿ እና መሪዎቿ ከሌሉና ከሌሉ ብቻ ነው። ከዛ በላይ ኢትዮጵያ የምትፈርሰው የመከላከያ ሃይላችን፣ የፀጥታ ሃይላችን፣ የደህንነት ሃይላችን ሲፈርስ፤ ወይም እሱ መስዋዕት ሆኖ ሲሸነፍ ብቻ ነው። ስለዚህ አሁን ያለን የሪፎርም ሥራዎች የአገራችንን ገናናነትና ሉዓላዊነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ ሥርዓት መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው፤ የሠራዊት ግንባታውም እንዲሁ ። በአስተሳሰብም በተግባርም ኢትዮጵያን የበለጠ የሚያጠነክር ሥራ ነው እየተሠራ ያለው።

ከዛ በላይ ሠራዊታችን እንደምታውቀው በመደበኛም ኢ-መደበኛም በየትኛውም ውጊያ ልምድ ያካበተ ሠራዊት ነው። ሰላም በማስከበር በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም የተሰማራና ውጤታማ የሆነ ነው። በውጭ አገር የምንሰራውን የሰላም ማስከበር ሥራ በአገራችንም እየሰራን ነው። ከዛ በላይ ደግሞ የዚህ ሠራዊት ቁመና መለካትም ያለበት በህዝባዊ አስተሳሰቡ፣ አመለካከቱ እና ጀግንነቱ ነው። ምን ጊዜም ቢሆን የሞራሉና የጀግንነቱ ምንጭ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደመሆኑ፤ ከጎኑ የሆነ ህዝብ ያለው ተቋምና ሠራዊት ደግሞ የጥንካሬ ምንጩ መሆኑን ካላየህ በአንድ ወቅት የታጠቀው ዘመናዊ መሣሪያ አሁን የትም ሊያደርስ አይችልም። ስለዚህ አሁን ሠራዊታችን ሆነ የመከላከያ ተቋሙ ከፍተኛና ጠንካራ የሆነ አቅምና ብቃት ያለው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማረጋገጥ ይቻላል።

ይሄ ብቻ አይደለም፤ ከሌሎቹ የፀጥታ ተቋማት ከፖሊስ፣ ከደህንነት እና ከክልል የፀጥታ ተቋማት እንዲሁም ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር ተናብበንና ተቀናጅተን ነው የምንሰራው። ሁሉም አቅሞች ተደምረው ለምንፈልገው የአገራችን ሉዓላዊነት መከበር፤ የውስጥ ሰላማችንን መከበር፤ እና የሕግ የበላይነትን መከበር ረገድ አሁን የተጀመሩ ሥራዎች በጣም አመርቂ ናቸው። የፀጥታ ተቋሞቻችን ከፍተኛ ጉልበት ያላቸው፤ ከፍተኛ አቅም ያላቸው፤ ቅንጅትና መናበብ ያላቸው ናቸው፤ ሠራዊታችን በውስጥም በውጭም እየተቃጡበት ያሉትን ትንኮሳዎችና ድርጊቶች አሁንም እየተከላከለ ነው። መረሳት የሌለበት በርካታ ኢትዮጵያን የማተራመስ ፍላጎት ያላቸው አካላት አሉ። የጎሳ ግጭት እንዲነሳ፤ የሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ፤ የብሔር ግጭት እንዲነሳ ያላሰለሰ ጥረት ተደርጓል። ይሄ ተቋርጦ አያውቅም። ይህን ታሳቢ ያደረገ የዕለት ተዕለትዝግጁነት አለ ።

ሠራዊታችን ከዳር ድንበሩ ጭምር የአገሩን ሰላም በማረጋገጥ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ፤ ከፍተኛ አቅም እየገነባ ያለ ተቋም ነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ ውስጥ መገባት የለብንም። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሪፎርም አጀንዳውም አንፃር ሠራዊታችን የበለጠ አቅሙን ለማጠናከር አዳዲስ አደረጃጀቶችን እንደ ባህር ኃይል፤ የሳይበር ሃይል ይዞና በዚህ ላይ አቅም ገንብቶ ለመሄድ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራን ነው። በአየር ሃይላችንም እንደዚሁ እየተሰራ ነው፤ በሁሉም መስኮች አገራችንን ሊያጋጥሟት ከሚችሉ አደጋዎችና ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችሉ ተጨማሪ አቅሞችን ለመገንባት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እተደረገ ያለበት ሁኔታ ላይ ነን ።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህ በሕዝብ ዘንድ ያሉ ሥጋቶች ተወግደው አገራዊ ለውጡም ህዝባዊ ለውጥ ሆኖ እንዲቀጥልና አገርም እንደ አገር ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንድትቀጥል ከማድረግ አንፃር በመከላከያ ሠራዊቱ ያለ ቁርጠኝነትና ወቅታዊ አቋም በምን ደረጃ የሚገለጽ ነው?

ጄኔራል አደም፡- ሠራዊታችን አሁን በውስጥም በውጭም የተሰጠውን ግዳጅ በትጋት እየተወጣ ነው። የትኛውንም ግዳጅ ለመወጣት በሁለንተናዊ መልኩ ዝግጁነቱ የተጠበቀ፣ የተስተካከለም ነው። ሠራዊታችንን አሁን በግልጽ ብናየው ባልተስተካከለ የሠራዊት የኑሮ ሁኔታም ቢሆን ግባ ባልከው ቦታ ላይ ሁሉ የሰጠኸውን ግዳጅ በብቃት የሚወጣ የግዳጅ ዝግጁነት ያለው ነው። ማሳያው አንዱ አገር ውስጥ ሰላምን በማረጋገጥ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት እያነበበ ህዝቦች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች መሃል እየገባ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ እጅግ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ እየሰራ ነው። ይሄ አንዱ የሠራዊታችንን ውጤታማነት ማሳያ ነው። በዚህ ምክንያት ከህዝባችን እያገኘን ያለነው ግብረ መልስ ሠራዊታችን በሄደበት ቦታ ሁኔታዎችን ካረጋጋ በኋላ ሕዝቡ ሠራዊቱ ወደነበረበት እንዲመለስ አይፈልግም። ሠራዊቱ እዛው እንዲቆይ ነው የሚጠይቀው ።

ምክንያቱም አሁንም ስጋቶች አሉ። እነዛ ነገሮች ተመልሰው ይመጣሉ የሚል የህብረተሰብ ክፍል አሁንም ሠራዊታችን እንዲለየው አይፈልግም። ይሄ በየትኛውም ሠራዊታችን በተሰማራበት አካባቢ ላይ ያለ ልምድ ነው። ይሄን ስናደርግ መራብ አንድ ነገር ነው፤ መድከም አንድ ነገር ነው፤ በሁለት ጎሳ ግጭት መሃል ገብቶ ሲያረጋጋ መሣሪያ እያለው ተተኩሶበት ከየት እንደተተኮሰ ሳያውቅ የሚሞት የሠራዊት አባል አለ። በዚህ መልኩ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው ሰላም እያስቀጠለ ያለው።

ከዛ በላይ በውጭ አገርም ያሉ የሰላም ስምሪቶችን ከወሰድን ሠራዊታችን አሁንም እጅግ የተከበረ፤ የተወደደም ነው። ሰላም ማስከበር በሄድንባቸው ህዝቦችና መንግሥታትም ተመሳሳይ መርህ ይዞ እዛም ያለው ሕዝብ፣ እዚህም ያለው ሕዝብ አንድ ነው ብሎ የሚያምን ሠራዊት ስለገነባን እዛም ውጤታማ ሥራ እየሠራ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ከዛ ባሻገር የአገራችንን ዳር ድንበር በየትኛውም አካባቢ እያስከበረ ያለ ሠራዊት ነው።

የአካባቢ አገሮችን ሁኔታ ደግሞ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ጠንካራ መንግሥታዊ መዋቅር የሌለባቸው አካባቢ፤ ከፍተኛ የሆነ የኮትሮባንድና የሰዎች ዝውውር፤ የመሣሪያ ዝውውር፤ የአክራሪ ቡድኖች (አልሸባብንና የመሳሰሉ አክራሪዎች) እንቅስቃሴ የሚስተዋልበት ነው። አክራሪ ሃይሎች አገራችንን ለማጥቃትም ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ይዘው በዕቅድ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው፤ ዕቅዳቸውን ያከሸፈ ሠራዊት ነው። ስለዚህ በየትኛውም መመዘኛ ከተመጣ ሠራዊታችን አሁን እንደ ተቋም፣ እንደ ሠራዊት ወስደህ ለውጡ በተፈለገው መንገድ እንዲሄድ ከሕዝቡ ጎን ነው።

ሕዝባችን ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የመለወጥ ፍላጎት አለው። ኢትዮጵያ እንድታድግ ይፈልጋል፤ ኢትዮጵያ እንድትለወጥ ይፈልጋል፤ ዴሞክራሲያችን እንዲያድግ ይፈልጋል፤ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ይፈልጋል፤ ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ ይፈልጋል፤ ከየትኛውም ቦታ ተነስቶ የትኛውም ቦታ ተንቀሳቀሶ ሀብት ማፍራት ይፈልጋል፤ የመኖር ነፃነቱ እንዲከበርለት ይፈልጋል፤ ሰብዓዊ መብቱ እንዲከበር ይፈልጋል። ስለዚህ እነዚህ ጥያቄዎቹን በተቻለ መጠን ሠራዊቱን በሚመለከተው ጉዳይ ላይ የህዝቡን ደህንነትና ፀጥታ በማስከበር፤ ልማቶች እንዳይቋረጡ ልማቱ እንዲቀጥል በማድረግና ሰላምን በማረጋገጥ እየሠራ ያለው ሥራ ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው፤ ሊበረታታ የተገባ፤ ለህዝብ ያለው ወገንተኝነትና ጠንካራ ዲሲፕሊን የተመሰከረ ነው።

በዚህ ደረጃ እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሥራውን የሚያከናውን ተቋም ነው፤ እዛም እዚም በግለሰብ ደረጃ ወይም በቡድን ደረጃ የሆነ ችግር ሊሰራ ይችላል። ያ በግለሰብ ሆነ በቡድን ደረጃ የሚታይ ነው። በተቋም ደረጃ መፈረጅ የለበትም። ስለዚህ ጥፋቶች ሲፈፀሙ ወይም ጥፋቶች ሲኖሩ መከላከያ ራሱ ሕግ አለው፤ ከዛ በላይ የሆነ ነገር ሲኖር ደግሞ በአገሪቷ ሕግ ይጠየቃል። ማንኛውም አካል ከሕግ በላይ ስላይደለ የሚጠየቅበት አሠራር አለ። እየተጠየቀም ያለ አካል ሊኖር ይችላል። እናም በዚህ ማዕቀፍ ነው ሠራዊታችን ግዳጁን እየተወጣ ያለው።

አዲስ ዘመን፡- በአንዳንድ ወገኖች መንግሥት ሠራዊት ሊያዘምትብን ነው፤ ወዘተ የሚሉ የአሉባልታ ወሬዎችን በማሰራጨት ሕዝቡን በማደናገር ወዳልተገባ ውጥረት ውስጥ እየከተቱት መሆናቸው ይሰማል። በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?

ጄኔራል አደም፡- መንግሥት ሕግ ማስከበር አለበት፤ ህዝባችንም መንግሥት ጠንክሮ ሕግ ማስከበር አለበት እያለ ነው። ስለዚህ ሕግ የማስከበር ሥርዓት የሁሉም የፀጥታ ተቋማት ተልዕኮ ነው። ከሕግ ውጭ ሆኖ፤ በተለይ በህዝቦች መካከል ቁርሾ በመፍጠር፤ ግጭት በመፍጠር፤ በሃይማኖትና በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች እየተፈረጁ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚደረጉ ሴራዎች ካሁን በኋላ ቦታ የላቸውም። ስለዚህ መንግሥት አንዳንዴ ጠንከር ብሎ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር መንግሥትን ብቻ ሳይሆን የፀጥታ ተቋማትንም ጭምር መንግሥት ባላተገባ መልኩ እየተጠቀመባቸው ነው ተብሎ መንግሥት ይወነጀላል፤ ተቋማችንም ይወነጀላል። ይሄ በአንድ መልኩ አንድ የትግል ስልት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ ነገሮችን በትዕግስት ሲያይና ሲመለከት ብሎም ሲጠብቅ፤ መንግሥት ዳተኛ ሆኗል፤ መንግሥት እርምጃ መውሰድ አልቻለም፤ መጠየቅ አልቻለም በሚል እነዚሁ ወገኖች በሌላ መንገድ መንግሥት አቅም የለውም፤ መንግሥት የለም ብለው ይከሱታል።

እንግዲህ መንግሥት ሠራዊት ሊያዘምት ነው ስለሚባለው፤ መንግሥት ሠራዊት የሚያዘምትበት አካባቢ የትኛው ነው? በምን ጉዳይ ነው የሚዘምተው? ሠራዊት ሲዘምት እንዴት ነው የሚዘምተው? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ሠራዊቱ የነጠረ ተልዕኮ አለው። የነጠረ ግዳጅ አለው፤ የነጠረ አሠራርና የሕግ ማዕቀፍ አለው። የሚያሰማራውም የመንግሥት አካል ይሄንን ሕግና ሥርዓት ተከትሎ ብቻ ነው። ይሄ አንድ ነገር ነው። ከዛ ውጭ ያሉ አጠቃላይ በአገራችን ያሉ ችግሮች ደግሞ በጥንቃቄ መታየት አለባቸው። ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩ፤ ጎሳን ከጎሳ የሚያጋጩ ሆን ተብሎ ሥራዎች የሚሠሩ ከሆነ፤ ይሄ ወደ ዘር ማጥፋት፣ ወደ እልቂት የሚያመራ ከሆነ መንግሥት እርምጃ ይወስዳል። ታዲያ የመንግሥት ተልዕኮ ምን ሊሆን ይችላል? እንደዚህ አይነት አደጋዎችን እንደ ሩዋንዳና ሌሎች አገሮች እንደሆኑት የሚጠብቅ መንግሥት ካለ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ማለት ነው።

ከዚህ ባለፈ መንግሥት ሠራዊቱን ለሆነ ላልሆነና ላልተገባ ዓላማ ሊያዘምተው አይችልም። ሊጠቀምበትም አይችልም። በዚህ ረገድ ቅድም ያነሳናቸው በርካታ የግንባታ ሥራዎች ይህ እንዳይሆን የሚያስችሉ ናቸው። የመንግሥት ሥልጣንም በሕግ የተገደበ ነው፤ የሠራዊቱም እንቅስቃሴ በሕግ የተገደበ ነው። እናም እንደፈለክ የምታደርገው ነገር አይደለም። ጉዳዩ ግን እሱ አይደለም፤ መንግሥት ሊያዘምትብን ነው የሚባለው ፕሮፖጋንዳ ዞሮ ዞሮ ቀድሞ ይሄ ሠራዊት የእኛ ነው ሲባል አሁን ደግሞ የእኛ አይደለም እየተባለም ሆን ተብሎ ለሚፈለገው የፖለቲካ አጀንዳ የሚፈልጉትን ሃይል ለማሰባሰብ የሚጠቀሙበት ማደናገሪያ ነው፤ መንግሥት ባልተገባ ሁኔታ ሠራዊት የሚያዘምትበት አመለካከትም አስተሳሰብም አለ ብዬ አላምንም። ይሆናል ብዬም አልገምትም።

Related stories   “ትህነግ ከጁንታነትም ወርዶ በየጫካው ተሹለክላኪ የእህል ሌባ ሆኗል፣ ከያለበት እየታደነ ነው “ሜ/ጀ መሐመድ ተሰማ

አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ግን መንግሥትና የመከላከያ ሠራዊት ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ እና አገርን የሚበትንና የሚያዳክም ማንኛውም ሕገወጥ የሆኑ ተግባራትን እያየ ዝም አይልም። ይሄ ግልጽ መሆን አለበት። ይህ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው ሃላፊነት ነው። የሠራዊቱም ተልዕኮ ይሄ ነው። መንግሥትም የሀገርን ሉአላዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት፤ ግዴታም አለበት። ስለዚህ ይሄ ሲሆን የሚሆነውን እናያለን ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ጦር ሊያዘምት ነው ከሚሉት በተቃራኒው እርሶም እንዳሉት መንግሥት ደካማ ነው የሚሉ አካላት አሉ። ይሄን ደግሞ ካለው ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘም ጭምር የሚነሳ ምናልባት ከፍትህና የፀጥታ አካላቱ ሥራ ጋር ሊያያዝ ስለሚችል በዚህ ላይስ የእርሶ ሐሳብ ምንድን ነው?

ጄኔራል አደም፡- በእኔ ግምት አንድ መንግሥት ጠንካራ ነው ወይም ደካማ ነው ለማለት በርካታ መስፈርቶች ያስፈልጋሉ። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ይሄን የህብረተሰብ የለውጥ እንቅስቃሴ ማመን ይገባናል። አገሪቷ ያለችው ለውጥ ላይ ነው። የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ያለበት አገር ነው፤ ያልተፈቱ የተወዘፉ የኢኮኖሚ ችግሮች ያሉበት አገር ነው፤ ያልተፈቱ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ያሉበት አገር ነው፤ ከፍተኛ የሆኑ የመልካም አስተዳደርና የማህበራዊ ዋስትና ችግሮችም እንደዚሁ የተወዘፉበት አገር ነው። ይሄ አመራርም ይሄን ተቀብሎ እየሰራ ነው። በዚህ የመጡት ለውጦች አሉ። ዋጋም እየተከፈለ ቢሆንም የፖለቲካ ምህዳርን ለማስፋት የተሰሩ ሥራዎች በርካታ ናቸው፤ የመጣው ለውጥም ከፍተኛ ናቸው።በኢኮኖሚው ረገድም በለውጥ ሂደት ሆና በጣም በርካታ ፈተናዎች (የኮቪድ 19 ችግር፣ የአምበጣ ችግርም፣ የተለያዩ ችግሮች) በአንድ ጊዜ የተጋረጡበት አገር እና መንግሥት ሆና እያለ፤ እነዚህን ችግሮች እንደየ አመጣጣቸው በመመለከት የአገሪቷ ኢኮኖሚ ከነበረበት መውደቅና መውረድ ወጥቶ ቆሞ ዕድገት እያሳየ ያለበት ሁኔታ ነው ሁላችንም እያየን ያለነው። ስለዚህ እነዚህ ወገኖች በየትኛው መመዘኛ ነው መንግሥትን ደካማ ነው እያሉት ያሉት? የሚለው መታየት አለበት። በኢኮኖሚው ነው? ወይስ በዴሞክራሲው ምህዳር በማስፋቱ ጥያቄ ላይ ነው? ወይስ በየቱ ነው? ስለዚህ ይሄ በእኔ ግምት መንግሥት በለውጥ ሂደት ውስጥ ያለ፤ ለውጥን እየመራ ያለ፤ ብዙ ችግሮችንም ተጋፍጦ እየሄደ ያለ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።

ከዛ ባሻገር ሕግ የማስከበር ጉዳይ ከሆነ ቅድም ካልነው የመንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ ከመሄድ፤ ካለፈው የፖለቲካ ጠባሳ ተነስቶ ህዝቡ ጥርጣሬ ውስጥ እንዳይገባ በተቻለ መጠን ማንኛውንም ነገር ለማስተናገድ መስዋዕት የከፈለ መንግሥት ነው ብዬ ነው የማስበው። ይሄ ማለት የመንግሥት ድክመት አይደለም። አሁንም ጠንካራ መከላከያ አለ፤ ጠንካራ ፖሊስ አለ፤ ጠንካራ ደህንነት አለ፤ ጠንካራ የፍትህ አካል አለ። በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ ለማጠናከር ሲባል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ናቸው ብዬ ነው የማስበው። ካልሆነ ግን መንግሥት በተለያዩ መንገድ የሚባሉ ነገሮች ከተወሰዱ፤ መንግሥትን ሕግ በማስከበር አቅሙም ከተለካ አሁንም ደካማ አይደለም፤ ጠንካራ ነው።

ይሄንን አሁንም ጀምሮታል። ከአሁን በኋላ የሰው ህይት እየጠፋ፤ ንብረት እየጠፋ ከዚህ በላይ ሆደ ሰፊ መሆን አይችልም ። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ሊያስገባ የሚችሉ ተግባራት እየታዩ በመሆኑ መንግሥት የሕግ የበላይነትን የሚያስከብሩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። ይሄ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ነው ያለው። አሁንም የመንግሥት የሰላም እጅ የተዘረጋ ነው፤ ፍፁም ሰላም ወዳድ ለሆኑ ኃይሎች የታጠፈ አይደለም። በጽናት የቆመ መንግሥት ነው ያለው፤ ይሄንን ወደፊትም ያረጋግጣል። ከዛ ውጭ ግን በሃይልና ባልተገባ መንገድ ይሄን አገር ለማፍረስ የሚደረጉ ሕገ ወጥ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ከአሁን በኋላ በምንም ተዓምር ቢሆን ተቀባይነት የሌላቸው ብቻም ሳይሆን፤ ልንታገሳቸው የማይገቡ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በደረስንበት ደረጃ የመንግሥትም ግልጽ አቋም የሕግ የበላይነትን ማስከበር፤ የህዝቡም ፍላጎት ሰላምን ማረጋገጥና የሕግ የበላይነት ይከበርልን የሚል ነው። ታዲያ መከላከያው ሕገ መንግሥቱን ከማስጠበቅ፣ ብሎም የአገርና የህዝብን ሉዓላዊነት ከማስቀጠል አኳያ ካለው ወቅታዊ ቁመና ባለፈ ቀጣይ ዝግጁነቱ እንዴት ይገለፃል?

ጄኔራል አደም፡- አንዱ የመንግሥት የሪፎርም አጀንዳ አጠቃላይ አገራችን መለወጥ አለባት፤ ማደግ አለባት፤ ወደ ታለመላት ከፍታ መውጣት አለባት ተብሎ የተገባውን ጉዳይ ለማረጋገጥ፤ አገራችንን ከውስጥም ከውጭም ለሚቃጡ ማንኛውም አይነት ጥቃቶች በመከላከልና በማኮላሸት ወይም በማክሸፍ ጭምር መሆን አለበት የሚል ነው። ይሄም የመከላከያ ዋናው ተልዕኮው ነው። የአገራችንን ሉዓላዊነት፤ የህዝቦችን ደህንነት፤ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችንን ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ይሄን በማድረግ የአገራችንን ሰላም እና የአገራችን ፈጣን ልማት እንዲረጋገጥ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ፤ ተልዕኳችንንም በሚገባ መፈፀም ነው።

ሁለተኛው ነገር፣ የሕግ የበላይነት በማስከበሩ መከላከያው ከፍተኛ ሚና አለው። ሌሎች የፀጥታ እና የፍትህ ተቋማት ፖሊስና ደህንነትን ጨምሮ ሕግን በማስከበርና ወንጀልን በመከላከል ተልዕኮ ያላቸው ቢሆኑም፤ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው መከላከያ እንዲወጣው ለማድረግ የሚያስችሉ አቅሞች የገነባ፤ የተሻለ ልምድ ያካበተ ተቋም ነው።

ዴሞክራሲን የመገንባት ጉዳይ ለአገራችን በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው። የዴሞክራሲ ሂደቱን ለማጠናከር የእነዚህ ተቋማት ገለልተኛ ሆኖ መደራጀት ወይም ሪፎርም የማድረጋቸው ጉዳይ የአገራችንን ፖለቲካም ዴሞክራሲም እንዲያድግ ያደርገዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የሕግ የበላይነት ያለ ዴሞክራሲ ዕድገት፤ የዴሞክራሲ ግንባታ ያለ ጠንካራ የሕግ የበላይነት ሊሳካ ፍፁም አይችልም። ስለዚህ የሠራዊታችንና ሌሎች የፀጥታ ተቋማት ተግባርና ተልዕኮ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ከፍተኛ የሆነ ትኩረት አድርገው መሥራት ያለባቸውና ለዚህም እየተገነባ ያለው አቅም አስተማማኝ ነው ብዬ ነው የማምነው። የተጀመረው የለውጡ ጉዞ ወይም ሕግ የማስከበር ጉዞ ከዚህ በፊት ከነበረውም በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

ከዚህ ባለፈ አሁን ያለን ሕገ መንግሥት ትልቁ የአገሪቷ የሁሉም ሕጎች የበላይ ነው። የሁሉም ሕጎች መነሻም መድረሻም ነው። ወደፊት የፖለቲካ አካሎች ወይም የፖለቲካ ሰዎች እና የህዝባችን ጥያቄ ሆኖ መሻሻል አለበት ተብሎ ከመጣ በህዝቦች ጥያቄና ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ እስካልተሻሻለ ድረስም ይሄ ሕገ መንግሥት ባለበት ፀንቶ የሚቀጥል ይሆናል። ይህ ሕገ መንግሥት የአገሪቱ ሕጎች የበላይ የሆነው ዶኩመንት፣ የሠራዊታችን ተልዕኮም ምንጭ ነው። ስለዚህ በዚህ በኩል ሕገ መንግሥቱ ተነካ፣ ሕገ መንግሥቱ ተጣሰ፣ ሕገ መንግሥቱ እንዲህ ሆነ የሚባለው ጉዳይ፤ በእኛ በኩል እንደ ሠራዊት ሲታይ (የተለያዩ ጥያቄዎች የሚነሱበት ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ፣ ይሻሻል የሚል አካል ሊኖር ይችላል፤ አይሻሻልም የሚል አካል ሊኖር ይችላል) የሠራዊታችን አጀንዳ አይደለም። የሠራዊታችን አጀንዳ መሆንም የለበትም። እሱ የፖለቲከኞች አጀንዳ ነው።

ይሄን አጀንዳ ካነሱት ደግሞ ወደ ውጊያ ለመግባት፤ ጦርነት በመቀስቀስና ጦርነት በማስነሳት መንቀሳቀስ በየትኛውም ወገን ቢሆን የሚሳካ ጉዳይ አይደለም። ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ጉዳይ ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንጂ፤ ይሻሻል የሚለውም፣ አይሻሻልም የሚለውም ኹከት በመፍጠር፣ ጦርነት በመክፈት፣ ህዝቦችን ወደ ግጭት በመውሰድ የሚፈፀም ተግባር ግን በፍፁም አይሆንም። እንዲህ አይነቱን ተግባርም ሠራዊታችን በምንም ተዓምር ቢሆን የሚቀበለው አይሆንም። ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ሥርዓት አለ፤ ሁሉም ነገር ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው መንገድና መንገድ ብቻ የሚፈፀም ነው።

አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ መከላከያ የሕዝብ ወገንተኝነቱን እያረጋገጠ ያለበት የሕዝብ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል። ከጅማሮ እስካሁን ብሎም እስከ ፍፃሜው የመከላከያ ሠራዊትና የህዳሴው ግድብ ቁርኝት በእርሶ እንዴት የሚገለጽ ነው?

ጄኔራል አደም፡- የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሀ ብሎ ሲጀመር ጀምሮ ሠራዊታችን ግድቡ ተገንብቶ እስኪያልቅ ድረስ ያለው አመለካከትና አስተሳሰብ ከፍተኛ ነው። ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የህዳሴ ግድብ ተገድቦ ለኢኮኖሚያችን የሚኖረውን አዎንታዊ አስተዋጽዖ በሚገባ ስለሚረዳ ነው። ስለዚህ ህብረተሰባችን በዚህ ግድብ ተጠቃሚ ሲሆን፤ በእያንዳንዱ ጎጆ መብራት ሲገባለት፤ ልማቱ ሲፋጠን፤ የሠራዊቱም ቤተሰብ፣ የሠራዊቱም አካባቢ አብሮ የሚቀየር ስለሆነ ሠራዊታችንም ከህዝባችን የተለየ አመለካከት አይኖረውም።

ልክ እንደ ህዝባችን በህዳሴ ግድቡ ላይ ሠራዊታችን ያለው አመለካከት እጅግ ከፍተኛ ነው። ይሄ በመሆኑ ሠራዊታችን የህዳሴውን ግድብ በዋነኛነት ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በዓይነ ቁራኛ የሚያየው ግድብ ነው። ከውስጥም ከውጭም ሊመጡ፤ በህዳሴ ግድባችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማንኛውንም ጥቃቶች ለመከላከል ከፍተኛ ጥረትና ሥራ እየሠራ ነው። በዚህም ግድባችን እስካሁን ድረስ ያለምንም እንከን እየተካሄድ ነው።

የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ እንደ ሠራዊት አንዱ የሉዓላዊነታችን መገለጫ አድርገን ስለምናየው፤ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ከፍተኛ የትኩረት አቅጣጫችን ነው። አመራሩም፤ አባሉም፤ በዛ አካባቢ ግዳጅ ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል ሌት ተቀን ግድቡን እየጠበቀ እስካሁን የመጣበት ሁኔታ አለ።

ሁለተኛ ደግሞ ህዳሴ ግድቡ የህዝብ ግድብ ነው፤ የአገር ግድብ ነው። በራሳችን ፋይናንስ እየተገነባ ያለ ልዩ ፕሮጀክት ነው። አገራችን እንደማንኛውም አገር ይሄን ግድብ የምትፈልገው ለሰላማዊ ነገር ነው። ሊውክለር አይደለም እየገነባች ያለችው፤ ወይም ሰፊ የእርሻ ልማት ለማካሄድ አይደለም እየገነባች ያለችው፤ ለልማቷ መሰረት የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው እየገነባች ያለችው።

ስለዚህ ይሄን ፕሮጀክት ሲታሰብ ጀምሮ በምንጀምርበት ጊዜም ግብጾች እንኳን እንዲህ አይነት ግድብ መገደብ ይቅርና በተለያዩ ቦታዎች የምንሰራቸውን የውሃ ማቆር ሥራዎች እስከመከታተል የሚደርሱ ስለሆነ፤ ግድባችንን ለማደናቀፍ ያልሠሩት ሥራ የለም። ፋይናንስ እንዳናገኝ አድርገዋል፤ ከዛ በላይ ህዳሴው ግድብ እንዲጓተት በተለያየ ምክንያት ሠርተዋል። በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ መንገድ የውክልና ጦርነት፣ የውክልና ግጭት በማካሄድም አገር ውስጥ ባለ ቡድን ጭምር ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ከባቢ አገራትንም እንደ መነሻ በመጠቀም ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲዋን ለማዳከም ከጎረቤት አገሮች ጋር በጥርጣሬ እንድትታይ በርካታ ሥራዎች እየሠሩ የመጡበት ሁኔታ አለ።

ይሄን ወንዝ ግብጾች የህልውና ጉዳይ ሊሉት ይችላሉ፤ ማወቅ ያለባቸው ግን ለእኛም የልማታችንም፤ የህልውናችንም ጉዳይ መሆኑን ነው። በመሆኑም ወንዙ ለእነርሱም የህልውና ለእኛም የህልውና ጉዳይ ነው። ሠራዊታችንም እነዚህን ሁሉ ነገሮች በጥንቃቄ ነው የሚያያቸው። ከዛም በላይ ደግሞ በራሳችን ፋይናንስ የሚገነባ ፕሮጀክት እንደመሆኑ እስካሁን ድረስ እስከ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዬን ብር በተለያዩ መንገድ ልክ ህብረተሰቡ እንደሚያዋጣው ያዋጣበት፤ እና ትልቅ አሻራውን የጣለበት ግድብ ስለሆነም በልዩ ሁኔታ የምንከታተለው፤ የምንጠብቀው፤ ከገንዘባችንም፣ ከጉልበታችንም በላይ ህይወትን እየከፈልንበት ያለ፤ ለመክፈልም የተዘጋጀንበት ትልቁ ፕሮጀክታችን ነው። ስለዚህ ግድቡን እኛ በዚህ መልኩ ነው የምናየው።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

ጄኔራል አደም፡- ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፤ የህዝባችን የሰላም ጥያቄ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረና እየተጠናከረ የመጣበት ሁኔታ አለ። በእኛ ሁኔታ ሰላምና ሠራዊት፤ ሰላምና ህዝብ፣ ሰላምና ልማት የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም። ሠራዊታችን ምንም እንኳን ሌት ተቀን ለህዝባችን ሰላም፤ ለአገራችን ደህንነት እና ለህዝቦች ደህንነት ያልከፈለው ዋጋ ባይኖርም፤ በዚህ ምክንያትም ያመጣቸውና ያስመዘገባቸው ከፍተኛ የሆኑ ድሎች ቢኖሩም፤ እነዚህ ድሎች፣ እነዚህ ውጤቶች ከቶውኑ ከህዝብ ተሳትፎ ውጭ አይደሉም።

ሠራዊታችን ከህዝብና ከህዝብ ጋር ሆኖ ስለሠራ በህዝባዊነቱ፣ በዴሞክራሲያዊነቱና በከፍተኛ ዲስፕሊን የህዝባችንን ባህልና ሃይማኖት እንዲሁም ልምድ አክብሮ በሁሉም አካባቢ ከህዝባችን ጋር አንድ ሆኖ በመሥራቱ፤ ሠራዊታችን መልሶ ህዝባችን ጋ የሚደርሰውን ማንኛውንም ችግር በቻለው ሁሉ ጉልበቱን ሳይሰስትና ገንዘቡንም ህይወቱንም በመስጠት ከህዝቡ ጋር አብሮ የሚውል የሚያድር፤ ለህዝብ የሚታገል፤ ለህዝብ የሚሞት ሠራዊት በመሆኑ፤ የሠራዊቱን ድልና ውጤት ከህዝባችን ነጥሎ ማየት ከቶውኑም አይቻልም። ስለዚህ ይሄ ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እላለሁ።

ሠራዊታችን የኢትዮጵያውያኖች ሠራዊት ነው። የኢትዮጵያውያኖች ሠራዊት ሲባልም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ብሔር ብሔረሰቦች ሠራዊት ነው። ሁሉም የሚኮሩበት ሠራዊት ነው። የአገሩንና የህዝቡን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ሌት ተቀን የሚጥር ሠራዊት ነው። ሠራዊታችንም ከየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ጋር አያይዞ ማየት ከዚህ በኋላ ህዝባችንም ሊታገለው የሚገባ፤ ህዝባችንም ሊቀበለው የማይገባው ነው። በተለይ ሠራዊታችንን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚብጠለጠልበት ጊዜ፤ ፖለቲሳይዝ የሚሆንበት ጊዜ ስላለ ህዝባችንም በተለይ ወጣቱ ከሠራዊታችን ጋር ሆኖ ሠራዊታችን ለሚከፍለው ማንኛውም ዋጋ ክብርና ምስጋና ሊሰጥ ይገባል።

ይህ ብቻም ሳይሆን ህዝባችን ካሁን በኋላ የተማሩ ልጆቹን በዚህ ተቋም እንዲቀላቀሉ፤ ልጆቹን እንዲሰጥና የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው እንዲቀላቀሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ። የሠራዊታችን ድሎች የሞራል ምንጭ ህዝባችን ነው። ህዝባችንም ነገ በምናደርገው ማንኛውም አይነት ሕግ የማስከበር ሥራ ከጎናችን እንዳይለይ፤ ከጎናችን ሆኖም የመረጃችን ምንጭ፣ የሞራላችን ምንጭ፣ የስንቃችንም ምንጭ ሆኖ ከጎናችን ተሰልፎ የአገሩን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲያሳካ አሁንም በድጋሜ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

በዚህ አጋጣሚ ሠራዊት እንመለምላለን፤ ሠራዊት ሲመለመል እጅግ ዲስፕሊን ያላቸው፣ ከምንም አይነት ሱስ ነፃ የሆኑ፣ ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ህዝብን የሚያከብሩ፣ ጥሩና ምስጉን የሆኑ ሥነ ምግባር ያላቸው ወጣቶች ሠራዊታችንን እንድትቀላቀሉ እያልኩ፤ መገናኛ ብዙሃኑም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጠን መልዕክቴን ማስለታለፍ እፈልጋለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ ከተጣበበ ጊዜዎት ላይ ቀንሰው ይሄን ሰፊ ቃለ ምልልስ ለማድረግ ፈቃደኛ ስለሆኑ እጅግ አመሰግናለሁ።

ጄኔራል አደም፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *