“Our true nationality is mankind.”H.G.

የውሃ ሙሊቱ ያን ያህል ቀላል ነበር አይደለም እንዴ? – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

ግብጽን ያመነና ጉም የዘገነ አንድ ነው - ከመርሐጽድቅ ...ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታው በመገባደድ ላይ ነው፡፡ ያን ያህል ምስጢር ባይሆንም አለቅጥ ንሮ የሰነባበተውን የዲፕሎማሲ ቴምፕሬቸር በመጠኑም ቢሆን ለማቀዝቀዝ ታስቦ በለሆሳስ ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሊትም አስራምስት ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን መንግሥት ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ለመላ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ለአለም-አቀፉ ሕብረተ-ሰብ በይፋ እንዳበሰረ ሰማን፡፡

ጥያቄያችን ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊና በአመክንዮ የተደገፈ ጭምር ነበር፡፡ ተፈጥሮም ይህንን አውቃ ነው መሰለኝ ከጎናችን ቆመች፡፡ ቸርነቷ በዝቶ በቂ ዝናብ ለገሰችን፡፡ ለሁለት ሳምንታት ያህል አከታትሎ የጣለው ዝናብ ትሩፋቱ የግብጻውያኑን ሟርት ገደል ከተተው፡፡ በአዎንታዊ ውጤቱም እስከ560 ሜትር ድረስ የገነባነው የግድቡ ክፍል ከአፍ እስከገደፉ ሞልቶ ሲያበቃ ውሃው በአናቱ ላይ ሲፈስ ለማመን በሚያዳግት ድባብ ተመለከትነው፡፡

ልቦናችን አብሮ በሀሴት ተመላ፡፡ አቀርቅሮ የቆየው አንገታችን ቀና አለና ኩራት ተሰማን፡፡ እንደዘርፉ ጠቢባን ሳይንሳዊ ማብራሪያ ከሆነ ከእንግዲህ ተጨማሪ ውሃ ለመያዝ ከፈለግን የግድቡን ከፍታ ይበልጥ ለማሳደግ ከመቸውም ጊዜ በላቀ ፍጥነት በስራው ላይ መረባረብ ይኖርብናል፡፡

እውነቱን ለመናገር በአሁኑ ወቅት ከግድቡ በስተጀርባ አስገድደን ያስተኛነው የውሃ መጠን አምስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትርን እንኳ አይሻገርም፡፡ አሃዙን በትክክል ለመጥቀስ ያህል 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ እንደሆነ ነው ሲገለጽልን የምንሰማው፡፡

ይህ በርግጥ ሁለት ተርባይኖችን ተክሎ የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨቱ ረገድ ቀላል የፍተሻ ሥራ ከማስጀመር የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ እርሱም ሊሆን የሚችለው ገና በሚቀጥለው ዐመት ነው፡፡

በሌላ አነጋገር የግድቡ ፍጻሜ ገና ብዙ ቀሪ ስራ የሚጠይቀን መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ተስፋው ብቻ ወደፊት አያሌ እርምጃዎችን ያንደረድረናል፡፡

በጥቁር አፍሪካ ክፍለ-አለም ግዙፉ ነው እየተባለ የሚነገርለት የባንዲራ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በጠቅላላው 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በሚይዝበት ጊዜ የሚኖረን ሀይል የማመንጨትና የማሰራጨት አቅም መጻኢውን የማደግ እድላችንን ያለጥርጥር ብሩህ ያደርገዋል፡፡

እጅግ የሚያስገርመው ጉዳይ ደግሞ ይህ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሊት የተከናወነው የታላቁ አስዋን ግድብ ራሱ ሳይጎድል መሆኑ ነው፡፡ ግብጻውያን ወንድሞቻችን ምንኛ ከሰሩ፣ ተዋረዱ?

“ቀድሞ የበላችው ያቅራታል፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንደሚባለው ጎረቤታችን ሱዳን እንኳ ለግብጽ አድራ ውሀዬ ቀነሰብኝ ማለቷን በዚያው ሰሞን ሰማሁ የሚለው አንድ የቆየ ወዳጄ አጫወተኝና ምን ያህል በሳቅ እንደፈረስኩ ልነግራችሁ ከቶ አልችልም፡፡

አሁን ማን ይሙት በእርጥቡና በሲሳያማው የሀበሻ ምድር ክረምቱ ገፍቶ በመጣ ቁጥር ለም አፈራችንን ያለርህራሄ ጠራርጎ እየተሸከመ ከከፍተኛ ተራሮቻችን ቁልቁል የሚምዘገዘገው ሀይለኛ ጎርፍ ደጋግሞ እንደሚጎበኛትና ክፉኛ እያጥለቀለቀ መከራዋን እንደሚያበላት የምናውቃት ጎረቤት አገር እንደምን ውሃው ቀነሰብኝ ስትል ያለይሉኝታ ልታማርር ትችላለች?

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

እንዲህ ያለው ሀሰተኛ ስሞታስ ክፉ አመል ከማስቆጠር ያለፈ ምን ያተርፍልኛል ብላ ይሆን ያን ያህል የምትወተውተው?

ለማናቸውም እኛ ዛሬ ላይ በሆነው ነገር ያለአንዳች ጥርጥር ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ቢሆንም ታዲያ ለጊዜው ጮቤ መርገጡን ቀነስ አድርገን ስራችንን በንቃት መቀጠል ይኖርብናል፡፡ “አይጥ ወልዳ ወልዳ…” እንዳይሆንብን ለሰከንዶችስ እንኳ ከጀመርነው የህዳሴ ጉዞ ተዘናግተን መታየት የለብንም፡፡

ታሪካዊ ጠላቶቻችን እስከወዲያኛው በራሳችን ተማምነን የመቆማችን ኩነት አብዝቶ ያስፈራቸዋል፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን በነጭ የበላይነት ላይ አይበገሬውን ክንዳቸውን ካሳረፉበት ከዝነኛው የአድዋ ድል ጋር ዝንት አለም ሲዘከር የሚኖረው የስማችን ገናናነት ከፍ ብሎ ሲወሳ ያስበረግጋቸዋል፡፡

በውስጥ አራጋቢዎቻቸው እየተረዱ ግብጻውያን በቻሉት መጠን አስፈራሩን፣ ፎከሩብንም፡፡ የሩቅ ጌቶቻቸው ሳይቀሩ ከሉአላዊ የግዛት ወሰናችን ሳናልፍ በራሳችን ላብና ደም በገነባነው ግድብ “ከግርጌው የተፋሰሱ አገሮች ጋር ሳትስማሙ የውሃ ሙሊቱንም ሆነ ሀይል የማመንጨቱን ፍተሻ ሥራ ከማካሄድ እንድትቆጠቡ” በማለት በግብዝነት ሊያስጠነቅቁን ሲከጅላቸው ታዝበናል፡፡

እነሆ ያ ሁሉ ባዶ ቱሪናፋ አለፈና በገነባነው ልክ ውሃውን ሞላነው፡፡ ከእንግዲህ በመሬት ላይ የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ የሚለውጥ ሀይልም አይኖርም፡፡

ሰውየው በልበ-ሙሉነት እንደተናገረው “እኛ በህይወት ቆመን ግድቡ በማንም አይደፈርም”፡፡ “እኛ ሳንፈርስ ኢትዮጵያ ከቶ አትፈርስም”፡፡ ይልቁንም ይህንን ውርደት የሚፈቅድ ሀሞት የለንም፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሊት መጠናቀቅ ምክንያት በማድረግ በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ምጥን፣ ግና ደግሞ ሳቢና ማራኪ መልእክት እዚህ ላይ ታወሰኝ፡፡

እርሳቸው በትክክል እንደጦመሩት “አባይ እስካሁን ድረስ ወንዝ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ወንዝ ብቻ ሳይሆን ሀይቅም ጭምር ለመሆን” ተገዷል፡፡

ሀበሾች ስንፈጠር እንደጎረቤቶቻችን ያን ያህል ስስታሞች አይደለንምና በድንበር ተሻጋሪ ወንዝነቱ ሱዳንና ግብጽን ጨምሮ ሁሉንም የናይል ተፋሰስ አገሮች በፍትሃዊነት ማገልገሉን እንዲቀጥል በሙሉ ልብና በቀና ህሊና እንተባበራለን፡፡ በሀይቅነቱ ግን አባይ ኢትዮጵያ ለፈለገችው አላማ ይውላል፡፡ እውነትም በዚህ ረገድ አባይ የኛ የራሳችን ሀብት ሆኗልና እንደቀድሞው ኢ-ፍትሃዊ ምርጫና የተስፋፋ ነጻነት እንዲኖረው አንፈቅድለትም፡፡ እኛን የተፈጥሮ ባለቤቶቹን ነጥሎ እየጎዳ የጎረቤቶቻችንን ምድር በብቸኝነት የሚያረሰርስበት አድላዊ አሰራር ለወደፊቱ ይቋረጣል፡፡

መላው አለም በከፍተኛ መደመም እስኪታዘባቸው ድረስ ግብጻውያን አይናቸውን በጨው አጥበው ጊዜ ያለፈባቸውንና ቀድሞ ነገር እኛ ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ያልተካፈልንባቸውን አሮጌ የቅኝ አገዛዝ ውሎች በዋቢነት እየጠቀሱ በአደባባይ ጭምር ሞግተዉናል፡፡ ሆኖም በዚህ የተወላገደ አቋማቸው ሳቢያ በብዙዎች ዘንድ ተወረፉበት እንጂ አልተከበሩበትም፡፡ ያሽሟጠጣቸው እንጂ ያዘነላቸው አገር ይሁን ተቋም ተፈልጎ አልተገኘም፡፡

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

የልእለ-ሃያሏ አሜሪካ አስተዳደርም ቢሆን አቋሙን እንደገና ቢመረምርና መልሶ ቢያጤነው በዲፕሎማሲ ረገድ የበለጠ ተጠቃሚው ከማንም በላይ እርሱ እንደሆነ በገዛ ዜጎቹ ሳይቀር እየተመከረ ነው፡፡ እነሆ ያ መከረኛ ምርጫ ተቃርቧልና አዛውንቱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በዘመቻው በቂ የጥቁር አሜሪካውያን፣ በተለይም የኢቲዮ-አሜሪካውያን መራጮቻቸውን የይሁንታ ድምጽ ለማግኘት አጥብቀው የሚመኙ ከሆነ ‘አምባገነኑ ወዳጄ’ ሲሉ ከሚያሞካሽዋቸው ከግብጹ ፕሬዚደንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ ጋር ያላቸውን ቃል ኪዳን ለማጽናት ብቻ በጭምጭምታ እንደምንሰማው በሀገራችን ላይ አፍራሽና በመረጃ ላይ ያልተደገፈ እርምጃ ለመውሰድ ከመወሰናቸው በፊት ሁለት ጊዜ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡

ያ ካልሆነ ግን ‘ውርድ ከራሴ’ እንዳይሆንባቸው ያሰጋል፡፡ በዴሞክራሲያዊ አውደ-ምርጫ ለተሳትፎ የወጣ የአንድ ሰው ድምጽ ዋጋ ራሱ አይናቅምና፡፡ ተከታዩን ኢትዮጵያዊ ብሂል ማስታወስ የሚበጀው ለዚህ ነው፡-

ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፤

አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ፡፡

አሜሪካውያን እንደራሳቸው የዘመን ቀመር በ1930ዎቹና አርባዎቹ የኮለራዶ ወንዝን ለማንበርከክና በጥቅም ላይ ለማዋል ሽቷቸው የሁቨር ዳምን ሁለት የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ እልፍኞች በአሪዞናና በኔቫዳ ክፍለ-ግዛቶች በሚገኙት የወንዙ ዳርቻዎች ላይ የመገንባቱን ፕሮዤ እንደዋዛ ቢጀምሩትም ሂደቱ ከጠበቁት በላይ ስለተወሳሰበባቸው የዜጎቻቸውን ህይወት ከመገበር አንስቶ በጊዜም ሆነ በወጪ ረገድ ምን ያህል ከባድ መስዋእትነት እንደከፈሉ ይዘነጉታል ብለን አናምንም፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን አዋጪነትና ዘርፈ-ብዙ ትሩፋት ላይ ብርቱ ተስፋ ጥለንበታል፡፡ ከእንግዲህ በሁለት እግሮቻችን ጸንተን እንቆማለን እንጂ እንዳንቀላፋን አንቀርም፡፡ እንራመዳለን እንጂ ባለንበት እንደቆምን አንቀጥልም፡፡ እንሮጣለን እንጂ በመራመድ ብቻም አንወሰንም፡፡

በመሰረቱ የአባይ ወንዝ አጠቃቀም፣ ልማትና አጠባበቅን አስመልክቶ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል አለም የሚያውቀው አሳሪ ስምምነት የለም፡፡ መላውን የናይል ተፋሰስ ተጋሪ አገሮች እርስበርስ ያስተሳስራል ተብሎ ከረዥምና አድካሚ ድርድር በኋላ እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ2010 ላይ የተደረሰበት የካምፓላው የትብብር ማእቀፍም ቢሆን በተለይ ግብጽና ሱዳን አሻፈረኝ በማለታቸው እስካሁን ድረስ ጸድቆ በገቢር ላይ አልዋለም፡፡

እንግዲህ ይህ ግልጽ የሕግ ክፍተት በሚታይበት ሁኔታ ሊጠቀስ የሚችለውና እነዚህን ነጻና ሉአላዊ አገሮች በፈቃደኝነት ላይ ለተመሰረተ የጋራ ውይይትም ሆነ ድርድር የሚያነሳሳው ብቸኛ ማእቀፍ ቢኖር የህዳሴውን ግድብ ግንባታ መጀመር ተከትለው የሶስቱም አገሮች መሪዎች ካርቱም ላይ በመገናኘት በማርች ወር 2015 የተፈራረሙት ልል የመግባቢያ ሰነድ መሆኑ ነው፡፡

በጠቅላላው አስር አንቀጾችን የያዘውና በጠባዩ አሳሪ ያልሆነው ይህ የመግባቢያ ሰነድ ‘የመርሆዎች መግለጫ’ (the Declaration of Principles) በመባል ነው የሚታወቀው፡፡ ከመጠሪያ ስሙ በቀላሉ ለመረዳት እንደሚቻለው ሶስቱ የራስጌና የግርጌ አገሮች ከድንበር ተሻጋሪው ወንዝ ጋር ባላቸውና በሚኖራቸው ግንኙነት ረገድ በመካከላቸው ሊከበሩ የሚገባቸውን አበይት መርሆዎች መርጦ ከመዘርዘር ባለፈ አዳዲስ የተናጠል መብቶችን አይፈጥርም፣ ተነጻጻሪ ግዴታዎችንም አይጥልም፡፡

Related stories   የተላላኪው ጠበቃዎች

ተጠቃሹ የመግባቢያ ሰነድ በአንቀጽ አምስት ስር ያካተተው መርህ ከህዳሴው ግድብ በስተጀርባ የሚተኛውን ሰው-ሰራሽ ሀይቅ ቀዳሚ የውሃ አሞላልና የራሱን የግድቡን ቴክኒካዊ ስራ አካሄድ ወይም አተገባበር ፖሊሲዎች በዝርዝር የሚመለከት ሆኖ ነው የምናነበው፡፡

ይህንን መርህ የሚያብራራው አንቀጽ አምስት ታዲያ ሶስቱም ተወዛጋቢ አገሮች ለተልእኮው ቀድመው ካሰማሯቸው ብሔራዊና አለም-አቀፍ ኤክስፐርቶች በኩል የሚቀርቡላቸውን የጥናት ውጤቶችና ሳይንሳዊ ምክረ-ሃሳቦች በመጠቀም ግንባታው ሳይቋረጥ የህዳሴው ግድብ ቀዳሚ የውሃ አሞላል የሁሉንም ወገኖች የጋራ ጥቅም ባማከለ መንገድ ሊካሄድ በሚችልባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች (scenarios) ላይ በግልጽ ተወያይተው አንድ አይነት ስምምነት ላይ ይደርሱ ዘንድ በቅን ልቦና ተባብረው እንዲሰሩ ለብ ባለ ድምጸት ከማሳሰብ ባለፈ ለዘመናዊ ዲፕሎማሲ ፍጹም ‘ጨዋነት’ ወይም እንግድነት የሚታይበት የትራምፕ አስተዳደር የግምጃ ቤት ሹም በአደባባይ ሊቀፍለን እንደሞከረው አንዳች ስምምነት ላይ ከመደረሱ በፊት ኢትዮጵያ አሁን እንዳደረገችው ሁሉ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሊት በራሷ ጊዜ እንዳታከናውን የሚከለክል ድንጋጌ ጨርሶ የለበትም፡፡

ስለሆነም የኛ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሊት ከተባለው ስምምነት በፊት ለማከናወን በመቻላችን የማድረግ አቅማችንን ለአለም ከማሳየት ባለፈ የተላለፍነው አንዳች አሳሪ ሕግ ወይም አስገዳጅ ስምምነት ባለመኖሩ እንዲመቸንና በተነቃቃ መንፈስ ስራችንን ቀጥለን ህልማችንን እንድናሳካ ያስፈልጋል፡፡

የሱዳናውያን ዲፕሎማሲያዊ ጅዋጅዌም ሆነ የግብጻውያን እዚህና እዚያ መርገጥ የፍርደ-ገምድል ተቆርቋሪዎቻቸው ብያኔ ታክሎበትም ቢሆን በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታ ከቶ ሊለውጠው እንደማይችል ከወዲሁ ተገንዝበን ኩራታችን የሆነውን የባንዲራ ፕሮጀክት በወጉ ለማጠናቀቅ ጨክነን እንረባረብ፡፡

በመጨረሻም ይህ ጸሀፊ ለበረሃው ትንታግ ለኢንጂኒየር ስመኘው በቀለ የማሳረጊያ መልእክት አለው፡፡

እልኸኛው ወንድማችን ከልብ እናመሰግንሃለን፡፡ ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ነፍስህን በመንግሥተ-ሠማያት እንዲያኖር ዘወትር እንመኛለን፡፣ እንጸልያለንም፡

እነሆ በአካል ብትለየንም በመንፈስ አብረኸን በመቀጠልህ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ እንደተመኘኸው አገባደን የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሊት ለማከናወን በቃን፡፡

ምነው ይህንን አስደሳች ኩነት እንኳ ለአንዳፍታ አንገትክን ቀና አድርገህ ለመመልከት እድሉን ባገኘህልን፡፡

መቸም ለዚያ ያድርሰን እንጂ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በይፋ የተመረቀ እንደሆነ ከአብራክህ የተከፈለ የስጋ ልጅህ ያህል ትሳሳለትና ትንከባከበው የነበረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በስምህ እንዲጠራና ለዘለአለም ሲዘከር እንዲኖር ደፍሮ አለመወሰን ፍጹም ውለታቢስነት የሚሆንብን ይመስለኛል፡፡

አበቃሁ፡፡

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0