በተለያዩ አጋጣሚዎች ቅርስ በእጃቸው ያለ ሰዎች ቅርሶችን በመመለስ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ ከደብረ ሰላም ወርቻሜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በ1962 ዓ.ም ጠፍቶ የነበረው የስንክሳር መጽሐፍ ተገኝቷል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ፀሐይ ጸዳሉ ነጋሽ እንዳሉት ከጠፋ ከ50 ዓመታት በኋላ የተገኘው ስንክሳር ከመጋቢት እስከ ነሐሴ የሚነበበውን የመንፈቅ ምንባብ የያዘ ነው፡፡ ስንክሳሩ ከ20 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት አለው፡፡
ስንክሳር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የቅዱሳንን እና የጻድቃንን ታሪክ የያዘ ትልቅ መገልገያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉ የሚዳሰሱ ቅርሶች መካከልም ትልቅ ሀገራዊ ገጽታ እና ትልቅ ሃይማኖታዊ ግልጋሎት ያለው ነው፡፡
ቅርሱ ከጠፋ ጊዜ ጀምሮ የማፈላለግ ሥራ ሲከናወን ቆይቶ ሐምሌ 4/2012 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ደብረ-ገነት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በማዳበሪያ ተጠቅልሎ ጸሎት በሚያደርጉ እናቶች ተገኝቷል፡፡ ሕጋዊ ሂደቱን ተከትሎ ወደ ቦታው መመለሱንም ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
መልአከ ፀሐይ ጸዳሉ እንዳሉት ዞኑ የበርካታ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች መገኛ ቢሆንም ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው ለጥፋት እየተዳረጉ ነው፡፡
ሀገረ ስብከቱም ከመንግሥት ጋር በመሆን በሰዎች እጅ የሚገኙ ቅርሶችን እያፈላለገ ነው፡፡ በዚህ ቅርሶች እየተገኙ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡም ሁለት ግለሰቦች ቅርስ ተገኝቶባቸው በሕግ ተጠያቂ ተደርገው በእስር ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ቅርስ በሚዘርፉ እና በሚያጠፉት ላይ የሚወሰደው ርምጃ አስተማሪ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
ቅርሶችን ለመንከባከብ በርካታ ሥራዎች ቢሠሩም ቅርሶች እየተዘረፉ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡ የሕዝቡ ተሳትፎ አናሳ መሆኑ፣ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ጠንካራ አለመሆኑ እና በርካታ ቅርሶች በሰዎች እጅ መገኘታቸው በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
የመምሪያ ኃላፊ ኃላፊው ወይዘሮ ሰናይት አስራደው እንዳሉት መንግሥት በቅርሶች ላይ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርግ እና አዳዲስ ቅርሶችን እንደሚመዘግብ አስታውቋል፡፡ የተመዘገቡት በየዓመቱ ኦዲት ስለሚደረግባቸው የመጥፋት ዕድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ይሰረቅብናል በሚል በእጅ ያሉ ቅርሶችን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ አለመሆን ግን ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም ግንዛቤ በመፍጠር ብዙ ቅርሶች ከማኅበረሰቡ ተመልሰው ምዝገባ ተደርጎላቸዋል፡፡
ቀደም ብሎ የተዘረፉ ቅርሶችን የማፈላለግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መምሪያ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ የታወቁ ጥንታዊ ቅርሶች ባሉባቸው ቦታዎችም የደብር ሙዚዬም በማሠራት ተገቢው እንክብካቤ ለቅርሶች እንደሚደረጉ ተመላክቷል፡፡ ሥራው በመንግሥት ብቻ ውጤታማ ስለማይሆን ሕዝቡ ቅርሱን ጠንክሮ ሊጠብቅ እንደሚገባም ወይዘሮ ሰናይት መክረዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በእጃቸው ያሉ ቅርሶችን ለመንግሥት እንዲያሳውቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ – (አብመድ)
ምስል፡- ከድረገጽ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   እኛ የምንመርጠው አባትና አያቶቻችን የመረጡትን ነው።

1 Comment

  1. ከዛጎ ዜና ብዙ የሀገር ውስጥ እና የውጭ መረጃዎችን አገኛለሁ። ዛጎሎች ብርቱ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *