ቄሮን በደፈናው ጽንፈኛ ማለት አግባብ አይሆንም። ጽንፈኛ የሚለውንም ስም ወደ ኦሮሞ ማጠጋጋት አይስኬድም። አብን ጽንፍ ረግጦ ነበር ዛሬ ልብ ገዛ እንጂ። በተለያዩ ክልሎች ጽንፍ የረገጡ ሃይሎች ተከስተው ከስመዋል። እያበቡ ያሉ አሉ። ልምድ ለመቅሰም የተዘጋጁና በጀት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙም አሉ። ሁሉም ግን በደፈናው የወጡበትን ማህበረሰብ አይወክሉም። ለልዩ ዓላማ ተደራጅተው አገር የሚያተራምሱ ሃይሎችን ሲቻል በመሪያቸው፣ አለያም በግብራቸው ብቻ ለይቶ መፈረጅ ያግባባል። ምክንያቱም ጥቂት አጉራ ዘለሎች ሚሊዮኖችን አይወክሉምና!!

በገመቹ – መቂ

“ቄሮ” በህቡዕ አደረጃጀት የተቋቋመው 2002 በኦነግ አማካይነት እንደሆነ ይነገራል። “ ቄሮ” በየአቅጣጫው ሲደረግ የነበረውንና ውጤታማ ሊሆን ያልቻለውን ትግል እንዲያግዝ ታስቦ ሲቋቋም ዛሬ በባለቤትነት የሚንጫጩት ሁሉ አልነበሩም።

“ ቄሮ” የወጣቶች አደረጃጀት ከቀድሞው የኢህአፓ የወጣቶች ሊግ ኢህአወሊ ጋር በአደረጃጀቱና በሚናው ተመሳሳይ ቅርጽ እንዳላቸው ስለ አደረጃጀቱ የሚያውቁ ይናገራሉ። ይህ በኦሮሚያ የውስጥ ለውስጥ ትግል እንዲያፋፍም የተመሰረተው የወጣቶች ክንፍ የታሰበውን ያህል እንዳይሰራ ግን የአመራርና የእቅድ ችግር አንቆት ጊዜውን መፍጀቱ ይፋ የሆነው ከቀርብ ጊዜ ወዲህ ቄሮ ስሙ ሲጎላ ነው።

ይህ አደረጃጀት ሁለት አበይት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ቄሮ ኦሮሚያና ቄሮ ቢሉሱማ ናቸው። ቄሮ ኦሮሚያ የሚመራው በጥቁር ኢንጪኒ ተወላጅ ሲሆን ቄሮ ቢሉሱማ ደግሞ በግንደበረት ወጣት ነው። ሁለቱም ከምዕራብ ሸዋ መሆናቸው ነው።

ቄሮ በከተማ ሆኖ ትግሉን እንዲያቀጣጥል፣ በህቡዕ እንዲሰራ ታስቦ ቢደራጅም የግንኙነት ሰንሰለትና የዕዝ እርከን በወጉ የተበጀለት ባለመሆኑ ስሙ እንኳን በወጉ ሳይታወቅ እድሜ ገፋ። በኢህአዴግ ውስጥ እያዘገመ የመጣው የኦህዴድ ጡንቻ በወጣቶች ከተሞላው ካቢኔና ከካቢኔው ስር ባሉ እስከ ቀበሌ ባሉ አደረጃጀቶች ህወሃትን ለመጣል ውስጥ ውስጡን ሲያድም አሰቀድሞ የሚያውቀውን የቄሮ አደረጃጀት መጠቀም እንዳለበት አመነ። በዚህም ሳቢያ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ያለ እንቅስቃሴ የኖረው የቄሮ አደረጃጀት ትንሳኤ አገኘ።

በዚህም እስከ ቀበሌ ተዘርግቶ ክልሉን የሚመራው የኦህዴድ እጅ ይህንን ሙት አደረጃጀት ነብስና ሃይል ሞልቶ እንዳሻው እንዲንቀሳቀስ በሩን በረገደለት። ቀድሞ ኮሽ ሲል ይጠፋ የነበረው ተቃውሞ እያደር ሲነድ ጉዳዩ በወጉ በመሪና በመረጃ አስተላላፊ ወይም ህዝብ ግንኙነት አማካይነት ሊመራ የሚገባው ደረጃ ደረሰ።ንቅናቄው በወጉ መመራት ግድና ግድ ሆነ።

የቄሮ እንቅስቃሴ ፈንድቶ ኦሮሚያን ወደ ማዳረስ እንደሚያመራ ሲታወቅ አንድ የዕዝ ማዕከል ወይም ሃብ አስፈለገ። ተቃውሞውን በተደራጀ መልኩ ለመምራትና ለማስተባበር፣ መረጃውን ለህዝብና ለዓለም ለማድረስ፣ የሚዲያ ቅስቀሳውን በወጉ ለማስኬድ ኦህዴድ አገር ቤት አገር እየመራ ሊያካሄደው ስለማይችል ጃዋር መሀመድ ለዚህ ስራ አገባብነት ያለው ሰው ሆኖ ተገኘ።

ኦህዴድን ጨምሮ በመዋጮ የሚያስተዳድሩት ኦኤም ኤን በጃዋር መሪነት አየሩን ሞላው። የኦሮሞ ትግል ነደደ። ቄሮ ብራንድ ሆነ። ይህን ጊዜ አቶ ዳውድ ከአስመራ በስካይፒ ብቅ ብለው ቄሮን ኦነግ ወይም እሳቸው እንዳደራጁት ተናገሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን ኦህዴድ ውስጥ ያለው የለውጥ ሃይል ለውጡን እየቆሰቆሰ ያጋግመው ነበር። በድርጅት እንደ ኢህአዴግ ሲሰባሰቡ ደግሞ “ ምን ይበጃል” እያለ ከህወሃት ጋር ሆዱ እየሳቀ ያምጥ ነበር።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ለመረጃ መዕከሉ የሚላከውን ማንኛውንም ጉዳይ እያደረጃ የሚያሰራጨውና ሚዲያውን የሚመራው ጃዋር ባገኘው አጋጣሚ ስሙን ተከለ። በኦሮሚያ “ ዛሬ ጃዋር ምን አለ” በሚል ከጸሃይ መውጣት ጋር ጃዋር አዲስ ጉዳይ አብሳሪ ሆኖ ቁጭ አለ።

ከማዕከል የሚካክለትን መረጃ እንዲያደራጅ፣ እንዲያራባና ለሚዲያ እንዲውል ተቀጣሪ ሆኖ ደሞዝ እየተከፈለው ሃላፊነት የወሰደው ጃዋር እያደር በዙሪያው ያሉትን እየገፈተረ ኦኤም ኤንን የግሉ አደረገው። ከዛም ሚዲያውን ሳይታክት በመጠቀም አብሪ ኮከብ ሆኖ ወጣ። ጃዋር ከሚዲያው ማበብ ጋር አብሮ ጎመራ። ጨውታውን በሜንጫ ጀምሮ “ ተጽዕኖ ፈጣሪ” ነኝ እስኪል ደረሰ።

ኦህዴድ አገር ቤት ሆኖ ትግሉን በኦፊሳል መምራቱን ማሳወቅ ስለማይችል፤ ያንን ቢያደርግ አደጋውም የከፋ ስለሚሆን ይህንን ለመከላከል ሲባል የተመለመለው ጃዋር ያንን እድል ተጠቅሞ በኦህዴድ የታችኛው መዋቅር ውስጥ ያለ አንዳች ችግር ዋኘበት። ኦህዴድ ዓይኑና ነብሱ ለውጡን ማጣደፍ ብቻ ላይ ስለተተከለ የጃዋርን ታችኛው መዋቅር ውስጥ መዝለቅ አደጋ እንደሚያስከትል ዘነጉት። ወይም በይደር እንደሚፈታ በማሰብ በይደር አስቀመጡት።

በዚህ ህወሃትን ባማስወገድ ላይ ትኩረት ተደርጎ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን መዋቅር የዘነጋው ኦህዴድ ለጃዋር ወርቃማ አጋታሚ ሆነ።አፍታም ሳይቆይ ጃዋር ኦሮሚያ ላይ እንደሚነግስ አምኖ አሳመነ። በዚሁ ስሌቱ አገር ቤት ከገባ በሁዋላ “ሁለት መንግስት አለ” በሚል በድፍረት በተደጋጋሚ አወጀ። ይህ ብቻ አይደለም “ ብፈልግ ጨርሱት እላለሁ፤ ስራዬን ያቀሉልኛል” ሲል አዲስ አበባ ከቦ መንግስት መቀየር እንደሚችል እስከመናገር ደረሰ። ይህንንም ሲል የሚታይበት መንፈስ ፍርኦንን ያስመስለው ነበር። ልቡ እጅግ ከመደንደኑ የተነሳ “ ከግራኝ መሃመድ ቀጥሎ ብቸና ተጽዕኖ ፈጣሪ ነኝ ” ሲል በይፋ የእብጠቱን ደረጃ አሳየ። አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ ከምስኪን ሃጂዎችና ሼካዎች ጋር ሰፊ ግንኙነት መስርቶ ኢትዮጵያ ላይ ይሰራባት ገባ።

ሐርርጌ ከመሰላ እስከ መልካ በሎ አርሲ ድንበር አባጃራ ሲንቀሳቀስባቸው የነበሩበትን ስፋራዎች የትውልዱ አካባቢ ጨምሮ የኢስላም ኦሮሞ ቅሬቶችን እየረዳ ዛሬ ከስፍራ ስፍራ የሚንቀሳቀሱ ነውጠኛ ሃይሎችን አፈራ። ኦህዴድ አኩራፊ፣ ሚናቸውን ያልለዩ፣ ተሃድሶውን ያልተቀበሉ፣ ሪፎርሙ ያስደነገጣቸውን በየመዋቅሩ ለማበጀት ደፋ ቀና ሲል ጃዋር በቀበሌና በወረዳ መዋቅር ውስጥ እንዳሻው እየተመላለሰ እንዳለው “ የቄሮ መርሃ መንግስት ” ሆኖ ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ። በሚፈለገው ደረጃም ባይሆን የክልሉን የጸጥታ ሃይል ሸርሽሮ ስለነበር የልቡ ድፍንነት ከድንጋይም ደደረ። እንዳሻው በሚነዳው ሚዲያ እየቀረበ መንግስትን በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲያበሻቅጥ፣ ሲሰድብና ሲያናንቅ በተቃራኒው አቶ ለማ መገርሳን ሲያሞካሽ ስሜቱ ከሰማይ ሰማያት የተቀባ እስኪመስለው ትቢቱ ሲፈላበት ይታይበት ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን የነካው፣ ተው ያለው ባይጠፋም አቶ ታዬ ደንደአ ብቻ ነበሩ ብዕር የሰበቁት።

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

ጃዋር በዚህ አላበቃም። ቀስ እያለ “ የሸዋን ድምጽ ለመያዝ ስል ኦፌኮን መረጥኩ” ሲል ተናገረ። በሕዝብ ግፊት ወደ ፖለቲካ ፓርቲ አባልነት መግባቱን በተናገረ ማግስት ኦፌኮ እድገቱን በኦሮሞ ደረጃ መዳቢነት እንዲገፋበት አስቻለው። ኦፌኮ ያለልማዱ “ በዲቃላ” ፖለቲካ አክሊል ብቅ ብሎ “ ኦሮሞ ካልሆነ አታግባ፣ ኦሮርሞ ባልሽን ፍቺ ” በሚል ሰርከስ መስል የመድረክ ትዕይንት ላይ አመራሮቹ ሲዝናኑ ላይቭ የማሳየት ወጉ ሆነ።

ጃዋርን አሜሪካ ሜኖሶታ ካገኙ በሁዋላ ድንገት ጽንፈኛ የሆኑት ትልቁ ወገናችን አቶ በቀለ ገርባ “ ቋንቋህን ከማይናገር አትሸምት፣ አትግዛ ” በሚል የዘር ሰረገላ ላይ ተሳፍረው መጋለብ ጀመሩ። በዚህም ንግግራቸው በእስር እያሉ ዋጋ የከፈለላቸውን ህዝብ አስከፉ። ደሙን ረገጡና አሳዘኑት። በኦሮሚያ ከሌሎች የተዋለዱትን አብላጫዎች አንገት አስደፉ። በገዛ እጃቸው የክብር ካባቸውን ገፈው ጣሉና እርቃናቸውን ሆኑ። ይህ ስሜታቸው በጃዋር መሰሪ ስብከት ተኮትኩቶ አስከሬን የሚቀማ ስብእና ባለቤት እንዲሆኑ አስቻላቸው።

እጅግ ታላቅ ክብርና ፍቅር የነበራቸው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናም በጃዋር ሚዲያና ድጎማ ታውረው አቅላቸውን ጣሉ። አገር ያረጋጋሉ ተብሎ የሚታመንባቸው መረራ ካጃዋር ጋር ጋብቻ መስርተው ለዘመናት የገነቡትን ስም ናዱት። በጩኸት ሲከበቡ አቅላቸውን ሳቱ። አቅል መሳት ብቻ ሳይሆን ሞገስ አልባ ሆነው አብዛኛውን የኦሮሞ ቅልቅል ትውልድ ከሰሩ። ዛሬ ስለ እርቅና ስለ መነጋገር ሲናገሩ የሚሰማቸው ያጡ ያረጡ ፖለቲከኛ ሆኑ። ጃዋር አቶ ለማ መገርሳን ይዞ ኦህዴድን ለማፍረስ በሚስጢር በደገሰው ድግስ አንድ ታላቅ የኦሮሞ ፓርቲ መስርተው ከህወሃት ጋር ማሪንጌ ቻቻ ለመጨፈር መስማማታቸው በአድፋጩና አብዛኛው የኦሮሞ ወገኖች ጆሮ ደረሰና “ አይ መረራ” ተብለው “ ሲያልቅ አያምር” ተዜመላቸው።

ዛሬ ሃጫሉ ማን ሊገለው እንደሚችል ይፋ ባደረገ ቀናት ውስጥ በቅጥረ ነበሰ ገዳዮች ሲበላ እነ መረራ ልባቸውና ሞራላቸው ጃዋር በጫነባቸው የትዕቢት አክሊል በመታወራቸው አልተቆጩም። ገዳዮችሁን እያወቁ አልተነፈሱም። ሃጫሉ አስከሬኑ ክብር አጥቶ ለቁማር ሲውል መራራ የሚሰማ ጆሮ፣ የሚያስብ ህሊና አጡ። በቴሌ ቋንቋ “ጥሪ አይቀበልምን” አስተጋቡ። የአስከሬን ሌቦችን ዛሬ ድረስ ይናፍቃሉ እንጂ ሞራላቸውን ሰብስበው ወደ ልባቸው ስለመመለስ አያስቡም።

ይህንን ያነሳሁት ከላይ የገለጽኩት ቄሮ በዚህ መልኩ እንዴት ከነሱ ጋር ያብራል? የሚለውን ጥያቄ ለማሳየት ነው። በምዕራብ ሸዋ ልጆች የሚመራው ቄሮ ሰሞኑንን የሚተላለፉትን የግደለው፣ እረደው፣ አጥፋው፣ አባረው፣ ሚስማር በትን ወዘተ የክተት ጥሪ የማይተገብርበትን ምክንያት ለማሳየት ነው።

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

አብዛኞች ከቄሮ አፈጣጠር ጀምሮ የተዛባ አመለካከት ስላላቸው እንጂ ዛሬ በየጉድባው እየመሸገ ሽብር የሚፈጥረው ሃይል ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር፣ በጀት ያለው፣ መነሻው ከላይ በገለጽኩት የምስራቅ ሃረርጌና አርሲ መዳረሻ የሆነ የጽንፈኞች አደረጃጀት እንጂ ጥቁር እንኚኒ የተለኮሰው የቄሮ አካል አይድለም።

አብዛኞች የጥቃት ሰለባ የሆኑ እንደመሰከሩት ጥቃት አድራሾቹ የአካባቢው ተወላጆች አይደሉም። በአይሱዙ ከቦታ ቦታ የሚደፉና የሚዘረገፉ የጥፋት ሃይል እሳት እራቶች ናቸው። አንድ ምሳሌ ላንሳና ልቋጭ

ሰሞኑንን ገላን አካባቢ ነውጠኞቹ ጥቃት ለማድረስና የፈለጉትን ጥፋት ለመፈጸም ሲነሱ ሕዝብ ሆ ብሎ ተነሳ። ሁሉም በቤቱ ያለውን መመከቻ አንስቶ ዘመተባቸው። እነሱም እየሸሹ ወደ አንድ ኮንዲሚኒየም ህንጻ አመሩና እየተግተለተሉ ገቡ። ህዝብ ከበበ። ፖሊስ መጣ። አብዛኞቹ ተያዙ። ለካስ ቤት ተከራይተውላቸው የሚያኖሯቸው ናቸው። የአካባቢው ነዋሪ አይደሉም። ከቦ እጅ ያሰታቸው ቂሮና ሌላው ህብረተሰብ እዛው አካባቢ አብሮ የሚኖር ነው።

በዚህ መነሻና በአርሲ፣ በሻሸመኔ በአዳባና በሌሎች አካባቢዎች ግፍ የተፈጸመባቸው እንደመሰከሩት የአካባቢው ነዋሪ ወይም ቀበልተኛ ያልሆኑ ጽንፈኞች ይህንን አሳፋሪ ተጋባር በኦሮሞ ስም እየፈጸሙት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ይሆናል። ይህ ባይሆን ኖሮ አደጋውና ጥፋቱ በተመሳሳይ ሰዓትና ጊዜ ድፍን ኦሮሚያን አዳርሶ ባየነው ነበር። እዚህ ላይ አደጋው ከተከሰተም በሁዋላ የጸትታ ሃይሉ የውሰደውን አጣዳፊ እርምጃ ባለመዘንጋት ነው። እናም ጽንፈኞችን ከሰላማዊው ኦሮሞ ለይቶ፣ ያደራጃቸውን አካል በመረዳት በትክክለኛ ስማቸው መጥራት ግድ ነው።

ጽንፈኞች ዛሬም ነገም ኩሩውን የኦሮሞ ህዝብ አይወክሉም። ሊወክሉ አይችሉም። በመሆኑም ጽንፈኞችን በስማቸው መጥራትና ባደራጃቸው መሪያቸው ስም መለየት እንጂ ከታላቁ የኦሮሞ ህዝብ ጋር ማዛመድ ለከሸፉ እፉኚቶች ፕሮፓጋንዳ መመቸት እንጂ ሌላ ውጤት አያስገኝም።

ቄሮ አመራሮቹ ሁለቱ  የሸዋ ልጆች እንዲህ ባለው ጽንፈኛ ተግባር የመሰማራት ዓላማም እምነቱም የላቸውም። እርግጥ ቄሮ ቢሊሱማን እንረዳለን የሚለው የውጪው አገር የሸኔ ድጋፍ ሰጪ ይህንን ሃይል ወደ ጥፋት ለማሰማራት ይጥራል። በሰላማዊ ትግል ስም አዲስ አበባ ቢሮ በተከሉ አክቲቪስትና ፖለቲከኞች ስም ብር ይልካል። ግን የታሰበውን ያህል ውጤት አላመጣም። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይኸው ጉዳይ ነው ዛሬ ኦነግን የናጠው።

በተመሳሳይ ሌሎችም ጽንፈኞች አሉ። በስመ ኢትዮጵያ ጽንፍ ይዘው ከዜጋ በላይ ዜጋ ለመሆን የሚቃጣቸው ክፍሎችም በተመሳሳይ ሊፈረጁ ይገባል። ጽንፈኛነት የኪሳራ ሁሉ ኪሳራ ነውና። ቄሮ፣ ወጣት ማለት በመሆኑ ሽብርን፣ ጽንፍንና ማውደምን ከዚህ ስም ጋር በደምሳሳው ማጎዳኘት የተጀመረውንም የህግ ማስከበር ዓላማ ያንገራግጨዋል እንጂ አያጠናክረውም።

ዝግጅት ክፍሉ – ይህ ጽሁፍ ከመቂ የተላከ ሲሆን አንዳንድ የማስተካከያ እርምቶች ከማድረግችን ውጪ ሃሳቡን አላዛባንም። በጽሁፉ የተጠርቀሰው ሃሳብ የጸሃፊው እምነት ብቻ ነው። ምላሽ ለመላክ የምትፈልጉ ብትልኩልን እናትማለን

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *