በልጆችዋ የማትተማመንና በአዲስ ትውልድ የማትመራ ትግራይ ልትቀየር፣ ልትለወጥ፣ ልትለማ ካሉባት ችግሮችዋ ልትወጣ እንደማትችል ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ሰው በሆነ ግዜ ሃሳብ ሊኖረው ይችላል ነገር ግን ያቺ አቅም ሁሌ ቁጭ ብላ አትጠብቅም፤ አዲስ ትውልድ ሲመጣ በአዲሱ ትውልድ እምነት ከሌለ፣ እየታገዘ ካልበቃ በቀጣይነት ልማት ማምጣት እንደማይቻል አመልክተዋል ።

የትግራይ ህዝብ በልጆቹና በልጅ ልጆቹ እምነት ሊኖረው እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ። የትግራይን ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ ከሃምሳ እና ስድሳ ዓመት በፊት በነበረ ሃሳብ መምራት እንደማይቻልም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፤የትግራይ ህዝብ በልጆቹና በልጅ ልጆቹ እምነት ሊኖረው እንደሚገባና ህዝቡ ለወቅቱ የሚመጥኑ የተማሩ ወጣት ልጆች እንዳሉት አስታውቀዋል ።

የራስን ህዝብ በመደብ ከፋፍለህ ግማሹ የኔ ነው፤ ግማሹ ተከፋይ ነው ፣ሌላው ባንዳ ነው እያልክ መምራት የሚቻል አይመስለኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይሄ ከፋፋይ ሃሳብ ትላንት ሰርቶ ሊሆን ይችላል ዛሬ ግን ይሰራል ብዬ አላስብም ብለዋል።

በልጆችዋ የማትተማመንና በአዲስ ትውልድ የማትመራ ትግራይ ልትቀየር፣ ልትለወጥ፣ ልትለማ ካሉባት ችግሮችዋ ልትወጣ እንደማትችል ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ሰው በሆነ ግዜ ሃሳብ ሊኖረው ይችላል ነገር ግን ያቺ አቅም ሁሌ ቁጭ ብላ አትጠብቅም፤ አዲስ ትውልድ ሲመጣ በአዲሱ ትውልድ እምነት ከሌለ፣ እየታገዘ ካልበቃ በቀጣይነት ልማት ማምጣት እንደማይቻል አመልክተዋል ።

የትናንቱን ትግል የመሩ አባቶችም በትላንት ችሎታቸው እና ማንነታቸው የዛሬ ፍላጎት መመለስ እንደማይቻል አውቀው፤ ትላንት የራሳቸውን ታሪክ እንደሰሩ ሁሉ፣ የዛሬ ትውልድ ወጣቱም የራሱን ታሪክ መስራት እንደሚፈልግ ተረድተው፣ ልጆቻቸው እና ልጅ ልጆቻቸው ከነሱ በተሻለ የተማሩና አቅም የፈጠሩ መሆናቸውን አምነው አዲሱን ምዕራፍ ለአዲሱ ትውልድ ሊሰጡት እንደሚገባ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ምሰረታ ጀምሮ ወሳኝ ቦታ የነበረው ትልቅ ህዝብ ነው፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ንቁ ተሳትፎ ያላደረገበት ግዜ የለም፤ ለወደፊትም አይኖርም የሚል እምነት አለኝ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ በለውጥ ግዜ ችግር መፈጠሩ የለውጥ ባህሪ ነው። እናት ምጥ ችላ ልጅ እንደምትወልደው ሁሉ እዚህም ትንሽ መታገስ ጥሩ ነው። በቅርቡ ችግሮቹ ሁሉ ቀስ በቀስ ይፈታሉ ብዬ አምናለሁ ብለዋል።

“በህወሓት እና በብልፅግና ልዩነት እንዳለ ግልጽ ነው፤ ሁሉም ሰውም የሚያውቀው የአደባባይ ሃቅ ነው። በፌዴራል እና በክልል ያለው እሰጥ አገባ በትግራይ ተጨማሪ ችግር መፍጠሩ ግልጽ ነው፣ ምክንያቱም አብሮ ተነጋግሮ የማይሰራ ከሆነ ችግሮች እንደሚፈጠሩ ግልጽ ነው” ብለዋል።

እንደብልጽግና ተፈጥረው ያሉ የሃሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ፍላጎት አለን። በህወሓትም በኩል ነገሮች በውይይት እንዲፈታ የሚፈልጉ አመራሮች እንዳሉ እናውቃለን፤ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፣ጥቂቶች ከህወሓት ጋር ያሉ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ችግሩን መፍታት የሚፈልጉም ክፍተቱን ለማስፋት የሚሰሩ እንዳሉ ለሁሉም ግልጽ እንደሆነ አመልክተዋል።

የትግራይ ህዝብ ወደ ጦርነት እንዲገባ እየገፋፉ ያሉ ሰዎች ተው ሊባሉና ሊመከሩ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ይህን ለማድረግ የትግራይ ህዝብ የአቅም ችግር እንደሌለው አውቃለሁ፤ ሰላም የሚፈልጉት መሪዎችን መደገፍ አለበት ፤ ህዝቡ ይህን ካደረገ አብዛኛው ችግር ይፈታል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል ። በህወሓት እና በብልጽግና መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በማስፋት እና በዚህ ክፍተት የሚኖሩ ሃይሎችም እንዳሉ ጠቁመዋል ።

ትግራይን ለመጉዳት የሚባል ሃሳብ በኔ በኩል በፍጹም የለም። በመንግሥት ውስጥ እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ካለ ችግር ውስጥ ነው ያለው ማለት ነው፤ ሊታገዝ፣ ሊገመገም ራሱም ባህሪውም በአግባቡ ሊታይ ይገባዋል ብዬ አምናለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፤ ከዚህ ውጪ ያለውን የፖለቲካ ጫወታ ህዝብን ጨምሮ ማየት ልክ እንዳልሆነም አመልክተዋል።

የምርጫ አስፈላጊነት እና ግዴታ መደረግ እንዳለበት ልዩነት ያለን አይመስለኝም። ምርጫ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘን እየተዘጋጀን እያለ ድንገት ሳናስበው ኮቪድ 19 በሽታ መጣ፤ የፌዴሬሽን ምክርቤት ሁሉም ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እንዲቀጥሉ ወስኗል። ይሄ ለብልጽግና ይሰራል፣ ለህወሓትም ይሰራል ብለዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ምርጫ የማይቀር ነገር ሁኖ እያለ የትግራይ ክልል መንግሥት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር በጀት መደቦ ምርጫ አደርጋለሁ ማለቱ የሚገርም ነው። በሌላ በኩል ኮቪድ 19 እያለ ምርጫ እናደርጋለን ማለት ኮቪድ19 ለትግራይ ስጋት አይደለም ማለት ነው፣ ትግራይ ላይ ሰው በኮረና አይያዝም ማለት ነው? ዘመናዊ ሆስፒታል መድሃኒት አለን ማለት ነው? ሎጂኩን ለመረዳት ከባድ ነው። እንደዚህ አይነት ጥያቄ እንድታነሳ ያደርግሃል፤ ኮረና አይደለም ለኢትዮጵያ ይቅርና አሜሪካንን እንዴት እያደረጋት እንዳለ እያየን በትግራይ ላይ ችግር አይፈጥርም ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።

‹‹የትግራይ መንግሥት ሚሊዮኖች አውጥቶ ምርጫ አደርጋለሁ ከሚል ትግራይ ላይ የውሃ ችግር እንዳለ ይታወቃል ፣ ሁለት ሦስት የውሃ ጉድጓድ ለምን አያስቆፍርም ? ለምን አንድ ሆስፒታል አያሰራም? ብለህ እንድትጠይቅ ያስገድዳል። ለልማት በጀት አጠረን፣ ፌዴራል መንግሥት በጀት ከለከለን እያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር አውጥቶ ምርጫ ማካሄድ አለብን ማለቱ ይገርመኛል›› ብለዋል።

“ህወሓት ምርጫ ይደረግ የሚለው ሌላ አማራጭ ላላቸው ሰዎች ማስረከብ ፈልጎ ነው እንዳይባል የተለየ ሃሳብ የያዙ ሰዎች ታፍነው ነው ያሉት፣ ራሱ ተመልሶ ለመምጣት ከሆነ ደሞ የፌዴሬሽን ምክርቤት እኮ ምርጫ እስኪደረግ ስልጣን ላይ እንዲቆይ ፈቅዶለታል፣ ትንሽ ግዜ ታግሶ ባገር ደረጃ ምርጫ ማድረግ ሲገባ በጀቱን ደግሞ ለውሃ ማስቆፈሪያ፣ ለሆስፒታል ማሰሪያ ቢጠቀሙበት ይሻል ነበር ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት በክልል ጉዳይ ላይ እጁን አስገብቶ አያውቅም ለወደፊቱም አያስገባም። ያሄን ስል ግን የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱን አሳልፎ አይሰጥም ። በህገ መንግስቱ የተሰጠን የስልጣን ክፍፍል መኖሩ ሊረሳ አይገባም ፤ የትግራይ መጠቀም ለኢትዮጵያ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፤ ለይቶ ትግራይን ማጥቃት የሚባል ሃሳብ የፌዴራል መንግሥትም የብልጽግና ፓርቲም እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮ ኤርትራ ያለው ግንኙነት በሁለት ሃገራት ያለ ግንኙነት ስለሆነ ይሄ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ስራ እና ሃላፊነት ነው። አሁን ተገኝቶ ያለው ሰላም ለትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም የሚጠቅመው ለሁላችንም ነው የሚጠቅመው። የተጀመረውን ግንኙነት አጠናክረን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታችንንም ለማጠናከር እየሰራን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ‹‹ማን ለማን ነው የሚዋጋው? ለምንድነው የፌዴራል መንግሥት ትግራይ ክልልን የሚወጋው? ይሄ የእብደት ንግግር ነው። ከተናጋሪው የደገመው ይብሳል፤ የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ህዝብን ሊወጋ ነው ብሎ ማሰብ ምን አይነት ሃሳብ እንደሆነ አይገባኝም። አይደለም ከህዝባችን ጋር ከጎረቤት አገሮች ጋር ውግያ አንፈልግም እያልን እኮ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።

ጦርነት የሚፈልጉ ሰዎች ጦርነት ጦርነት ይላሉ፤ እንደ ዘፈን ጠዋትና ማታ የጦርነት ንግግር ሲናገሩ ትሰማለህ እና ራሳቸው የሚያስቡትን ነው እየነገሩን ያሉት። በዚህ ዘመን ጦርነት የሚያስነሳ ምክንያት አለ ብዬ አላምንም። በሁሉም በኩል አንዳንድ ወጣ ያሉ የፖለቲካ ጫዋታዎች ሊታዩ ይችላሉ ነገር ግን ወደ ውጊያ ሊያስኬድ የሚችል አይደለም፣ አይገባምም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን መንግሥት ኢትዮጵያን ውጋ ብሎ ይጠራል ብሎ ማሰብ ሃጢያት ነው። እንዴት ብሎ ነው ህዝብን ውጋልኝ ብሎ የሚጠራው ? ይሄ በታሪካችን እንዳልታየ፤ ለወደፊትም እንደማይኖር አስታውቀዋል ። የኤርትራ መንግሥት በዚህ ግዜ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን ችግር ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት አመራሮች ውስጥ እንደነ ዶ/ር ደብረጽዮን ያሉ ሰዎች ልማት እና ሰላም ስለሚፈልጉ ሊደግፋቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። እነ ዶ/ር ደብረጽዮን ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ችግር በውይይት ለመፍታት ዝግጁ ነበሩ ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ በተለይ ዶ/ር ደብረጽዮንን ሊያግዙት ይገባል ፣በዚህም አብዛኞቹ ችግሮች ይፈታሉ ብዬ አስባለሁ፤ በሌላ ጎን ደሞ ሰላም ለማይፈልጉ ሰዎች ተው የጥፋት መንገድ ነው ሊላቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 22, 2012

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *