መካ-የኢድ አል አድሐ በዓል፣ሐጅና ኮሮና
የኢድ አል አድሐ በዓል የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመቀነስ ከሚደረግ ጥንቃቄ ጋር ዛሬ በመላዉ ዓለም እየተከበረ ነዉ።ባለፈዉ ሮብ የተጀመረዉ የሐጅ ፀሎትም ዛሬ ይጠናቀቃል።በኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት ምክንያት ዘንድሮ ሐጅ ያደረጉት ምዕመናን ቁጥር እጅግ አሽቆልቁሎ፣ ሥርዓቱን ያደረጉት በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ብቻ ናቸዉ።ዓምና ከመላዉ ዓለም ሐጅ ያደረገዉ ምዕመን ከ2.5 ሚሊዮን ይበልጥ ነበር።ዘንድሮ ሐጅ ካደረጉት አብዛኞቹ የሳዑዲ አረቢያ እና እዚያዉ ሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ የዉጪ ዜጎች ናቸዉ።ምዕመናኑ ሲፀልዩም ሆነ ሲንቀሳቀሱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጥልቀዉ፣ አካላዊ ርቀትን ጠብቀዉ፣ወደየ መሳጂዶቹና መካ፣ መዲናና ሚናን ወደመሳሰሉ አካባቢዎች ሲገቡ ትኩሳታቸዉ እየተለካ ነዉ።የሳዑዲ አረቢያ የጤና ሚንስቴር ዛሬ ጠዋት እንዳስታወቀዉ ሐጂ ከሚያደርጉ ምዕመናን እስከ ዛሬ ድረስ በተሕዋሲዉ የተያዘ ሰዉ የለም።
መቀሌ-የትግራይ ምርጫ ዝግጅት
የትግራይ ክልላዊ መስተዳድር በቅርቡ ሊያካሒድ ባቀደዉ ክልላዊ ምርጫ ለመወዳደር 5 የፖለቲካ ድርጅቶችና 11 የግል እጩዎች መመዝገባቸውን የክልሉ ምርጫ ኮምሽን አስታወቀ፡፡ ምርጫ የሚደረግበትን ዕለትም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ኮምሽኑ ገልፆል፡፡የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመሠረተዉ የምርጫ ኮምሽን ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ሲያካሂደው የነበረዉን የተወዳዳሪ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ምዝገባን ትናንት ማምሻ አጠናቅቋል፡፡
ኮሚሽኑ እንዳስታወቀዉ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዢዉ ፓርቲ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ (ባይቶና)፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እና ዓሲንባ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ በምርጫዉ ለመወዳደር ተመዝግበዋል።የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለስላሴ ኮሚሽኑን ጠቅሶ እንደዘገበዉ ከፓርቲዎቹ በተጨማሪ «መስፈርት ያሟሉ» 11 የግል እጩዎች በምርጫው ለመወዳደር መመዝገባቸውን አስታዉቋል።
አረና ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት (አረና) እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ግን በምርጫዉ እንደማይሳተፉ አስታዉቀዋል።በተለይ አረና የምርጫዉን ዝግጅትና ሒደት ሕገ መንግሥትን የጣሰ፤ ነፃ ያልሆነና የሕወሓትን ስልጣን ለማራዘም ያለመ በማለት አዉግዝቶታል።
ሕወሓት መራሹ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ምርጫ እንዲደረግ የወሰነዉ የኢትዮጵያ የፌደሬሽን ምክር ቤት የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭ ሥጋትን ምክንያት በማድረግ በመላዉ ኢትዮጵያ ለመጪዉ ነሐሴ ሊደረግ ታቅዶ የነበረዉ ምርጫ እንዲሰረዝ ያሳለፈዉን ዉሳኔ በፃረር ነዉ።
ትራምፕ ምርጫ ይራዘምን በማድበስበስ አስተባበሉ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሕዳር 2020 የሚጠበቀዉ ምርጫ ይራዘም ብለዉ መጠየቃቸዉን አላልኩም አይነት መልስ በመስጠት አድበሰበሱ። ትራምፕ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋትን ተከትሎ በዩናይትድ ስቴትስ ምርጫው ቢራዘም ዜጎች ደህንነታቸው ጠብቀዉ ፣ ምርጫዉን ማካሄድ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዉ ነበር። ፕሬዚዳንቱ ቀደም ብለዉ ምርጫ ይራዘም ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄያቸዉን ፤ የምርጫ ቀጠሮ ቀን እንዲቀየር አልፈለኩም ሲሉ በማድበስበስ አስተባብለዋል።
እንድያም ሆኖ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው በፖስታ ቤት አገልግሎት የሚካሄድ ከሆነ ከፍተኛ መጭበርበር ይከሰታል ሲሉ አሁንም ግምታቸዉን ተናግረዋል። ቀደም ሲል ፕሬዚዳንቱ ባቀረቡት ጥያቄ በአሜሪካ ፌዴራል መንግስት ምክር ቤት በራሳቸዉ የሬፑብሊካን ፓርቲ እና በተቃዋሚዉ ዴሞክራቶች ፓርቲ አባላት ከፍተኛ ተቃዉሞ ገጥሞአቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ አንድ ፕሬዚዳንት ምርጫን የማራዘም ሙሉ መብት የለዉም። በዩናይትድ ስቴትስ ምርጫን ማራዘም የሚቻለዉ የአሜሪካ ኮንግረስ ማለት ሴኔቱ እና የተወካዮች ምክር ቤት ስምምነት ላይ ሲደርሱ ብቻ ነዉ።
ቴሕራን-«ኢራን ከአሜሪካ ጋር አትደራደርም» ኻሜኔይ
ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር እንደማትደራደር የኢራኑ ላዕላይ መሪ ዓሊ ኻሜኔይ አስታወቁ።የፕሬዝደንት ትራምፕ መስተዳድር ከኢራን ጋር «ያለምንም ቅድመ ሁኔታ» መደራደር እንደሚፈልግ፣ ነገር ግን እስላማዊቱ ሪፐብሊክ ላይ የሚያደርገዉን ግፊት እንደሚቀጥል በቅርቡ አስታዉቆ ነበር።አያቶላሕ ዓሊ ኻሜኔይ የኢድ አል አድሐ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ግን የትራምፕ መስተዳድር «እንደራደር» የሚለዉ ድርድሩን ለፕሮፓጋንዳ ሊጠቀምበት ነዉ።ኻሜኔይ እንደሚሉት ሐገራቸዉ እንደ ሰሜን ኮሪያ መታለል አትፈልግም።ኢራን የኑኩሌር መርሐ ግብሯን ለማቆም ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ከአምስቱ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባላት እና ከጀርመን ጋር ያደረገችዉን ስምምነት ፕሬዝደንት ትራምፕ አፍርሰዉታል። ትራምፕ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ2015 የተፈረመዉንና የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ያፀደቀዉን ስምምነት በተናጥል ካፈረሱ ወዲሕ የዋሽግተንና የቴሕራን ጠብ በጦር ኃይል ወደ መጓሸም ንሯል።
ቻይና እና የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ የሚገነባውን የአፍሪካ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዋና መሥሪያ ቤት የመጀመሪያ ምዕራፍ ለመጀመር ሥምምነት ተፈራረሙ።
ሥምምነቱን የፈረሙት የቻይና የንግድ ምክትል ምኒስትር ኪያን ኬሚንግ እና የአፍሪካ ኅብረት ማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር አሚራ ኤልፋዲል ናቸው።
መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዋና መሥሪያ ቤት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 23 ሺሕ 244 ስኩዌር ሜትር ይሸፍናል። ዋና መሥሪያ ቤቱ ሁለት የቢሮ ሕንፃዎች፣ ሁለት የቤተ ሙከራ ሕንፃዎች፣ የድንገተኛ ማዕከል፣ የመረጃ ማዕከል እና ላብራቶሪ ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 90,000 ስኩዌር ሜትር ቦታ ለዋና መሥሪያ ቤት ግንባታው አቅርቧል። የኅብረቱ መረጃ እንደሚጠቁመው የሕንፃ ግንባታው 40,000 ስኩዌር ሜትር ላይ ይከናወናል።
ግንባታውን ለማስጀመር ስምምነቱ ሲፈረም የአፍሪካ ኅብረት የማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር አሚራ ኤልፋዲል የአፍሪካ ኅብረት ፕሮጀክቱን በፍጥነት ለማስጨረስ ከቻይና ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   እኛ የምንመርጠው አባትና አያቶቻችን የመረጡትን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *