ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

” አርበኛው ጳጳስ “

ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
በ1885ዓ/ም ፍቼ ከተማ ፣ የተዎለዱት አቶ ኃይለማሪያም በ1900 ከመነኮሱ በዃላ በ1921 ዓ/ም በእስክንድርያ ቅዱስ ማርቆስ ከአራት ጳጳሳት ጋር ጳጳስ ሲሆኑ ስሜቸው ጴጥሮስ ተባለ በማለት ሰኔ 30 ቀን 1938 ዓ/ም የወጣው ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ማንነት አብራርቶ አትቶት ይገኛል ::
አቡኑ የጵጵስናውን ሹመት ካገኙ በዃላ መዝና ፣ ግሸን፣ ወረይሉና ጅማ፣ ቦረና ፣ ደራ ፣ ይፍራታ ፣ አንፅኩያ ፣ ግድም ሳይንት ፣ አምባሰል ፣ ወረሂመኖ ወረባቦ ፣ወረባቾ ፣ ተኩላ ፣ ድሬ ፣ ጨረቻ ፣ ለጋቦ ፣ ለገጉራ ለገሀዲ ፣ ሲሆኑ የወር ደመወዛቸውም አምስት መቶ ብር እየተከፈለ መንፈቁን ወረኢሉ ፣መንፈቁን ደሴ በመቀመጥ ሀገርና ወገናቸውን በቅድስት ቤተክርስቲያን በትጋት አገልግለዋል ::
ነገር ግን በ1928 ዓ/ም ሐምሌ 22 ቀን አድስ አበባ ከተማ ውስጥ በፋሽሽት ኢጣሊያኖች ትዕዛዝ የሞት ተፈርዶባቸው በጥይት ተደብድበው ተገደሉ ::
ለዚህ ሞት ያበቃቸውም የኢጣሊያ ፋሽሽት ጦር በኢትዮጵያ ላይ በተነሳ ግዜ በሰሜን ጦር ግንባር ከሰራዊቱ ጋር አብረው ከዘመቱ በዃላ ፣ ሰራዊቱ ድል ሆኖ ሲመለስ ፣ አቡኑ ማያዚያ 24 ቀን ደብረ ሊባኖስ ገቡ ::
ከዚያም የስላሴ አርበኞችን በስብከት ሲያነቃንቁ ስለተደረሰባቸው በወቅቱ የነበሩት የኢጣሊያ ባለስልጣኖች በኢጣሊያ ላይ የሚነዙትን አጉል ስብከት አቁመው ወደ ኢጣሊያ መንግስት እንዲገቡ በደብዳቤና በቃል ቢነገራቸው ፍቃደኛ ሁነው ካለመገኜታቸውም በላይ ለሀገርና ለወገን ያላቸውን ጥልቅ የፍቅር፣ውሜት እንዲህ በማለት ገልፀውታል
” ከአገሬና ከህዝቤ የሚበልጥ ነፍስ የለኝም ::
” በእንግሊዝ ለጋስዮን የነበረው ፖትሪስ ሮበርትስ ለእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀምሌ 30 ቀን ባስተላለፈው ሪፖርት የኢትዮጵያውያን ኃይል በምእራብ በኩል አጠቃ ኢትዮጵያውያንም የሚያስገርም ከባድ
ውጊያ አደረጉ :: ወደ አዲስ አበባ ከተማም እየተጠጉ ሲሔዱ ጥቅጥቅ ካለው ደን ውስጥ በመግባታቸው የኢጣሊያን ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት ስለደረሰባቸው ሁለት ቀን ሙሉም በጀግንነት ተዋግተው ኢትዮጵያዊያን ይዘውት የነበረውን ቦታ ትተው ሲመለሱ ጳጳሱ አቡነ ጴጥሮስ ተማረኩ ::
በውቅቱም ፖጃሊ የተባለው የዚያኑ ዘመን የኮርዮር ዴላ ሴራ ጋዜጠኛ ” ድአርዮ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መፃህፍ ሀምሌ 30 ቀን እ.ኤአ ጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝቡ በተሰበሰበበት አደባባይ እንዲገደሉ ፈረደ ::
ይህ ሲሰማ በከተማው ሕዝብ፣ ዘንድ ሽብር ፈጠረ ጉዳዩም በጋዜጣ እንዳይወጣ ፋሽሽቶች ታላቅ ቁጥጥር አደረጉ ::
ለኛም ትዕዛዝ ተሰጠን :: ማንኛውም ጋዜጠኛ አቡኑ ተገደሉ ብሎ ወደ ኢጣሊያ አገር ቴሌግራም እንዳያረግ ተከለከልን ::
አቡኑ ታሰሩ ብላችሁ ግን ዜናውን ማስተላለፍ ትችላላችሁ ተባልን ::
” አቡኑ ሲገደሉ በዚያው በቦታው ነበርኩ ::
” ጴጥሮስ ረጅም ብሩህ ገፅታ ያላቸው ናቸው ::
ጥቁር ካፖ ለብሰዋል በጉዞና በእስራት ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል ::
የሞት ፍርድ በተፈረደባቸው ጊዜ በፀጥታ አዳመጡ ::
አቡኑም በአስተርጏሚ የመከላከያ ሀሳባቸውን አቀረቡ ::
የሞት ፍርዱም እንደፀደቀባቸው በተነገራቸው ጊዜ ጴጥሮስ ስአታቸውን አውጥተው ተመለከቱ ወዲያውም አጠገባቸው ያለውን ኢጣሊያውይ ለመቀመጥ እንዲፈቅድላቸው ጠየቁት ::
ቀና ብለው ሰገነት ላይ ወደ ተቀሙጥነው ጋዜጠኞችና መኳንንቶች አይተው የመቀመጥ ጥያቂያቸውን ትተው ቀጥ ብለው በመቆም፣ለገዳዮቻቻው፣ተመቻቹላቸው ::
ጴጥሮስ ከሚገደሉበት ቦታ ሲደርሱ አራቱንም ምአዘን በመስቀላቸው ባረኩ ከህዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ በማለት በድፍረት ተናገሩ
” ፋሽሽቶች የአገራችን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸውም እውነት አይምሰላችሁ ሽፍታ ማለት ያለ ሐገሩ መጥቶ የሰውን አገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔ የኢጣሊያ ፋሽሽት ነው ::
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሱ እንዳይገዛ ውግዝ ነው :: የኢትዮጵያም መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን በማለት ተናገሩ ::
ይህን መሰሉ አርበኛው ጳጳስ ከዚህ ግዝት በዃላ ምንም ቃል አልተናገሩም :: ግፈኛ የፋሽሽት ወታደሮች እሳት በሚተፋ መትረየስ አርበኛውን ጳጳስ ደብድበው አራዳ ጌዎርጊስ ሀውልታቸው ከቆመበት ትንሽ ዝቅ አድርገው ገደሏቸው :: የሞቱበትም ቦታ እስካሁን ድረስ ምልክት ተቀምጦበት ይታያል ::
ይህ ግፍ የተፈፀመው የዛሬ 84 አመት ሐምሌ 22 ቀን ነበር ::
ሰማዕቱን ጳጳስ የተለያዩ አገር ደራሲዎችና ጋዜጠኞች ስለ ጀግንነታቸው
ብዙ ብዙ ብለዋል እኔም ለዛሬው ከታሪክ ማህደር ያገኘሁት አካፈልኳችሁ በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን ::
አለባቸው ደሳለኝ አበሻ ( ለንደን )
ሸር በማድረገውት ደስ ብሎኛል
Alebachew Desalegn
ኢትዮጵያዊነት ከዘር በላይ ነው!!!

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0
Read previous post:
ኢትዮ ቴሌኮም 318 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር እዳ ከፈለ፤ 47.7 ቢሊዮን

ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት 47 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። የድርጅቱ ዋና...

Close