“Our true nationality is mankind.”H.G.

ህወሃት በጠላትነት ስሙ እንዳይነሳ ከዳር ሆኖ ሴራዎችን እንዴት እንደሚያመርት … አቶ ታዬ

በኢትዮጵያ አሁን ላይ እየገነገነ የመጣው የሴራ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን የአብሮነትና አንድነት እሴታቸው ላይ ጥላ እያጠላ መሆኑ ይነገራል። ይህ የሴራ ፖለቲካ ደግሞ በተለይ የዘውጌ ፖለቲካን አቀንቅነው ከሃሳብ እስከ ተግባር ላስጓዙት ጥቂት የህወሓት ቡድኖች የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ተደርጎ የተያዘ ቁልፍ መሳሪያ ስለመሆኑም ብዙ እየተባለ ነው። በዚህም ከአርባ ላላነሱ ዓመታት ከማስጓዛቸውም በላይ ፤ በ27 የስልጣን ዘመን ጉዟቸው ተክለው ለፍሬ ያበቁትም የተጠቀሙበትም ሆኗል። ሆኖም -የተንኮልን ጉድጓድ አትቆፍር፤ ከቆፈርክም አታርቀው የሚገባበት አይታወቅምና” እንዲሉም፤ ይህ በሴራ የተተበተበ የፖለቲካ ጉዞ እንደታሰበው ህዝቦችን አባልቶና አገርን አፍርሶ ህልማቸውን ዳር ያደረሰ አልሆነም። የዘረጉት ወጥመድ እነርሱኑ ጠልፎ ከመሃል ወደ ዳር ገፋቸው።

ይሁን እንጂ -እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንደሚባለው አይነት ብሂል ፤ እኔ ያልመራኋትና ያልበዘበዝኳት ኢትዮጵያ ትጥፋ በሚል ብሒል የማባላትና የማተራመስ መረባቸውን ከጉድጓዳቸው ሆነው መወርወራቸውን አላቋረጡም። ከሰሞኑም በኦሮሚያ ክልል የሆነው የዚሁ ሴራ አብይ ማሳያ ነው። እኛም በዛሬው እትምችን በሴራ ፖለቲካኞችና ሰሞንኛ ሴራቸው ዙሪያ በማጠንጠን ከኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ጋር ያደረግነውን ሰፊ ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።

 አዲስ ዘመን፡– አገራዊ ለውጡን ለማጨናገፍ የሚደረጉ ጥረቶች አሁን ላይ እንዴት ይገለጻሉበዚህ ላይ ዋንኛ ተዋናዮች እነማን ናቸውለውጡን ማደናቀፍስ ለምን ዋና ስራቸው አደረጉ?

አቶ ታዬ፡ መጀመሪያ ይሄ ለውጥ ከመምጣቱ በፊትም ለውጡ እንዲመጣ የሚታገሉ ኃይሎችና ለውጡ እንዳይመጣ ለማስቀረት የሚጥሩ ኃይሎች ነበሩ። ለውጡ የመጣውም በእነዚያ ፍትጊያዎች መሃል ነው። ይሄ ለውጥ ከመጣም በኋላ በኢትዮጵያ በርካታ መሰረታዊ ለውጦችን አምጥቷል። ጠቅለል አድርጎ ለማንሳት ፣ በዋናነት የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን መግለጽ ይቻላል፤ የሚዲያ ነጻነትን መግለጽ ይቻላል፤ የተሰደዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ወደአገራቸው ተመልሰው በመሰላቸው መንገድ እንዲታገሉ መንገድ መክፈት ተችሏል።

ከኢኮኖሚም አንጻር ቀላል የማይባሉ ለውጦች መጥተዋል። ምክንያቱም በወቅቱ (ለውጡ ሲመጣ) ይህች አገር ካዝናዋ ለሁለትና ሶስት ወር እንኳን ደመወዝ መክፈል የማይችል ነበረ። ማክሮ ኢኮኖሚውም አደጋ ላይ ነበር። በማይክሮ ደረጃም ዜጎች በጣም ችግር ውስጥ ነበሩ። አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት ባይቻልም፤ ማክሮ ኢኮኖሚው ማንሰራራት ጀምሯል። ለውጡ እነዚህንና ሌሎችም በርካታ ውጤቶችን ማምጣት ቢችልም ይሄ ለውጥ ወደፊት እንዳይሄድ የተለያዩ ኃይሎች ለማደናቀፍ ጥረት ሲያደርጉ ነበረ።

በዋናነት የዚህ ለውጥ እንቅፋት ተብለው የተለዩት፣ ኢህአዴግም በሃዋሳው ጉባኤ ላይ የለየው በአስተሳሰብ ደረጃ ጽንፈኝነትን ነው። በአደረጃጀት ደግሞ ህወሓት ለውጡ እንዳይመጣም ሲታትር የነበረ፤ ከለውጡ በኋላም ደግሞ ወደኋላ እንዲመለስ ለማድረግ እንደ ኃይል የተደራጀ ነበረ። የለውጡ ትልቁ እንቅፋትም የሚመነጨው ከዛ ነው። ለ27 ዓመታት የነበረበትን የሴራ አይነት በየጊዜው እየመዘዘ እየተጠቀመ ህብረተሰቡን ለማደናገር፤ የለውጥ ኃይሉንም ለማዳከም ብዙ ጥረት አድርጓል።

የሚጠቀምባቸው ስልቶችም አንደኛው የብሄር ግጭት መቀስቀስ ነው። ለምሳሌ፣ ለውጡ እንደመጣ አብዲ ኢሌ ከመያዙ በፊት በሶማሌ ክልል ላይ መሰረት በማድረግ የተሰራ ሲሆን፤ በዚህም በቤተ ክርስቲያን ላይ ቃጠሎና ጉዳት እንዲደርስ ሲያደርግም ነበር። ከለውጡ በፊትም ቢሆን የኦሮሞ ማህበረሰብና የሶማሌ ማህበረሰብ እንዲጋጩ በሰሩት ስራ የኦሮሞ ማህበረሰብ በገፍ ከሶማሌ አካባቢ እንዲፈናቀል አድርገዋል። ለዚህ ደግሞ ከመከላከያው ውስጥም፣ ከደህንነትም፣ ከአብዲ ኢሌ ጋርም ተመሳጥረው ትልቅ ሸር/ሴራ ሰርተው ነበረ።

ለውጡ ከመጣም በኋላ የመጀመሪያው በትር ያረፈው እዛ ነው። ለዚህ ደግሞ “ሄጎ” የተባለ ሃይል በማደራጀት በዜጎች ላይ ዘረፋ፣ ግድያ፣ ድብደባና እንግልት እንዲፈጽሙ አድርጓል። ይሄ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በኩል ዞሮ ከድል ማግስት ትግል የጀመረውን ኦነግ ሸኔ በመጠቀም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማህበረሰብ ጋር የኦሮሞ ህዝብ እንዲጋጭ ተደርጎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ሆኗል።

በዚህም የጀመርነውን የዴሞክራሲ፣ የነጻነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና የልማት እንቅስቃሴዎችን ወደፊት እንዳንወስድ፤ በግጭት አጀንዳ እንድንጠመድ ተደረገ። በዚህም ብዙ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል። ይሄኛው እንዳለፈና ሰከን ሲል ደግሞ ጌዲዮና ጉጂን በማጋጨት በርካታ ህዝብ ከጌዲዮ ወደ ጉጂ፣ ከጉጂም ወደ ጌዲዮ እንዲሰደዱ የተደረገበት፤ ወንድማማች ህዝቦችን የማባላት ስልት ተጠቅመዋል። ለዚህ ደግሞ በ27 ዓመት እድሜያቸው አብረው የዘረፉትና አብረው የሰረቁትን ሀብት እንደ ብትር በመጠቀም መምቻ አድርገው ችግሮቹ ተፈጥረዋል።

ከዚህ ባሻገር የ2012ቱን የተማሪዎች ግጭት ማየት ትችላለህ። ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ በተለይ በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አብረው እየተማሩና አብረው እየተመገቡ በጽንፈኝነት ስሜት እንዲበከሉ በራሱ በአሻንጉሊቶቹ በኩል ከሰራ በኋላ፤ ገንዘብ በመመደብና አጀንዳም በመቅረጽ ብሎም ፕሮግራም በማዘጋጀት ተማሪዎች በተማሪዎች ላይ እንዲነሱ በመስራት፤ አንድ ተማሪ ሲገደል ደግሞ ያንን አጀንዳ የበለጠ ሌላ ግድያ ማስከተል እንዲችል ከእርሱ ጋር በሚሰሩ ኤጀንቶቹ/ወኪሎቹ ከፍ ብሎ እንዲጮህ በማድረግ ሁለቱን ብሔሮች በተለይ አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት በጣም ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል።

ስለዚህ በዋናነት ህወሓት የሰራቸው ስራዎች እንዳሉ ሆነው ፤ ከእርሱ ስር በመሆን ጽንፈኞች በኦሮሚያ ክልልም አሉ፤ በአማራ ክልልም በዛው ልክ አሉ፤ በሁሉም አካባቢ የእሱን አጀንዳ የሚያራግቡ (ለምሳሌ፣ ደቡብ ላይም 11/11/11 ብለው የተፈጠረው ይታወሳል) አሉ። እነዚህ ሁሉ የእርሱ አጀንዳዎች ናቸው። ለ27 ዓመታት ለአንድም ቀን አንድንም አንቀጽ አክብሮት የማያውቀውን ህገ መንግስት የመጨረሻውና ትልቁ ጠበቃ ሆኖ በመቅረብ፤ ፌዴራሊዝም ፈርሷል፤ አሃዳውያን መጥተዋል፤ በሚል ብሔር ብሔረሰቦች እንዲጠራጠሩ ለማድረግ ሞክሯል። ሥርዓቱንም በአንድ በኩል የተረኞች ሥርዓት ነው ብሎ አማራ ክልል ላለው ማህበረሰብ በዛ ደረጃ በጽንፈኞች በኩል እንዲደርሳቸው፤ ራሱም በራሱ የፌስቡክ ሰራዊቱ በአንድ በኩል ኦሮሞን በመምሰል፣ በሌላ በኩል አማራን በመምሰል በዚህ መሃል የሚነሳውን እሳት ወይም ሊፈጠር የሚችለውን ማንኛውም ግጭትና ቁርሾ ለማድረግ ሰርቷል።

በዛ በኩል ይህ ሥርዓት የተረኞች ነው በሚል እዛ ያለው ማህበረሰብ እንዲጠራጠረውና እንዳይተማመንበት፤ በዚህ በኩል ደግሞ የነፍጠኞች ነው፤ ነፍጠኛ ወርሮሃል ብሎ በዚህ በኩል ያለውን ጽንፈኛ እየተጠቀመ ሲሰራ ከርሟል። በዚህ ደረጃም ጥርጣሬ አምጥቷል። እናም ዋናው የዚህ ለውጥ እንቅፋት ከለውጡም በፊት ጀምሮ፣ ከለውጡም በኋላ ህወሓት ላይ ያጠነጥናል።

አዲስ ዘመን፡– ህወሓት በዚህ ልክ ተላላኪዎችን መርጦ ይሄንን የሚያደርገው ለምንድን ነው?

አቶ ታዬ፡ አንድ ጊዜ የበላይነትን የለመደ አካል እኩል ሁን ስትለው የተዋረደ ይመስለዋል። አሁንም ድረስ ምናልባትም በሚዲያዎች እንደሚሰማው ህወሃቶች እኛ በታሪክ ካለን አስተዋጽዖ አንጻር የተለየና የበለጠ ቦታ፤ የበለጠ ስልጣንና ኢኮኖሚ ይገባናል ብለው በግልጽም ያነሳሉ። ከዚህ ባለፈም በዚህ አገር ውስጥ በአንድ በኩል የተዘረፉና የተሰረቁ በርካታ ነገሮች አሉ፤ እናም ይሄ ለውጥ መሰረቱን ይዞ በትክክለኛው አቅጣጫ የሚዘልቅ ከሆነ ምናልባትም ነገ ተጠያቂነት ይመጣል የሚል ስጋትም አለ።

እነዚህ ሃይሎች ያለፈውን ትተን እሱ ስለማይጠቅመን መልካም ነገሮችን አጎልብተንና የተበላሹትን ለማስተካከል ከዚህ ጀምረን እንስራ፤ የይቅርታ መንገድ እንከተል የሚለውንም ለማመን አልፈለጉም። ለማመን ያልፈለጉት ደግሞ እነርሱ ስለማይታመኑ ሁሉም እንደዛው ይመስላቸዋል። እነርሱ በአፋቸው የሚሉት ሌላ፤ በልባቸው የያዙት ሌላ ስለሆነ ሰው በቅንነት በዚህ ደረጃ ነው ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው ብሎ ቢናገር ከራሳቸው አንጻር ስለሚመነዝሩት ይሄንንም ሊያምኑ አልቻሉም። እየተጠራጠሩ ነው የመጡት።

ሁለተኛ ደግሞ እነርሱ ለዛ ክልልም ሆነ ማህበረሰብ በስሙ ነገዱበት እንጂ ላለፉት 27 ዓመታትም ሆነ ዛሬም ድረስ ያ ማህበረሰብ ችግረኛ ነው። እነርሱ የሚሰሩት ለራሳቸው ስለሆነ ይህች ኢትዮጵያ እኛ ካልገዛናት፤ እኛ እንደፈለግን የማናደርጋት ከሆነች “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አይነት የአህያ ብሂል ኢትዮጵያን ወይ እኛ እንግዛት ካልሆነ ደግሞ ትጥፋ በሚል የሚያደርጉት ነው። ከዚህ አንጻር መልሶ ሥልጣን ለመቆጣጠር ፍላጎት አለ፤

ያ የማይሳካ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል የለባትም፤ እኛ በዳር የዛን ክልል ማህበረሰብ ለይተን እንገዛዋለን (እናስተዳድረዋለን ሳይሆን እንገዛዋለን ነው)፤ ሌላው ደግሞ ሀገር ሲቃጠል ዳር ሆነን እናያለን የሚል ስሜት አላቸው። ይህ ሁሉ የሚሆነውም ለዚሁ ነው።

አዲስ ዘመን፡– በለውጥ ጉዞው ውስጥ ከተስተዋሉ የአደናቃፊነት እንቅስቃሴዎች አንጻር ሃወሓትና የሴራ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎቹ እንዴት የሚገለጹ ናቸው?

አቶ ታዬ፡ የሴራ ፖለቲካ የህወሓት የተካነበት ነው። የሚያውቁት የሚናገሩትም ይሄንኑ ነው። ለምሳሌ፣ ደርግ የመሬት ላራሹ ጥያቄን ሲመልስ ሁሉም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በአዎንታ ነው የተቀበሉት። ያ ደግሞ ትግራይም ላይ ጭሰኛ የነበሩ ዜጎች መሬት ሲያገኙ ደርግን ተቀብለውት ነበር። ህወሓት መጀመሪያ መጥቶ ሲሰብካቸውም “እኛ መሬት አግኝተናል፤ ከዚህ በኋላ ሌላ አንፈልግም” ሲሏቸው፤ ሲያደርጉ የነበረው የደርግ ልብስ በመልበስ ደርግን መስለው ማታ ማታ እየገረፉና እየገደሉም ጭምር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየመጡ ደርግ ገዳይ ነው፤ ደርግ እንደዚህ ነው፤ ይደፍራል፣ ይገድላል፣ ይገርፋል ብለው ይሰብኳቸው እንደነበር የሚያውቋቸው ይናገራሉ።

ከኢህአፓ ጋር የነበረውም በአሲምባ ላይ በሴራ ነው በርካታ ሺህ አባላቱ እንዲያልቁ የተደረገው። የሀውዜንም ሁኔታ ሰዎች የሚመነዝሩት ያኔ ደርግ ከትግራይ ጥሎ ስለወጣ ከዚህ በኋላ የሰበካችሁን ትግራይን ነጻ እናውጣ ነበረ፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ ትግራይ ውስጥ ደርግ የለም፤ ስለዚህ ከዚህ በኋላ አንዘምትም በሚል የእነርሱ ወታደሮች ጥያቄ ሲያነሱ በደርግም ውስጥ ከነበሯቸው ሰዎች ጋር በመቀናጀት ነው በሴራ ያ እልቂት እንዲፈጠር ያደረጉት። ከዛም ደርግ ከምንጩ ካልጠፋ በስተቀር እዚህ ሰላም ልናገኝ አንችልም የሚል ሰበካ አመጡ። እናም ከመጀመሪያው ጀምሮ በሴራ ነው እዚህ የደረሱት። አሁንም በሴራ እንጂ በትክክለኛ መንገድ በያዝነው አስተሳሰብ ልናሸንፍ እንችላለን ብለው አምነውም አያውቁም።

ይሄ ሴራ ባለፉት 27 ዓመታትም በኦሮሞና በአማራ መካከል በኢህአዴግ ውስጥም በነበሩ ብአዴንና ኦህዴድ ውስጥም፤ ከዛ ውጪም በልሂቃን መካከል መቃቃር እንዲኖር ሆን ተብሎ የተሰራና የተሰላ ስሌት ነበር። ያ ስሌት ደግሞ አማራና ኦሮሞ ሊታረቅ የማይችል ቅራኔ አላቸው የሚል ሲሆን፤ ይሄንንም በመጽሀፍ ጭምር ጽፈዋል፤ በሚዲያዎችና በጋዜጣም ብዙ ተሰብኳል። ይሄ ሲሰበክ የሆነው ደግሞ ህወሓትን በመፍራት ሳይሆን እነዚህ ትልልቅ ማህበረሰቦች አንዱ ሌላውን እየፈራ ለዚህ አናሳ የህወሓት ቡድን ይገዛለት ነበር። ለምሳሌ፣ ፓርላማው ውስጥ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልልን ብቻ ወክለው ያሉት ከ300 በላይ ድምጽ ነው። አለመተማመን ሆኖ ነው እንጂ ይሄ ሃይል የማይደግፈው ረቂቅ ህግ ሊሆን አይችልም ነበር። በአንጻሩ ይሄ ኃይል የሚፈልገው ረቂቅ ደግሞ ህግ ሆኖ የማይወጣበት ሁኔታ አልነበረም።

ይሁን እንጂ አንዱ ሌላውን እንዲፈራ ሆን ተብሎ ስለተሰራ፤ እሳትና ጭድ ተብሎ ስለተሰበከ፤ አህያና ጅብ ተብሎም ስለተነገረ፤ ዛሬ ላይ ምን ጉዳዮችን አብረን ሰርተንና ምን ለውጠን ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለ ህይወት የሚለው ሳይሆን፤ የዛሬ 100 እና 150 ዓመት በፊት የነበሩ ጉዳዮች የዛሬውን ሁኔታ አስረስተው እንዲይዙት ተሰርቷል። ይሄ ብቻ ትልቅ ሴራ ነው። ይሄ ሴራ ባህር ዳር ላይ፣ ከባህርዳርም በፊት ጎንደር ላይ ወጣቶች እዛም ግድያ ነው፤ እዚህም ግድያ ነው፤ እዛም አፈና ነው፤ እዚህም አፈና ነው፤ ስለዚህ ተለያይተን አንችልም፤ በሚል የኦሮሞ ደም የእኔ ደም ነው፤ የአማራ ደም የእኔ ደም ነው በሚል መናበብ ሲፈጠር፣ በሴራ የተገነባው ግንብ እየተሰበረና እየተናደ ሲመጣ፤ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ባህር ዳር ላይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ሲፈጠርና ህዝቡ እንባ ሲራጭ እዛ ላይ ተሆኖ ለውጡ እንቅስቃሴውን ቀይሯል።

ይሁን እንጂ ይሄ የዱርዬዎች ግንኙነት ነው እንጂ ኦሮ-ማራ የትም ሊደርስ አይችልም በሚል አንስተው ሲተቹት ነበረ። ሆኖም ግንኙነቱ እየተጠናከረና እየተስማሙ፤ ሂደቱ በአመራርም ሆነ በልሂቃን በኩል በውጪም በውስጥም ያለው በመናበብ መስራት በመጀመራቸው ለውጡ መጣ። ለውጡ እንደመጣ ደግሞ አሁንም ኦሮ-ማራ ፌክ ነው የሚል ተረክ አመጡ። ለውጡ መጥቶ ሁለት ወር እንኳን ሳይሞላው በዚህ ስሌት መልሰው ማህበረሰቡን ለመለያየት አበክረው ሲንቀሳቀሱ ነበር። በዚህም በሁለቱ ህዝቦች መካከል ከሚያከናውኑት ሴራ ባለፈ፤ በወላይታና ሲዳማ መካከል ሴራ ተሰርቷል፤ በኑዌርና አኙዋ መካከል ሴራ ተሰርቷል፤ አንዱን ይዘው ሌላውን በማጣቃት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየቀያየሩ በሁሉም ቦታ ሴራ ተሰርቷል። ሁሉም ግን እንዲከሽፉ ሆኗል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ያመጡት ነገር እነርሱ የሚሰብኩት (በዲጂታል ወያኔም ሆነ በሌሎች መደበኛ ሚዲያዎቻቸው) ሰበካ ውጤት አላመጣ ሲል፤ የግድያ ሴራን አመጡ። ለምሳሌ፣ በመጀመሪያው ሰኔ ላይ ግድያውን ያቀነባበሩት ራሳቸው ናቸው፤ ሎጀስቲክና መኪና ጭምር አቅርበውም ቦንቡን ያስወረወሩት ደግሞ ኦነግ ሸኔን ነው። ይሄ በራሱ ትልቅ ሴራ ነው። ሴራውም በተግባሩ አንደኛ ፣ የማይፈልጉት አመራር ይወገድላቸዋል፤ በኋላ ደግሞ ማነው እንዴት ነው የፈጸመው ሲባል ኦሮሞ ራሱን በራሱ አጠቃ የሚል ትርክት ለማምጣት ነው። ጠላትነቱ ወደ እነርሱ እንዳይሄድ በዚህ ደረጃ ተሰልቶ የተሰራ ነው።

ከዛ በኋላም በአማራ ክልል አመራሮች ላይ የተፈጸመውም አሳዛኝ ተግባር የዚሁ የሴራ ፖለቲካ አካል ነው። ይሄም በምርመራ እስካሁን ባይወጣም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የእነርሱ አስተዋጽዖ ሊኖርበት እንደሚችል በርቀት ይታወቃል። ያ ሲሆንም እነርሱ እጅግ ደስ ብሏቸዋል። ምክንያቱም እነዚህ ታጋይ አርበኞች ይሄ ለውጥ ሲመጣ የነበራቸው ሚና ይታወቃል። እንዴት ቢባል፣ ለለውጡ የውጪ ግፊቱ እንዳለ ሆኖ በውስጥ እንደ እነ ዶክተር አምባቸው እና አቶ ምግባሩ ያሉት በጀግንነት ሲታገሏቸው ነበርና ነው።

ከዚህ በኋላ ደግሞ ይሄኛውን ሰኔ፣ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መረጡ። ይህ አርቲስት እንደሚታወቀው እነርሱ ጉልበት በነበራቸው ጊዜ፤ ሁሉ ነገር በእጃቸው፣ ሁሉ ነገር በደጃቸው በነበረበት ወቅት፣ ሌሎች በርካቶች ፈርተው ዝም ባሉበት፤ ሌሎችም ፈርተው በሸሹበት እዚሁ በሚሊኒየም አዳራሽ ግፈኞች እንደነበሩና መውረድ እንዳለባቸው በግልጽ በቀረርቶ በጀግንነት አሰምቷል። ይንን ሙዚቃም ኮንነዋል።

አዲስ ዘመን፡– የሃጫሉ ግድያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሴራ ፖለቲካ አዲስና አደገኛ መንገድ ውስጥ ስለመግባቱ ማሳያ እንደሆነ ይነገራል። እርሶ ይሄንን እንዴት ይረዱታል?

አቶ ታዬ፡ የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን በተመለከተ ሁለት ነገሮችን መመልከት ይቻላል። ለምሳሌ፣ ኮቪድ 19 በመምጣቱ ምርጫ ተራዝሟል። ይሁን እንጂ ኮቪድ ሲመጣ የፌዴራል መንግስቱ ቸልተኝነት አሳይቷል በሚል ቀድሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁት ህወሓቶች ናቸው። በኋላ ላይ ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አውጆና ተከትለው የሚመጡትን እርምጃዎች መውሰድ ሲጀምር፣ የምርጫ ጉዳይንም በህግ አግባብ ኮቪድ 19 ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መካሄድ አለበት በሚል ተወስኗል። ይሄ ሲሆን ህወሓትና የእርሱ ጀሌዎች (ባንዳዎች) ይሄንን ተቃወሙ። ሲቃወሙም ይሄ ህገመንግስትን የሚጥስ ስለሆነ ከመስከረም በፊት ምርጫ ይካሄድ፣ ወይ የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት፤ ወይም የባላደራ መንግስት ካልተመሰረተ ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም የሚል አቋም ይዘው ሲሰሩ ነበር።

ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓባይ ግድብን ውሃ መያዝ ትጀምራለች፤ ይሄ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ነው። ትልቅ ስኬትም ነው። ስለዚህ መስከረም ላይ የተያዘው እቅድ እያለ ስፖንሰር የሚያደርጋቸው የውጭ ኃይል ደግሞ ይሄ ነገር ለመስከረም ስለሚዘገይና ውሃው ከተያዘ በኋላ ምንም አይነት ጩኸት ብትጮሁና ምንም አይነት ነገር ብታደርጉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ትልቅ ስኬት በኋላ እናንተን የሚሰማበት ጊዜም የለም፤ ለእኛም አይጠቅምም ስላሏቸው ይህችን አገር ወይ መንግስትን ገልብጠን መልሰን ስልጣን መቆጣጠር፤ ያ ካልሆነ ደግሞ ይሄ የብልጽግና ጉዞ/አካሄድ እየሰረጸ ከሄደ ማቆም ስለማንችል ይሄ የመጨረሻው እድል ነው ብለው አገር ለማተራመስና ለማፍረስ ጭምር አቅደው ነው ይሄን ያደረጉት።

ከግድያው በፊት ግንቦት 20 አካባቢ የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ሲወጣ በኦሮሚያ በተለይ በጉጂ ላይ ሰብዓዊ መብት ተጥሷል የሚል ሚዛኑን ያልጠበቀ ሪፖርት ወጥቶ ነበር። ያ ሲወጣ የነበረው ዓላማ ውስጥ ላይ ረብሻ በማስነሳት፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደግሞ መንግስት ሰብዓዊ መብቶችን እየጣሰ ነው፤ ዜጎችን እያሰቃየና እየገደለ ነው፤ የሚል ስዕል እንዲኖረው ሁሉ ነገር ስፖንሰር ተደርጎና ለሌሎች ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች ሁሉ ነገር ከተመቻቸ በኋላ በዚህም ጥሪ ተደርጎ ነበር። ሆኖም ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቱ አካሄዳቸውን እያየ ስለነበረ አካሄዳቸው አይጠቅመኝም በሚል በዛ አልተሳተፈም።

እናም ወጣቱ በዛ አልሳተፍ ሲል “ከዚህ በኋላ በተለየ ስትራቴጂ ይዘን እንመጣለን” የሚል አንስተዋል። ያ የተለየ ስትራቴጂ ደግሞ ከዚህ በፊት ያልነበረ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው ግድያ ሳይሆን የሆነ አጀንዳ ይኖራል፤ በዛ አጀንዳ ዙሪያ ህብረተሰቡ ተነስቶ እንዲያምጽ ማድረግ ነበር። ስለዚህ የተለየ አጀንዳ የተባለው ይሄን ህብረተሰብ ለመቀስቀስ የሚያስችል ታላቅ ሰው፤ የሚወደድና የሚከበር ሰው፣ ከጫፍ እስከጫፍ ሁሉንም ሊያስደነግጥ የሚችል ሰው ማነው የሚል ስሌት ውስጥ ገብተዋል። ከዚህ ስሌት በኋላ ይሄን ወጣት ጀግና ኢላማ ያደረጉት።

ለዚህ ኢላማቸው ደግሞ አንደኛ፣ ህወሓቶች በአርቲስቱ ላይ ቂምም አለባቸው። እነ ኦነግ ሸኔም ደግሞ የእነርሱን አጀንዳ የሚያቀነቅን ሙዚቃ እንዲዘፍን በተደጋጋሚ ሲጠይቁት ነበረ። አላደርግም ብሏቸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በታህሳስ አካባቢ በኦ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ላይ በመቅረብ አሁን የሚያደርጉት የጫካ ትግል በጣም ኋላ ቀር እንደሆነ፤ ትግል በሚያስፈልግበት ወቅት በቦታው እንዳልነበሩ፤ ከነጻነት በኋላ ህዝቡን እንደሚረብሹ በደንብ ተችቷቸዋል። በዛን ጊዜ በፌስ ቡክም ሆነ በነበሯቸው የራሳቸው (ኦ.ኤን.ኤን በሚባል) ሚዲያ በጣም ዘልፈውታል። ስለዚህ ይሄ ሁሉ ቂምና ጥላቻ አለ።

ከዚህ ባለፈ ያለው ደግሞ ይህ ሰው የሚወደድ እንደመሆኑ ቢገደል ሰዉ ሆ ብሎ በብዛት ይወጣል የሚል እምነት አሳድረዋል። ከህዝቡ ሆ ብሎ ከመውጣቱ በፊት ደግሞ የእነርሱን የጥፋት ድግስ የሚያዘጋጁና የሚፈጽሙ በየቦታው እንደተከሉ የሚያሳዩ የምርመራ ውጤቶች አሉ። ለዚህ እንዲሆናቸውም ሃጫሉን ከመግደላቸው በፊት በኦ.ኤም.ኤን ቴሌቪዥን አቀረቡት። በርካታ ጉዳዮችንም ስለጠየቁት እሱም ዘርዘር ያሉ ጉዳዮችን አንስቷል። የተገደለውም በሳምንቱ ነው።

በዚህ ቃለ ምልልስ የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ተቆርጠው እንዲወጡ ተደርጓል። ይሄንንም በኢቢሲ. ኦ.ቢ.ኤን እና ሌሎችም ሚዲያዎች እንዲታዩ ሆኗል። ተቆርጠው በወጡ የቃለ ምልልሱ ክፍሎች ላይ ሶስት ነገሮችን መመልከት ይቻላል። በአንድ በኩል ይሄን ለውጥ ታግለን ነው ያመጣነው ለውጥ ነው፤ ስለዚህ ወደ ኋላ መመለስ ሳይሆን እየደገፍንና እያጎለበትን ወደፊት መሄድ አለብን የሚል ነበረ፤ እሱን ቆረጡት። ይሄ የተቆረጠው ከተገደለ በኋላ የመንግስት እጅ አለበት ለማለት ስለማያስችላቸው ነው። ስለዚህ ይሄ እንደሚሆን ቀደም ብሎም ይታወቃል ማለት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ፣ በኦ.ቢ.ኤስ የሰነዘረውን ትችት ተከትሎ ከዛን ጀምሮ ሊገሉት እንደሚፈልጉና እንደሚያስፈራሩት ከኦነግ ሸኔ ጋር ተያይዞ በራሱ አንደበት ዘርዘር አድርጎ አንስቷል። እሱንም ቆርጠው አወጡት። ይሄም ከተገደለ በኋላ ነፍጠኛ ነው የገደለው ለማለት ስለማያስችላቸው ነው የቆረጡት። በዚህ ረገድም ምን መደረግ እንዳለበት ቀደም ብሎ ይታወቃል ማለት ነው። ሶስተኛው፣ የኦሮሞም ህዝብ፣ የኢትዮጵያም ህዝብ ባደረገው ትግል ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሸነፉን አስረግጦ ተናግሮ ነበር። በዚህ ረገድ ጌታቸው አሰፋ ሲሰራ የነበረውን ግፍ ሁሉ ነበር ያስቀመጠው። ይሄንንም ቆርጠው አወጡት። ይሄን የቆረጡት ደግሞ ይሄ በወቅቱ ከተነገረ በኋላ በድምጸ ወያኔም ሆነ በትግራይ ቲቪ ህወሓት ያሰማው ለቅሶ ትርጉም ሊኖረው ስለማይችል ያደረጉት ነው። እናም ይሄ ሁሉ ሆን ተብሎ እየታወቀ የተደረገ ነገር ነው።

Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች

እናም የነበራቸው አዲስ የሴራ አቅጣጫ ይሄን ጀግና ወጣት በመግደል በሚቀሰቀሰው የህዝብ ቁጣ ከቻልን ስልጣን እንቆጣጠራለን፤ ካልቻልን ደግሞ ኢትዮጵያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንበታትናታለን የሚል ነው። የመጨረሻውን አቅማቸውን ተጠቅመውም ሃጫሉን ገደሉ። ይሄ ትልቅ ሴራ ነው። በርካታ ጉዳቶችንም አድርሷል። በዋናነት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ በርካቶች ቆስለዋል፤ በርካታ የመኖሪያ፣ የሆቴልና የንግድ ቤቶች እንዲሁም ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል።

የተጎዱ ወገኖች (እናቶች፣ አባቶች፣ እህቶችና ወንድሞች) እንዳሉ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ ሊረዳ የሚገባው ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያው የኦሮሞ ህዝብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደሚያውቁት አቃፊ ነው። አፍቅሮ፣ ተባብሮ፣ ከሁሉም ጋር ተዋዶና ተዋልዶ አብሮ የኖረና አብሮም የሚኖር ነው። አሁን እነዚህ ሴረኞች በጠነሰሱት ሴራ ኦሮሞ በብሔር ብሔረሰብ ላይ ጉዳት አድርሷል፤ የብሔር ብሔረሰቦችን ብቻ ሳይሆን በራሱም ውስጥ በክርስቲያንና ሙስሊም ስም ተቧድኖ አንዱ ሌላውን በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገድል ተደርጓል፤ ያለምንም ምክንያት ከተሞች እንዲወድሙ ተደርጓል፤ በርካታ ንብረትም እንዲወድም ተደርጓል። ይሄ በኦሮሞ ማንነት ላይ ትልቅ ጠባሳ የጣለ አደገኛ ሴራ ነው።

እነዚህ ባንዳዎች ህወሓት የሚያደርገውና ጉዳቱ የት ድረስ እንደሚሆንም አልተረዱትም። እነሱ አይገባቸውም። ስልጣን ትይዛላችሁ ስለተባለ ብቻ እሱ በሸረበው ሴራ ገብተው ይጫወቱለታል። ይሄ ግን ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ፤ በማንኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው፤ ከሃይማኖትም ያፈነገጠ (ክርስትናንም ሆነ እስልምናን የተቃረነ)፤ የሰው ስብእናንም የተቃረነና እጅግ አሰቃቂ የሆነ፤ በኢትዮጵያ ምድር ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ መጥፎ ድርጊት ነው።

ሁለተኛው ጉዳይ፣ በእኛ አገር ትልቁ ችግር የስራ አጥነት ነው። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እጅግ ብዙ ወጣቶች ስራ አጥ ናቸው፤ ስራም የላቸውም። ይሄንን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት ዋናውና ትልቁ ነገር ደግሞ ኢንቨስትመንትን በሰፊው መሳብ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው። አሁን ግን ወደ ኦሮሚያ የመጡትንና ኦሮሚያ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩትን፤ ለኦሮሞ ወጣቶችም የስራ እድል የፈጠሩትን፤ የኦሮሞ ወጣቶችን ያለበሱና ያበሉትን ኢንቨስተሮች ንብረታቸውን በዛ ደረጃ ማቃጠል ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። የዚህ ተግባር ትርጉም የኦሮሞ ህዝብ በድህነት አረንቋ ለዘላለም እንዲኖር መፍረድ ነው።

ተግባሩ በአንድ በኩል እኛ የምንሰራቸውና የምናስተካክላቸው ነገሮች ቢኖሩም፤ እዚህ አካባቢ የታሰበው ሴራ፤ አንደኛ፣ የሆነውን አይቶ በ“እኔን ያየ ይቀጣ” አይነት ብሂል አዲስ ኢንቨስተር ወደዚህ ክልል ከዚህ በኋላ እንዳይመጣ ማድረግ ነው። ሁለተኛም፣ ቀደም ሲል እዛ ኢንቨስት አድርጎ የሚሰራ ኢንቨስተርም ከዚህ በኋላ ፈርቶ አካባቢውን እንዲለቅቅ ለማድረግ ነው። ኢንቨስተር ለቀቀ ማለት ደግሞ አካባቢው፣ ክልሉ፣ ከተሞች መልማት አይችሉም ማለት ነው። ስለዚህ ይሄ ትልቅ ኪሳራ ነው።

ሶስተኛው ጉዳያቸው፣ ኦሮሞን በራሱ በኦሮሞ ላይ ማነሳሳት ሲሆን፤ በሃይማኖትና በጎሳ በመከፋፈል ውስጣዊ አንድነቱን ለማሳጣት የተሸረበ ሴራ ነው። ይሄም የህወሓት ሴራ ነው። የሚፈጽሙት ግን አያውቁም። ስልጣን ስልጣን ይላቸዋል፤ አደግፋችኋለሁ ይላቸዋል፤ አሃዳዊ መንግስት መጣባችሁ፣ ፌዴራሊዝም ሊፈርስ ነው ይላቸዋል። ህገ መንግስቱ ተንዷል፣ ቋንቋችሁ ወደ ኋላ ሊመለስ ነው ኦሮሞነትና ብሄርተኝነት እየተዳከመና እየጠፋ ነው፣ የኦሮሞ ጥያቄ አልተመለሰም፣ ወዘተ ብቻ ነው ለእነርሱ የሚነገራቸው። ከዚህ ጀርባ ያለውን ግን እነርሱ አላወቁም፤ በስንት ትግል ያመጣውን ውጤትና አንድነት በዚህ ደረጃ እርስ በርሱ ችግር እንዲደርስበት አድርጓል።

በአራተኛ ደረጃ መታየት ያለበት ደግሞ፣ የኦሮሞ ማህበረሰብ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያለው በኦሮሚያ ክልል ብቻ አይደለም። በተለያዩ ክልሎች ከወንድሞቹ ጋር ተጋብተውም፤ በስራ ምክንያትም ሄዶ ይኖራል። አሁን ኦሮሚያ ክልል ላይ (ሻሸመኔ፣ ባቱ፣ አዳማና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ) የኦሮሞን ጭንብል የለበሱ ሰዎች በኦሮሞ ስም ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ ጉዳዩ ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ይሄን ሲያደርጉ በሌላ አካባቢ ሌላ ወንድሞቹ ጋር እየኖረ ያለ ኦሮሞ ላይ ችግር እንዲደርስ አስበው ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ትልቅ ስለሆነ፤ ታላቅም ስለሆነ፤ ይሄ ደግሞ ሴራ መሆኑንም ስለተገነዘበ እነሱ የሸረቡት ሴራ ጉዳት ቢያደርስም በዛው ከሽፏል። ይሄ ትልቅ ስራ ነው፤ ለህዝባችንም ትልቅ ምስጋና ማቅረብ ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት በህውሀት እና በኦነግ ሸኔ መካከል የተፈጠረውን ህብረት ከቀደመ ታሪካቸው አንጻር እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ታዬ፡ ትልቁ ጉዳይ የጀርባ ታሪካቸውን ማየት ነው። ለምሳሌ፣ እኔ እንደ ግለሰብ ኦነግ ውስጥ ነው የነበርኩት። ኦነግ ውስጥ ሆኜ ኦነግ ብዙ ድጋፍ ነበረው። እኔ ወደ አባልነት ከመቀላቀሌ በፊትም እደግፈው ነበር። ነገር ግን ይሄ ሁሉ ድጋፍ እያለው የዚህ ድርጅት ትግል ለምንድን ነው ወደፊት ገፍቶ የማይመጣው? የሚል ጥያቄ ነበረኝ። በርካታ ወጣቶች፤ በርካታ ምሁራንና መምህራንም ይሄንኑ ይጠይቃሉ። ምክንያቱም በየጊዜው ዘመን መለወጫ ላይ “ገዳን ገዳ ቢሊሱማቲ” (ቀጣዩ ዘመን የነጻነት ዘመን ነው) ይላሉ። ይሄ ደግሞ ዘመን በተለወጠ ቁጥር በቃል ብቻ የሚባል ፍሬ አልባ ጉዞ ነበረ። እናም ምክንያቱ ምንድን ነው? ብለን ብናስብም በወቅቱ ሊገባን አልቻለም። ከዛ በኋላ ኦነግን ተቀላቀንንና ውስጡ ገባን። ስንገባ ነገሩን ተረዳን።

ነገሩ ምንድን ነው ካልክ፤ ኦነግ ሸኔ እና ህወሓት አብረው ሲሰሩ ነበር። ኦነግ ሸኔ ህወሓት የሚጠቀምበት የራሱ መጠቀሚያ ነው። በእርግጥ ኦሮሞ ጠባብ፣ አማራ ደግሞ ትምክህተኛ ይባላል፤ ትምክህተኛና ጠባብ በፍረጃ ደረጃ ነበር የነበሩት። ኦነግነት ደግሞ የህወሓት ትልቁ መጠቀሚያ ነበረ። እንዴት ነው የሚጠቀምበት ካልከኝ ደግሞ፤ አንደኛ፣ የኦሮሞ ህዝብ ነጸነት ይፈልጋል፤ (ኦሮሞ ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያውያንም ነጻነት ፈልገው ዋጋ ሲከፍሉ ነበር፤)፤ ነገር ግን ይሄን ነጻነት ማን ያመጣልኛል ብሎ ሲያስብ አንድ በነጻነት ስም የተደራጀ ድርጅት አለ። ይሄ ድርጅት ግን ጭንቅላቱ በህወሓት ተይዟል።

ህዝቡ ደግሞ ይሄ ድርጅት በወያኔ እጅ የተያዘ መሆኑን አያውቅም፤ እናም አንድ ቀን ይመጣልኛል ብሎ ይጠብቃል። ሆኖም ይህ ድርጅት ጭንቅላቱ ተይዞ በያዘው አካል ፍላጎት የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ ይህ ድርጅት ሊመጣለት አይችልም ነበር። ስለዚህ ህወሓት ኦነግ ሸኔን ሆን ብሎ በዛ ደረጃ የኦሮሞ ህዝብ፣ የኦሮሞ ወጣት፣ የኦሮሞ ምሑር የሌለ ነገር እንዲጠብቅ፤ በሴራ ያስቀመጠው ነው። ይሄንንም ለሃያ ዓመታት ያህል የኖሩበት ሲሆን፤ በተለይም አቶ ገላሳ ዲልቦ ከስልጣን ወርደው የአሁኑ የሸኔ ሊቀመንበር ስልጣን ከያዘ በኋላ በቀጥታ ትብብሩ ውስጥ ነው የነበሩት።

ሁለተኛው መታየት ያለበት ጉዳይ፣ ኦህዴድ ውስጥ ሆነህ ኦሮሞ ላይ ጉዳት ደርሷል ብለህ ካነሳህ ኦነግ ትባላለህ። የኦሮሞ ባለሀብት ሆነህ ሊዘርፉህ ከፈለጉ ኦነግ ይሉሃል። ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ ኦነግ የሌለ ከሆነ የሚፈርጁበት ስለሌለ ስለሚቸገሩ ነው። ስለዚህ ኦነግ እንደሌለና በእነርሱ ስር እንዳለ ቢያውቁትም፤ በኦነግ ስም ተማሪን ለመደብደብም፣ መምህራንን ለማሰርም፣ ነገ ይገዳደረኛል ብሎ የሚያስቡንት ለመግደልም ይጠቀሙበታል። እናም ኦነግ ሸኔና ህወሓት በዛ ደረጃ አብረው ነበሩ።

በሶስተኛ መታየት ያለበት፣ ኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ታጋዮች አንድ ወጥመድ መሆኑ ነው። ለምሳሌ፣ እኔ ሁለት ጊዜ ነው የታሰርኩት። አስር ዓመት ነው እስር ቤት የቆየሁት። ሁለት ጊዜ ስታሰር ሁለቱንም ጊዜ ያሳሰረኝ የኦነግ ሸኔ አባል ነው። ያሳሰረኝ ኦህዴድ አይደለም፤ ህወሓትም ራሱ ፈልጎ አላገኘኝም። ለህወሓት የሰጠኝ ኦነግ ሸኔ ነው። ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ በአንድ በኩል አብረው ስለሚሰሩ ሲሆን፤ በገንዘብም ይሸጡሃል። እንደውም አንዳንዴ አደራጅተውና የኦነግን ባንዲራ አሲዘው አሳልፈው ይሰጣሉ።

ለምሳሌ፣ ግርማ ጥሩነህ የሚባል የሸኔ ተወካይ የነበረ 2008 አካባቢ ቦሌ ላይ 20 ሰዎችን ማህበር ብሎ በአንድ ጊዜ አደራጅቶና የኦነግ ሸኔ ባንዲራ አስቀምጦ ደህንነትን ጠርቶ አስይዟቸዋል። እናም በዛ ደረጃ ነው በሰው የሚጫወቱትና የሚነግዱት። እናም በገንዘብ ይሸጡሃል፤ ከተያዝክና ከታሰርክ በኋላ ደግሞ ጀግና ታሰረ ብለው ውጪ ያሉት አባሎቻቸው በስደት እያሉ የህዝቡን ነጻነት ከሚፈልጉ የዋሆች ላይ ገንዘብ ይሰበስባሉ።

ከዛ ባሻገር ደግሞ ሶሎሎ የሚባል አካባቢ እነሱ የመሸጉበት አለ። እዚህ መከራ ሲያይ፤ ሲታሰርና ሲገረፍ የተቸገረ ሰው በቃ ሄጄ ታጥቄ ልታገል ብሎ እዛ ይሄዳል። እዛም ይታይና ሃሳብ ያለው ከሆነና ጀግንነት ያለው ከሆነ እዛው ይገደላል፤ ወይ ይቃጠላል። ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ ይህ ሰው ነገ ሪቮሉሽን (አብዮት) ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።

እናም ህወሓትና ኦነግ ሸኔ አብረው የሚሰሩ፤ መረጃም የሚለዋወጡ ናቸው። ለአብነት፣ ህብረተሰቡ ሲያምጽ የወያኔ መልስ ጥይት ነው፤ ግድያ ነው። በተለያየ ጊዜ በተማሪ ደረጃ፣ በወጣት ደረጃ፣ በ2006 ከዛም በፊት በ1998፣ በ1996 እና በተለያየ ጊዜ የተለያዩ አመጾች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ተደርገዋል። በጣም የሚያሳዝንህ ግን በዚህ ውስጥም የሴራ ፖለቲካ እንዲታይ ሆኗል። ሴራውም ህወሓት በአጠቃላይም የኢህአዴግ መንግስት ንጹሃን ኦሮሞዎችን ገድሏል፤ ሰብዓዊ መብትም ተጥሷል በሚል በዓለምአቀፍ ደረጃ (በአምኒስት ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ዎችና ሌሎችም) ክስ ይቀርብበታል።

ይህ ክስ ሲቀርብ ህወሓት የሚያደርገው ነገር በእኔ ትዕዛዝ ነው ህዝቡ ያመጸው በልና መግለጫ አውጣ ብሎ የሚያነበውን መግለጫ ጽፎ ለኦነግ ሸኔ ይልክለታል። ኦነግ ሸኔም አስመራ ላይ ሆኖ በህወሓት ተጽፎ የቀረበለትን መግለጫ ያነብባል። የእኛ ትግል ነው ብሎ ያነበበውን የእርሱን መግለጫም እነ ቪኦኤና እንደ ዶቼቬሌ ጭምር ያስተላልፉታል። ህወሓት/ኢህአዴግ ደግሞ ይሄንን ተጠቅሞ እንቅስቃሴው የህዝብ አልነበረም፤ የአሸባሪው ኦነግ ነው ብሎ ራሱን ለመከላከል መልስ ይሰጣል። እናም በዚህ ደረጃ በረቀቀ መልኩ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ አብረው ነበሩ።

ይሄንን በደንብ ማየት የሚያስችልህ በኢሬቻ ጊዜ በርካታ ዜጎች ህይወታቸው አልፏል። በተቃውሞ ጊዜም በተለይ “ግራንድ ራሊ” ተብሎ በተደረገው ትልቅ ሰልፍ የብዙ ወጣቶች ህይወት አልፏል። የኦሮሞ ህዝብ በአብዲ ኢሌ እና በህወሓት ሴራ በሚሊዮን የሚቆጠር ከሶማሌ ክልል ተፈናቅሏል፤ ሞቷልም። እንግዲህ ተኩስ ቢያስፈልግ ያን ጊዜ ጀግና ወጥቶ መተኮስ ነበረበት። ወጣቱ በሰላማዊ መንገድ ወጥቶ ባዶ እጁን መንገድ ላይ ሲራገፍ ኦነግ ሸኔ የሚባለው አንድ ጥይት አይደለም ወደጠላት ወደ ሰማይ አልተኮሰም። ይሁን እንጂ እነ ጌታቸው አሰፋ ከስልጣን እንደወረዱ ጫካ ታያቸው። ይህ ምን ማለት ነው? ትግሉ የነጻነት ነው ወይስ ፀረ ነጻነት ነው? ያኔ ህዝቡ ለነጻነት ሲታገል የት ነበሩ? አዲስ አበባ ላይ፣ አማራ ክልል፣ ኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ሶማሌ ክልል ህዝቡ መከራ ሲያይ፣ ሲገረፍ፣ በግፍ ሲረግፍና ሲገደል አንድ ጥይት ለመተኮስ እንኳን አልሞከሩም።

በወቅቱ ከእነርሱ ጋር የነበረ ሰው አለ፤ ኮሎኔል አበበ ገረሱ። እንደምንም ለዚህ ህዝብ እንድረስለት ብለው ሲጠይቃቸው፣ አይ ኢትዮጵያን ሶሪያ አናደርጋትም፣ ተኩስ እዛ ቢካሄድ ሶሪያ ነው የምትሆነው፤ ህብረተሰቡ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ በሰላማዊ መንገድ ቢታገል ነው የሚሻለው፤ ነው ያሉት። ታዲያ ትጥቅ፣ ተኩስና ግድያ ከዛ በኋላ ለምን አስፈለገ? የሚገድሉት ደግሞ እግር የቆረጠውን፤ ያኮላሸውን፤ ጥፍር የነቀለውንና ሌላም ግፍ ያደረሰውን አይደለም። ትናንት ይሄን ያደረገው ዛሬ የእነርሱ ወዳጅ ነው። አብረው ነው የሚሰሩት። እንደውም ሎጀስቲክስም ስትራቴጂም ከዛ ነው የሚቀበሉት። ስለዚህ ግንኙነታቸው ከድሮም ጀምሮ ያለ ነው።

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ማወቅ የሚገባው እና በተለይም የኦሮሞ ህዝብ ሊነቃበት የሚገባው የኦነግ ሸኔ ፕሮፖጋንዳ የኦሮሞ ህዝብ እንደ ጭራቅና ገዳይ እንዲታይ፤ እንደ ሰይጣን እንዲፈራ እና እንዲጠረጠር የሚያደርግ ፕሮፖጋንዳ ሲያደርግ ነበር። የኦሮሞ ህዝብ የተለየ ጥያቄ እንዳለው እና ኦሮሞ ከኢትዮጵያ የተለየ እንደሆነ እንጂ፤ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ያለ እና ተመሳሳይ ጥያቄና ችግር ነው ያለን፣ መፍትሄውም በጋራ ብንታገልና በጋራ ብንሰራ ነው የምናገኘው፤ የሚል አስተሳሰብ እንዲመጣ አይፈልግም። በዚህም ለምሳሌ፣ በኦሮሞና ሶማሌ ነዋሪዎች መካከል ትንሽ እንኳን የግጦሽ ሳር ግጭት ብትፈጠር የፍረጃ ወሬን በማጋጋል ኦሮሞና ሶማሌን የሚያቃቅር፤ በተመሳሳይ በሲዳማና ኦሮሞ አዋሳኝ ላይ ትንሽ ግጭት ቢፈጠር እሱኑ አጋግሎ በኦሮሞና ሲዳማ መካከል ትልቅ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረግ ስራቸው ነው።

ሌላው ቀርቶ ራሳቸው በፈጠሩት ግርግር በቤንሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ አካባቢዎች ጉዳት በደረሰ ጊዜ የሚጠቀሙት ቃላት ለሌሎች ማህበረሰቦች እጅግ ፀያፍ፤ የሚያበሳጭና ግጭትና ቁርሾን የሚያባብስም ነበር። እናም በዚህ ደረጃ ይሄን አቃፊ እና የኢትዮጵያ ትልቅ መሰረት የሆነውን ማህበረሰብ፤ ኢትዮጵያውያንን ወዶና አክብሮ አብሮ ኢትዮጵያን የመሰረተ እና ብሎም ለማሳደግና ለማሻገር የሚፈልገውን ማህበረሰብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዳይስማማ፤ እሱ ተስማምቶ እየኖረም እነርሱ በሚሰሩት የፕሮፖጋንዳ ሴራ ሌሎች እንዲጠራጠሩት እየሆነ ነው። ይሄን ማድረግ ደግሞ የህወሓት ባህሪ ሲሆን፤ ይህ በራሱ የህወሓትና ኦነግ ሸኔ ግንኙነት የት ድረስ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር በህወሓትና በጽንፈኛ ሃይሎች መካከል የታየው መናበብ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?

አቶ ታዬ፡- መናበቡ ከግድያው በኋላ ብቻ አይደለም። መናበቡ የጀመረው ከግድያው በፊት ነው። በትግል ስም እስር ቤት ገብተው ተገርፈውና መከራ አይተው የተፈቱ ሰዎች ራሳቸው፤ ህወሓት ምንም የሰራው ወንጀል የለም፤ በስህተት ነው ስሙን ስናጠፋ የነበረው ብለው ምስክርነት ሲሰጡ ተሰምቷል። ይሄን ማለታቸው ደግሞ ቀጥሎ ለሚመጣው ነገር መንገድ መጥረግ ነው። ህወሓት ዲሞክራትም እንዳልነበረ ፤ ህወሓት ህገ መንግስቱንም አንድም ቀን አክብሮ እንደማያውቅ፤ ህወሓት ፌዴራሊስትም እንዳልነበረ፤ እየታወቀ ፌዴራሊዝም እንፈልጋለን ብሎ መቀሌ መመላለስ የጀመሩት ከዛ በፊት ነው። ፌዴራሊዝም ከአዲስ አበባ ሸሽቶ መቀሌ ገብቷልና ፈልገን እናምጣው፤ ዴሞክራሲ እዛ ሄዷል ከዛ እናምጣው፤ ህገመንግስትም ተጥሷልና ከዛ እናምጣው ብለው እዛ ሲመላለሱ የነበረው ከዛ በፊት ነው።

እናም ግንኙነትና መናበቡ ከዛም ቀደም ብሎ ነው የተሰራውና የነበረው። ትብብራቸው ደግሞ ለውጡ ላይ ነው። ፍላጎታቸው እኛ አካባቢ ያለው የባንዳ ቡድንና ህወሓት እንደነገርኩህ ለማህበረሰቡ ምንም የያዙት ነገር የለም። ማህበረሰቡን ሊጠቀሙበት ሲሉ ብቻ ስሙን ያነሳሉ፤ እንጂ ፍላጎታቸው የግል ወይም የቡድን ጥቅም ብቻ ነው። ይሄንን ማንም ማወቅ ይችላል። ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ይገድላሉ፤ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ያጣላሉ፤ ህብረተሰቡ እንዲስማማ የሚያደርጉት ለዚህ ነው።

ህብረተሰቡ ደግሞ የሚጠቅመው አንድነት ነው። ህብረተሰቡ የሚጠቅመው መስማማት ነው። ህብረተሰብ የሚጠቅመው ሰላም ነው። እዚህ አካባቢ ያለው ኦነግ ሸኔም ሆነ ህወሓት እነዚህን ሁሉ ህዝቡ የሚፈልጋቸውን ነገሮች አይፈልጉም። ይህ መሰል ትስስራቸው ደግሞ ከድሮም የመጣ ነው፤ አሁን ግን ለውጡን በመቃረን ነው አብረው የቆሙት። ሁለቱም ይሄ ለውጥ መደናቀፍ አለበት፤ ለውጡ ከተሳካ እና በዚህ አገር ነጻነት ከሰፈነና ትግሉም የህዝቡ ሃሳብ ከሆነ እኛ ሃሳብ የለንምና ቦታ አይኖረንም የሚል እምነት አላቸው። ሃሳባቸው አንዳንዶቹ ከ150 በፊት የነበረ አስተሳሰብ ነው የያዙት። አንዳንዶቹ ደግሞ 1983 ላይ ተቸንክረው የቆሙ ናቸው። ዛሬ ያለንበትን እውነታ እና ወደፊት የምንሄድበትን አቅጣጫ ሊገነዘቡ የሚችሉ አይደሉም። ስለዚህ ይሄ ለውጥ ወደፊት መሄድ የለበትም የሚል አቋም ስላላቸው እዛ ላይ ነው የተናበቡት።

ግድያውንም በመናበብ ነው የፈጸሙት። ቅድም እንዳነሳሁት ሃጫሉ ባደረገው ቃለ መጠይቅ ውስጥ የተቆረጡ ሃሳቦችን ጠቅሻለሁ። ለምሳሌ፣ ህወሓትን የሚመለከተውን ኦ.ኤም.ኤን የቆረጠው ለምንድን ነው? ሃጫሉ ይገደላል፤ ሲገደል ህወሓት ያለቅሳል። ያ ሃሳብ ባይቆረጥ ግን የህወሓት ለቅሶ አያምርም፤ አይመስልምም። እንዲመስል ተብሎ መናበቡ ቀደም ተብሎ ነው የተጀመረው። የታሰበው ደግሞ ወይ ይሄ መንግስት መገልበጥ አለበት፤ ካልሆነ ኢትዮጵያ መበጥበጥ አለባት፤ ያ የሚሆነው ደግሞ በንጹሃን ደም፣ በተለይ ደግሞ በኦሮሞና በአማራ ወጣቶች እንዲሁም ማህበረሰብ እርስ በእርስ ተባልተው የሚመጣ ውጤት ይምጣ ነው። ሁለቱም እዛ ላይ ተስማምተው ነው የሰሩት።

ስለዚህ ሲሰሩም ተስማምተዋል፤ ከዛ በኋላም ነፍጠኛ ነው ብለው ፍሬም ሲያደርጉት ምርመራ ሊደረግ ቀርቶ ሳይታሰብ (እንዴት እንመርምር ሳይሆን ልጁን እናትርፍ በሚባልበት 30 ደቂቃ አካባቢ)፣ እንደውም ብዙዎች መሞቱን ባልሰሙበት ሰዓት) ነፍጠኛ ነው የገደለው የሚል አጀንዳ ይዘው ወጥተዋል። ይሄንንም ኦንላይንም የነበሩት ሆኑ ሚዲያ ላይ የነበሩት ቀደም ብለው ጥቁር ለብሰው ለለቅሶው ተዘጋጅተዋል። በዛው ወቅት ድርጊቱ ተፈጽሞ አንድና ሁለት ሰዓት ሳይሞላው ቃጠሎውም፤ ግድያውም ተጀምሯል። ይሄ ሁሉ አብረው ተናብበው የሰሩት ነው።

ቅድም እንዳልኩት ህብረተሰቡም ሆነ ወጣቱ ዝም ሲል ይሄን መንግስት ለመጣል የተለየ ስትራቴጂ እናመጣለን ብለዋል። ህወሓት ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ተጀምሮ አዲስ አበባ ላይ የሚያልቅ ጦርነት ደግሰናል አለ፤ ይሄን ያለውም ስዩም መስፍን ነው። ይሄ ቀደም ብለውም ሁለቱ ተናብበው የሰሩበት ነው ማለት ነው። ስለዚህ ህብረተሰባችን ይሄንን የጠላት ሴራ አውቆ ባያከሽፈው ኖሮ አይደለም ሌላው ቦታ ቢቀር እንኳን አዲስ አበባ ላይ ብቻ ይከሰት የነበረው እልቂት እጅግ በጣም አስከፊ ይሆን ነበር።

አዲስ ዘመን፡– .ኤም.ኤን እና ህወሓት የሚያስተዳድራቸው ሚዲያዎች ከግድያው በፊትም ሆነ ቦኋላ የሄዱባቸው መንገዶች ከግድያ ሴራው አንጻር እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ታዬ፡ መናበባቸው፣ አንደኛ የሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ይሄ ለውጥ እንደተቀለበሰ፤ የአንድ ሰው አገዛዝ እንደሆነ፤ አምባገነንነት እየተገነባ እንደሆነ በኦ.ኤም.ኤን የሚነገረውና በትግራይ ሚዲያ የሚነገረው የቋንቋ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ምንም ልዩነት አልነበረውም። እንደውም ህብረተሰቡም ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ የሚገባው ሃጫሉ ከመገደሉ በፊት ሁለትና ሶስት ቀን ቀደም ብሎ ነው በድምጸ ወያኔ የኦሮምኛ ፕሮግራም የተጀመረው። ይሄ በራሱ የሚያሳየው ነገር አለ።

በለውጡ ላይ አሃዳውያን መጥተዋል የሚለውን ዘመቻ ሁለቱም ይዘምቱበታል። ፌዴራሊዝም ፈርሷል የሚለውንም ቀደም ብለውም አብረው አዚሙውት ነበር። በዚህ ደግሞ ዲጂታል ወያኔን ማየት ትችላለህ፤ በተለይ ግልጽ መሆን ያለበት ኦሮሞና አማራ ሽኩቻ ውስጥ እንዲገቡና አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር ነው የሚሰሩት። ከግድያው በኋላም ቢሆን ልሳነ አማራ በሚል በተከፈተ የሀሰት (ፌክ) ፌስቡክ አማራ እንደገደለው በማድረግ፤ የገደለው አማራ ነው፤ እናም ምኒልክን የተተናኮለውን ሰርተንለታል፣ ወዘተ በሚል ጽፎ አውጥቷል። በዛው ደረጃ ያንን የሚመስል ስራ የሚሰሩ በፌስቡክ የሚሰሩ የተደራጁ የፕሮፖጋንዳ ሰዎች አሉ።

ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ግን አንዱ ለሌላው ምን እንደነበር ይታወቃል። ኦ.ኤም.ኤን አሸባሪ ነበር፤ የኦ.ኤም.ኤን ዳይሬክተር የነበረውም በሽብርተኝነት የተፈረጀና በዚሁ ተከስሶ በክስ ላይ የነበረ ነው። ዛሬ ደግሞ ፍቅሩ ከሚገባውና ከሚባለው በላይ ሞቋል። ይህ ፍቅርና ትብብር ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ዘመን ታግሎ ያመጣውን ለውጥ ማክሸፍ ላይ ስላተኮሩ ነው። በመሆኑም ከግድያው በፊትም ሆነ ከግድያው በኋላ በዚህ ላይ ነው የተስማሙት።

አዲስ ዘመን፡– በዚህ መልኩ አገር የማተራመሱን ስራ በበላይነት የግብጽ መንግስት እያስፈጸመ እንደሆነ ይነገራል፤ ይሄን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ማሳያዎቹ ይኖሩ ይሆን?

አቶ ታዬ፡ ሌሎች የሴኩሪቲ መረጃዎች እንዳሉ ሆነው፤ ማሳያ መሆን የሚችሉ አንድ ሁለት ጉዳዮችን መጥቀስ ይቻላል። በአንድ በኩል ይሄ ግድያ የተፈጸመው ኢትዮጵያና ግብጽ የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌት በሚመለከት ድርድር በሚያደርጉበት ቀን ማታ ነው። ይሄ ደግሞ በአጋጣሚ ነው የሆነው? የሚለውን ማየት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ግድያው ተፈጽሞ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን ባልሰሙበት ሁኔታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቲውተራቸው “ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በውስጥ ጉዳዮቿ ስለምትጠመድ የዓባይ ጉዳይን የምታነሳበት ሁኔታ የለም፤ ይህ ጉዳይም አሳሳቢም አይደለም፤” ብለዋል።

Related stories   የኢትዮዽያ የቁርጥ ቀን ልጅ "ስለአባይ እውነቱን እንካችሁ" – መካ አደም አሊ

ይህ ማለትስ ምን ማለት ነው? ትርጉሙስ ምንድን ነው? ሁኔታውን እንዴት አወቀ? መረጃውን በራሱ ምን ነው የሰጠው? አንድ ግለሰብ ሲሞት በዚህ ደረጃ አገር እስከመተራመስና እስከመፍረስ ይደርሳል ብሎ እንዴት አሰበ? ይሄን ትዊት ሲያደርጉም ቃጠሎም አልተጀመረም፤ ግድያም አልተጀመረም። ታዲያ ይሆናል ብሎ ያለው እንዴት ነው? ስለዚህ ይሄ የሚያሳየው ይሆናል ብለው ተነጋግረዋል፤ ስፖንሰርም አለው የሚለውን ነው። ጉዳዩ የተከሰተው የህዳሴ ግድቡን ለመሙላት ጫፍ ላይ በደረስንበት ጊዜ ነው። በእርግጥ ማንም ሊያቆመን እንደማይችል እነርሱም ያውቃሉ፤ ይሄን ደግሞ አይደለም ዛሬ ድሮም ያውቃሉ። ስለዚህ የሆነውን ነገር ከዚህ አንጻር ማየቱ ተገቢ ነው።

ከዛ በኋላ ድምጸ ወያኔ እና ትግራይ ቲቪ ከሆት በርድ ሳተላይት ሲወርዱ ወዲያውኑ ናይል ሳት ላይ ወጡ። በተመሳሳይ ኦ.ኤም.ኤን ከነበረበት ሳተላይት ወደ ናይል ሳይት አምጥቷል። ጂ.ኤን.ኤን (ገዳ ኒውስ ኔትዎርክ) የሚባል ጥላቻን፣ ግጭትን ጦርነትን እየሰበከ የሚውልና የሚያድር ቴሌቪዥን ግብጽ ላይ ነው ያለው። ፋይናንስ እየተደረገ ያለውም በእነርሱ ነው። ሌሎች ጉዳዮችም አሉ። እነዚህ ሁሉ ደግሞ በነጻ ነው ናይል ሳተላይትን ያገኙት። ያ ሳተላይት ደግሞ የግብጽ ነው። ታዲያ ይሄ ምን ማለት ነው?

በአንድ በኩል ኢትዮጵያውያንም እንደሚያውቁት የህዳሴ ግድብ ተሸጧል ብለው የአዞ እንባ ሲያነቡ ታያለህ። ሆኖም ለህዳሴው ግድብ ከድሃ መቀነት የተሰበሰበውን ገንዘብ ቆርጥመው የበሉት እነሱ ናቸው። ከአራትና አምስት ዓመት በፊት ማለቅ ሲገባው እንዲጓተት ያደረጉና የሸጡም እነሱ ነበሩ። ዛሬ ግን የለውጡ ኃይል ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ በሁለት ዓመት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ታይቷል። ውሃ ለመያዝ ደረጃም አብቅተናል። እናም ተሸጧል እያሉ በዚህ ደረጃ እያወሩ እዛ ግን ስራቸውን ይሰራሉ። የሚገርመው ግድቡ ተሸጧል የሚሉን በግብጽ ሳተላይት ላይ ሆነው መሆኑ ነው።

ስለዚህ ሶስቱ (በክልላችን ያለው ኦነግ ሸኔ እና ተያያዥ ባንዳዎች በአንድ በኩል፤ ህወሓት በሌላ በኩል፣ ግብጽ ደግሞ በሶስተኛ ደረጃ) ባላቸው ግንኙነት የተናበበ የጋራ እቅድ ይዘው ነው ያደረጉት። በዚህ ስምምነታቸውም እኛ አካባቢ ያለው ባንዳ የህወሓትንና የግብጽን አይረዳም፤ አልተረዱምም። እነሱ ድጋፍ ሲደረግላቸው ስልጣን ላይ ትወጣላችሁ ነው የተባሉት። እነዛ ደግሞ የያዙት (ምናልባት ህወሓት የእጅአዙር አገዛዝ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ መጥተው አታልለው ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ገርፎ ሊገዛ እንደማይችል ያውቁታል) ዋናው ግቡ ኢትዮጵያ የተዳከመች፤ ከተሳካ ደግሞ የፈራረሰች እንድትሆን ይፈልጋሉ። እነሱ የተነገራቸውም ስልጣን ላይ እናወጣሃለን፤ አንተ ትገዛለህ፤ ከዛ አብረን እንሰራለን የሚል ነው። በመሆኑም ቅንጅቱ በዚህ ልክ በማሳያዎች ተሳትፏቸው የሚገለጽ ነው።

አዲስ ዘመን፡– የሚዲያዎቹ ተናብቦ መስራት እና ከግድያው ቀድሞ ናይል ሳት ላይ መውጣት ከግድያው በፊት ለሚሰሩት ብቻ ሳይሆን በኋላም ሊመጣባቸው የሚችል ነገር እንዳለ ቀድመው እንዳሰቡ የሚያሳይ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ታዬ፡ ለዚህ በደንብ እንደተዘጋጁ ከኦ.ኤም.ኤን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እና ተቆርጠው የወጡት ዋና ዋና ሶስት ጉዳዮችና ሃሳቦች ያረጋግጣሉ። ኢንተርቪው የተደረገውና ለአንድ ሳምንትም ፕሮግራሙ አየር ላይ የቆየው ብዙ ሰው እንዲመለከተው እና ግድያው ሲሰማ በሁሉም ሰውጋ የታወቀ እንዲሆን ታስቦ ትልቁን እልቂትና ጭፍጨፋ ሊያስከትል በሚችል መልኩ ነው የታሰበው። አዲስ አበባ ላይ ጀምረን አዲስ አበባ ላይ እንጨርሳለን ሲሉኮ የሴራውን ትልቅነት ነው የሚያሳየው። በዚህ በኩል ባልደራስ በሚል የተደራጀው ሃይል ቤተክርስቲያን ሊቃጠል ነው፤ ቄሮ መጥቶ ሊያጠፋህ ነው፣ ተዘጋጅ ተብሎ መሳሪያም፣ ዱላም ገንዘብም ሲከፋፈል እንደነበር ይታወቃል።

እናም በዚህ በኩል የሚጠብቅ አለ፤ በዛ በኩል ደግሞ በስሜት የሚመጣ አለ፤ በዚህ መሃል የሚፈጠርና ራሳቸውም የሚፈጥሩት ሽብር ይኖራቸዋል። ከዚህ ትይዩ አስከሬን ከቤተሰብ በጉልበት ዘርፎ፣ ባለቤት ተወርውራ፣ አባት ተገፍትሮ ወድቆ፣ እናት ተገፍትራ ወድቃ አስከሬን ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ሲደረግ ለተጨማሪ እልቂት ነው። ኢንተርቪው ውስጥም “ከሞትክ ምን ትናዘዛለህ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለታል። ይሄን የ36 ዓመት ወጣት አርቲስት ምናልባት ብትሞት ምንድነው የምትናዘዘው ብሎ መጠየቅን ምን አመጣው? ቃለ ምልልሱን ጨርሶ ሲወጣም ወታደራዊ ሰላምታ ተሰጥቶት ነው የተሸኘው። ይሄም ተደርጎ የማይታወቅ በራሱ ሊታይ የሚገባው ጥቁምታ ነው።

እነዚህ ከግድያው በፊት የነበሩ መናበቦችና መቀናጀቶች የወለዳቸው ሚዲያውን የመጠቀሚያ አካሄዶች ናቸው። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ከግድያው በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ማለፍ እንዲቻል ቀድመው መዘጋጀታቸውን የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ፣ ኦ.ኤም.ኤን ወደ አገር ውስጥ ሲገባ የውጪ ስቱዲዮውን ዘግቶ ነበር። ከግድያው ጋር ተያይዞ ባሉ ሂደቶች በላይቭ (ቀጥታ ስርጭት) ጦርነትን በመስበክ፤ የተጀመረው ተቃውሞ በሁሉም አካባቢዎች እንዲቀጥልና ህዝብ በብዛት ወጥቶ ቁጣውን እንዲገልጽ እውነቱን የማዛባት ስራ ሰራ። ይሄን ጊዜ መንግስት ጣቢያውን ተቆጣጠረው። ወዲያውኑ ውጭ ያለው ጣቢያ ተመሳሳይ ስራ ጀመረ። ታዲያ ተዘግቶ የነበረው ውጭ ያለው ማሰራጫ ጣቢያ መቼ ነው የተከፈተው? ይሄኛው እንደሚዘጋ እንዴት አውቀው ያንን ከፈቱ? ይሄ ቀድመው እንደተዘጋጁበት ግልጽ ነው።

በተመሳሳይ ድምጸ ወያኔ ቀድሞ ተዘጋጅቶ ስለነበረ ማታ ከሆት በርድ ወርዶ ጠዋት በናይል ሳት ላይ ወጣ። ኦ.ኤም.ኤንም ቀደም ብሎ በግብጽ ናይል ሳት ላይ ዝግጅት ነበረው። ይህ ዝግጅታቸው ደግሞ የተጀመረውን ኹከት ለማቀጣጠልና ለማስቀጠል ሲሆን፤ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ቢኖሩ እንኳን ቀጥሎ ምን አማራጭ ይኖረናል በሚለው ጉዳይ ላይ በደንብ አስበው የገቡበት ስለሆነ ነው። ይህ በግልጽ መታወቅ ያለበት ሲሆን፤ ሳተላይቱን በነጻ ማግኘታቸውም የዚሁ ማረጋገጫ ነው። ለሳተላይት ብቻ ሳይሆን ለግድያውም የሚውል ገንዘብ እንዳለ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- ከግድያውን ተከትሎ እንዲፈጠር ከታሰበው አንጻር ከግድያው በኋላ የተከሰውን ሁከትና ግርግር የዘርና የሃይማኖት ቅርጽ ለማስያዝ የተደረጉ ጥረቶችን ተከትሎ ያስከፈለውን ዋጋ እንዴት ያዩታል?

አቶ ታዬ፡- ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በኹከቱ በሰውም በንብረትም ላይ ጉዳት ደርሷል። በዋናነት 167 ሰው ህይወት ጠፍቷል። ወደ 800 የሚሆኑ ዜጎችም ቀላልና ከባድ ቁስለት ደርሶባቸዋል። 500 ያህል የዜጎች መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ከ95 በላይ ሆቴሎች፣ እንዲሁም ፋብሪካዎችና ተሽከርካሪዎችም ተቃጥለዋል። ሂደቱ በሃይማኖቶች መካከልም ግጭትና መሻከሮች ተፈጥረው ግጭት እንዲቀሰቀስ የሚያደርግ ስሌትም ነበረበት። በተመሳሳይ በብሔር ችግር ለመፍጠር የታሰበ ስሌትም ነበር። ይሄ ትልቅ ኪሳራ ነው። የሆነውም በሴራ ነው። ግን ደግሞ ከታሰበው አንጻር ሲታይ ከሽፏል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የታሰበው በ100 ሺዎች ነው። እናም ያለው የፀጥታ ሃይልም፤ ህብረተሰቡም ተረባርቦ በዚህ ደረጃ መግታት መቻላችን ትልቅ ስኬት ነው። አገርን እንዳልነበረችና ኢትዮጵያም የሩዋንዳና የሶሪያ አይነት እጣ ፈንታን እንዲደርሳት የማድረግ ሴራ ነው የተሸረበው። ይሄ ሁሉ ግን በነበር ቀርቷል።

የአንድም ዜጋ ህይወት ሲያልፍ ማየት በጣም ያሳዝናል። ግን ደግሞ አገር ላይ ሊደርስ ከነበረው አደጋ አንጻር ሲታይ በቀላሉ አምልጠናል ማለት ነው። ምክንያቱም ንብረት ብቻ ሳይሆን አገር ባጠቃላይ እንዲቃጠል ነው። በተለይ አዲስ አበባ ላይ የታሰበው ስሌት ሊሳካ አልቻለም እንጂ፤ አስከሬኑን ለአስር ቀን እዚህ እንዲሆን ማቀዳቸው በሂደቱ ማን ገደለው በሚል የጥላቻ ፖለቲካ በመስበክና በመዘመር በአስረኛው ቀን ከየአካባቢው የሚመጣውን ማህበረሰብ በመጠቀም የጥፋት ስራቸውን ለመፈጸም ነበር። በዚህ ሂደት ደግሞ እዚሁ ውስጥ ተቃራኒ ሆኖ የሚቆም ይኖራል፤ በዛ መሃል የሚፈጠረው እልቂትና ቃጠሎ በሂሳባቸው በጣም ከባድ ነበር። ያሁሉ ሴራ ግን በነበረበት ነው ደርቆ የቀረው። ይሄን ያደረገው ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሆን፤ ይሄን ላደረገው የኢትዮጵያ ህዝብም በግሌም እጅግ የከበረ ምስጋና ላቀርብለት እወዳለሁ።

አዲስ ዘመን፡– የኦሮሞ ህዝብ የሚታወቀው በአቃፊነቱ ነው። ይሁን እንጂ ኦሮሞ አገር ማፍረስ እንጂ አገር መገንባት አይችልም ከሚለው የህወሓት ካድሬዎች ትርክት አንጻር የሚታይ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በክልሉ በሚስተዋሉ የሰላምና ፀጥታ ችግሮች ምክንያት የኦሮሞ ህዝብ አቃፊነቱ እየተሸረሸረ አፈናቃይና ለሀገር አንድነት ስጋት ወደመሆን እየሄደ ነው የሚያስብሉ ተግባራት እየታዩ መሆናቸው ይነገራል። እርሶ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ታዬ፡ በህወሓት በኩል “የኦሮሞ ህዝብ አገር ያፈርሳል፤ ሊመራም አይችልም፤” የሚል ብሂል ነበረ። ህወሓት ሁሉንም ለማሸማቀቅ ነው የሚሰራው። ለአማራም የሚሰጠው ፕሮፖጋንዳ አለው፤ ለኦሮሞም የሚሰጠው ፕሮፖጋንዳ አለው። አማራን ትምክህተኛ ብሏል፤ ኦሮሞን ጠባብ ብሏል። ትምክህተኝነት ማለት ግን ከእኔ በላይ የለም እኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ ነው፤ በእርግጥ ያንን ይል የነበረውና እንደዛ አይነት ባህሪ የነበረው ራሱ ህወሓት ነበር። ጀግና እኛ ነን፤ አዋቂ እኛ ነን፤ ሁሉ ነገር እኛ ነን የሚሉ እነሱ ነበሩ።

በሌላ በኩል ደግሞ ጠባብ ማለት አንድ ነገር የእኔ ብቻ ነው፤ ሌላው ወደ እኔ መምጣት የለበትም፤ የሆነን ነገር ለብቻዬ ልያዝ፤ እኔ ብቻ፣ እኛ ብቻ የሚል አስተሳሰብ ነው። ይሄ የበላይነት ስሜት ሳይሆን የተጎጂነት ስሜት የሚንጸባረቅበትም ነው። በዚህ ረገድም ንግዱንም የተቆጣጠረው፤ ሚዲያውንም የተቆጣጠረው፤ ስልጣኑንም የተቆጣጠረው፤ ሁሉ ነገር የእኔ ብቻ ብሎ ሌላውን የገፋው በጠባብነት ነገሮችን ተቆጣጥሮ የያዘ ራሱ ህወሓት ነው። በመሆኑም ጠባብነትም፣ ትምክህተኝነትም የነበረው በራሱ በህወሓት ውስጥ ነው።

ከዚህ አንጻር ኦሮሞ አገር ያፈርሳል ሲል፤ ኢትዮጵያን የሚወዳት በጣም ብዙ ማህበረሰብ እንደመኖሩ ይህ ማህበረሰብ ኦሮሞን እንደ ጭራቅ እንዲያይ ለማድረግ ነው። ሌላው ህዝብ ኦሮሞን እንዲፈራውና ኦሮሞ ፎቢያ እንዲይዘው ለማድረግ ነው። ምናልባትም አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ይሄ ፎቢያ ሰርቶላቸዋል። ያ ከተባለና ከተደረገ በኋላ ከኦሮሞ ጋር ጓደኝነት መሆን፤ ለኦሮሞ ቤት ማከራየት ጭምር ስጋት እንዲሆን ተሰርቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ አማራ ቢመጣ ቋንቋ አይኖርህም፤ ትሰደባለህ፤ ባህልህ ይጠፋል፤ ስምና ማንነትህ ይሰረዛል፤ የሚል ፕሮፖጋንዳ ሰርቷል። በዚህ መልኩ ማን ቢመጣ ምን እንደሚል አለው። ስለዚህ ኦሮሞ አገር ያፈርሳል የሚለውም ኦሮሞ አቃፊ አይደለም፤ ኦሮሞ አጥፊ ነው፤ ገዳይ ነው፤ የሚለውንና ከዚህ በፊት የነበረውን ትርክት እውን ለማድረግ ነው ይሄን ሴራ የፈጸመው። የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ ያኔም በመከራ ውስጥ ሆኖ እንኳን የአንድም ሰው ህይወት፤ የአንድም ሰው ንብረት አላጠፋም።

በዛን ወቅት አምስት ሺህ ወጣት ሲሰዋ፤ በአንድ ቀን 600 እና 700 ሰው ገደማ በኢሬቻ በዓል ላይ ገደል ውስጥ ገብቶ ሲሞት፤ ከዛ ወጥቶ የመንግስትና ከመንግስት ጋር የሚያያዙ ነገሮች ላይ ጥቃት አደረገ እንጂ፤ አንዱንም በብሔሩ፣ አንዱንም በሃይማኖቱ አላጠቃም። ሌላው ቀርቶ አብዲ ኢሌ እና ህወሓት ተመሳጥረው ከሶማሌ ኦሮሞዎችን አፈናቅለውና ገድለው ከዛ ሲያባርሩ፤ ኦሮሚያ ውስጥ ለነበረው ሶማሌ የኦሮሚያ ህዝብ ጥበቃ ነው ያደረገለት።

አሁን እየሆነ ያለውም ቀደም ብለው የዘራፊ ቡድን ተዘጋጅቶ ቅድም እንዳነሳሁልህ የኦሮሞ ማንነት ላይ ጥላሸት በመቀባት የኦሮሞ ማንነት እንዲጎድፍና እንዲጠለሽ፤ ኦሮሞነትን ሰው እንዲፈራው ሆን ተብሎ በህወሓት ሴራና በባንዳዎች ፈጻሚነት የሆነ ነው እንጂ፤ ይሄ የኦሮሞን ህዝብ ማንነት አይገልጽም። ይሄ የኦሮሞን ህዝብ ማንነት ቢገልጽ ኖሮ አደጋው ቅድም በጠቀስነው ልክ ሊቀር አይችልም። ለምሳሌ፣ የሞተው 167 ሰው ነው፤ ይህ ብዙ ነው። ግን ደግሞ ኦሮሚያ ውስጥ እየኖረ ያለው ከኦሮሞ ውጪ ያለው ማህበረሰብ ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ነው።

ከዚህ አንጻር ይሄንን የኦሮሞ ህዝብ ስዕል አድርጎ መሳል ልክ አይደለም። ኦሮሞ አገር ይገነባል፤ ኦሮሞ በአገር ግንባታ ውስጥ ከዚህ በፊትም ከወንድሞቹ ጋር ዋጋ ከፍሎ ተሳትፏል። ስለዚህ ይሄ የሚባለው ትርክት ኦሮሞን አይገልጽም፤ ውሸት የውሸት ትርክት ነው። የተፈጠረው ችግር ግን ሆን ተብሎ ተሰልቶ በዚህ ደረጃ ሲተረክ የነበረውን ተረክ እውነት ለማስመሰል የተሰራ ሴራ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን፡– የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንጻር መንግስት እያሳየ የነበረው መለሳለስ ሀገርን ዋጋ ስለማስከፈሉ ይነገራል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ታዬ፡ የህግ የበላይነት ለሁሉም ጉዳዮች መሰረት መሆኑ ይታወቃል። የሕግ የበላይነት ከሌለ እናስቀጥለዋለን የምንለው ይሄ ለውጥ ወደፊት ሊሄድ አይችልም። የሰፋው የዴሞክራሲ ምህዳር በመንግስት በኩል ቢለቀቅም፤ በጉልበተኞች በኩል ደግሞ ለምን መንግስትን ደገፋችሁ በሚል ሲፈነጩ ይታያል። ለምን እገሌን ደገፋችሁ፣ ለምን የእኔን አስተያየት ተቃወማችሁ፣ ተቻችሁ፤ በሚል ጉልበተኞች የሰው ህይወት ሊያጠፉ ይችላሉ፤ የሰውን ክብር ሊደፍሩ ይችላሉ። እየደፈሩም አሳይተውናል። ስለዚህ ነጻነትም ሊኖር የሚችለው፣ ፍትህም ሊረጋገጥ የሚችለው፤ የምንፈልገው ልማትም ብልጽግናም ሊመጣ የሚችለው የህግ የበላይነት ሲኖርና ሲኖር ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት።

ከዚህ አንጻር መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ተቋማትን እየገነባ ነው የመጣው። ምክንያቱም ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ ካደረሳቸው በደሎች ትልቁና አንደኛው ተቋማትን ማፍረስ ስለነበር ነው። ትምህርት ቤት ትምህርት ቤት እንዳይሆን፤ ፖሊስ ፖሊስ እንዳይሆን፤ ፍርድ ቤት ፍርድ ቤት እንዳይሆን፤ በሁሉም ሙስና እንዲገባ፤ በሁሉም የተዳከመ አቅም እዛ ውስጥ እንዲሰባሰብ ነው ያደረገው። ከዚህ ባለፈም መከላከያ መከላከያ እንዳይሆን እዛም ውስጥ በብሔርና በሌሎች የተለያዩ ነገሮች አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር፤ የሀገር ፍቅር እዲዳከም፣ እንዲሟሽሽና እንዲሞት ነው የሰራው። በዚህ ረገድ ትልቅ ኪሳራ ነው የደረሰው።

ስለዚህ ይሄ የለውጥ መንግስት ወደስልጣን ሲመጣ እነዚህን ተቋማት ነው የተረከበው። በእነዚህ ተቋማት ምንም ለውጥ ሳያደርግ፤ በስልጠናም ለውጥ ሳያመጣ እና በሰው ደረጃም ሪፎርም ሳያደርግ በቀጥታ ህግን ማስከበር ይችል ነበር ወይስ እንዴት ነው ሲባል፤ እንደውም እነዛ ተቋማት ይዞ ችግሩን መሻገር በቻሉ በራሱ ትልቅ ስኬት መሆኑ መታወቅ አለበት። ምክንያቱም በመጀመሪያው ሰኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ቦምብ ሲወረወር ቅንጅት የተደረገው ከዛው ከጸጥታ ተቋማት ውስጥ ነው ሁሉ ነገር የተመቻቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ደመወዝ እንቀበላለን ብለው ተሰብስበው ወደዛ የሄዱት የመከላከያ አባላት መኖራቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቃል። ያን ሲያደርጉ ምን ለማድረግ ነው? እናም እነዛን የመሰሉ ተቋም ይዞና እንደገና ሪፎርም አድርጎ የአገር ፍቅር እዛ ውስጥ ገንብቶ መሄድ ያስፈልግ ነበር።

ለምሳሌ፣ ከለውጡ በፊት የአገር ኩራት የሆነው የመከላከያ ሰራዊቱ የነበረው ገጽታ ይታወቃል። መከላከያ መጣ፤ ፌዴራል ፖሊስ መጣ ሲባል ሁሉም ይፈራቸው ነበር። እናም የፍርሃት ምንጭ ነው የነበረው። አሁን ግን ያ ገጽታ ተቀይሮ የጸጥታ ተቋማት ችግር በነበረበት ህብረተሰቡ እየወደደና እየፈለጋቸው ይምጡልን እያለ እየጠራቸው ነው። እነርሱም ራሳቸውን ለህብረተሰቡ እየሰጡ ሰላም ማስከበር ጀምረዋል። ከዛ በፊት ግን አይችሉም ነበር። ለምሳሌ፣ ኦሮሚያ ክልል አዲስ የሰለጠነ ልዩ ኃይል ነበር። ካለው አጠቃላይ ሁኔታ ሪፎርሙ ሳይደረግ በፊትና ይሄንን ሃይል በበቂ ማሰማራት ሳይቻል የበፊቱን ሥነልቡናና አቅም ይዘው ከስድስትና ሰባት ወር በፊት የአሁኑ አይነት አደጋ ቢገጥመን ኢትዮጵያ ትተርፍ ነበር ወይ የሚለውም ማየት ጥሩ ነው?

ምክንያቱም ከስድስትና ሰባት ወር በፊት እንዲህ አይነት ሴራ ተሸርቦ ተሰርቶ ቢሆን፤ የሲቪል ኃይሎ ውዥንብር ውስጥ በነበረበት እና የጸጥታ ተቋሙም ሪፎርም በሚያስፈልግበት ሁኔታ በዚህ ደረጃ ይሄ አደጋ ቢከሰት ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ሊጤን ያስፈልጋል። ፈጣሪም ረድቶን አሁን ላይ ሙሉ ቁመና መጥቷል። ህግ ማስከበርም ተችሏል። ከዚህ በፊት ግን ምን ማድረግ እንችል ነበር? ለውጥና ሪፎርም ሳይደረግ ምን ይዘን? በሰባራ ዱላስ ምን ማድረግ ይቻለን ነበር? ችግር ነው።

ስለዚህ ዋጋ ከፍለናል። ይሄ የከፈልነው ዋጋ ደግሞ ቀላል አይደለም፤ ከባድ ነው። ነገር ግን ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር እና ከተሰራው ሴራ አንጻር ልንከፍል የነበረው ዋጋ ከዚህ እጅግ የከፋ ነበር። ዋጋውንም ከፍለን ላንተርፍም እንችል ነበር። እናም በዚህ ደረጃ ማየቱ ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ጋር ተያይዞ ከለውጡ በኋላም ቢሆን የክልሉ መንግስት በርካታ ልዩ ኃይሎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ አስገብቷል። እነዚህስ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥም ሆነ በቅርቡ የተፈጠረውን ችግር ቀድሞ መከላከል ለምን አልቻሉም?

አቶ ታዬ፡ በዚህ ረገድ ይሄ ታላቅ አርቲስት የመሞቱ ወሬ ሲሰማ የልጁ ፍቅር በውስጡ የሌለ ስላልነበረ በዛ ቅጽበት የጸጥታ ሃይሉም ሆነ እኔን ጨምሮ አጠቃላይ ህብረተሰቡ ያልደነገጠ አልነበረም። እነዛ ግን እንደሚሞት አውቀው ጥፋት ለማጥፋት ተዘጋጅተዋል። ይሄንን ተከትሎም በወቅቱ ያን አይነት ነገር ይፈጠራል ብሎ የገመተም የለም። ይሄንን ማየት አንድ ነገር ነው። ከዛ ባለፈ ግን እነሱ ያቀዱት በትልቅ የጥፋት ደረጃ ከመሆኑ አንጻር ያ ችግር እንዳይደርስና በአጭር እንዲገታ ከማድረግ አኳያ፤ የቀድሞውም ሆነ አዲሱ ልዩ ኃይል ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ባይሰራ ኖሮ ችግሩ የሚፈጥረው ጉዳት ከዚህም የከፋ ይሆን ነበር።

ይሁን እንጂ በአንድ አንድ አካባቢዎች ላይ ደግሞ በዚህ ጉዳይ የተሳተፉ የጸጥታ ሃይሎችና አመራሮችም ነበሩ። በዚህ ደረጃም 20 ፖሊሶች እና 40 አመራር እንዲሁም በታችኛው ደረጃ ደግሞ ሌሎችም ነበሩበት። ምክንያቱም ሲሰራ የነበረው የጥላቻ ሰበካ እውነት እየመሰላቸው የብዙ ሰዎችን ስሜት ወስዷል፤ ገዝቷልም። ነፍጠኛ እየመጣ ነው፤ አሃዳውያን እየመጡ ነው፤ የሚል ዲስኩር በየቀኑ አለ። ብዙ ሰው ደግሞ ይሄንን በጥልቀት መርምሮ ከመመዘን አንጻር ችግር አለ። እናም በዛ ማዕበል የተወሰደ አለ ማለት ነው። ይህ የተወሰነ ነው። ለምሳሌ፣ ጠመንጃም የሰጠ አካባቢ አለ። እንዲህ አይነቶች ጥቂት ቢሆኑም ፤ ይሄን አደጋ ሊቀለበስ የቻለው ይሄ ኃይል ስለነበረ ነው። ይሄ ሃይል ባይኖርና ችግሩ ከሰባትና ስምንት ወር ቢፊት ተከስቶ ቢሆን አደጋው መያዣ መጨበጫ የሚያሳጣን ሆኖ ጥፋቱም የከፋ ይሆን ነበር የምልህም ለዚሁ ነው።

አዲስ ዘመን፡– አሁን ላይ እንደ አገር የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ ከመሆናችን አንጻር እግራቸውን በአግባቡ መሬት ላይ ያላሳረፉ ፖለቲከኞች መንግስትን ዋጋ እያስከፈሉት እንደሆነ ይነገራል። ከዚህ አንጻር የኦሮሚያ የብልጽግና ፓርቲ ቁመና እንዴት ይገለጻል?

Related stories   “የግድቡ ግንባታ ውሃ ይቀንስብኛል የሚለው የግብጽ ጩኸት የማጭበርበሪያና የተለመደ የሃሰት ክስ ነው››

አቶ ታዬ፡ አሁን ከደረሰው አደጋ አንጻር የተቀመጠው አቅጣጫ በቀጥታ ጠላት ሆኖ አገር ለማፍረስ ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር የወገኑ አሉ። እነዛ በወንጀላቸው ልክ የብልጽግናም ሆኑ ከብልጽግና ውጪ ለህግ ይቀርባሉ፤ ይጠየቃሉም። ከደረሰው ጉዳት አንጻርም፤ የህግ የበላይነት ከማስፈንም አንጻር ከራሳችን እንጀምራለን፤ የህግ የበላይነትም ይረጋገጥባቸዋል። መሃል ሰፋሪ ሆነው ደግሞ አደጋን ማስቀረት እየቻሉ ወይ በቸልተኝነት፤ ወይም ደግሞ ይሄ መንግስት ቢወድቅ በሌላኛው ላይ ታሳቢ በማድረግ በዛ ደረጃ ሁለት ልብ በሆኑትም የፖለቲካ እርምጃ ተወስዶ ወደሚገባቸው ቦታ ይሄዳሉ ማለት ነው። ተቀላቅለን አንድ ላይ አንሄድም።

ብልጽግና ደግሞ የያዛቸው እሴቶች አሉ። አንደኛው ህብረ ብሔራዊነት ሲሆን፤ ብዝሃነትን ያከበረ ብሔራዊ አንድነትን በመፍጠር ውስጥ አንድነቷ የጠነከረ ኢትዮጵያን መገንባት ነው። ሌላኛው ደግሞ፣ ነጻነትና የዜጎች ክብር ነው። በመሆኑም ብልጽግና በዛ ደረጃ እሴቶች ያሉት እንደመሆኑ፤ ፖለቲካ ሲሰራ እነዛን እያየ ነው። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በዚህ መሰረት ላይ ሆኖ ነው። ማህበራዊ ስራዎችን ሲሰራም ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም በዚሁ ስሌት ነው የሚሄደው። ይሄንን አምኖ ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን፤ ለሁሉም ሃይማኖቶች የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚሰራ ካለ እሱ ብልጽግና ነው። በሁሉም ክልል ሊሆን ይችላል በዚህ ደረጃ እንሄዳለን። ከዚህ ውጪ የሆነ ደግሞ የራሱን ቦታ ፈልጎ ይሄዳል። እናም ውስጣችንን አጥርተን በዚህ ደረጃ ነው የምንቀሳቀሰው።

አዲስ ዘመን፡– ብልጽግና ፓርቲ እንደ አገራዊ ፓርቲ በፖለቲካ መዋቅሩ ላይ ጠንካራ ስራ ባለመስራቱ የተፈጠሩ ክፍተቶች ለጽንፈኛ ሃይሎች እድል ፈጥሯል፤ ይህም ፓርቲው ገዢ ፓርቲ ከመሆኑ አንጻር ችግሩ ከራሱ አልፎ አገርን ዋጋ እያስከፈለ ነው። ይህንን እንዴት ይገመግሙታልችግሩን ለመፍታት እየተደረገ ያለ ስራ ካለስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ታዬ፡ በፖለቲካ መዋቅሩ ላይ በጣም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። ያ ስራ ባይሰራ ኖሮ በዚህ ደረጃ ኢትዮጵያ ትልቅ የአደጋ ድግስ ተደግሶባት መትረፍ አትችልም ነበር። ኦሮሚያ ላይ የሆነውእኮ ኦሮሚያ ላይ እንዲቀር አይደለም። ተመሳሳይ ጉዳይ በደቡብ ክልል፤ ተመሳሳይ ጉዳይ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሌሎችም ክክሎች በነጋታው እንዲከሰት ተብሎ ነው። ኦሮሚያም እኮ ችግር የተከሰተበት የተወሰነ አካባቢ ነው። አጠቃላይ ይሄንን ሰፊውን ኦሮሚያ በዛ ተመሳሳይ እሳት ለማቃጠል ነው ጠላት ያቀደው።

ስለዚህ የፖለቲካ ስራችን ከፓርቲያችንም አልፎ የማህበረሰቡንም አመለካከትና አስተሳሰብ ባይገዛው ኖሮ ይሄ የምንለው ህብረ ብሔራዊነት፤ ይሄ የምንለው የኢትዮጵያ አንድነት፤ ይሄ የምንለው የብልጽግና አቅጣጫ እና የያዝነው የመደመር መንገድ ህብረተሰቡ ዘንድ ባይደርስና ገዢ ባይኖር ኖሮ ይህ ክስተት በዛ ልክ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ልንቆጣጠረው አንችልም ነበር። ከዚህ አንጻር ሲታይ በርካታ ስራዎች ሰርተናል። የሚቀሩን ስራዎች ግን የሉም ማለት አይደለም።

ምክንያቱም እያካሄድን ያለነው አብዮት አይደለም። ሁሉንም ነገር አንድ ጊዜ ጠርገን ጥለን አዲስ ነገር አምጥተን እየተከልን አይደለም። የነበረውን እያሻሻልንና አዳዲስ ነገሮችን እየጨመርን፤ ደካማ የሆኑትን እያወጣን በዛ ደረጃ እያስማማን መታደስ /የሪፎርም/ ስራ እየሰራን ነው። በመሆኑም ከዚህ አንጻር ሲታይ እጅግ የተሳካ የፖለቲካ ስራ ሰርተናል። እጅግ የተሳካ የፀጥታ ስራም ሰርተናል ማለት እንችላለን።

ይሄን የምንለካው በተፈጸመው ጉዳት ብቻ አይደለም። በታቀደው እቅድና ከዚህ በፊት ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር ነው። ህዝብ እንደ ህዝብ ሌላው ላይ እንዲነሳ ለረዥም ዘመን ከተሰበከው የጥላቻ ስብከት አንጻር ነው። ጎሳ በጎሳ ላይ፤ ሃይማኖት በሃይማኖት ላይ እንዲነሳሳ በሚዲያ ጭምር ውስጥ ለውስጥ ሲሰራ ከነበረው፤ እንዲሁም ሆን ተብሎ ተቋማት እንዲዳከሙና ትውልድም እንዲበላሽ ሲሰራ ከነበረው ሴራ አንጻር ስናስበው የሰራነው ስራ እጅግ የተሳካ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን።

አዲስ ዘመን፡– በክልሉ የሚገኑ አንዳንድ ባለሀብቶች ለህዝ የልማት ተስፋ ከመሆን ይልቅ የሰላሙ ጠር እየሆኑ፤ በገንዘባቸው የጥፋት ሃይሎችን እስከ መደገፍ የዘለቀ ተግባራትን እያከናወኑ፤ ከዛም ባለፈ እራሳቸውን እንደ መንግስት ለማየት የሚዳዳቸው እንዳሉ ይነገራል። ይህ በተጨባጭ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ታዬ፡ በዚህ ደረጃ የሚነሱ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ። ያው አክቲቪስትም እኔ መንግስት ነኝ ይላል፤ አንዳንዴም የተወሰነ ገንዘብ በዘረፋና በመሬት ሽያጭ ያከማቸም ባለሀብት ነኝ፤ ከዚህ በኋላ እኔ ነኝ የምሾመው፤ እኔ ነኝ የምሽረው ማለት አለ። ኦዲፒ ላይ የዛሬ ዓመት (2011) በማዕከላዊ ጽህፈት ቤት በሚደረጉ የሃላፊነት ድልድል ስራዎች ላይ ጭምር እጅ አስረዝሞ በመግባት ይሄ ሰው ይነሳ፤ ይሄ ይቀመጥ ለማለት ይጥሩ ነበር። ለምሳሌ፣ ማነው የጽህፈት ቤት ሃላፊ መሆን ያለበት፤ ማነው ከንቲባ መሆን ያለበት፤ ማነው የወረዳ አስተዳዳሪ መሆን ያለበት፤ ወዘተ በሚል በከፍተኛ ደረጃ ሳይሆን ታች ድረስ በዛ ደረጃ ማሾምና ማሻር የሚፈልጉ ኃይሎች ነበሩ።

ከዚህ አንጻር በክልላችን ይሄ መንግስት በሶስት ወር ከስልጣን ይወርዳል ተብሎም ተሰብኳል። እናም ይሄ እውነት የመሰላቸው የእነዛን የድል ማግስት አርበኞች የውሸት ትርክት አምነው ገንዘባቸውን አፍስሰው ነበር። በእነርሱ እቅድና እይታ ቢሆን ኖሮ በተለይ ሃጫሉ ላይ በተሰራ ሴራ ይሄ መንግስት የለም። እናም በውስጥ መስመራቸው ይሄ መንግስት የለምና ከሰኔ በኋላ በዚህ ደረጃ ስሩ፤ ለእኛም ድጋፍ አድርጉልን ብለው ብዙዎችን አታለዋል። ተታልለው የተያዙ ጥቂቶችም አሉ። ደግሞ እዛ ውስጥ ያልተሳተፉ በእውነትና ሀቀኝነት ሰርተው ራሳቸውንም አገራቸውንም ክልላቸውንም የሚያግዙ ጥሩ ባለሀብቶችም አሉ። እናም አቅጣጫው ግልጽ ነው። ህግ ደግሞ በሁሉም ላይ እኩል ነው የሚሰራው። ለህግ ትንሽና ትልቅ የለም። ባለሀብትና ደሃም የለም። ሁሉም ህግ አክብሮ ይሰራል፤ ህግ የጣሰ ይቀጣል። ከዚህ በኋላ ይሄ ግልጽ ነው።

አዲስ ዘመን፡– የአሁኑን ኹከትና ግርግር ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ለህዝብ የላቀ ተጠቃሚነትና ለለውጡም መዝለቅ አጋር ሆነው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ባለሀብቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው በስፋት ይነገራል። ይሄን ምን ያክል ገምግማችሁታልበቀጣይ የእነዚህ ባለሀብቶች ደህንነት እንዲጠበቅም ሆነ ሌሎች ባለሀብቶች መተማመን እንዲፈጥሩ ለማድረግ ምን የታሰበ ነገር አለ?

አቶ ታዬ፡ ከመንግስት ጋር ተባብረው የሚሰሩ ባለሀብቶችን መንግስትን ባይደግፉ እንኳን ገለልተኛ ሆነው ስራቸውን ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ባለሀብቶችን ማሸማቀቅ፣ ማስፈራራት እንደነበረ ይታወቃል። አክቲቪስቶች ግብርም ሲጠይቁ እንደነበረ እናውቃለን። ግብር ካልከፈላችሁ ቄሮን እንልካለን ሲሉ እንደነበረ ይታወቃል። ግር ግር በተነሳ ጊዜ ደግሞ እነሱ የሚደሰኩሩትን ዲስኩር አምነው የሚደግፏቸው ካልሆነ በስተቀር፤ በትክክል ግብር ከፍለው ስራቸውን በአግባቡ የሚከውኑና ለአገራቸው የሚሰሩ ባለሀብቶችንና ንብረታቸውን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ማድረጋቸው ይታወቃል።

ያ ደግሞ አጠቃላይ ከነበርንበት ሁኔታ ጋር ይያያዛል። ምክንያቱም የህግ የበላይነት በአግባቡ አልተከበረም። ከዚህ በፊት በነበረው እንደሚታወቀው ተቃዋሚን የሚደግፈው ሰዉ ተደብቆ ነው። ምክንያቱም የነበረው ሥርዓት አፋኝ ስለነበረ የሚቃወሙትን ሁሉ ያስርና ያሳድድ ስለነበረ ነው። አሁን ግን መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ሲያሰፋ የተገላቢጦሽ ነው የመጣው። መንግስትን የሚደግፍ ሰው እንዲፈራ ነው የተደረገው። ብልጽግናን የሚደግፍ ሰው በቀበሌው እንዲፈራና እንዲሰጋ፤ በከተማው፣ በወረዳውና በዞኑ እንዲሰጋ ነው የተደረገው።

ስለዚህ የተሰጠው ነጻነት ድንበሩ ተዘሎ የሌላውን ነጻነት እስከመግፈፍ ነው የደረሰው። ይሄ ደግሞ የሚስተካከለው በአንድ በኩል የህግ የበላይነትን በማስፈን ነው። ማንም ሰው የራሱን አስተሳሰብ ማንሸራሸር ይችላል፤ የፈለገውን በህግ ማዕቀፍ ውስጥ መስራት ይችላል። ሌላው ላይ ግን መፎከርም አይችልም፤ ንብረቱ ላይም ሆነ ህይወቱ ላይ አደጋ ሊፈጥር አይችልም። ምክንያቱም በአንድ በኩል ምህዳሩን ለማስፋት ተብሎ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በነበረን የተቋማት ብልሽት አንጻር ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ ህግ አስከብር ብለህ የምትልከው እንኳን የሚያስፈራሩትን የመንደር ጎበዞች የሚፈራበት ሁኔታ ነበረ። አሁን ግን ከዛ ውስጥ ስለተላቀቁና ባለሀብቶቻችን የሚሰሩት ለአገራቸው እንደመሆኑ፤ ሁሉም ደግሞ ህግን ተከትለው እስከሰሩ ድረስ እነርሱ ላይ የሚደርስ ማንኛውንም በደል የመከላከል ግዴታ የመንግስት ነው።

ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፤ ከየትኛውም ቦታ ኦሮሚያም ክልል፣ ደቡብም ሆነ አማራ ክልል መጥተው በተመቸው ቦታ ላይ ህጋዊ በሆነ መንገድ ኢንቨስት ማድረግ ይችላል። ለወገኖቹ የስራ እድል መፍጠር ይችላል። ህጎችን ማክበርና ለአገሩም ግብር መክፈል ይኖርበታል። ከዛ ውጪ ባለው መንገድ መብቶቹንም ሆነ ንብረቶቹን የሚጎዳ ማንኛውንም ተግባር መንግስት መከላከል ይኖርበታል። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሁሉም ነገር ሊኖር የሚችለው ህግ ሲኖርና የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ ስለሆነ ይሄንን ለማረጋገጥ መንግስት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ መተባበር ይኖርበታል። ሚዲያው ደግሞ ዋናው ግንዛቤ ስለሆነ አጠቃላይ በህግ የበላይነት ላይ፤ በነጻነት ድንበር ላይ የቱና የቱ ነው በሚለው፤ መብት ሲኖር አብሮ ግዴታ መኖሩን በተለይ ወጣቱ እንዲገነዘብ ሰፊ ስራ ይጠበቅበታል። ባጠቃላይ ከዚህ በኋላ ሁሉም ነገር በህግና በህግ ብቻ እየተዳኘ የኢትዮጵያ ፣ብልጽግናና የተጀመረው ለውጥ በታለመለት አቅጣጫና ፍጥነት ይጓዛል።

አዲስ መን፡– ከተፈጠረው ኹከትና ግርግር በኋላ አሁን በክልሉ ያለው ተጨባጭ እውነታ እንዴት የሚገለጽ ነው?

አቶ ታዬ፡ ከግርግሩ በኋላ ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ተይዘዋል። በመንግስትም በማህበረሰቡም ድጋፍ ደግሞ ችግር የደረሰባቸው ባጠቃላይ እስኪቋቋሙ ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። የሰላም ኮንፍረንሶች በተለያየ አካባቢ(በከተሞች፣ በዞኖች) እየተደረገ ነው። ህብረተሰቡም አስተያየቱን እየሰጠ ነው።

ህብረተሰቡ ትልቁ ጥያቄና ትልቁ ፍላጎት መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት፤ እኛም መንግስት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነን እንተባበራለን፤ ወንጀለኞችና ጥፋተኞች በብሄር ወይም በሃይማኖት የሚታዩበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም፤ የፈለገው ብሔር ቢሆን ወንጀል ከሰራ ወንጀለኛ ነው በወንጀሉ ይጠየቃል፤ ከፈለገው ሃይማኖት ቢሆን ወንጀል ከፈጸመ በወንጀሉ ልክ ለህግ ይቀርባል፤ ስለዚህ ህብረተሰቡ በዚህ ደረጃ የእኔ ልጅ ወይም የወንድም ልጅ ወይም የእህት ልጅ ቢሆንም እንኳ በህግ ነው መገዛት ያለበት፤ ህግን ጥሶ የድሃን ንብረት ካቃጠለ፣ የዜጋን ህይወት ካጠፋና ጉዳት ካደረሰ በዛ ልክ ለህግ መቅረብ አለበት ተብሎ ሁሉም ቦታ ስምምነት ተደርሷል።

የፍትህ ተቋማትም ሆኑ የፀጥታ አካላት በዚህ ደረጃ እንቅስቃሴ ላይ ናቸው። የፖለቲካ አካሉም ደግሞ በዚህ ልክ ራሱን እየፈተሸ ነው። ቀደም ብዬ እንዳነሳሁትም በጉዳዩ ውስጥ የተሳተፉትን፤ ጉዳቱን ማስቀረት ሲችሉ ቆመው የተመለከቱትን እየለየና እነርሱን መስመር እያስያዘ ነው።

አዲስ ዘመን፡– በብርቱ ፈተናዎች ታጅቦ እየተጓዘ ያለው አገራዊ ለውጥ ዛሬ ላይ በምን ደረጃ ላይ ይገኛልችግሮቹን ተቋቁሞ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥስ ህዝብን አሳትፎ ከመሄድ አንጻር ምን አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው?

አቶ ታዬ፡ ይሄ ለውጥ ከመጀመሪያው ሰኔ ጀምሮ በተለያየ ጊዜ እንዲደናቀፍ አደጋዎች ተደቅነውበታል። እነዛን እንቅፋቶችም እያለፈ ነው የመጣው። የአሁኑ ከሃጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ የተደቀነው አደጋ ደግሞ ከሁሉም አደጋዎች አንጻር እጅግ የታቀደና ፋይናንስም የተደረገበት ብሎም ከግድያው በኋላ ቀጣይ እርምጃዎች ላይ አቅጣጫ ተቀምጦበት የተሰራ ከመሆኑ አንጻር እጅግ የከፋው ነው። ይሄ ለውጥ ደግሞ ይሄንን ትልቅ አደጋ ተሻግሯል።

ከዚህ በኋላም ችግር ሊነሳ ይችላል፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ከዚህ አደጋ ጋር የሚስተካከል ሌላ ችግር ሊመጣ አይችልም። ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ነው። አንደኛው የፀጥታ ሃይሉ እና አጠቃላይ የፖለቲካ ሃይሉም እየጠራና እየተጠናከረ ነው። የተሻለ ቁመና ላይም ደርሷል። ሁለተኛው ደግሞ ይሄ ለውጥ ከየት ወደየት እንደሆነ ህብረተሰቡ ተገንዝቧል። እየተሰራበት ያለውን ሴራም ህብረተሰቡ በሚገባ እየለየና እያወቀ እየተገነዘበም መጥቷል። ስለዚህ ከዚህ በኋላ የሚመጣ ማንኛውም አደጋ ከአሁኑ አደጋ ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ነው የሚሆነው። እናም ይሄንን ለውጥ ወደኋላ ሊመልስ የሚፈልግ የትኛውም ሃይል አይኖርም።

በዚህ ላይ ደግሞ የህግ የበላይነቱም፤ የህብረተሰቡም ትብብር ከዚህ በኋላ ተጠናክሮ ስለሚሄድ (እቅዳቸው ብዙ እንደመሆኑና ሃጫሉን አይነት ተመሳሳይ ሌላ የሴራ ግድያ ሊኖር ስለሚችል ችግር አይኖርም ባይባልም) ምንም አይነት ችግር ቢኖር በዚህ ልክ ሊያስደነግጥ አይችልም። ምክንያቱም አውቀናል። ህብረተሰቡም አውቋል። እናም ከመንግስት አመራሮች ጋር ተያይዞም የሚያደርጉት ነገር ሊኖር ይችላል፤ ከሃይማኖት ጋር አያይዘው ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ሊኖር ይችላል። ግን ሁሉም ሃይማኖት የእነርሱን ሴራ በሚገባ ስለተገነዘበ ከዚህ በኋላ ውጤቱ እነሱ ላይ እየቆጠረ ነው የሚሄደው እንጂ የእኛን ሂደትና ጉዞ ለማደናቀፍ አይችልም።

አሁንም ህብረተሰቡ ለውጡ የእርሱ መሆኑን በግልጽ ማወቅ አለበት። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲ የታገለውና በትግል ሂደቱ ልጆቹን፣ ሀብትና ንብረቱን ብሎም ጊዜውን ሰውቷል። በተለያየ ጊዜም ልጆቹ ታስረዋል፤ ተሰደዋልም። የኢትዮጵያ ተማሪዎች በ1966 ወይም በ1960ዎቹ አጠቃላይ ካነሷቸው ጥያቄዎች ዋነኛውና መሰረቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በመረጠው መንግስት መተዳደር አለበት፤ እናም ዴሞክራሲ መረጋገጥ አለበት የሚል ነው።

ዴሞክራሲ መረጋገጥ አለበት ሲባል ደግሞ ዴሞክራሲ በራሱ ዳቦ ስለሆነ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚቆጣጠረው መንግስት የራሱን ልማትና ብልጽግና ማረጋገጥ እንዲችል ነው። በዚህም የሚሰራለትን መሾም፤ የማይሰራለትን ደግሞ መሻር እንዲችል ነው። የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን ነው። የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን ሲባል ደግሞ ተቆርጦ ለብቻው መውጣት ከሚል ጋር የሚያያዝ አይደለም። በልማቱ፣ በብልጽግናው፣ በትምህርትና በጤናው ላይ የሚወስን አካል በዴሞክራሲያዊ መንገድ መወሰን መቻልን የሚመለከት ነው።

ህዝቡ የታገለውም ለዚህ ነው። ሆኖም ዋጋ ተከፍሎበት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሁለት ጊዜ ነው የከሸፈው። በ1966 ብዙ ዋጋ ተከፍሎ የመጣው ግን ደርግ ነው። ደግር ደግሞ የመሬት ጥያቄን መልሶ በዛው ነው የቀረው። ዴሞክራሲና የማንነት ጥያቄን ዘነጋው። 1983ም በተመሳሳይ ከሸፈ። ምክንያቱም የማንነት ጥያቄ ዴሞክራሲ ሳይኖር የሚመለስ ስላልሆነ በስም ደረጃ እንዲመለስ ተደርጎ እዛው ከሽፎ ቀረ። አሁን ሶስተኛ እድል ነው። ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል ካለባት ዴሞክራሲ ያስፈልጋታል፤ ለዜጎቿ ነጻነት ያስፈልጋታል። ትውልዱ አገሩን ለመገንባት በነጻ ማሰብ አለበት። በነጻ የማያስብ ኢንተርፕሩነር ሊሆን አይችልም፤ በነጻ የማያስብ ጥሩ ኢንጂነር መሆንም አይችልም፤ ስለዚህ ነጻነት ያስፈልገናል።

ነጸነት ሲያስፈልግ ግን በህግ የበላይነት ማዕቀፍ ውስጥ መሆን እንዳለበት መገንዘብ፤ ለዚህ ደግሞ ንቃትና ስልጣኔ ያስፈልገናል። ስለዚህ የጀመርነውን ለውጥ ማስቀጠል የህልውናችን ጉዳይ መሆኑን በደንብ መገንዘብ ያስፈልጋል። ለውጡ ካልቀጠለ በዘራፊዎችና አፋኞች ለመገዛት እንኳን እድል አይኖረንም ማለት ነው። አገራችን እንደ ሊቢያም፤ እንደ የመንም ልትሆን ትችላለች። ያ ደግሞ ኪሳራው አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩም ትውልድ የሚተርፍ ነው። እናም ህብረተሰባችን ተባብሮ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሰሩትን ሁሉ ሃይ ማለት አለበት። የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መስራት አለበት። ለብልጽግናው ዘብ መቆም አለበት፤ ማለት እፈልጋለሁ።

አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻም ቀረ የሚሉት ሃሳብና ለኢሮሞም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚናገሩት መልዕክት ካለዎት እድሉን ልስጥዎ?

አቶ ታዬ፡ ብዙ ሃሳብ አንስተናል። ሆኖም አንድ ነገር ግልጽ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ይሄ የጥላቻ ፖለቲካ፣ ሀሳብ የሌላቸውና ለህብረተሰቡ ለእንግልቱም ለሞቱም ለስቃዩም ደንታ የሌላቸው ናቸው የሚሰብኩት። የጥላቻ ፖለቲካ ግን የሚያድገው በሌላ በኩል ተመሳሳይ መልስ የሚሰጥ ሲኖር ነው። እናም ሴራዎችን የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ልክ መገንዘብ ይኖርበታል። በተለይ ከኦሮሞ ህዝብ አንጻር አሁን የተፈጠረውን ብዥታ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ማየት ያለባቸው ሁኔታው የኦሮሞን ማንነት ለማጠልሸት እና ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ያለውን መስተጋብር ለማበላሸት ሆን ተብሎ የተሰራ ሴራ መሆኑን ማወቅ አለባቸው።

እዚህ አካባቢ በኦሮሞ ስም ወንጀል ይፈጽሙና ሌላ ቦታ ደግሞ በኦሮምኛ ተናጋሪ ላይ ተመሳሳይ ነገር የሚፈጠር ከሆነ፤ ይሄው እኛ እንደነገርናችሁ ይጠሏችኋል፣ ይሄን ነፍጠኛ እንዲህ አደረገ፣ ይሄው እገሌ እንዲህ አደረገ፣ በሚል ለሌላ ሰበካና ለሌላ ቅስቀሳ ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ። በሁሉም አካባቢ በዜጎች ላይ በሃይማኖት ወይም በብሔርና በጎሳም ሊሆን ይችላል፣ በሌብነትም ሊሆን ጉዳት ያደረሱትን ተከታትለን ለህግ እናቀርባለን። ወንጀለኛ በየትኛውም ጫፍ ይጠየቃል። ከዚህ ባሻገር ግን ጠላት የሚፈልገውን ስሜት ማስተናገድ አይጠበቅብንም።

ጠላት አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ዘንድ በተለየ መልክ (በጥላቻ፣ በስጋት) እንዲታይ ይፈልጋል። አሁን ወደ ኦሮሚያ የሚደረገው ሰበካ አማራ ሁሉ ነፍጠኛ እንደሆነ፤ ጉልት የሚነግድ ደሃም በዛ ደረጃ እንዲታይ ሰበካም በሚዲያ ቅስቀሳም አለ። ነፍጠኛ ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ትርጉም እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በዛ ደረጃ ግን ከኦሮሞ እኩል ሲሰቃይ የነበረ የአማራ ማህበረሰብ በኦሮሞ ዘንድ በሌላ መልክ እንደ ጨቋኝ፣ ራሱ ሲሰቃይና ሲበዘበዝ የነበረ ህዝብ እንደ በዝባዥ ሆኖ እንዲታይና እንዲሳል የተሰራበት ሁኔታ አለ።

በዚህም በኩል ደግሞ ኦሮሞ፣ በሲዳማ ወይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወይም በጋሞ ወይም በአማራ ህዝብ ዘንድ አሁን ከተፈጠረው ችግር አንጻር፤ ኦሮሞ ገዳይ ነው፣ ኦሮሞ ጨፍጫፊ ነው፣ ኦሮሞ አጥፊ ነው፣ ኦሮሞ አገር አፍራሽ ነው፣ በሚል በዚህ ደረጃ ሊመጡ ይችላሉ። ከዚህ በፊትም በዚህ ደረጃ ሲሰሩ ነበረ። እናም እነዚህን ስሜቶችና አመለካከቶች በዚህ አግባብ ካስተናገድን እነዚህ ጠላቶች (የኢትዮጵያው የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጠላቶችና ባንዎች) የሚፈልጉትን የቤት ስራ መስራታችን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል።

ከምንም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል። በሃይማኖት ወይም በብሔር ሊሆን ይችላል የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፤ አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠርና እንዲፈራ የሚያደርግ ትርክት ወይም አጀንዳ ካለ፤ ያ አጀንዳ የሩቅ ወይም የቅርብ ጠላት አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል በደንብ መገንዘብና ትብብራችንን የበለጠ ማጠናከር ይጠበቅብናል ማለት እፈልጋለሁ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012

ወንድወሰን ሽመልስ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0