ነጻ አስተያየት – በከድር መሐመድ kedir Mohamed 
ታሪካዊ ጠላቶቻችን እነ ግብጽ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ማፈራረስ ተገንጣይና አስገንጣዮችን በሚያደራጁበት ጊዜ የተጠቀሙት አጀንዳ ከብሄረሰብና ሃይማኖት ጋር የተያያዘ ብዝኀነታችንን ነው፡፡ በተለይ ተገንጣዮችና መገነጣጠሉን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀም የሚፈለጉ ኀይሎች በመሳሪያነት የተገለገሉት ደግሞ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ የቀረበውን የዋለልኝ መኮንን ጽሁፍ ነው፡፡
ሕገ መንግስቱ ጽሁፉን መነሻ አድርጎ ከመግቢያው ጀምሮ በዓለም የሪፐብሊክ ታሪክ ባልታየ መልኩ ዜጎችን በማግለል በዋነኛነት ዘርና ቋንቋን መሠረት ያደረጉ ቡድኖች ብቻ የፖለቲካ፣ ሕገ መንግስት፣ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ያደረገ ነው፡፡ ሀገር አልባ የሆንበት ሕገ መንግስት የጸደቀውም ዋለልኝ የሀገራችንን አውሮፕላን ከኤርትራውያን ጋር ሆኖ ሲጠልፍ በተገደለበትና በየዓመቱ የብሄረሰቦች ቀን ተብሎ በሚታሰበው ኀዳር 29 ቀን ነው፡፡ በአሉታዊም ሆነ አዎንታዊ መንገድ ዋለልኝን ለመተቸት እነሆ ሙሉ ጽሁፉ ቀርቦላችኋል፡፡
በዋለልኝ መኮንን በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈው “የብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ”
ዋለልኝ በብሄር ብሄረሰብ አጀንዳ ዙሪያ በእንግሊዝኛ ያቀረበው ጽሁፍ ሰኞ ዕለት ህዳር 08 ቀን 1962 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ውስጥ በንባብ አሰምቶታል፡፡ በመቀጠልም “ትግል” በሚባለው መጽሄት ላይ ታትሞ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የጽሁፉ ዓላማና በይዘቱ ላይ የተነሱት ዝርዝር ነጥቦች አንድም ሳይቀሩ ከዓላማና መግቢያው ቀጥሎ በ10 ቦታ ተለያይተው በትርጉም መልክ ደግሞ እነሆ እንደሚከተለው ተሰንደዋል፡፡
1) የጽሁፉ ዓላማና መግቢያ
ዋለልኝ ከርዕሱ በመቀጠል በመንደርደሪያነት የጠቀሰው ጽሁፉ ሊዘጋጅ የቻለበትን ምክንያት ነው፡፡ አጀንዳው እንደ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ተቆጥሮ በይፋ አንስቶ ለመነጋገር የሚፈራ እሱ ”sacred” በማለት የሰየመው ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ጽሁፉ የተዘጋጀበት ዓላማ አይነኬ ሆኖም ግን በጣም ጠቃሚ የሆነው የሀገሪቷ የብሄረሰቦች ጥያቄ ላይ ውይይቶች እንዲደረግ መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደሆነ በመነሻው አንቀጽ ላይ ገልጿል፡፡
ለልዩ ፕሮግራም እንዲሆን የተሰናዳው ጽሁፍ በጊዜና ሌሎች ችግሮች የተነሳ ዝርዝር ማድረግ ባለመቻሉ የተነሳ ድምዳሜዎችና በቂ ያልሆኑ ትንታኔዎችን እንደያዘ ከጅምሩ ጠቁሟል፡፡ ሆኖም ግን ውይይት ለማስጀመሪያነት እንደማያንስ እምነቱን አስቀምጧል፡፡
አንባቢዎች ሀረጎችን ከአውዳቸው ውጪ በመምዘዝ የተለየ ትኩረት እንዳያደርጉበትና እያንዳንዱ ነጥብ ከጠቅላላው ትንታኔ አንጻር እንዲታይለትም ከጅምሩ ተማጽኗል፡፡
2) በዋለልኝ ጽሁፍ ይዘት ላይ የተነሱት አስሩ መሠረታዊ ጉዳዮች
ዓላማውንና መግቢያውን ካስቀመጠ በኋላ የመጀመሪያው የዋለልኝ መወያያ ነጥብ የተማሪው ንቅናቄ የደረሰበት ደረጃ ግምገማ ነው፡፡
በወቅቱ የተማሪው ሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም ዝም ብሎ እንደ ተራ ነገር እንደተወሰደና ለውጡን የሚቃወም ኃይል በተለያየ መልክም መከላከልን መሠረት እንዳደረገ ይተቻል፡፡ ከዚያም በሁለቱ ተቃራኒ ጎራዎች መሀከል ያለው ግንኙነት የአብዮት እና ጥገናዊ ለውጥ (reform) እንዳልሆነ ያሰምርበታል፡፡ በዚሁ መሠረት በሁለቱ ጫፍ የረገጡ አቋሞች መሀከል ያለው ልዩነት በአንዱ ወገን ትክክለኛ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም እና በተቃራኒው በኩል ደግሞ ከመስመር መውጣትና ፋሽን ተከታይነት (perversion and fadism) እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ሁለተኛውና መሠረታዊው የጽሁፉ ማጠንጠኛ የብሄረሰቦች ጥያቄ ትኩረት መነፈጉን ይመለከታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አጀንዳው በግልጽ እንዳይነሳ ምክንያት ያደረገውን በተማሪዎች ንቅናቄ የሶሻሊስት ኃይሎች የተወሰኑ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ይፋ ማድረግ በጣም አደገኛና የማይመች ሆነው መገኘትን ይጠቅሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በተሳሳተ መልኩ ሌላው ማህበረሰብ እንዳይረዳቸው መፍራት ነው፡፡
እስከ አሁን ድረስ መፍትሔ ካላገኙትና በጥንቃቄ ካልተያዙ አደጋኛ ውጤቶችን ከሚያስከትሉ ጉዳዮች መሀከል አንዱ የብሄረሰቦች ጥያቄ ነው፡፡ ጥቂቶች ዋጋ አልባ እንደሆነ ቆጥረው በማጣጣል ጎሰኝነት (tribalism) ይሉታል፡፡ ሆኖም ግን እኔ ብሄርተኝነት (nationalism) ብዬ መጥራቱን እመርጣለሁ በማለት ይገልጸዋል፡፡
የብሄረሰቦች ጥያቄ በፓናል ውይይቶች፣ ትግላችን በሚለው መጽሄት ላይ በሚታተሙ ጽሁፎች፣ አልፎ አልፎ ተናጋሪዎች ሃሳባቸው በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ በድብቅ በሚሰራጩ ጽሁፎችና በሚስጥር በሚንሾካሾኩ ቡድኖች በሚገባ እንዲብላላ እንዳልተደረገ ያትታል፡፡ በእርግጥ የተወሰነ የተማሪው ማህበረሰብ በሌላው እንዲገለል ሊያደርገው ይችላል እንዲሁም በቀናነት የሚደረግ ውይይትን ያለ አግባብ በመተርጎም አብዮታዊ የተማሪ ንቅናቄ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው መንግስት ይጠቀምበታል የሚል ስጋት ነበር፡፡
ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በአብዛኛው ለህዝብ በማይታዩ ቦታዎች የተወሰነ ቡድን ብቻ በጣም ጥንቃቄ የሚሻውን አጀንዳ በድብቅ ይነጋገርበታል ብሏል፡፡ በሚስጥር የሚደረጉ ንግግሮች አፈትልከው እንደሚወጡና ምክንያቱ ደግሞ በግልጽ ውይይት ስለማይደረግባቸው ለሀሜት፣ የተሳሳተ አረዳድና እጅግ ለተጋነነ አሉባልታዎች መንገድ በመክፈቱ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
ተማሪዎች በጣም ስሜታዊ እንደሆኑ ያምናል፡፡ ሆኖም ግን ተጨባጭ እውነታን ለመጋፈጥ በቂ ብስለት እንዳላቸው ደግሞ ያስቀምጣል፡፡
ባለፉት 2 ሳምንታት እየተበተኑ የሚገኙ ጥቂት ፈራቸውን የለቀቁ በራሪ ወረቀቶች እንዳሉ መረጃ ይሰጣል፡፡ በእነዚህ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ እየተሰራጩ በሚገኙ ጽሁፎች የሚተላለፉት መልዕክቶች የዝቅጠት ማሳያ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ ይህንን መከላከያ ብቸኛው መንገድ ደግሞ በግልጽ የሚደረግ ውይይት እንደሆነ ምክሩን ይለግሳል፡፡
ሦስተኛው በዋለልኝ የተነሳው መሠረታዊ ነጥብ የኢትዮጵያዊ ሕዝብ ማንን ያቅፋል? የሚለውን ጥያቄ ይመለከታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሆነ ብሎ በብዙ ቁጥር ህዝቦች (peoples) የሚለውን አስቦበት ቃሉን መርጦ በማስቀመጥ በዚያን ጊዜ ከማህበረሰባዊ ጥናት አንጻር ኢትዮጵያ አንድ ብሔር (nation) አይደለችም ብሎ በቀጥታ ይደመድማል፡፡
ኢትዮጵያ የተሰራቸው ደርዘን በሚሞሉ የራሳቸው ቋንቋ፣ አለባበስ፣ ታሪክ፣ ማህበራዊ አደረጃጀትና ግዛት ባላቸው ህዝቦች እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ቀጥሎ ታዲያ ከዚህ ሌላ ብሄር ምን ሊሆን ይችላል በማለት ይጠይቅና መልሱንም በጥያቄ መልክ መልሶ ያቀርባል፡፡ ከዚያም ላጠቃለው ይልና በኢትዮጵያ የኦሮሞ ብሄር፣ ትግራይ ብሄር፣ አምሀራ ብሄር፣ ጉራጌ ብሄር፣ ሲዳማ ብሄር፣ ወላሞ (ወላይታ) ብሄር፣ አደሬ (ሀረሪ) ብሄር እና ብዙዎቻችሁ ባትወዱትም የሶማሌ ብሄር አለ በማለት ያስቀምጣል፡፡
አራተኛው ሀሰተኛ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት (fake Ethiopian Nationalism) በማለት ያቀረበው ነው፡፡ ይህም በገዢው መደብ እንደሚራመድና ባለማወቅ ተቀባይነትን እንዳገኘም ይጠቁማል፡፡ እንዲያውም በቀና ሰዎች ደግሞ እንዲስፋፋ እንደሚደረግም ይገልጻል፡፡
ይህ ሀሰተኛ ኢትዮጵያዊ ማንነት ምንድነው? ብሎ ጠይቆ እንደገና የአማራ ወይም ደግሞ በተወሰነ ደረጃ የአማራና ትግሬ የበላይነት እንጂ ሌላ ምንድነው? እያለ መልሶ ይጠይቃል፡፡ ማንኛውንም ሰው ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሙዚቃ እና ብሔራዊ ልብስ? ምንድነው ብላችሁ ብትጠይቁ በማለት እያንዳንዳቸውን ነጣጥሎ በጥያቄ መልክ ያቀርባል፡፡ ከዚያም ለሁሉም ጥያቄዎቹ አማራ ወይም አማራ-ትግሬ እንደሆነ መልሱቹን ራሱ ይሰጣል፡፡
እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ለመሆን አንድ ሰው በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ አማርኛ መናገር፣ የአማርኛ ሙዚቃ መስማት፣ የአማራ-ትግሬ ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ክርስትናን መቀበል እና የአማራ-ትግሬ ሸማን መልበስ አለበት ይላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ስምህን መቀየር ሁሉ ይኖርብሀል፡፡ ፋኖንስ የሚባል ምሁርን አገላለጽ ለመጠቀም ይልና ኢትዮጵያዊ ለመሆን የአማራነትን ጭምብል መልበስ ይጠበቅብሀል (Amhara mask) እያለ ይገልጻል፡፡
ዕድለኛ ሆነህ አምሀራ ሆነህ ካልተፈጠርክና ማንነትህን ለማረጋገጥ ከሞከርክ ጎጠኛ ተብለህ ትጠራለህ፡፡ በሕገ መንግስቱ መሠረት ትምህርት ቤት ለመግባት፣ ሥራ ለማግኘት፣ ጥቂት ቢሆንም መጽሀፍ ለማንበብና ሬድዮ ለመስማት እንኳን አማርኛ ቋንቋን ማወቅ አለብህ፡፡ በልዩ ሁኔታ በሚታወቁ ምክንያቶች ሶማሌና ኤርትራ ካልሆንክ በስተቀር በቋንቋህ ሬድዮ አትሰማም ብሎ ሃሳን ይሰነዝራል፡፡
አምስተኛው ባህልን ከማርክሲዝም ፍልስፍና ጋር በማያያዝ የሰጠው ትንታኔ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ባህል የኢኮኖሚ መሠረት ታላቅ አወቃቀር (super-structure) ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የባህል የበላይነት የኢኮኖሚ ጭቆናን በቀጥታ ያስከትላል፡፡
ከባህል የበላይነት የመነጨ የኢኮኖሚ ጭቆናን ለማሳየት ምሳሌዎች አድርጎ ያስቀመጣቸው የአማራና በተወሰነ ደረጃ የትግራይ ነፍጠኛ ሥርዓት በደቡብ ያጎናጸፈውን የበላይነት እንዲሁም የአማራ-ትግሬ ጥምረት በከተሞች ያስገኘው የበላይነትን ይጠቅሳል፡፡
የተለመደው ማሳሳቻ ሰፊ የአማራና ትግራይ ማህበረሰብ በገጠር በድህነት እየማቀቀ መገኘቱ ነው፡፡ የብሪቲሽ ኢምፔሪያሊዝም ከፍተኛው ደረጃ ላይ እያለ ሰፊ የብሪታንያ ሠራተኞች ኢ-ሰብዓዊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ይኖር ነበር እያለ አቋሙን ያጠናክራል፡፡
ሌላው በተቃራኒ የሚቀርበው ክርክር በካቢኔ ውስጥ አማራ-ትግሬ ካልሆኑ ብሄረሰቦች መሀከል የወጡ ሚኒስትሮች በካቢኔ ውስጥ መገኘታቸው፤ አንድ ወይም ሁለት ጀነራሎች በጦር ሠራዊት ውስጥ፤ አንድ ወይም ሁለት ገዢዎች እና ደርዘን የሚሆኑ ባላባቶች በገጠር ከሌላው ወገን መኖራቸውን ነው፡፡
ሆኖም ግን እያለ ዋለልኝ በመቀጠል ብሪታንያን የመሳሰሉ ኢምፔሪያሊስቶች በቁጥጥራቸው ስር የሚገኙ ቅኝ ግዛቶቻቸውን በሚያስተዳድሩበት ጊዜ የጎሳ መሪዎችን ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህ የጎሳ መሪዎች ደግሞ በብሪታንያ ከተሞች ውስጥ ከሚኖር አማካይ ገቢ ካለው ዜጋ እጅግ በሚበልጥ መልኩ ሀብታም ናቸው፡፡ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከመውጣታቸው በፊት (ሁፔት) ቦኜ (Houpet) Boigne እና ሴንጎር (Sengor) የፈረንሳይ ብሔራዊ ጉባዔ አባልና እንዲያውም ሚኒስትሮችም መሆናቸው እንደ ቅደም ተከተላቸው የአይቮሪኮስት እና ሴኔጋል ፖለቲካዊ ነጻነት ማጣትን ቅንጣት ያክል አይቀንሰውም በማለት ይከራከራል፡፡
በእርግጥ የአምሀራዎችና ታናሽ አጋሮቻቸው የትግሬዎች ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጭቆና ታሪካዊ ክስተት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ አማራዎች የበላይ የሆኑት ኢምፔሪያሊስት ሆነው ተፈጥረው አይደለም፡፡ ኦሮሞዎችም ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ወላሞዎች (ወላይታዎችም) ሊፈጽሙት ይችላሉ፡፡ በታሪክ ሙከራም እንዳደረጉ ተረጋግጧል፡፡ ሆኖም ግን ሁኔታውን ለማስቀጠል በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ አንገብጋቢው ጥያቄያችን የበላይነት እንዲቆም ማወጃችን ነው፡፡ እውተኛ ብሔራዊ ሀገር (national-state) መገንባት አለብን በማለት አጽንኦት ሰጥቶ ያስቀምጣል፡፡
ስድስተኛ የዋለልኝ ራሱን የቻለ አጀንዳ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችለው ይህ እውነተኛ ብሔራዊ ሀገር ምንድነው? በማለት ያብራራው ነው፡፡ ይህ ሁሉም ብሄረሰቦች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዕኩል የሚሳተፉበት ነው፤ እያንዳንዱ ብሄረሰብ ቋንቋውን፣ ሙዚቃውንና ታሪኩን እንዲጠብቅና እንዲያዳብር ዕኩል ዕድል የሚያገኝበት ሀገር ነው፤ አምሀራዎች፣ ትግሬዎች፣ ኦሮሞዎች፣ አደሬዎች (ሀረሪ)፣ ሶማሌዎች፣ ወላሞዎች (ወላይታዎች)፣ ጉራጌዎችና ሌሎች ዕኩል የሚተናገዱበት ሀገር ነው፡፡ ከዚያም ማንኛውም ብሄር በሌላው ላይ የኢኮኖሚ ወይም ባህል የበላይነት የማያገኝበት ሀገር እንደሆነ አጽኦት በመስጠት አንቀጹን ያጠናቅቃል፡፡
ሰባተኛ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊና መደብ አልባ ሀገር (genuine democratic and egalitarian state) ለመፍጠር እንቅፋት የሚሆኑ ሁኔታዎችን ያስቀመጠበት ነው፡፡ በወታደራዊ መንገድ ይቻላል? ብሎ ይጠይቅና እንደማይሆን መልሱን ራሱ ይሰጣል፡፡
ወተዳራዊ መፈንቅለ መንግስት ከግለሰቦች ለውጥ ውጪ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ከወደቀው መንግስት አንጻር በተወሰነ መልኩ ለዘብተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን በመደቦች ወይም ብሄረሰቦች መሀከል ያለውን ቅራኔ መቼም ሊቀርፈው አይችልም፡፡
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያደረጉት የንዋይ ወንድማማቾች ወይም ታደሰ ብሩዎች ሊፈጽሙት አይችሉም፡፡ የመንግስቱዎችና ታደሰ ብሩዎች መፈንቅለ መንግስትን በተመለከተ መነጋገር ይቻላል፡፡ የቤተሰብና ከወርቅነህ ውጪ የሸዋ አማራዎች የተወሰነ ክፍል የሆነው የመንግስቱዎች መፈንቅለ መንግስት በጣም ታዋቂ ሆኗል፡፡ ይህም ዝና ኢትዮጵያውያኖች በሆኑ አማራዎች በመፈጸሙ ነው፡፡
የታደሰ ብሩ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ የጎጥ አመጽ ነው፡፡ ለምን? በማለት ይጠይቅና ኦሮሞ የሆነው ታደሰ ብሔራዊ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ አይችልም፡፡ እሱ ማሳካት የሚችለው የኦሮሞ የበላይነትን ነው (Oromo Supermacist) ብሎ ይደመድማል፡፡
መፈንቅለ መንግስትን በማውገዝ ረገድ የማያወላውል አቋም እንዳለው ዋለልኝ አስምሮበት ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም ግን የታደሰ ብሩ መፈንቅለ መንግስት ቢያንስ አንድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ በጣም ጠቃሚ ገጽታ አለው ይላል፡፡ ይህም ኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የራስ ክብር (self-respect) እንዲሰማቸው ማድረጉ ነው ይላል፡፡
በኦሮሞ ማህበረሰብ ለራስ የሚሰጥ ክብር ሰፊ መሠረት ሊኖረው ለሚገባ አብዮት ጠቃሚ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ መፈንቅለ መንግስቱን የሚያጣጥሉ የተማሪውን ማህበረብ ዓይነት አብዮተኞች ነን የሚሉ ወገኖች ይህንን ገጽታውን አይረዱትም፡፡ ከዚህ ክስተት ላይም የአማራ-ትግሬ የበላይነት ስሜቶችን በግልጽ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ ጥያቄ ላይ ተማሪዎቹ ከመንግስት ፕሮፓጋንዳ ውጤቶች ያለፈ ምንም እንዳልሆኑም አረጋግጠዋል በማለት ይኮንናቸዋል፡፡
የኤርትራ ነጻነት ግንባር እና የባሌ ትጥቅ ትግል ዓላማችንን ሊያሳኩ ይችላሉን? ብሎ ይጠይቃል፡፡ መልሱንም አሁን በያዟቸው ዓላማዎችና አደረጃጀት አያሳኩም ብሎ ራሱ ምላሽ ይሰጣል፡፡ እነዚህ ንቅናቄዎች አግላይ ባህሪ አላቸው፡፡ የሚመሩትም የመጀመሪያው በአካባቢው ቡርዣ እና በሁለተኛው ደግሞ በአካባው የፊውዳል ከበርቴዎች እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ለዓላማችን ወሳኝ የሆነው ዓለም አቀፋዊ እይታ የላቸውም፡፡ ብሄራዊ ጭቆና እንዳለ መግለጻቸው ግን ትክክል ናቸው፡፡ በዚህ ነጥብ ዙሪያ ልዩነት የለንም፡፡
ሆኖም ግን የኤርትራው ነጻነት ግንባርና የባሌ ትጥቅ ትግል እቅድ እዚያው መቆም ነው፡፡ ትግሎቻቸውን ወደ ሌሎች ብሄረሰቦች ማሸጋገር አይሞክሩም፡፡ ባለው መንግስት መሠረቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማድረስ ሙከራም አያደርጉም፡፡ እያወቁ በአካባቢው ገዢ መደቦችና ብሄራዊ ጭቆና መሀከል ያለውን ግንኙነት ይዘነጋሉ፡፡
በአጭሩ እነዚህ የኤርትራና ባሌ ንቅናቄዎች በአርሶ አደሮችና ሠራተኞች አይመሩም፡፡ በመሆኑም ሶሻሊስቶች አይደሉም፡፡ ለህዝቦቻቸው (masses) የሚያስገኙት ውጤት የገዢዎች መቀያየር ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ግን በተቃራኒው በሶሻሊስቶች ጎራ የገዢዎች ለውጥ ሳይሆን የህዝቦች ደህንነት ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡
የጎጃም አመጽም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በድጋሚ እዚህ ካምፓስ ውስጥ የአማራ የበላይነት ምን ያህል ዝም ብሎ እንደ ተራ ነገር እንደተቆጠረ ማሳየት እፈልጋለሁ በማለት ለማሳያነት ጀብሃን በምሳሌነት እየጠቀሰ ይቀጥላል፡፡
የኤርትራውን ጀብሃ ኢኤልኤፍን መደገፍ ሃጢያት ነው፡፡ ማንኛውም የድጋፍ ጽሁፍ በሚጻፍበት ጊዜ በአህጽሮተ ቃል ባሰቀመጣቸው ዩኤስዩኤኤ (USUAA-University Students Union of Addis Ababa) እና ኤንዩኢዩኤስ (NUEUS-National Union of Ethiopian University Students) ወዲያው ተቃውሞ ይቀርብበታል፡፡ ሆኖም ግን የጎጃም ጉዳይ በተለየ መልኩ ይታያል፡፡ እነሱን መደገፍ በተግባር ከአብዮተኞች ጎን እንደ መሰለፍ ይቆጠራል፡፡
እዚህ ጋር ግን ልብ ሊባልልኝ የሚገባው እነዚህ ንቅናቄዎች የመጨረሻ ግባችን ለሆነው እውተኛ ብሔራዊ ሀገር ዘላቂ መፍትሔዎች እንዳልሆኑ መግለጼ ነው፡፡ ያለውን መንግስት በመገዳደርና በማዳከም እንዲሁም በኃላ ላይ በእውነተኛ የሶሻሊስት አብዮት አገልግሎት ላይ የሚውል ቅራኔን በመፍጠራቸው ከኢኤልኤፍ፣ የባሌ ንቅናቄዎችና የጎጃም ንቅናቄዎች ጎን ነኝ ይላል፡፡
ስምንተኛ ተብሎ ለብቻው ሊጠቀሰው የሚችለው ነጥብ በድጋሚ ግልጽ ሊሆን የሚገባ ነጥብ በማለት ያስቀመጠው መገንጠልን የሚመለከተው አቋሙ ነው፡፡ እነዚህ ንቅናቄዎች ተገንጣዮች በመሆናቸው ብቻ አልቃወማቸውም፡፡ መገንጠል በራሱ ምንም ችግር የለውም፡፡ እዚህ ጋር ሌኒን የተናገረውን እንዳለ አስቀምጣለሁ፡- “…ህዝብ ወደ መገንጠል የሚያመራው ብሄራዊ ጭቆና እና ብሄራዊ ቅራኔዎች በጋራ መኖርን የማይቻል በሚያደርጉበት ጊዜና ማንኛውምና ሁሉም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ላይ መሰናክልን ሲፈጥሩ ነው፡፡ ”
በመቀጠል በ1896 በለንደን ዓለም አቀፍ ኮንግረስ የጥቅምት የሩሲያን አብዮት እውን ያደረጉ ቦልሼቪኮች ተገኝተው ደግፈው ያጸደቁት የብሄረሰቦች ጥያቄ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ልጥቀስ፡- “ይህ ኮንግረስ በወታደራዊ፣ ብሄራዊ ወይም ሌላ አምባገነናዊ ቀንበር ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞችና አርሶ አደሮች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሙሉ መብታቸው መከበሩን እንደሚደግፍና በአጋርነት ከጎናቸው እንደሚሰለፍም ያረጋግጣል፡፡”
መገንጠል በአርሶ አደሮችና ሠራተኞች የሚመራ ከሆነና በዓለም አቀፋዊ ግዴታቸው የሚያምኑ እስከ ሆነ ድረስ ከጎናቸው መቆም ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ወታደራዊ እገዛም ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
ህዝብ እየተበዘበዘ ተመሳሳይ የንቃት ደረጃ ላይ ደርሰን ተመሳሳይ የመገንጠል ጥያቄ እስክናቀርብ ጊዜ ድረስ አጋሮች ሆነን እንቀጥል በማለት መጠየቅ ፍጹም ኋላ ቀርነትና ራስ ወዳድነት ነው፡፡ መገንጠል ያስፈልጋል አያስፈልግም በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ መቼም ቢሆን መነጋገር አያስፈልግም፡፡ የመገንጠል ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ መታየት ያለበት ተራማጅ ወይም አድሃሪ መሆኑ ነው፡፡
ሶሻሊስታዊ ኤርትራ እና ባሌ ለሀገሪቷ አብዮት ትልቅ ኃይልን ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መልሰው ለመዋሃድ መደብ የሌለበትና ዲሞክራሲያዊ መሠረት እንዲጣል ለማድረግ ይችላሉ፡፡ ፡
ዘጠነኛ ዋለልኝ የጽሁፉ ማጠንጠኛው ወደ ሆነው ነጥብ እንመለስ በማለት እውነተኛ የሆነ መደብ አልባ ብሄራዊ ሀገር እንዴት እንፍጠር? የሚለውን ጥያቄ ያነሳል፡፡ ይህንን ማሳካት የሚቻለው በአብዮታዊ ትግል በኃይል ብቻ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥቶታል፡፡
ሆኖም ግን ሀሰተኛ ብሄራዊ ከሆነው መንግስት ፕሮፓጋንዳ ራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡ አብዮቱ የትኛውም ቦታ ሊጀመር ይችላል፡፡
አጀማመሩ ከመገንጠልም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ብሄረሰቦች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ነጻነትን እንዲጎናጸፉ ጥንቃቄ በማድረግ ተራማጅ በሆኑ አርሶ አደሮችና ሠራተኞች መገንጠሉ ከተከናወና የመጨረሻ ግቡ ሰፊውን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ነጻ እስካወጣ ድረስ ችግር የለውም፡፡
እያንዳንዱ አብዮተኛ መጠየቅ ያለበት ንቅናቄው ሶሻሊስት ወይም አድሃሪ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ተገንጣይ መሆን ወይም አለመሆኑ አጀንዳ ሆኖ መቅረብ የለበትም፡፡
በጊዜ ሂደት ሶሻሊዝም ዓለም አቀፋዊነት ነው፡፡ የሶሻሊስት ንቅናቄ ተገንጣይ ሆኖ ለመልካም ዓላማ እንዳለ ሊቀጥልም አይችልም፡፡
አስረኛውና የመጨረሻው ደግሞ የዋለልኝ ጽሁፍ ማጠቃለያ ነው፡፡ ይህም ትልቅ የጋራ ሀገር ጥቅምን በሚመለከት የሌኒንን ሃሳብ እንዳለ ያሰፈረበትና ዳግም ለመዋሃድ የሀገር መፈራረስ አይቀሬነትን በሚመለከት የበኩሉን አስተያየት የሰነዘረበት ነው፡፡
የሌኒን እንደሆነ በጠቀሰው አስተሳሰብ፡- “ከዕለት ተዕለት ተሞክሯቸው ህዝቦች የመልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች እንዲሁም የትልቅ ገበያና የጋራ ሀገርን ጥቅም በሚገባ ያውቃሉ፡፡“ ከዚህ አንጻር ትግሉ በሚቃኝበት ጊዜ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጫና የሚፈጠርበት የኛን ዓይነት መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈራርሳል፡፡
ሆኖም ግን የብሄረሰቦች ንቃት በተለየየ ደረጃ ላይ በሚገኝበት ጊዜ በጣም ንቁ የሆነው ማኅበረሰብ ሌሎቹ እስኪነቁ ጊዜ ድረስ ሳይጠብቅ አስቀድሞ ራሱን ነጻ ማውጣቱ መብት ብቻ አይደለም፡፡ እንዲያውም ግዴታ ጭምር ነው፡፡
ከዚያም ለጠቅላላ ነጻነት በቅድሚያ በመንቃት ራሱን ነጻ ያወጣው ሌሎችም የሚያደርጉትን ትግል ማገዝ አለበት፡፡ ይህ በኮሪያ እውን አልሆነምን? በማለት ጥያቄ አቅርቦ እንደበቃ ወዲያው ራሱ ንቅናቄውን በጽኑ እንደግፋለን በማለት መልስ ይሰጣል፡፡ ከዚያም መልሶ አንደግፍም እንዴ? የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ታድያ ጎጠኝነት፣ መገንጠልና የመሳሰለው አገላለጽ ምንድነው? በማለት ጥያቄ አንስቶ ዋለልኝ መኮንን ጽሁፉን ያበቃል፡፡
Bego Urge and 10 others
22 Comments
1 Share
Like

 

 
Comment
 
Share
 
 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *