በድርጅታችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ በመሆኑ ደህንነታችን ለአደጋ እየተጋለጠ ነው ሲሉ የራይዘን ኮንስትራክሽንና ፀሜክስ ግሎባል ኢንተርራይዝ ሠራተኞች አመለከቱ።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉና በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የድርጅቱ ሠራተኞች በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ በመስሪያቤታቸው በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሠራተኞች ቁጥር በመጨመር ላይ ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመስሪያቤቱ ጥቂት የማይባሉ ሠራተኞች የታመሙ ሲሆን፤ ሥራአስኪያጁን ጨምሮ አስራአንድ ያህሉ በሦስት ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ህክምና በመከታተል ላይ ናቸው።

በድርጅቱ እስከአሁን የተለየ ጥንቃቄና ግንዛቤ ካለመኖሩ ጋር የሠራተኞቹ መታመም በምስጢር ተይዞ ቆይቷል ያሉት እኒሁ ሠራተኞች፤ በዚህ የተነ ሳም አብዛኞቹ ሠራተኞች ለቫይረሱ እንዲጋለጡና ብሎም ተገቢውን ምርመራ እንዳያደርጉ ሆነዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በለይቶ ማቆያ ውስጥ ከሚገኙ ሠራተኞች መካከል አንደኛው በሰጠው አስተያየት በቫይረሱ መያዙን ያወቀው የሌሎች መታመምን ሰምቶና ተጠራጥሮ ባደረገው ምርመራ ሲሆን፤ ይህን እስኪያረጋግጥ ግን ከድርጅቱ ያገኘው ምንም መረጃ ያለመኖሩን ተናግሯል።

ድርጅቱ ሠራተኞቹ በማቆያው ከገቡ በኋላም የት ደረሳችሁ አለማለቱ እንዳሳዘነው የጠቀሰው አስተያየት ሰጪው፣ አሁንም የበርካቶች ጤንነት በስጋት ላይ መሆኑንና ድርጅቱ ለምርመራው ካልፈጠነ የሁሉም ሠራተኞች ህይወት አደጋ ላይ መውደቁ ሊታወቅ ይገባል ብሏል።

ለቫይረሱ መስፋፋትና ለሠራተኞቹ መታመም ተጠያቂው ድርጅቱ ነው የሚሉት ሠራተኞቹ ፣ መስሪያ ቤቱ ከጤና ይልቅ ሥራን ብቻ የሚያስቀድም በመሆኑ ከጉዳዩ መታወቅ በኋላም ሠራተኞች በሥራ ላይ እንዲገኙ በማስገደድ ላይ ነው ብለዋል።

በቅርብ ቀን በአካባቢያቸው በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው በቤታቸው እንዲቆዩ የተደረጉ ሠራተኞች ጭምር ወደሥራ እንዲገቡ ተደርገዋል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ድርጅቱ በቅንነት እያገለገሉት ያሉ ሠራተኞቹን ያለምንም ዕረፍት እንዲሠሩና ጤንነታቸው ስጋት ላይ እንዲወድቅ በማድረጉ ሊጠየቅ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።

በድርጅቱ ለበርካታ ዓመታት አገልግያለሁ የሚ ሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በሙሉ ጊዜ ሠራተኞችን እያሠራ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ድርጅቱ ችግሩ ከታወቀ ወዲህ የተወሰኑ ሠራተኞች በንክኪ ምክንያት ቤት እንደቀሩ ከመስማታቸው ውጪ በግልጽ የተወሰደ ዕርምጃና የተሰጠ ማስጠንቀቂያ አለመኖሩ የሁሉም ተቀጣሪ

Related stories   በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የነፍስ አድን መድኃኒቶች ጥቁር ገበያ ደርቷል

ስጋት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

እንደ አስተያየት ሰጪው ገለጻ በተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ሠራተኞች የሥራ ባህርይና የእርስ በርሰ ግንኙነት ለቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገልጸሉ። ድርጅቱ በየጊዜው የሚደርሰውን ችግር እያወቀ ዝምታን መምረጡም ብዙዎች በመሳቀቅ እንዲኖሩና ለቤተሰቦቻቸው ጤንነት ጭምር ስጋት እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል።

ሠራተኞች ለሚያነሱት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂነትና ሥጋት ተጠያቂ ነው የተባለው የራይዘን ኮንስትራክሽንና ጸሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ አስተዳደር ኃላፊ አቶ አውሎአለም ወልዱ በበኩላቸው፣ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ እንደማንኛውም ተቋም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜ በድርጅቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሠራተኞች እየተመረመሩ ራሳቸውን ስለማወቃቸው መረጃው እንዳላቸው የሚናገሩት የአስተዳደር ኃላፊው፣ ድርጅታቸው ለሠራተኞቹ ምን ያህል እገዛ እያደረገ ነው ለሚለው ጥያቄ ግን ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም።

ከሠራተኞች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በአሁኑ ጊዜ ዋና ሥራ አስኪያጁን ሳይጨምር በቫይረሱ የተጠቁ አስር የድርጅቱ ሠራተኞች በሚሊኒየም አዳራሽ፣ በእንዶዴና በተስፋ ኮከብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተከፈቱ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም

በመልካምስራ አፈወርቅ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *