በፍርድ ቤት ውሎ ዘገባ ህብረተሰቡ ተገቢና ሚዛናዊ መረጃ ሊቀርብለት እንደሚገባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ገለፁ።
 
የችሎት ዘገባ የሙያ ስነምግባርን እና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ÷ የፍርድ ቤቶችን ነጻና ገለልተኛነት ያላማከለ፣ የተጠርጣሪዎችን ንጹህ ሆኖ የመገመት መብትን የሚጋፉ የችሎት ዘገባዎች በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሰለሞን አረጋ ተናግረዋል።
 
ዛሬ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዘጋጅነት ከመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ጋር በተደረገ ውይይት÷ ከኢትዮጵያ ህግ አንጻር የሚገደቡና የማይገደቡ የችሎት ውሎ ዘገባዎች ምን መምሰል አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ አቶ ተስፋዬ ነዋይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
 
በዚህ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ተጠርጣሪዎችን ወንጀል እንደፈጸሙ አድርገው የሚዘግቡ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን እንዳሉ አመላክተዋል።
ይሁንና በሚዘገቡ የፍርድ ቤት ዘገባዎች ላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እና መሰል ዘገባዎችን ከማስተላለፍ መቆጠብና በጥንቃቄ ሊዘገብ እንደሚገባ ተገልጿል።
 
ከዚያም ባለፈ ዘገባዎች ፍሬ ነገርን የማያዛባ የዳኝነት አካሉን ተጽኖ ስር የማይከቱ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ተጠቅሷል።
 
ይሁንና በአንዳንዶች በኩል ተጠርጣሪዎች የሚናገሩትን ብቻ የሚዘግብ ሚዲያ ሚዛናዊነት የሚጎለው እንደሆነ የገለጹት አቶ ተስፋዬ በተቻለ መጠን የሁሉም አካል በሚዛናዊነት ሊካተት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
 
በውይይቱ ላይ የተጠያቂነት ደረጃዎች እስከምን ድረስ የሚለውም የተነሳ ሲሆን÷በሚቀርቡ ሚዛናዊ ባልሆኑ ዘገባዎች ላይ ተጠያቂነት ማስፈን እንደሚገባ ተጠቅሷል።
 
ከዚያም ባለፈ በውይይቱ ላይ ወቅታዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መነሻ በማድረግ የውጭ ሀገራት የችሎት ውሎ ፣ የመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎ ገደብን በንጽጽር ለማሳያነት ቀርቧል።
Related stories   አጠያያቂው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኝነት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *