ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለትግራይ ሕዝብ ሲባል ትዕግስት ቅድሚያ እንደሚሰጠው ባስታወቁ ማግስት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልልን ለህገ መንግስትን አደጋ እንደሆኑ በመጥቀስ ደብዳቤ መላኩ የጉዳዩን መካረር የሚያረጋግጥ መሆኑ እየተሰማ ነው።

የትግራይን ክልል የምርጫ ደፋ ቀና ህገመንግስትን የሚጥስና ተቀባይነት የሌው እንደሆነ የፌደሬሽን ምክር ቤት የላከውን ደብዳቤ ክልሉ የማይቀበለው ከሆነ ቀጣዩ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል አልተገለጸም። ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ላይ የጠበቀ እርምጃ ለመውሰድ እንደመነሻ መሆኑ እየተጠቆመ ነው።

ሰሞኑንን በተካሄደው የፓርቲዎች ውይይት ክልሉ ወታደሮች በስፋት እየመለመለ እንደሆነ፣ በገጠር አካባቢ ድርቆሽና በሶ  እንዲዘጋጅ በማድረግ ላይ መሆኑ ተመልክቷል። በሌላ በኩል የፈንቅል አመራሮች በገጠር ነዋሪዎችን ምርጫ እንደሚመርጡ በመጠየቅ ባዶ ወረቀት ላይ እያስፈረሙ መሆናቸውንና ይህም ምርጫውን ተከትሎ  የሪፍረንደም ውሳኔ አድርጎ ለማዘጋጀት እንደሆነ አስታውቀዋል።

እነዚሁ ክፍሎች እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት ኤርትራ ወደ ሱዳን የሚወስደውን በር መዝጋቷን፣ ለዚህም ከሱዳን ጋር ስምምነት ላይ መድረሷን አስታውቀዋል። በአማራ ክልልም ትንኮሳ እንደበዛ በመጥቀስ ራስን ለመከላከል የመገደድ አዝማሚያ መኖሩን ተመልክቷል። በዚሁ መነሻ ውጥረት መስፈኑንን ለጉዳዩ የሚቀርቡና፣ ጉዳዩን የሚከታተሉ ባለሙያዎች እያስታወቁ ነው። በሌላ በኩል ድግሞ ብሄራዊ የሽግግር መንግስትና አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ከህወሃት ጋር ጊዜያዊ ህብረት የፈጠሩ ድርጅቶች እየወተወቱ ነው። የወልቃይት አስመላሽ ኮሚቴ መንግስት ጣልቃ እንዲገባለት እየወተወተ ሲሆን ምን አልባትም የውልቃይት ጉዳይ በሪፈረንደም እንዲወሰን የሚያድርግ ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚችል ተሰምቷል። ፋና የፌደሬሽን ምክር ቤትን ደብዳቤ እንደሚከተለው አስፍሮታል።

የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የጀመረውን ኢ-ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

ምክር ቤቱ ለትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ያቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የሕገ መንግስት ትርጉም እንደተሰጠበት አስታውሷል፡፡

በዚህም የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ምርጫን በወቅቱ ለማካሄድ ከአቅም በላይ የሆነ እክል ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ባለመደንገጉ እና ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ክፍተቱን በህገ መንግስት ትርጉም መሙላት ተገቢ መሆኑን በማመን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑንም አስታውሷል፡፡

Related stories   የ26 ዓመት ወጣት መንገድ በመጣሱ ተደብድቦ ለሞት ተዳረገ፤ ፖሊሶቹ ታስረዋል ተብሏል

ይሁንና የትግራይ ክልል መንግስት ይህን ውሳኔ ወደጎን በመተው በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ወስኖ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠናል ያለው ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ አንደቀጽ 102 መሰረት በፌዴራልና በክልል ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛነት ማካሄድ የሚችለው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ እንደሆነና በክልል ደረጃ የሚቋቋም ምርጫ ቦርድ አለመኖሩን ጠቅሷል፡፡

በመሆኑም የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት የወሰነው ውሳኔና የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት ያሳለፈውን ውሳኔ ያላከበረ ከመሆም ባሻገር ግልጽ የሆነ የህገ መንግስት ጥሰት ነው ::

በተጨማሪም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 (9) መነሻ በማድረግ ማንኛም ክልል ህገ መንግስቱን በመጣስ ህገ መንግስዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 12 መሰረት በአንድ የክልል መንግስት ተሳትፎ ወይም እውቅና ህገ መንግስቱን ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ህገ መንግስታዊ ሰርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ በግልጽ መደንገጉን ጠቅሷል፡፡

በመሆኑም የትግራይ ክልል ምርጫን ለማካሄድ የጀመረው እንቅስቃሴ ህገ መንገስቱን የሚቃረን፡ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥልና የኢዮጵያን የፌዴራል ስርዓት የሚጎዳ አካሄድ ነው ብሎታል፡፡

በተጨማሪም በህገ መንግስቱ አንቀጽ 50 (8) መሰረት ለፌደራል መንግስት የተሰጠው ስልጣን በክልሎች መከበር ያለበት መሆኑና የህገ መንግስት የበላይነት በሚደነግገው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 (1) መሰረት፡ ማንኛውም ህግ ወይም የመንግስት አካል ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ታውቆ የክልሉ መንግስት ህገ መንግስቱንና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ እንዲያከብርና የጀመረውን ኢ-ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም ሲል ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

Related stories   ከአሜሪካ የጥላቻ ንግግርን የሚያሠራጩ ኢትዮጵያዊያን እንዴት በህግ ይጠየቃሉ?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *