ስልጣኔው አይሏል። ጠባብ፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ፣ አሸባሪ፣ ሽብረተኛ … የፍረጃ ቋንቋዎች ፋብሪካቸው በከፊል ሲዘጋ አንድ መለያ አበጅተው ሃውልት ተከሉ። ለሃውልቱ ምርቃት ከ300 ሚሊዮን በላይ ተረጨ። ድግሱ “ ቂጡን የጣለ” ነበር። ሞንስተሮች ደለቁበት። አዲሱ መፈረጃ “አሃዳዊ” !! ሆኖ ጸደቀ!! አሃዳዊ ጠቅላይ ሆኖ ጠቅላዩ ላይ አነጣጠረ። “አሃዳዊ” በካቢኔ ተሞሽሮ በከፍተኛ በጀት ወደ “ አሃዳውያን” ተራባ። የጅምላ ተሸካሚዎች ላይ ተጫነ። እነ ሙስጣፌም ከጸበሉ ተዳረሱ!! “ አሃዳዊያን ሊበሉህ ነው” የሚለው አስተምሮ በዲጂታል ጥብበኞች እንደ ኮቪድ ተሰራጨ። አሃዳዊይን!! ያበድው ፈገግ አለ።

እንደምን ከረማችሁ። ያበደው ነኝ። የኑሮ ግብግቡ ለያየን። እንኳን ለዛሬው የሚሊሺያ ሰልፍ አደረሳችሁ። እንኳን… ያበደው ሰላምታውን መጨረስ አልቻለም። ሮጠ። አዋጅ አለበት!!

ያበደው እርቃኑን ነው። ምናምኑም አደባባይ ነው ። እጁን እያውናጨፈ፣ አይኑንን እያጉረጠረጠ ይጮሃል። “ ሰዎች ” የሚናገረውን ሳይሆን መላመላውን እያዩ ይስቃሉ። እሱ አይስቅም ግን “ አዋጅ አዋጅ…” እያለ ያልሰማ ላልሰማ እንዲያዳርስ ይማጸናል።

“ አዋጅ አዋጅ ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው። ወሃ ሲወስድ እያጫወተ ነው። ወሃ ሲወስድ በሙዚቃ ነው። ውሃ ሲወስድ እያደደበ ነው… እናንተ የደደባችሁ ነቁ፣ እናንተ በሁሉም ሰፈር ያላችሁ ዋልታ ረገጦች፣ የደም ላይ ዳንሰኞች …” እያለ ያስጠነቅቃል። ሰሚ የለም። ሁሉም ብልቱን እያዩ ይሳለቃሉ። ብልት የሌለው ማን አለ? የብልት ውጤቶች በብልት ይስቃሉ። በራሳቸው አባት ላይ!! ምጽ …

“የሰማህ ላልሰማህ” እያለ ሲከንፍ ድንገት የሰማዕታት ሃውልት ጋር ሲደርስ ነቃ። ደነገጠ። ለሃውልቱ ክብር ሲል ተረጋጋ። ያበደው ሰማዕታትን ይመርጣል። ሳያውቁ ተነድተው የተደፉትን “ሰማዕት” ይላቸዋል። ያስደፏቸውን ግን “ ሉሲፈሮች” ሲል በአጋንንት አለቃ ይመስላቸዋል።

ረጋ ብሎ ሃውልቱ ስር ተቀመጠ። የለደለደውን ምራቁን ተፋው። መሬቱ ላይ ሳይሆን አለቃቸው ላይ ለደፈበት። ከዛም እጁ ላይ የያዘውን ካርቱን ቢጤ እያየ አዲስ የሚመጡ “ ሰማዕታት” ን ስም ዝርዝር እየጠራ ለቀደሙት “ ሰማዕቶች” አስተዋወቀ። ቤት ለንቦሳ እንዲሏቸው አሳሰበ።

አዎ !! እዛም እዚህም የጦርነት አታሞ ይደለቃል። እዛም እዚህም የጥላቻ መርዝ ይረጫል። ከየ አቅጣቻው ለየትኛዋ አገራቸው እንደሚተጉ ባናውቅም ክተት ይጠራል። አጫፋሪዎችም ያጫፍራሉ። ትንተናው፣ ማብራሪያው ሁሉ የትኛዋን አገር ለማትረፍና ምን አይነት አገር ለማስቀመጥ፣ ምን አይነት መሪና አመራር ለመትከል እንደተፈለገ ፍንጭ አይሰጥም። “ ተሸካሚዎች” ማጣራትና መመርመር አያውቁም። ሳያነቡ፣ ሳይገባቸው፣ ስያኝኩ ይውጣሉ። ውጠው ይተፋሉ። ተፍተው ያስተፋሉ። ትፋት ከዳር እሰከዳር በክሎናል። ማስተዋል የለም … ያበደው ተቆጣ !!

ቦሰና ከሚስትም በላይ ናት። ያበደው እንደ አጅማመሩ ቢሆን ኖሮ ዛሬ … ቦሰና “ ነ – ዲሲ” ትላለች። ተወኝ ባክህ ማለቷ ነው። ነብሰ ገዳይ ደረታቸው ላይ ለጥፈው “ እኔም እገሌ ነኝ” ሲሉ ያማታል። ቀለም አልገባትም። የትምህርት ደረጃ ስትጠየቅ “ ልበ ብርሃን በሉት” ነው እምትለው። ልበ ብረሃን ቦሰና እያለች ሌሎች “ፕሮፌሰር” !!

ያበደው ሲብስበትና አናቱ ሲግል ቦሰና ታስፈልገዋለች። ውሻው ደጎልም ትዝ ይለዋል። ደጎል የህጻናት ፊልም ይወዳል። ዛሬ ድንገት ከውጭ ተገናኙ። ደጎልም ከ “ ሰማዕታቱ” ሃውልት ስር ይቆፍር ነበር። ያበደው እንዳላየ አለፈው። ደጎል በአገጩና በመዳፉ ስር ዘልቆ መቃብሩን ይምስላ። ይምሳል። ይመሳል። ወደ ውስጥ እየዘለቀ ማሰ። መግቢያውን ካበጀ በሁዋላ ቀና ሲል ተያዩ። ደጎል ጭራውን ሳይቆላ ተፈናጥሮ አሳዳሪውን ገፋው። እየመራ ወደማሰው ማስገቢያ መራው።

ያበደው በደረቱ ተንሸራቶ እመቃብሩ ገባ። ሰባ ሺህ ሲደመር መቶ ሺህ ከዛም በላይ ምስኪኖች ተኮልኩለዋል። ውስጡ እንደ ስታዲየም ነው። ዙሩያው ተከቧል። ሁከት ይሰማል። ክልል የለም። ብሄር የለም። ጎሳ የለም። ጎጥ የለም። አክቲቪስት የለም። ደላላ የለም። ቲቪ የለም። ሬዲዮ የለም። ጠብ መንጃ የለም። ገጀራ የለም። ቀረርቶ የለም። መፈረጅ የለም። ምርጫ ግን አለ።

ቀኑ የምርጫ ነበር። ምርጫው አንድ ነው። ሪፈረንደም የሚካሄድበት። ሪፈረንደሙ የክልልነት ጥያቄ አይደለም። የመገንጠል ጥያቄ አይደለም። ተጨማሪ “ ሰማዕታትን እንቀበል ወይም አንቀበል” የሚል ነው። ድምጽ መስጠት የተፈለገው ከስጋት ነው።

እዛም እዚህም የሚመታው የመጨራረስ አታሞ እዛ ድረስ ተሰምቷል። የላይ ነዋሪዎችን ኮሮና፣ የታች ነዋሪዎችን ጦርነት አስግቷቸዋል። የድምጽ መስጠት ስነስረዓቱ ከመከመሩ በፊት አንድ ቅንድባም መሬት ለመሬት የሚጎተት ቀይ ካፖርት ለብሶ ንግግር ማድረግ ጀመረ። ይህን ጊዜ ያበደው ጆሮውን አቀና። ንግግሩ በብሄራዊ ቋንቋ አልነበረምና አስተርጓሚ ፈለገ።

ተናጋሪው “ እንግዳ እንዳለ ስለገባኝ” አለና ያበደው በሚገባው ቋንቋ ተናገረ። በብሄር ከፋፍለን፣ በጎሳ አቧድነን። በጥቅም ታውረን። ማገድናችሁ። ወንድም በወንድሙ ላይ አስነስተን በላናችሁ። እኛ በተለይ እኔ ወደ እናንተ ስመጣ እጃችሁን ዘርግታችሁ ተቀበላችሁኝ።… ያበደው ምን እየሰማ እንደሆነ ማመን አቃተው። ተርበተበተ።

ተናጋሪው ቀጠለ። እኔ ዛሬ እንዴት እንደምጸጸት ሄዶ የሚናገር ምስክር ስለለ ነው የምናዘዘው። የጅምላ ሞት ይብቃ!! ዛሬ ድምጽ ሊሰጥ ነው። ካሁን በሁዋላ “ ሰማዕት” ብሎ ነገር የለም። በሃጫሉ ዘግተነዋል። ካሁን በሁዋላ የሰማዕት ምድር ሞልታለች። ተስማምታችሁ ጣጣችሁን እዛው ጨርሱ በሏቸው … ድምጽ የሚሰጡት ጮሁ። ጭብቸባው ከምድር በላይ የቆመውን ሃውልት አናጋው። አንገዳገደው። ይህን ጊዜ አንድ ትልቅ ድምጽ ተሰማ። ፍንዳታ

ደጎል ያበደውን እየጎተተ ወጡ … ያበደው ወደ ቦሰና ሄደ። ደጎል የስራውን ለቦሰና አጫወታት። ቦሰና ለደጎል ክበረት ሰጠች። ቡና ተጣደ። “ሃጫሉ” አለች። እንባዋ ቀረረ። ፎቶውን እየለጠፉ የሚቆምሩትን ረገመች። እርጥብ ልጁን መረቀች። ወደ ላይ አንጋጣ “ እመብርሃን “ አለች። በሆዷ ፍትህ ናፈቀች። መለስ ብላ የሰማችሁትን አሰሙ። ቢሰሙም ባይሰሙም ተናገሩ።

እንጀራ ቀረበ። ሽሮውን እያፈሰሰች ለካ “እንጀራ አትብሉ ተብሏል” ስትል ፈተለች። ደጎል ቸዋታው እንደገባው ሆኖ ፈገግ አለ። ቦሰና “ ውሻ አሉህ” ስትል ደጎልን ከዘመኑ ፈላስፎች ጋር አወዳድራ አነገሰችው። ቦሰና የቱለማ ወገን ናት። የልጅነት ባሏ “ዲቃላ” በአዲሷ አገራቸው ያበደው ቦታ የለውም። ቦሰና ማዕዱን በጸሎት ባረከች።

“ይህንን የጤፍ እንጀራ ስለሰጠኸን ተመስገን፤ እንጀራ በወጥ ድንቅ ምግባችን ስለሆነ ተመስገን። ጽንፈኞች አፋቸውን አዘጋልን። ጽንፈኛነትን በጽንፈኝንተ የሚታገሉትን አደብ አስይዝልን፤ ጽንፈኝነት ኢትዮጵያን አያቆማትምና እርዳን። ሁሉም ጽንፈኛ ሆነዋልና አምላክ ሆይ አብዛኞች የዋሆችን ተመልከትና አገራችንን ፈውሳት። እንደቀደመው ዘመን ገንፎ እንድንጎራረስ አድርገን። እመብረሃን ጥቂት ጽንፈኞች ረብሽውናልና እርጂን። ደም ዳግም እንዳይፈስ እብሪተኞችን መላ በይልን። ልጆቻችን እንዳይጫረሱ አንቺ አማልጂን…”

ያበደው ጸሎቱ ቢረዝምም ሰማ። “ አሜን ” አለ። በቦሰና ይመካል። ልቧንና አስተሳሰቧን ያመልከዋል። አሁን የሚቀረው ከቦሰና ጋር ማረፍ ነው። ቦሰና እንደ ስሟ ጭድ ናት። እንደ ጥቅጥቅ ጫካ መደበቂያ ናት። ቦሰና ደስ ሲላት ታስታውቃለች፡፤ ቡናው ኮረንቲ ነበር። እንቅልፍ የለም። እናም እንጠጋጋለን። እሞቃታለሁ። እገጥማታለሁ። ድርና ማግ ሆነናል። እየተሳሳቅን አንድ ሆነ። ቦሰና ስታሳስቅ መጣበበቅ ነው። ውሃ ግን እያሳሳቀ ይወስዳል። የሰማእትም ደጅ ሞልቷል። ለማንም ቦዘኔ ነብሰ ገዳይ እኔም እገሌ ነኝ የምትል ወደ ቀልብህ ተመለስ። ነገም ሌላ ቀን ነው። አሁን እየስፋሁ ነው … ሻሎም!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *