ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ግብጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የምታወጣውን ጊዜና ወጪ ለአባይ ተፋሰስ ሥርዓተ ምህዳር መጠበቂያ ማዋል አለባት “

ግብጽ ለዘመናት ስትሄድበት እንደነበረው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የምታወጣው ጊዜና ወጪ ለሥርዓተ ምህዳሩ መጠበቂያ ማዋል እንዳለባት የኢነርጂ ባለሙያና የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባል ዶክተር ብርሃኑ ግዛው አስታወቁ። በግድቡ ዙሪያ ያሉ የውሸት ትርክቶችን በጋራ ቆመን እውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ ማሳወቅ ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል።

ዶክተር ብርሃኑ ግዛው በተለይ ከአዲስ ዘመንጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ግብጽ የአባይ ውሃን በብቸኝነት

 ለመጠቀም ካላት የዘመናት ፍላጎት አንጻር ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ብዙ ሀብትና ጊዜ አባክናለች።አሁን ግን ለዚህ የምታውለውን ሀብትና ጊዜ የአባይ ተፋሰስ ስነ ምህዳር ለማልማት ልትጠቀምበት እንደሚገባ አመልክተዋል ።

አሁን መንግስት የጀመረውን የደን ተከላ ሂደት ግብጽ መደገፍና ማገዝ እንደሚኖርባት ያመለከቱት ዶክተር ብርሃኑ፤ በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚደረገውን የተፈጥሮ ሀብት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በራሳቸው ተነሳሽነት ማገዝ ያለባቸው የመጀመሪያዎቹ የታችኞቹ የተፋሰስ አገራት መሆን እንደነበረባ ቸው አስታውቀዋል።

“አሁን በተያዘው ድርድር የሀገራት የውሃ አበርክቶን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች አካባቢ የአፈር ለምነት መራቆት አለ ። የገጸ ምድር እንጂ የከርሰ ምድር ውሃ እጥረት ስላለ በዚያ አካባቢ ስርዓተ ምህዳሩን የመቀየር ስራ መሰራት ይኖርበታል።ይሄ ጉዳይም አንዱ የስራ አካል ተደርጎ መታየት አለበት። ምክንያቱም ዘመናዊ የሀይል አቅርቦት ሲኖርና ማቅረብ ሲቻል የማገዶ እንጨቱና በረሃማነትንም ይቀንሳል “

ግብጽ አንድ ዛፍ ሳትተክል ለዘመናት ብቻዋን ባለቤት ሆና የተጠቀመችበትን ውሃ እንዳይደርቅ መስራት እንደሚጠበቅባት ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ከጀርባ በመስራት ሳይሆን በአጋርነት መንፈስ ለስርዓተ ምህዳሩ አስተዋጽኦ በማድረግ እና በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባት አሳስበዋል ።

“አሁን በተያዘው ድርድር የሀገራት የውሃ አበርክቶን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች አካባቢ የአፈር ለምነት መራቆት አለ ። የገጸ ምድር እንጂ የከርሰ ምድር ውሃ እጥረት ስላለ በዚያ አካባቢ ስርዓተ ምህዳሩን የመቀየር ስራ መሰራት ይኖርበታል።ይሄ ጉዳይም አንዱ የስራ አካል ተደርጎ መታየት አለበት። ምክንያቱም ዘመናዊ የሀይል አቅርቦት ሲኖርና ማቅረብ ሲቻል የማገዶ እንጨቱና በረሃማነትንም ይቀንሳል “ብለዋል ።

Related stories   አውሮፓ ህብረት - ላለፉት 28 ዓመታት በኢትዮያ ተላላኪ መንግስት እንደነበር ለኢትዮጵያ ህዝብ አመነ

እንደ ዶክተር ብርሃኑ ገለጻ፤86 በመቶው አባይ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ መሆኑ ግልጽ ነው። ይሄ ውሃ ለዘመናት ሲፈስ በተለይም የደጋውን የሰሜኑን ክፍል አፈር አራቁቶ በመውሰድ በድህነት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲወድቁ አድርጎ የቆየ ከመሆኑ የተነሳ መልሶ የማገገሚያ ስልቶችም መታሰብ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ይሄ አካባቢ የተራቆተ ሆኗል። በምግብ አቅርቦት በኩል ራሱን በራሱ ለመሸፈን እየተንገዳገደ የሚገኝና በጥረት ብዛት እየኖረ የሚገኝ በመሆኑ የአካባቢውን ስነምህዳር የማስተካከል ስራ መሰራት ይኖርበታል።

በግድቡ ዙሪያ ያሉ የውሸት ትርክቶችን በጋራ ቆመን እውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ ማሳወቅ ይኖርብናል ያሉት ዶክተሩ፤ በቴክኖሎጂ አለም እየተቀራረበ በሚገናኝበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።የሕዝብ ቁጥራችንም እያደገ መጥቷል።ፍላጎታችንም እያደገ ነው። በነበረው መቀጠል ስለማይቻል ነገሮች ይለወጣሉ። ለኢትዮጵያ ጥሩ የሆነ ተስፋ ሲታይ መቀበል ሊያስቸግረን አይገባም። ለራሳችን የሆነን ነገር መቀበል ካልቻልን ችግሩ የከፋ ሊሆንብን ይችላል ሲሉ አብራርተዋል ።

“የሀይል(ኢነርጂ) አቅርቦት ጉዳይና የውሃ አቅርቦት ለዜጎች መሰረታዊ ጉዳይ እንጂ ፖለቲካዊ ተደርጎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም።መለያየት አይገባንም።ችግሮች የትኛውም አገር ይኖራሉ የእኛ አገር ግን የተወሳሰበና የከፋ ሊሆን ይችላል። ከዚያ ችግር የመውጫ መንገዶችን ካልደገፍን ከችግሩ እንዴት መላቀቅና መውጣት ይቻላል?” ብለዋል ።

እንደ ዶክተር ብርሃኑ ገለጻ፤ ጊዜው እንደ አገር በአንድ ላይ በመቆም፣ ማንነታችንን የምናስመሰክርበት ነው። የ21ኛውን ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ መላበስ ይገባናል።በፖለቲካ አመለካከት፣በጎሳ፣በቀለም …ወዘተ እየተራኮቱ መሰረታዊ የሆነውን የአገርን ጥቅም ማሳጣት እና የአገርን ሰላም ማወክ በጣም የወረደ ድርጊት ነው።

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል

“አገርን አፍርሶ ከየት ላይ ተኩኖ ስለምን ሊያወራስ ይችላል? ስለዚህ ማንኛውም ነገር የሚከናወነው አገር ስትኖር

 ነው።አገርን ማፍረስ እንዴት ይታሰባል።›› ሲሉ ይጠይቃሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ሀገሪቱ ብዙ የስራ እድል ያልተፈጠረላቸው ዜጎች ያላት አገር ነች።ስለዚህ መፍጠን ይገባል። የአባይ ግድብ ብዙ የስራ እድል ይፈጥራል።ገጽታን ይቀይራል። ኢትዮጵያን በአፍሪካ ካርታ የተለየ ቦታ እንዲሰጣት ያደርጋል።ለሌሎች የተፋሰሱ አገራት ሁሉ ልክ እንደነጻነት ቀን ድል ትሆናለች። ሌሎችን የአፍሪካ አገሮች አስተባብረንም ጭምር መሆን ያለበት እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ግብጽ እንድትጎዳ አይደለም፤ መሆን ያለበትንና እውነታውን እንድትቀበል ማስቻል ተገቢ ነው”ብለዋል ።

ሌላው ቀርቶ በፖለቲካው መድረክም ተሰሚነታችንን የምናሳይበት መድረክ መሆኑ ነው የሚገባኝ። ይህ ጉዳይ ጎልቶ የወጣ ተጨባጭ ሐቅ ነው። በመሆኑም ለድርድርም ለክርክርም የሚቀርብ ጉዳይ አይሆንም።

በመንግስት በውጭ አገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶች፣ ዳያስፖራው እና ማንኛውም ዜጋ በቀላሉ ከድረገጽ አውርዶ ሊጠቀምበት የሚችል አንድ ወጥ ስለአባይ ግድብ ሕጋዊ ሰነድ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ብርሃኑ፤ ሰነዱ በጥቂት ገጾች የተዘጋጀ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ለምን አባይን መገደብ እንዳስፈለገን፣ከአለም አቀፍ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች የውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ፣ከአገሪቱ ገጸ ምድር ፣ የኃይል አጠቃቀም እና የተፋሰሱን አገራት ጥቅም እንደማይጎዳ፣ ፍትሃዊ መሆኑን የሚገልጽ፣የኢትዮጵያን ውሃ አስተዋጽኦ የሚገልጽ፣የድህነት ደረጃችንን የሚያሳይ ፣ይሄን ዘመናዊ ኢነርጂ ማስፋፋት ብንችል ለራሱ ለአባይ ውሃ የፍሰት መጠን በቀጥታ ከሚያስገኘው ፋይዳ በተጨማሪ በተዘዋዋሪ በስነ ምህዳሩ ላይ ስለሚያበረክተው አስተዋጽኦ የሚገልጽ ሰነድ ማዘጋጀት እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።

ሁሉም የመሰለውን ከሚያቀርብ አንድ ወጥ ሰነድ በውጭ ጉዳይና በመስኖ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካኝነት ተዘጋጅቶ መቅረብ አለበት ያሉት ዶክተር ብርሃኑ፤ ሰነዱን ማንኛውም ሰው ለስብሰባዎች፣ለስልጠናዎች እና ለፈለገው አላማ አውርዶ ሊጠቀምበት ይችላል ብለዋል።‹‹ስለዚህ አንድ ወጥ ሰነድ መዘጋጀት አለበት ብዬ አምናለሁ። ይሄ የሚዘጋጀው በአንድ ቋንቋ ብቻ አይደለም። በተለያዩ መንገዶች መዘጋጀት አለበት። በትርጉም እንዳይንሻፈፍ በአገር ውስጥም በውጭም ተርጉሞ ማቅረብ ተገቢ ነው›› ሲሉ ጠቁመዋል ።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

እንደ ዶክተር ብርሃኑ ማብራሪያ፤ዲፕሎማቶች ሰነዱን በያሉበት አካባቢ ማህበረሰብ በቀላሉ በሚገባውና በሚረዳው ቋንቋ አስተርጉመው ማቅረብ አለባቸው። ማንውኛም ዜጋ ያንን አውርዶ ጓደኛውንም ቢሆን ማግባባት ይኖርበታል።ሰዎች በተለያዩ መንገዶች በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች የዲፕሎማሲ ስራን መስራት ይኖርባቸዋል። አባይን በተመለከተ መረጃ ለማግኘት ከተደራዳሪዎች ብቻ የሚጠበቅ ሊሆን አይገባም። በኢትዮጵያ በኩል ተዘጋጅቶ በቀላሉ የሚገኝ ሕጋዊ ሰነድ ካለ ሰዎች እንዲያመዛዝኑ እድል ይፈጥርላቸዋል። ምክንያቱም ብዙው ነገር እውነት ነው። ስታስቲክስ ነው።መረጃ ነው።ለምን እንደምንፈልገውም ግልጽ ነው”ብለዋል ።

የአባይ ውሃ 86 በመቶ ከኢትዮጵያ እንደሚሄድ (እንደሚመነጭ) ብዙ ሰዎች አያውቁም። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን ለዘመናት የተንሻፈፈውን አመለካከት ለማስተካከል ወጥ ሰነድ ቢዘጋጅ የሚል ሐሳብ አለኝ ሲሉ ተናግረዋል። ሁለተኛው መንግስትም ሆነ ሲቪል ማህበረሰቡ ልክ በጤና አጠባበቅ ላይ፣በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ላይ በስነ-ተዋልዶ ዙሪያ እና በሌሎችም በርካታ ዘርፎች የሚደረገውን ሕብረተሰቡን የማስተማር፣ የማስረዳትና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በአባይ ጉዳይ ላይም መደገም እንዳለበትም አስታውቀዋል ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012

 ሙሐመድ ሁሴን