ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ለዘመናት የታገለለትን የፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ግቡን እንዲመታ ለማገዝ ከየትኛውም በሀገራችን ካለ የፖለቲካ ፓርቲ በላይ እራሱን በማደራጀት እያዘጋጀ የሚገኝ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።
የፓለቲካዊ ለውጥ ወይንም ሽግግር አስተማማኝ ዋስትና ተቋማት ብቁ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው መቆም መጀመራቸው እና መቀጠላቸው ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ አያጠራጥርም። እነዚህ ለአንድ ሀገር ሕዝብ በሰላም እና በአንድነት የመኖር ዋስትናን የሚያረጋግጡ ተቋማት ከየትኛውም የግለስብም ሆነ የፓርቲ ፍላጎት እራሳቸውን በማላቀቅ በሂደት በሕግና በሕግ ብቻ የሚሠሩበት ሁኔታ እየፈጠሩ መሄድ እንዳለባቸው ኢዜማ ያምናል፤ ለሂደቱም ውጤታማነት በፅናት ይታገላል። በተለይም የሕግ የበላይነትን ማስከበር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፤ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እና የሀገር አንድነትን ለማረጋገጥ ዋነኛው ግብዓት ነው። በዚህ ደረጃ የሚሠሩ ተቋሞችን መገንባት የረጅም ጊዜ ሥራ እንደሚፈልጉ ብንረዳም ሕግን ማስከበር የሚገባቸው ተቋማት የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽር ተግባር ላይ ሲሳተፉ መመልከት ደግሞ አሰዛኝ ክስተት ይሆናል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአንባገነናዊ ሥልጣኑ የተባረረው እና ለውጡ የመጣባቸው ኃይሎች እንዲሁም ለውጡን ራሳቸው በቆፈሩት ቦይ ብቻ እንዲፈስ የፈለጉ ቡድኖች በጋራም ሆነ በተናጥል በፈጠሯቸው ትርምሶች ክቡር የሆነው የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ ንብረት ጠፍቷል። በእነዚህ ግዚያት ውስጥ የክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥት አስተዳደሮች እንዲሁም የፀጥታ እና የፍትህ አካላት ባሳዩት ከፍተኛ የዝግጅትና የአፈፃፀም አቅም ውሱንነት ለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት በግልፅ ይቅርታ ሊጠይቁና አስፈላጊውን ካሳ ሊከፍሉ እንደሚገባ ማሳሰባችን ይታወሳል።
ሕዝብ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስክንሻገር ድረስ ከቀጥተኛ ውክልና ፍጹም ባነሰ ስምምነት ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ፈቅዶ ከለውጡ በፊት ያጠፋውን ጥፋት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር አግዞ እንዲክስ ሌላ ዕድል የተሰጠው ገዢው ፓርቲ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች (እኛንም ጨምሮ) ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሊያዘገዮን ከሚችሉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ መታቀብ የሚገባን ወቅት ላይ ደርሰናል። በተለይ ገዢው ፓርቲ ከመቼውም ጊዜ በላይ የያዘው ሥልጣን የሰጠውን የሕግ የበላይነትን የማስከበር ዋነኛ ኃላፊነት እና ታሪካዊ አደራ አሁን የደረስንበት ወቅት ግድ የሚለውን ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ብስለት ጋር መወጣት ይገባዋል። የሕግ የበላይነትን ማክበር በጣም አስፈላጊው ግን ደግሞ በጣም ትንሹ ግዴታው ነው ብለን እናምናለን።
በሀገራችን ያሉ የፍትህ ተቋማት በተግባር የሚፈተኑበት ወቅት አሁን ነው። ከየትኛውም አካል የተፈጠርን ወይምን ሊፈጠር ይችላል ከሚሉት ሥጋት ወይንም ከግለሰብም ሆነ ከየትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ ከሚመጣ ሙገሳም ሆነ ወቀሳ በራቀ መልኩ ፓሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ዜጎች የተቀላጠፈ እና እውነተኛ ፍትህ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚከበርበትን መንገድ በማረጋገጥ ማኅበረሰቡ በፍትህ ተቋማት እና ሥርዓቱ ላይ ለረጅም ጊዜ ያጣውን ዕምነት መልሶ መገንባት የሚጀምሩበት ወቅት መሆን ይገባዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥራ እስፈፃሚ አባል እና የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ሂሩት ክፍሌ ከሐምሌ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለ22 ቀናት በፓሊስ ቁጥጥር ሥር ቆይተው ሐምሌ 29 ቀን በ6000 ብር ዋስ ከእስር ተለቀዋል። ሂሩት በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ «ለምን ታሰሩ?» ወይንም «ይፈቱ!» የሚል ጥያቄ ከማቅረብ ይልቅ ጉዳዩን በቅርበት ስንከታተል እና ሁሉም ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ ስንጠይቅ ቆይተናል።
ፓሊስ የዜጎችን መብት ለማስከበር እና አጥፊዎችን ለመለየት የሚረዳው ዜጎችን ከማሰሩ በፊት ከጥርጣሬ በላይ በወንጀል መሳተፋቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ እንዲኖረው የሚያስገድደውን መሰረታዊ መርህ በመተው ሂሩት በወንጀል ድርጊት ተሳታፊነት ጠርጥሬያቸዋለው በማለት ለሁለት ግዜ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል። ለሁለተኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ቀን ለፖሊስ የፈቀደው ፍርድ ቤት በተጨማሪው ቀናት ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ፖሊስ የተሰጠውን ትዕዛዝ ሳያከብር ተፈጽሟል ያለው ወንጀል 35 ቀን ካለፈው በኋላ ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት የፖሊስ ጥያቄን ውድቅ አድርጎ ሂሩት በ6,000 ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፖሊስ ፍርድ ቤቱ በግልጽ የሰጠውን ትዕዛዝ የመፈቻ ወረቀቱን አልቀበልም በማለት ጥሷል። ሂሩትንም ያለምንም ምክንያት በእስር እንዲቆዩ በማድረግ መሠረታዊ መብታቸውን ረግጧል። ይህ ድርጊት በምንም ዓይነት ተቀባይነት የሌለው እና ሕግን አስከብራለው ከሚል ተቋም በፍጹም የማይጠበቅ እንዲሁም አልፈነዋል ያልነውን የፖሊስ እራሱን ከሕግ በላይ አድርጎ የመቁጠር ፍጹም የሆነ የማን አለብኝነት ትዕቢት አሁንም እንዳለ የሚያረጋግጥ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል። ፖሊስ ተመሳሳይ ድርጊት ሌሎች ዜጎች ላይ በተከታታይ ይህ ድርጊት ለሕግ ግድ የማይሰጠው አንድ ፖሊስ ወይንም ጥቂት ፖሊሶች ያደረጉት ሳይሆን እጅግ አሳሳቢ የሆነ ተቋማዊ ችግር እንደሆነ ተገንዝበናል።
አሁንም ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ያለመቀበል መደበኛ ተግባር እንዳያደርገው ስጋት ያለን ሲሆን፤ ፖሊሶች በመንገድ ላይ ዜጎችን ስብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲሁም ዜጎች ሃሳባቸውን በሚመቻቸው መንገድ የመግለፅ መብትን ለማፈን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፤ ተቋሙ ለለውጥ ሩቅ መሆኑን የሚያመላክት ሆኖ አግኝተነዋል። መንግሥት ይህን ተቋም በማረም ማስተካከያ የማያድረግ ከሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጅምሮቻችን አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ፖሊስ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ መልሶ መገንባት ትልቁ የቤት ሥራው መሆኑን የሚገነዘብ እና ቅንጣት ታክል የሚያሳስበው ጉዳይ ከሆነ፤ ይህንን ድርጊት የፈጸሙ አባላቱ ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ፣ ለሂሩት እና ተመሳሳይ ድርጊት ለፈጸመባቸው ዜጎች ሁሉ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ እንዲሁም ከእንደዚህ ዓይነት አይን ያወጣ ማንአለብኝነት ከአሁን በኋላ እንዲታቀብ እናሳስባለን።
በዚህ አጋጣሚ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፖሊስ ለዜጎች መብት ግድ ሳይሰጥ በእስር ላይ ለማቆየት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና የዜጎችን መብት ለመጠበቅ ለሰጡት ውሳኔ ያለንን አክብሮት እና ምስጋና እንገልጻለን።
በመጨረሻም ከፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውጪ አሰተማማኝ ሰላም፣ ዕድገት እና አንድነት የተጎናፀፈች ኢትዮጵያን መገንባት የማይታሰብ መሆኑን ሁላችንም ተረድተን ለፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ሁላችንም ባለድርሻ አካላት የበኩላችንን አውንታዊ አስተዋፅዖ እንድናደርግ አጥብቀን እንጠይቃለን።
ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም
የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *