ዓለም አልሰማሁም እንዳይል – ሁሉም ወገን አልሰማሁም እንዳይል …

“ በሃጫሉ ድንገተኛ ግድያ እጅግ እንደሚያዝኑ፣ ነገር ግን የሃጫሉን ሞት ተከትሎ ” የሚባለውን አገላለጽ እንደማይወዱት የሚናገሩት አቶ ኦባንግ “ ድርጊቱ ሆን ተብሎ የታቀደ፣ መሪዎች ያሉት፣ ስምሪት የሚደረግበት፣ ስም ዝርዝር ያዘጋጀ፣ ሰዎችን የለየና በተለየው መጠን የሚደርሰው የጉዳት መጠንም ተለይቶ የተቀመጠ መሆኑን ለሚረዱ ጉዳዩን ካሃጫሉ ድንገተኛ ህልፈት ጋር ማያያዝ ልክ አይሆንም። ሃጫሉ እንዲ አይነት ድርጊት እንዲፈጸም አልሞም፣ አስቦም አያውቅም። ” ብለዋል። አያይዘውም “ ይህንን ድንቅ ልጅ / ሃጫሉን ቃል አወጡበት። ቃል ያጠፋልና እሱን ተገን አድርገው ዓላማቸውን አሳኩ። በአግባቡ ያዘጋጁትን እቅድ ተገበሩ፣ ህልፈቱን ተከትሎ የተስተጋባው የሃዘን መግለጫ ሳይሆን የተላለፈው ግደል፣ አቃጥል፣ አውድም… የሚል ብሄርን ለይቶ የሚያስጠቃ ጥሪ ነበር። ይህን መካድ አይቻልም። ይህንን መካድ…”

በኢትዮጵያ የተፈጸመው ግድያ በዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ማሳያዎችን ሙሉ በሙሉ በሚያሟላመልኩ የተፈጸመ መሆኑንን ማስረጃዎች ስለሚያረጋግጡ ኢትዮጵያ በተባበሩት የጄኖሳይድ ፍኖተ ካርታ እንደትያዝ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኦባን ሜቶ አስታወቁ። ይህ የሚደረገው ይህን አደጋ አለም ዓቀፍ እውቅና በማሰጠት ድራማውን የሚመሩት ወገኖች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንዲጠየቁ ለማስቻል ነው።በተመሳሳይ ነገ ዓለም ይህንን ጉድ አልሰማሁም እንዳይል ነው። ኦባንግ ሚዲያዎችንም አካተዋል።

የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሚቶ ከዓለም ታዋቂ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ከዚሁ ስራ ጋር ካሉ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ይታወቃል።በዓለም ዓቀፍ ተቋማት በኩል በቂ ተሰሚነት ያላቸው ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለዛጎል እንዳሉት በሻሸመኔና ዝዋይ ቡድን በመያዝ በአካል ተገኝተው መረጃ አሰባስበዋል። በዚሁም መሰረት እንዳረጋገጡት ጄኖሳይድ ተፈጽሟል። ማንም ሊሸፍነውና ሊያድበሰብሰው አይችልም። ይህ ለዓለም እንዲደርስ ይደረጋል። በዚህ ዙሪያ መለሳለስ የለም።

ሰዎች በዘራቸው፣ በእምነታቸውና በሰውነታቸው ከሚኖሩበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ በተደራጁ ሃይሎች ተገለዋል። ንብረታቸው ተቃጥሏል። ተዘርፈዋል። አቶ ኦባንግ ተጠቂዎችን በማነጋገርና የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ እንዳረጋገጡት የጸጥታ ሃይሎች ተባባሪ ሆነዋል። እርዳታ ከመስጠት ይልቅ አሻፈረኝ ብለዋል።

“የህዝብ ሰላም እንዲያስጠብቅ የተደራጀ ታጣቂ ሃይል ሰዎች ተመርጠው ሲገደሉ ዝም ካለ ጄኖሳይድ መካሄዱን የሚያረጋግጥ አንዱ ማሳያ ነው” ያሉት ኦባንግ ሜቶ ጥቃቱ ተጠንቶ፣ የስም ዝርዝር ተዘጋጅቶለት፣ በዕቅድ የተመራ መሆኑንን በግልጽ እንዳረጋገጡ አመልክተዋል። ይህም የጄኖሳይድ ማሳያ ነው።

ጄኖሳይድ በይፋ ከመጀመሩ በፊት 563 ሰዎች በስም ተመዝገበው ተይዘዋል። እነዚህ በዘራቸው፣ በእምነታቸውና በማንነታቸው ተለይተው ለጥቃት የተዘጋጁት ሰዎች የሚደርስባቸው ጥፋትም አስቀድሞ የተወሰነ ነው። እንደ ኦባንግ መረጃ ከሆነ ሶስት ዓይነት እርምጃዎች ይወሰዳሉ።

የተለዩትን የመግደል እርምጃ ብቻ የሚወሰድባቸው፣ ግድያና ንብረታቸው እንዲወድም የሚደረጉ፣ ንብረታቸው ብቻ እንዲወድም የተበየነባቸው መኖራቸውን አቶ ኦባንግ በአካል ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

ሃብት ያፈሩ፣ ነፍጠኛ የተባሉ፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑ ተለይተው መገደላቸው፣ ግድያው ከቦታ ቦታ የተለያየ ቅርጽ እንዳለው፣ በባሌና አርሲ ከተሰማራው ቡድን ጭምር ማረጋገጣቸውን የሚናገሩት ኦባንግ ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይህን መረጃ እንዳለ እንደሚያገኙት፣ ከዛም በተጨማሪ በአካል መጥተው እንዲመለከቱ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

“የሚገርመው” አሉ ኦባንግ “ የሚገርመው ከበርካታ ቤቶች መካከል ሁለት ወይም አንድ ቤት ተቃጥሎ ታያለህ፣ ሶስትና አምስት ደቂቃ ከነዳህ በሁዋላ በተመሳሳይ ተለይቶ የነደደ ቤት ይግጥምሃል፤ ጠጋ ብለህ ስታጣራ ቤቱ የተቃጠለባቸው ሰዎች በዘራቸው፣ በእምነታቸው ወይም በማንነታቸው የተጠቁ መሆናቸውን ልብ በሚሰብር ሁኔታ ትሰማለህ። ይህንን ማስተባበል ከሰውነት ደረጃ መውረድና ለጉዳዩ ተባባሪ መሆንን ያሳያል። ተወደደም ተጠላም ይህን አስነዋሪ ተግባር ዓለም እንዲዋጋው እንሰራለን። ጄኖሳይድ ተፈጽሟል። ”

ጄኖሳይድ ፈጻሚዎች ሊፈጁት ያሰቡትን ወገን አስቀድመው ስም እንደሚሰጡት የሩዋናዳን የቅርብ ጊዜ ትዝታ በማንሳት ያስታወሱት ኦባንግ በኢትዮጵያም አንድን ህዝብ መርጦ ጠላት የማድረግና የፍረጃ ስም በመስጠት የጥቃት ዒላማ እንዲሆን ተደርጓል። ፍረጃው የሚካሄደው አጥፊዎች ሰውን ሳይሆን አንድን ክፉ ተደርጎ የተሳለ ነገር እንደሚያተፉ በማሰብ ከህሊና ወቀሳ ውጪ እንዲሆኑ ለማድረግ መሆኑን አመላክተዋል። በሩዋናዳ ሁቶዎች ቱሲዎችን ሲጨፈጭፉ ሰው ሳይሆን ቢራቢሮ “ ኮክሮች” እንደገደሉ ነበር የሚያስቡት። በዚሁ ፍረጃ ሁቱዎች ቱሲዎችን ያለጸጸት በረሮ እያሉ ጨፈጨፏቸው። ኦባንግ በፍርሃቻና በሃዘኔታ ስሜት ውስጥ ሆነው “ እንደ ሩዋንዳ ሰፊ ቁጥር ይኑረው የሚል ፍላጎት እስከሌለ ድረስ በአገራችን የተፈረጁ የህብረትሰብ ክፍሎች አልፈዋል። ገና ማስፈራራት አለ። ወንጀሉን አሳንሶ የማየት ችግር አለ። ማንም ምንም ቢል ዓለም ይህን ወንጀል እንዲፋረደው ይደረጋል” ብለዋል።

“ እኔ ስበደል የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፣ ሌላው ሲበደል ትክክል ነው የሚል ዘር ላይ የተንጠለጠለ አስተያየት እጅግ የወረደ ነው” በማለት የተፈጠረውን የእሳቤ መዛባት የሚኮንኑት ኦባንግ፣ ይህ የአመለካከት ክሽፈት የመጣው ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት ከበቂ በላይ በተራገበው የዘር ፖለቲካ ሳቢያ ነው። እነዚህ ወገኖች ዛሬም ድረስ የአመለካከት ለውጥ እንዳይኖር ይሰራሉ ሲሉም ወቅሰዋል። ከእንዲህ ያለ አሳዛኝና አስደንጋጭ ቀውስ ምን እንደሚጠቀሙም እንደማይገባቸው ጠቁመዋል።

አሁን ሪፖርት እየተዘጋጀ መሆኑንን ኦባንግ አስታውቀዋል። ረፖርቱ እንዳለቀ የተባበሩት መንግስታት ኢትዮጵያን በጄኖሳይድ ፍኖተ ካርታ እንዲያስቀምጥ ይደረጋል። በዚህም ነገሮች ከዚህ በላይ ሄደው ወደ ሩዋንዳ ዓይነት ደም መፋሰስ እንዳናመራ የተባበሩት መንግስታት ጥበቃ እንዲሰጥ ጥረት ይደረጋል።

ልዩ ሃይል በሻሸመኔ “ ትዕዛዝ አልተሰጠንም፣ የራሳችን ሰዎች ላይ አንተኩስም አሉን” የሚል መልስ እንደሰጡዋቸው የገለጹላቸውን ጨምሮ በርካታ ልብ የሚነካ፣ ሰውነትን የሚፈታተን ማንም ሊያስተባብለው የማይችለውን ምስክርነት መያዛቸውን አቶ ኦባንግ አስታውቀዋል።

“ በሃጫሉ ድንገተኛ ግድያ እጅግ ማዘናቸውንና ፍትህ እንደሚመኙ፣ ነገር ግን የሃጫሉን ሞት ተከትሎ ” የሚባለውን አገላለጽ እንደማይወዱት የሚናገሩት አቶ ኦባንግ “ ድርጊቱ ሆን ተብሎ የታቀደ፣ መሪዎች ያሉት፣ ስምሪት የተሚደረግበት፣ ስም ዝርዝር ያዘጋጀ፣ ሰዎችን የለየና በተለየው መጠን የሚደርሰው የጉዳት መጠንም ተለይቶ የተቀመጠ መሆኑን ለሚረዱ ጉዳዩን ካሃጫሉ ድንገተኛ ህልፈት ጋር ማያያዝ ልክ አይሆንም፤ ” ብለዋል። አያይዘውም “ ይህንን ድንቅ ልጅ / ሃጫሉን ቃል አወጡበት። ቃል ያጠፋልና እሱን ተገን አድርገው ዓላማቸውን አሳኩ። በአግባቡ ያዘጋጁትን እቅድ ተገበሩ፣ ህልፈቱን ተከትሎ የሃዘን መግለቻ ሳይሆን የተላለፈው ግደል፣ አቃጥል፣ አውድም… የሚል ብሄርን ለይቶ የሚያስጠቃ ጥሪ ነበር”

ሃጫሉ በግፈኞች መገደሉን ተክትሎ “ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች በዘራቸው አማራ ስለሆኑ ወይም ሌላ ብሄር ስለሆኑ ወይም በዕምነታቸው ለይቶ ማጥቃት በየትናውም መስፈርት ተቀባይነት አይኖረውም” ሲሉ አቶ ኦባንግ ለጀመሩት ስራ ፍትህ ወዳዶች ከጎናቸው እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የናይሮኒ ቅርንጫፍ የዘር ከረጢት ውስጥ መቀረቀሩን ያወሱት አቶ ኦባንግ ይህ እንዲስተካከል እየሰሩ መሆናቸውን አመክተው እግረመንገዳቸው ልርሚዲያዎችም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሚዲያ ክፍት ማድረግቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ያመለከቱት ኦባንግ “ እኛ ግን ይህንን መብት በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም” ሲሉ ሃዘኔታቸው ገልጸዋል።

“ ነፍጠኛል ግደለው፣ ንብረቱን አውድም ” በሚል የዘገቡ ሚዲያዎች በሪፖርቱ ተካተው በዓለም ዓቀፍ መድረክ እንዲጠየቁ እንደሚሰራ ኦባንግ አስረግተው ተናግረዋል። የተጀመረ ስራ መኖሩንም አመልካተዋል። ይህ በእንዲህ እያለ ግን የጋዜጠናነት ስነ ምግባር እጅግ ትኩረት እንደሚያሻው ደጋግመው ገልጸዋል። በሩዋንዳ አንድ ሚዲያ ያስከተለውን መዘዝ በማንሳት ሚዲያዎች የሚያፈርስ ቃል ከመማረትና ከመከፋፈል በራሳቸው ተነሳሽነት ሃላፊነት ወስደው እንዲቆጠቡ ተማጽነዋል። መንግስትም አንድ ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በዝግጅትና በዕቅድ ለተፈጸመው ጄኖሳይድ የሚዲያ እንጅ እንዳለበት ያስታወቁት አቶ ኦባንግ በውጭ አገር ሆነው እልቂትን የሚያዙና የሚቀሰቅሱ ሰዎችና ሚዲያዎች ራሳቸውን እንዲያዩ መክረዋል። የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ወደ እርምጃ ሲዞር ማንም ከፍርድ ሊያመልጥ እንደማይችልም አስገንዝበዋል። ይህ እንዲሆን ኢትዮጵያ በጂኖሳይድ ፍኖተ ካርታ እንድትያዝ ከተባበሩት መንግስታት ጋር የሚደረገው ስራ ተጠናክሮ ይሰራል።

አቶ ኦባንግ በሻሸመኔና በዝዋይ ያናገሯቸው ወገኖች ያሉዋቸውን አጋርተውናል። ሪፖርታቸው ይፋ ሲሆን አካተን እንመለስበታለን።

ፎቶ ከአዲስ ዘመን የተወሰደ

ዝግጅት ክፍሉ

በዚህ ዜና መነሻነት አስተያየት ወይም ጥቆማ ያላችሁ ወገኖች በፊስቡክ ወይም በኢሜል ለትልኩልን ትችላልችሁ። ለህዝብ ጥቅም ሲባል ዝምታችሁን ሰብራችሁ ተሳትፎ ለምታደርጉ ምስጋናችን ሰፊ ነው።
 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *