“Our true nationality is mankind.”H.G.

የሽመልስ አብዲሳ ከአስር ወር በፊት የተደረገ ንግግር ዛሬ ለምን ይፋ ሆነ? ከብልጽግና አባል የተላከ ማስታወሻ

ከብልጽግና ፓርቲ አባል አንዱ ነኝ። ይህን ጉዳይ ወደፊት በዝርዝር ይፋ የማደርገው ቢሆንም ለጊዜው አጭር መረጃ ለመስጠት ይህቺን አጭር መልዕክት ልኪያለሁ።

ከኦሮሚያ ክልል መሪ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አንደበት የወጣውና አደባባይ የዋለው መረጃ በድብቅ የተቀዳ እንዳልሆነ አረጋግጥላችኋለሁ። ድምጹ በስልክ በድብቅ የተቀዳ እንዳልሆነ እመሰክራለሁ። በዚህ መነሻ የአቶ ሽመልስን ጥርት ያለ ድምጽ “በሚስጢር ሾልኮ እጃችን ገባ” የሚሉ ወገኖች ” ለራስ ሲቆርሱ” አይነቶች ናቸውና እርሱዋቸው።

እውነታው ይህ ከሆነ ይህ አነጋጋሪና በብልጽግና ውስጥ ያሉ ድርጅቶችን፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመሩት የኦሮሚያ ብልጽግና አባላትና አመራሮች፣ ከዛም በላይ ፓርቲውን ለሚያምኑና ድጋፍ እየሰጡ ላሉ መላው ኢትዮጵያዊያን ድንገተኛ የሆነው ይህ መረጃ የተለቀቀው ሆን ተብሎ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። እኔ ምስክር ነኝ። እነማን ይህን አደረጉ የሚለው ወደፊት እናየዋለን።

ግምገማውና የአቶ ሽመልስ የከረመ ንግግር

አቶ ሽመልስ በተደጋጋሚ በክልሉ የበታች መዋቅርና የጸጥታ አድረጃጀት ዙሪያ ቀደም ሲል ጀምሮ የነበረውን ድክመት እንዲያሻሽሉ መመደባቸው ይታውሳል። በአመራር ክህሎት ማነስና ብስለት ዙሪያ የልምድ ማነስ ችግር ቢኖርባቸውም በወቅቱ አስፈላጊም በበሩ። አደባባይ ሲወጡ እንደ መሪ መናገር እንዳለባቸው አስተያየት ቢሰጣቸውም ንግግራቸው የሌሎችን ፖለቲካዊ ሃይሎች ታሳቢ ያደረገ መሆኑንን መገንዘብ ግን ከአስተዋይ ወገኖች የሚጠበቅ ነው።

በድርጅቱ ካላቸው ከፍተኛ ሃላፊነት አንጻር ራሳቸውን እንዲያበቁ ድጋፍ የሚደረግላቸው አቶ ሽመልስ አቶ ለማ መሪ በነበሩበት ወቅት መረን ተለቆ የነበረውን የተጻራሪ ሃይሎች ለማረቅ ከፓርቲው በሚሰጥ አመራር ደክመዋል። ወቅቱ ያልረጋ በመሆኑ ስህተት ቢሰሩም ዛሬ ከህግ ማስከበር አንጻር ያላቸውን አቋም በሰሞኑ ንግግራቸው ማረጋገጥ ይቻላል።

አቶ ሽመልስ ሰሞኑንን በሚታወቅና በሚታወቅ መድረክ የተገመገሙ መሆኑ አይካድም። በዚሁ ግምገማ የሚወስዱት የድራሻ ሃላፊነት እንዳለ በመጠቆም የከረመው ንግግራቸው ዛሬ ይፋ እንዲሆን የተደረገበትን ምክንያት ማጤን ግድ ሆኖ እንደሚሰማኝ ለመግለጽ እወዳለሁ።

በንግግሩ ውስጥ አላስፈላጊ የሆኑንና አጋሮችን የሚያበሳጩ ሃረጎች፣ መፍክሮች ወይም ሴራ መሰል ተጋባሮች ቢካተቱም በወቅቱ ግለት ከወራት በፊት ይህ አቋምና ንግግር ምን አልባትም አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ራቅ አድርጎ በማሰብ ስሌት መስራት ይገባል።

የሰሞኑ ዘር፣ ማንነትና እምነት ላይ ያተኮረ ጥቃት

የቀደሙት ግምገማዎች እንዳሉ ሆነው ሰሞኑንን ህዝብ በይፋ ያየውና እንባውን የተራጨበት አስከፊ ጭፍጨፋ ተከትሎ ከተገመገሙት መካከል ከአካባቢው አመራሮች፣ የጸጥታ መዋቅር በተጨማሪ አቶ ሽመልስ ዋናው ነበሩ። ይህ አይካድም። በይፋ ባልተነገረው ግምገማ አቶ ሽመልስ ከሃላፊነታቸው ጥንካራ በትር ወርዶባቸዋል። ኣሳቸውም የተጋሯቸው ጉድለቶች አሉ። ይሁን እንጂ ድርጅታችንን አውራ ታጋይ ሆነው የተጣቡ ተንሸራታች ሃይሎች በጎን የመሰረቱት ግንኙነት ጉዳት ማስከተሉን መካድ አይቻልም። ብዙ ሊገለጹ የማይችሉ ሸፍጦች ተሰርተዋል። ድርጅታችንን ለማክሰም ሁሉ ስምምነት የተፈጸመበት ኩዴታ መስለ ክህደት ከሚተቀሱትና ከከሸፉት ውጥኖች መካከል የሚጠቀስ ነው።

በኦሮሚያ ክልል እሳቸው መሪ ሆነው እንዲህ ያለ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም በበነጋታው ራሳቸውን ከሃላፊነት ማንሳት እንደነበረባቸው፣ ከዛም በሁዋላ በእሳቸው አመራር እንዲህ ያለ አሰቃቂ ድርጊት በመፈጸሙ አደባባይ ወጥተው ይቅርታ መጠየቅና ለተጠያቂነት መዘጋጀት አለባቸው ከሚለው እምነት ጀመሮ በርካታ ትችት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ገዢ ፓርቲ ቀርቧል። ይህ እንዳለ ሆኖ ይህንን እውነት በመቀበል የዳግም ማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጋቸውን ግን አውቃለሁ። ለተግባራዊነቱም አመራር እየሰጡ ነው። ይህንን ስል ለመሸፋፈን ሳይሆን እንዳንደነቃቀፍ የሚረዳንን መንደርደሪያ ለማጋራት ነው።

ማንም ሊሸፍነው በማይችለው ደረጃ በእቅድ የተካሄደውን ግድያና ዘረፋ ተከትሎ አቶ ሽመልስ ቀደም ሲል ከተሰጣቸው የአቅም ማጎልበትና ስል ፖለቲከና እንዲሆኑ ከተሰጣቸው ምክር አንጻር፣ በድርጅታችን ውስጥ ያለውም ሁለት ቦታ የማነከስ ችግር የሚረዱ አካላት ድርጅቱ ግምገማ ሲቀመጥ አዲስ ስልት ነደፉ። ስልቱም ይህ አሁን በየማህበራዊ ገጹ የተበተነውን ንግግር ሆን ብሎ ማሰራጨትና መጠየቅ ሲመጣ የብሄር ዋሻ ውስጥ መሸሸጊያ ለማግኘት ሲባል ነው። ይህንን ሃሳብ የድርጅቱ ግምገማ ቁንጽልን ውሳኔ ሳይሆን ሙሉ መግለጫ መልስ የሚያበጅለት ይመስለኛል። ካልሆነም ከላይ እንዳልኩት እመለስበታለሁ።

የተለቀቀው ንግግር – ማመልከቻ

በብልጽግና ውስጥ ያሉ ድርጅቶችን ቅር በሚያሰኝ፣ ለጽንፈኛ አመለካከት ተጠቂ ኦሮሞዎችን በሚያስደስት መልኩ ከወራት በፊት በአንድ መድረክ ያቀረቡትን ዲስኩር ሆን ብለው በዚህ ሰዓት ይፋ እንዲሆን ያደረጉት እየተካሄደ ባለው ግምገማ እርምጃ የሚወሰድባቸው አካላት ” ለኦሮሞ መብት ይህንን ብዬ በመታገሌ ነው” በሚል ማመልከቻ ለማስገባት ነው። ምንም ሆነ ምን ድርጅታችን የማጽዳት ተግባሩ አይቆምም። እንኳን ዛሬ ምንጣሮው ከዳር በደረሰበትና የታሰበው መፈንቅለ መንግስት በከሸፈበት፣ቀደም ብሎም ቢሆን ህገወጦችን አደብ የማስገዛቱ አካሄድ እውን ሊሆን ዳር ደርሶ ነበር።

ሁለት ቦታ የሚረግጡት አድርባዮች በሚያቀባብሉት መረጃ መነሻ ህግ ተጋባራዊ ሳይሆን ለመቅደምና አገሪቱን አተራምሶ ከተቻለ በሃይል፣ ካልተቻለ በሽግግር ስም ግንባር ቀድመው ሊያዳሽቁን የተነሱ ሃይሎች ባላቸው የውስጥ ቦርቧሪ አማካይነት እጃቸው ላይ ያለውን መረጃ ለክፉ ቀናቸው አዋሉት። በግምገማው የሚወሰነውን መሰረታዊ እቀባ ከወዲሁ ለማጠልሸት ተጠቀሙበት። ዓላማቸው ይህ ባይሆን ኖሮ ለወራት ይህን መረጃ አሽገው ባላስቀመጡት ነበር። ድሮውኑ ይፋ ባደረጉት ነበር።

ቀውሱ በተካሄደባቸው አንዳንድ አካባቢ የሸዋ ኦሮሞዎች ሳይቀሩ በአካብቢያዊነት ስሜትና በእምነታቸው ሳቢያ መጠቃታቸው እየታወቀ ” ኦሮሞ ኦሮሞን አይገልም” ሲሉ አቶ ሽመልስ ድሮ የተናገሩትን ንግግር ይፋ ማውጣት ሌላ የእርስ በርስ ግጭት ለመቀስቀስ እንጂ ሌላ አንዳችም ዓላማ ሊኖረው እንደማይገባ ለመረዳት የግድ የፖሊት ቢሮ አባል መሆን የሚያስፈልገው አይመስለኝም።

Related stories   እስራኤል አልጃዚራ ቴሊቪዥን፣ አሶሲየትድ ፕሬስና ሌሎች ሚዲያዎች የሚጠቀሙበትን ህንጻ አወደመች

ሰዎች በዘራቸው፣ በእምነታቸው፣ በማንነታቸው ጥቃት እንዲደርስባቸው ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ አይመኝም። ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ በማንም ላይ የበላይ ሆኖ ሊፈነጭ አይፈልግም። የሚገባውን እንዲከለከል የማይመኘው የኦሮሞ ሕዝብ የተጠየፈውን ግፍ ሌሎች ላይ መደገም አለበት ብሎ አያምንም። ይህማ ቢሆን ኖሮ አገራችን አሁን ባልተረጋጋች ነበር። እልቂቱ ድፍን ኦሮሚያ ላይ በተጋጋመም ያሰናል። ግን አይደለም። ይህንን ቆም ብሎ መረዳት፣ አብዛኛውን ህዝብ ከትቂት ተላላኪዎች መለየት እንደ ቦይ ውሃ ዝም ብሎ ከመፍሰስ ያድናል ባይ ነኝ።

አንድ ጉዳይ ብቅ ባለና ሴረኞች ተሻርከውም ይሁን ፈጥረው አጀንዳ በላኩ ቁጥር፣ ወይም የቆየ ፋይል ተመሳጥረው እያሰራጩ መርዝ በጋቱን ቁጥር በስሜት ሌሎችን የሚጎዳ ግምገማ ውስጥ መግባት ትክክል አይመስለኝም። ሰፊ የሆነውን ህዝብ የማይወክሉ፣ በተጨበጨበላቸው ቁጥር በስሜት የሚጋልቡ እንጪጭ ፖለቲከኞችን ከብስሉ መለየት አስፈላጊ ነው። አገር ሰከን ሲል የቅርቡን በመርሳት ለመተራመስ መጣደፍ ማንንም አይጠቅምም። ነውጥ እንደሚመኙልን ክፉዎች እባብ ባንሆንም ቢያንስ ልባም መሆን ያስፈልጋል።

መቼም ይነገር እንደ አንድ ኦሮሞ ሶስት መሰረታዊ ስህተቶች አይቻለሁ። አቶ ሽመልስ በወቅቱ ጭብጨባ ሲጎርፍለት ከፕሪንሲፕል ወጥቶ ያስተጋባቸው ሶስቱ መሰረታዊ ጉዳዮች / አልደግማቸውም/ አግባብ እንዳልሆነ አምናለሁ። ከዚህ በተለየ መልኩ መቅረብ ይችል ነበር። ከላይ እንዳልኩት የንግግርና የአመራር ጥበብ ማነስ ተዳምሮ ባልተገባ መልኩ ቢቀርብም ፣ኦሮሞ በምንም መልኩ እስከወዲያኛው የህወሃትን ታሪክ አይደግምም። ይህ የሆነው ይህ እንዳይመጣ የሚዋደቁትን፣ ሌቦችን የሚጠየፉትንና አገሪቱን ወደተሻለ መንገድ ለመውሰድ የሚተጉትን መሪ ከኦሮሞና ከሌሎች የአገሪቱ ዜጎች ጋር ለማቃቃር እንደሆነ መዘንጋት እንደሌለበት ለማስታወስ እወዳለሁ። ይህን አጋጣሚ በተዳፈነው ዓመድ ላይ ቤንዚን ለመነስነስ ሊያውሉት የተነሱትን አካላት ሩጫ በማስተዋል እንደለመድነው በጥበብ እናልፈው ዘንድ እመክራለሁ።

ለሁሉም ግን ንጋትና ጥራት እያደር እንዲሉ ነውና በማስተዋል እንሂድ። እንመርመር። እንንቃ። ከተንኮለኞች ሴራ ራሳችንን መከላከል ካልቻልን እንሰበራለን። ሃዘናችንም ይከፋል። ስንተች እንጠንቀቅ። ህዝብ ሁሌም ትክክል ነውና ህዝብን አንንካ። ከሌሎች መሻላችንን በማስተዋል በምናደርገው እናስመስክር። ስጠቀልለው ግን ኦሮሚያ ብስል መሪ እንደሚያሻት እምነት እንዳለ ግን አልሸሽግም። ኢትዮጵያ በርካታ ብስል ዜጎች አሏትና።

ዝግጅት ክፍሉ – አስተያየቱን የተቀበልነው በስልክ በመሆኑ ለንባብ እንዲመች አድርገን አስተካክለነዋል። ይህንን አስመልክቶ የተለየ አስተያየት ወይም ተጨማሪ ላላቸው መድረኩ ክፍት ነው።

የአቶ ሽመልስ ሙሉ ንግግር ትርጉም

ቅድሚያ ትርጉሙን አዘጋጅተው ላቀረቡት አቶ ጥላሁን ግርማ ምስጋናዬ ከፍተኛ ነው። በተርጓሚው ክታብ የኦቦ ሽመልስ ቃለ መጠይቅ ትክክለኛ ትርጉም እንደወረደ ከዚህ የሚከተለው ነው። በትርጉሙ ስህተት እንዳለ ማሳሰብ ለሚወዱ ከወዲሁ አክብሮት እንዳለን ለመግለጽ እንወዳለን።

ኢህአዴግ የተሰራው ለህውሃት ነው። የተሰራበት ምክንያት ደግሞ ስልጣን ላይ ለመቆየት ነው። እኛም ብልፅግናን የሰራነው ከስልጣን ለመውረድ አይደለም። ብልፅግና ደግሞ ወደዳችሁም ጠላችሁም የኛ ነው። እኛ ነን የሰራነው።ለኛ እንደሚሆነን አድርገን!! ስለዚህ ህወሃት ለሱ እንዲሆነው ነበር ኢህአዴግን ገና ሲፈጠር የቀድሞዎቹ የኦህዴድ መስራች ሰዎች ለመታገል ሞክረዋል ግን አልቻሉም።

ያልቻሉበት ምክንያት ደግሞ ጠብመንጃ ስለሌላቸው፣ ሀይል ስለሌላቸው ነው። ሳይመሰረት በፊት አሁን የምናወራውን አንስተው ነበር፤ አሁን ዶ/ር ቢቂላ ያነሳውን ነገር ሁሉ አንስተው ነበር፣ እነ ኢብራሂም መልካ ተገምግመው የተባረሩት በዚህ ነው፣ ስለ ውክልና፣ ስለ ፍትሃዊነት ስለ ጠየቁ። ግን majorityን minority የሚያደርጉበት instrument ስለሆነ፣ minorityን majority አድርገው እዚህ ሀገር ላይ የማዕከላዊ መንግስት ስልጣንን ለመቆጣጠር ሲባል ነው አሳምረው የሰሩት።

ከተሰራበት መንገድ ውጭ እንዳያድግ ደግሞ ሲንከባከቡት ኖሩ። የተንከባከቡት በመጀመርያ ዙር በሞግዚት ነው፣ እነ ሰለሞን ጢሞ፣ እነ ቢተው በላይ፣ እና በመሳሰሉት ሲንከባከቡት ነበር። ሞግዚትን እንደምንም በትግል ማሸነፍ ሲቻል ደግሞ internally clique ገነቡ ማለት ነው። በ clique ደግሞ ሲንከባከቡት ቆዩ። ይህ እውነት ነው። ስለዚህ በ 2008 ክረምት ውስጥ ሊቀመንበር መቀየር ሲቻል ነው ትግሉ አንድ አቅጣጫ የያዘው። ህውሃትም እንደ ኢህአዴግም እኛ ሳናውቅ ሊቀመንበር ቀየራችሁ እኛ ሳናውቅ ፕሬዝዳንት ሾማችሁ ብለው ያበዱት ማለት ነው። ማበዳቸውም ልክ ነው።

ስለዚህ ቁጭ ተብሎ አማራጭ ሲሰላ በሶስት መንገድ ለውጥ ማምጣት እንችላለን ተባለ። አንደኛው አብዮት እናካሂድ ተባለ። አንዱ አማራጭ እሱ ነበር። አብዮት አይሆንም ፣ ሌላ ችግር ያመጣል እንደዛ አይነት ዝግጅት የለንም፣ plus ሁልጊዜ ከዜሮ መጀመር ነው የሚሆነው ተብሎ፣ አብዮት ለፍጥነት ጥሩ ነው፣ ጣጣ የለውም፣ ጭቅጭቅ የለውም ፣የጨረስከውን ጨርሰህ ወደ አንድ አቅጣጫ ትወጣለህ፣ ማሰር ያለብህን አስረህ ማለት ነው። ያ መንገዱን ቢያቃልልንም ለኦሮሞ ሌላ ጠላት ፣ ለኦሮሞ ሌላ ቁስል ፣ሌላ ቂም ሌላኛው አካል ላይ ይፈጥራል ብለን ቂም በቀል፣ ጥላቻ፣ አብዮት አይበጀንም፣ አያዋጣንም ተብሎ ነው ተጠንቶ የተተወው ይህ አማራጭ እንዲቀር። ሁለተኛው በ evolutionary መንገድ ለውጥ ማምጣት ነው ቀስ በቀስ።

ያም ሰዎቹ ጉልበት ስላላቸው፣ ስልጣን ስላላቸው easily መልሰው ሊያፈርሱን ስለሚችሉ፣ የሚላላክላቸው ስለማያጡ፣ ከኛ ውስጥም የሚላላክላቸው ብዙ ስለሆነ፣ ብዙ ሰልፍም ስላለ፣ ግዜ ከሰጠናቸው ደግመው regain ማድረግ ይችላሉ ብለን በ evolutionary መንገድ መለወጥ አይቻልም ተባለ። ሶስተኛው ለውጥ ማምጫ መንገድ reform ነው reform ትንሽ ፍጥነትም አለው፣ structurally ነገሩን ለመቀየርም የተመቻች መንገድ አለው፣ in between ስለሆነ፣ ሌላውንም ህዝብ ሳያስደነብሩ፣ ዘመድ እያበዙ፣ እያፈሩ፣ የኦሮሞን ጥያቄ እና ፍላጎት በ reform መንገድ መመለስ እንችላለን ተባሎ ነው reform የተመረጠው። ይህ ነው በ 2009 በድርጅት conference ወስነን የገባንበት።

Related stories   ኤፒ ለቅጥፈቱ ይቅርታ አልጠየቀም – ምርጫ ተራዘመ፤ለምን?

ይህ ሪፎርም ፣ basically ብዙ ሪፎርም አለ ግን፣ ሪፎርምን በሙሉ መንገድ ለማካሄድ ኦሮሚያ ውስጥ መጀመርያ ላይ ሰዎቹን ለማስደንገጥ፣ እረፍት ለመንሳት አጀንዳ ለነሱ ለማቀበል፣ እነሱን corner ለማድረግ፣ ብዙ ነገር አድርገናል። የመሬቱን ታስታውሳላችሁ፣ የማዕድኑን ታስታውሳላችሁ፣ የህገ ወጥ ንግድን ታሳታውሳላችሁ፣ ስለ ኮንትሮባንድ ታስታውሳላችሁ፣ ስለ አዲስ አበባ ታስታውሳላችሁ፣ ስለ አፋን ኦሮሞ ብዙ አጀንዳዎችን ፈጠርን እረፍት ለመንሳት። እእእእ ቄሮ ስለምትሉትም፣ ትንሽ ያው እነ ፍቃዱን እና እሱን አያካትትም እንጅ እኔ ቄሮ ነኝ። ይህን ቄሮን ወደድክም ጠላህም ኦህዴድ ነው የፈጠረው፣ እዚህ ውስጥ ያላችሁ young የሆናችሁትን ያሳየን ኦህዴድ ነው። ትምህርት ቤት በሙሉ ኦሮሚያ እንዲከፈት ተደርጎ እንዲማር የተደረገው በኦህዴድ ነው።

የዚህ ዘመን ቄሮ conscious ስለሆነ fearless ሆኖ እንዲሄድ ያደረገው ስለ ተማረ ነው፣ conscious ስለሆነ ነው። So, አብዮቱ በሚካሄድበት ግዜ በነበሩት አመታት፣ ብዙ ነገሮች አሉ ማለት ነው ወደፊት በታሪክ የምንፅፈው። ሰልፍ እየበተንም እያወጣንም ነበር ማለት ነው። አሁን ሁሉም ሰው እንዲህ አድርገን፣ እንዲያ አድርገን እያለ የሚያወራው አይደለም ማለት ነው። ከውጭም ከውስጥም ሁሉንም coordinate አድርገን ቁማሩን በደንብ ነው የተጫወትነው። ቁማሩን ስለተጫወትን ነው የበላነው መጨረሻ ላይ፣ እንጂ በስጦታ የሰጠን ሰው፣ እባካችሁ እንጅ ምነው ብሎ የሰጠን የለም። ይህ clearly መታወቅ አለበት።

ፖለቲካ ደግሞ እናንተ ሰዎች ተንኮል ነው ሌላ ነገር አይደለም፣ ምን ያክል ተንኮል ትችላለህ ነው፣ ምን ያክል በ intrigue መጫወት ትችላለህ ነው፣ ምን ያክል power calculusሷን properly calculate አድርገህ መጫወት ትችላለህ ነው። ልክ ፍቄ እንዳለው በስሜት አይቻልም በስሜት እማ ተሞክሯል hundred years, ማሸነፍ የሌለው ትግል ብዙ አድርገናል፣ ማሸነፍ የሚችል ትግል ያመጣነው calculate ተደርጎ ስለተሰራ ነው ማለት ነው። ዘመድ ለማብዛት calculate ተደርጎ ብዙ ነገር ተሰርቷል፣ ደቡብ ብዙ ተሰርቷል፣ ባህርዳር አባይ ተኪዶ ብዙ ሰርተናል፣ ብዙ ነው ማለት ነው፣ የምንችለው convince አድርገን፣ ያልቻልነውን confuse አድርገን።

አሁን የሚያስቸግረው ምንድነው ሌላው ሰው ለምን confused ሆነ ብላችሁ ትጨነቃላችሁ፣ ምን አገባችሁ? በእንደዚህ አይነት ጨዋታ ነው መጨረሻ ላይ ህወሃት ወደሚሄድበት ግራ ገብቶት ያሰለፈውን ሃይል ሁሉ ከእጁ አውጥተን፣ ደቡብንም ከእጁ አውጥተን፣ የአማራን ፓርቲንም ከእጁ እውጠተን፣ እኛ ውስጥም የሚላላኩትን መርምረን አባርረን፣ አባርረን ነው ራሳችንን አፅድተን ተሰልፈን አማራጭ አሳጥተነው ወደ ምርጫ እንዲገባ የተደረገው። ህዝቡ ተደራጅቷል፣ አብዮት ነው ያለው፣ እሳት ነው እየነደደ ያለው፣ internally ደግሞ እሱ የሚንጠለጠልባቸውን ሁሉ በትነንበት አንድ ሰው እንዳይኖረው አድርገን የኛ ሰው ሲወጣ እና ሲገባ የሚያወራውን ሁላ እእእእ የምንችለውን በምንችለው።

አሁን የቤት እመቤት ነን ማለት ነው፣ seriously ማለት ነው፣ እንዲህ በዋዛ አልመጣም፣ ምክንያቱም የሚላላክ ብዙ ስላለ ነው ዛሬም ለመላላክ ሰልፍ የገባው፣ መላላክ ደግሞ ከኛ በላይ የሚችል የለም። so wisely ነው ማለት ነው የተቀበልነው፣ በጨዋታ ነው የተነጠቅነው (×2)። ፓርቲ ሰራን ይሄው፣ የሰራነው ፓርቲ እንደ ምሁር እንድትረዱ የምንፈልገው፣ ጅማሬውም ፍፃሜውም የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም እና ፋይዳ እና የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን ጥቅም እና ፋይዳ ማስከበር ነው።

ከዚህ ውጭ ምንም አላማ የለውም። ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራሙ ፍቃዱ እንዳብራራው የመተዳደርያ ደንቡ የኦሮሞን ህዝብ ፍላጎት እና ጥቅም እንዲመልስ ነው የተሰራው፣ እንዴት፣ የመጀመርያው እና ዋናው በዚህ ፓርቲ ውስጥ ያለን ተሳትፎ በህዝብ ብዛት እና በብሄር ብዛት እንዲሆን ተብሎ ነው የተቀመጠው። በፊት በዛ መላላክም ተሳትፎዋችን ትንሽ ነው፣ አሁን ተሳትፎዋችን በህዝባችን ልክ ዴሞክራቲክ በሆነ መንገድ እንዲሆን አደረግን ማለት ነው፣ አንደኛው ይህ ነው።

ሁለተኛው የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና ምክትሉ ምርጫ ጉባኤ ይካሄድ ብለን ነው የወሰንነው። So, አርባ ፐርሰንት ቢሆን እኛ ያለን ተሳትፎ በህዝብ ቁጥራችን ልክ ፓርቲው ውስጥ ያለን፣ ያ አርባ ፐርሰንት ካልመረጠህ ፕሬዝዳንት (ሊቀመንበር) አይደለም ምክትልም መሆን አትችልም ማለት ነው። ስለዚህ የሃገር ባለቤትነትን ጉዳይ ከስልጣን ጋርም ያለውን በአሰራር ዘግተነዋል ማለት ነው።

ብልፅግናን minimum ካሁን በኋላ የሚመራው ኦሮሞ መሆን አለበት ካልሆነ ደግሞ ኦሮሞ ሊፈቅድለት ይገባል ፣ እንደዛ አይነት ፓርቲ ነው የገነባነው። ሁለተኛ ያነሳችሁት አፋን ኦሮሞን የተመለከተ አንድ ዳታ ልስጣችሁ። በ87 አፋን ኦሮሞ በ12 በ13 % ከአማርኛ በታች ነበር። አሁን አፋን ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛን ከ 10% በላይ ይበልጠዋል። የአማራን ብሄር አላልኩኝም እኔ አፋን ኦሮሞ በተናጋሪ አማርኛ ቋንቋ ይበልጣል ነው ያልኩት። አማርኛ ነው አፋን ኦሮሞን በተናጋሪ ብዛት የሚበልጠው ብላችሁ ካሰባችሁ ትልቅ ስህተት ውስጥ ናችሁ። ቤንሻንጉል 37% አፋን ኦሮሞ ይናገራል፣ ጋምቤላ፣ ሃረሪ፣ ሶማሌ ውስጥ፣ ነው ያልኩት።

Related stories   “ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

አማርኛ እየሞተ ነው የመጣው፣ ወደታች ነው እየሄደ ያለው። So, አፋን ኦሮሞ ይዋጣል ይሞታል ምናምን የምትሉ፣ ኦሮሞ ይዋጣል የምትሉ ስነስርዓት ያዙ። ኦሮሞ እኮ የሆነ handicapped ነገር አይደለም ኦሮሞ፣ ወይም ክኒን አይደለም ኦሮሞ። ድሮም አልተዋጠ፣ በአፋኝ ስርዓት ውስጥም አልተዋጠም፣ forget it። ኦሮሞን ልክ እንደ wheelchair እነሱ በ AC ውስጥ oxygen ሰጥተውት፣ መርፌ ወግተው እያኖሩት እንዳሉ አስመስለው የሚያወሩልን እነሱ እየዋሹ ነው፣ እየዋሹ ነው ያሉት።

ኦሮሞን እኔ አላኖረውም አንተም አታኖረውም ፣ እኛ ላይ depend አያደርግም የሱ ኑሮ፣ ይህን እወቁ። So, እዚህ state building ውስጥ የሚወጡ ህግጋት፣ የሚወጡ ስትራቴጂዎች፣ የሚወጡ ስርዓቶች፣ የሚወጡ ሲስተሞች ነው ኦሮሙማችንን በውስጡ treat የምናደርገው፣ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰብ ወደ center የምናመጣው። አምስት ቋንቋ ስንል ለሌላው ክልል ተጨንቀን አይደለም፣ ትግርኛና አማርኛ already አሉ።

ፌዴራል ውስጥ በቂ ነው ያለው። ሶስት አምጥተንበት ለማውረድ ነው። ገባችሁ ለማመጣጠን። ሁለቱ almost 90% አላቸው፣ አሁን ሁሉም institution ውስጥ፣ አሁን እኛ የፌዴራል ቋንቋ እናድርግ ስንል ሶማሌኛ፣ ኣፋርኛ፣ እና አፋን ኦሮሞ ስንል በኋላ ፕሮፖርሽናል ይሆናል ማለት ነው። የፌዴራል public service፣ ፕሮፖርሽናል ሲሆን ሶስቱ ይገባል ማለት ነው።

ሁለቱ የሚጨመር ነገር የለውም ማለት ነው ይወርዳል እንጂ! ሶስቱ ናቸው የሚገቡት ማለት ነው። So, እኛም እንደኛ፣ ሁሉም እንደ ራሱ፣ ይኖረዋል ማለት ነው። ስለዚህ የሚወጡ ሲስተሞችን እና ህግጋትንም በዛ መንገድ ነው። የአፋን ኦሮሞ ጉዳይ የኛን ሞትም አይፈልግም ሃጂ፣ አፋን ኦሮሞ ተመልሷል ሰዎች። የቋንቋ ፖሊሲ ከሁለት፣ ከሶስት ሳምንት በኋላ ለካቢኔ ይቀርባል። ተጠናቋል። ለፌዴራል ካቢኔ ማለት ነው። ፓርቲዎች ወስነዋል። ስድስት ክልሎች ነው እንዲወስኑ የምንፈልገው። እነዛ ስድስቱ ክልሎች ደግሞ አሁን እንደ ድሮው አይደለም ፓርቲው ስር ነው የሚተዳደሩት።

ብልፅግና ስር፣ ስለዚህ ህግንም ሆነ ምንንም ለማስተካከል ምርጫ ድረስ መድረስ ያለብን አይመስለኝም። ስለዚህ ብልፅግና የአፋን ኦሮሞን ጉዳይ መልሶታል። ስለዚህ ለstate building ዕድል አለን፣ ያለንን ስልጣን ተጠቅመን፣ እኛን የምትመስል state መገንባት እንችላለን ነው አንደኛው፣ ብልፅግናን ለዚህ ነው እየገነባነው ያለነው። ሁለተኛው ብልፅግናን እየገነባን ያለነው ለnation building ነው፣ የቀድሞው (የሰዎቹ) nation building aborted ሆኗል። መቶ አመት ተሞክሮ፣ አንድ ብሄር፣ አንድ ሃይማኖት ፣ አንድ ባህል፣ አንድ ሃይማኖት የሚባለው ወድቋል።

አሁን እኛ እንደ ኦሮሞ እኛን የምትመስል ኢትዮጵያ መልሰን reconstruct ለማድረግ ፣ superstructure ውስጥ ኦሮሞነትን ለመትከል እድል አለን ማለት ነው። እሱ ላይ መስራት እንችላለን። እንደምታውቁት ድንበሩም አልቋል አዋጁም ተጠናቋል፣ አዋጁ ግን ምንም አይጠቅመንም እውነቱን ነው የምነግራችሁ፣ ብናፀድቀውም ለስም ነው እንጅ long lasting solution አያመጣም። አዲስ አበባ ላይ መፍትሄ የሚያመጣው ሶስት ነገር ነው፣ አንደኛው ሰውን ማስፈር ነው፣ በስራ፣ ከማውራት በስራ፣ አትጠይቁን የምንችለውን እያደረግን ነው። ሁለተኛው አዲስ አዲስ አበባን irrelevant ማድረግ ነው።

አዲስ አበባን irrelevant ለማድረግ እየሰራን ነው። ከተሳካልን ከምርጫ በኋላ የፌዴራል መንግስቱን መቀመጫ፣ አራት አምስት ቦታ ለመክፈል እንፈልጋለን። ዝም ብሎ አዲስ አበባን በስራችን እናስገባለን ብሎ መለፍለፍ አይደለም። እንዴት ታደርገዋለህ ፣ ፈንጂውን እንዴት ታፈነዳዋለህ? አሁን እኛ ኦሮሚያ ከልክ በላይ እየለማች ነው፣ ሌላው ክልል ከልክ በላይ እየተጎዳ ነው። ይህ ደግሞ እየሆነ ያለው የፌዴራሉን መንግሥት ኦሮሚያ ስለተቆጣጠረው ነው። የፌዴራሉ መንግስት መከፈል አለበት ብለን ከሌላው ህዝብ ጋ ተጨንቀንበት እየሰራን ነው።

ስለዚህ ይሄንን ስናደርግ irrelevant ትሆናለች አዲስ አበባ። ሶስተኛ አዲስ አበባ ላይ ያለው ሌላ economic option መፍጠር ነው። ለዚህ በቂ ዝግጅት አድርገናል። አሁን በቅርቡ ለጨፌ እናቀርባለን እድሉ ስላለን። ይሄንን አድርገን ነው እንጅ የምንፈታው ሰውም ማባረር አንችልም። ሰው መግደልም አንችልም። ማጫረስም አንችልም። እንዲህ አድርገን ነው ነገሩን የምንፈታው ብለን ነው እየሄድን ያለነው። ስለዚህ ከፈጣሪ ጋር፣ ከእውነት ጋር፣ እየሰራን ካለነው ስራ ጋር፣ ከእናንተ ጋር ከሁሉም የኦሮሞ ህዝብ ጋር ብልፅግና ይቀጥላል።

የኦሮሚያን ብልፅግና እናረጋግጣለን! ምስራቅ አፍሪካን እንመራለን! ኢትዮጵያን እንደምትመቸን አድርገን እንገነባታለን! እየገነባናትም ነው። ስለዚህ መክዳት፣ መከዳት የሚባለው ነገር የለም፣ ሊኖርም አይችልም፣ እንዲህ አይነትም ቦታ የለም፣ እንዲህ አይነት አመለካከትም የለም ይህንኑ ለማለት ነው በርቱ! በግልፅ ስለተናገራችሁን አመሰግናለሁ ልላችሁ እፈልጋለሁ።

Subscribe to our newsletter!

[newsletter_form type=”minimal” lists=”undefined” button_color=”undefined”]

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0