በወላይታ ዞን የህዝቡ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዳይመለስና በህዝብና በመንግስት መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር ለውጡን ከማይደግፉ አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ ነው ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ፋና  ገለጸ፡፡ ቪኦኤ ከአስር በላይ ሰዎች  መሞታቸውንና የቆሰሉም እንዳሉ አቶ ኪዳኔ የሚባሉ እማኝ ጠቅሶ አመልክቷል። የቦዶቲ ሆስፒታል ሃኪም የሞተ ሰው እንደሌለ ጥቅሰው አራት መቁሰላቸውን ዘግቧል።

የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ከትናንት ጀምሮ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉት አካላት እየተነሳ ያለውን የክልል እንሁን ጥያቄ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንዳይፈታ ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ 10 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የማጣራት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አመራሮቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በአካባቢው መንገድ የመዝጋትና ግርግር የመፍጠር አዝማሚያ መታየቱንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና ሌሎች ደግሞ መቁሰላቸውንም ጠቁመዋል፡፡ አሁን ላይም አካባቢው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲመለስ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በደቡብ ክልል የተነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች መንግስት ባስቀመጠው ህጋዊ መንገድ እየተመለሱ እንደሚሄዱ የተናገሩት አቶ አለማየሁ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠብቅና ህገ ወጥ ከሆኑ አካሄዶች እንዲቆጠብም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ሲል ፋና ቀን ላይ ዘግቧል።

ቪኦኤ የክልሉን አመራር ጠቅሶ እንዳለው መንገድ በመዝጋት፣የመከላከያ ሰራዊት ላይ እርምጃ ለመንጠቅ የሞከሩ ላይ በተተኮሰ ጥይት አራት የሚጠጉ መሞታቸውንና 26 የሚሆኑ ህገወጥ በሆነ መንገድ የህዝብን ስልጣን ለመጥለፍ የሞከሩ መያዛቸውን ገልጿል።

በሌላ ዜና በእነ ጃዋር መሀመድ መዝገብ ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ማሰማት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም እነ አቶ ጃዋር ዳኛው ከመዝገባችን ይነሳልን ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ችሎቱ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በልደታ አዳራሽ መስማት ተጀምሮ ነበር።

ይሁን እንጅ እነ አቶ ጃዋር ዳኛው ጉዳያችንን ገለልተኛ ሆኖ ላይመለከትልን ስለሚችል ከመዝገባችን ላይ ይነሳልን ሲሉ ባለ 7 ገጽ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

Related stories   አቶ ጃዋር በድብቅ የባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎችን ስልክ ይጠልፉ እንደነበር ፖሊስ ተናገረ፤ አቶ ጃዋር ምርመራው እኔን አይመለከትም ብለዋል

ፍርድ ቤቱም አቤቱታውን ተመልክቶ ዳኛው መዝገቡ እንዲመረመርና በመዝገቡ ላይ ትዕዛዝ እስከሚሰጥበት ድረስ ተጠርጣሪዎቹ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲቆዩ እና መጥሪያ ሲደርሳቸው የሚመጡ ይሆናል በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

መዝገቡም ወደ መዝገብ ቤት እንዲመለስ አዟል፡፡

ከዚህ በፊት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በዚህ መዝገብ ላይ በአጠቃላይ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ 5 ምስክሮች ከመጋረጃ በስተጀርባ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲል አቤቱታ ማቅረቡ ይታወሳል። ፍርድ ቤቱም አምስቱ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ከመጋረጃ በስተጀርባ ቃላቸውን እንዲሰጡ ብይን መስጠቱ የሚታወስ ነው።

ፋና እንደዘገበው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *