“Our true nationality is mankind.”H.G.

በደም የጨቀየው የህወሃት ውስጠ ታሪክ ሲገለጥ – ምስክር ሊላይ ኃይለማርያም

“ህወሓት ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፉ ብዙ ምሑራንና ባለተሰጥዖ ታጋዮችን ፈጅታለች” – አቶ ሊላይ ኃይለማርያም የህወሓት ነባር ታጋይ
“ህወሓት ፍጹም ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ድርጅት ነው፤ በአሁኑ ሰዓት ቢኖሩ ትግራይና ኢትዮጵያን ቀርቶ ለአፍሪካ እና ለዓለም የሚተረፉ ብዙ ምሑራንና ባለተሰጥዖ ታጋዮችን በግፍ መፍጀቷን ትቀጥልበት ነበር” ሲሉ የህወሓት ነባር ታጋይ አቶ ሊላይ ኃይለማርያም አስታወቁ። ከቤተ ክህነት እስከ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት፤ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እስከ መቀሌው አፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት ሀገሪቱን ሲገዙ የነበሩት የአንድ ቤተሰብ አባላት እንደነበሩም አመልክተዋል።
የቀዳማይ ወያኔ መስራችና የብላታ ኃይለማርያም ረዳ ልጅ የሆኑት አቶ ሊላይ ኃይለማርያም በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ህወሓት ትግራይና ኢትዮጵያን ቀርቶ ለአፍሪካ እና ለዓለም የሚተረፉ ብዙ ምሑራንና ባለተሰጥዖ ታጋዮችን ፈጅታለች፤ ምናልባት እንዳያንስ እንጂ ደርግ፣ ኢዲዩ፣ ኢህአፓና ጀበሃን ጨምሮ ከአምስት ድርጅቶች ጋር ተዋግተን ከተሰው ሰማዕታት በላይ በድርጅቱ የተገደሉት ይበልጣሉ ብለዋል።
ድርጅቱ ሁለት አይነት አመለካከት ባላቸው ሰዎች የተፈጠረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሊላይ፣ በአንድ በኩል እውነተኛ ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊታገሉ የወጡ የህዝብ ልጆች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሴራ /በሸር / እና ተንኮል እንዲሁም የበታችነት ስሜት ይዘው የመጡ እንደነበሩ አመልክተዋል።
በሸር እና በበታችነት ስሜት ወደ በረሀ የመጣው ስብሃት ነጋ፣ አረጋዊ በርኸ እና አባይ ፀሓዬን የያዘው ብድን እንደነበር አመልክተው ፣ ወላጆቻቸው ፀረ ቀዳማይ ወያኔ ንቅናቄ ውስጥ የነበሩ ናቸው ብለዋል። አጋሜ፣ ክልዕተ አውላሎ፣ እንደርታ፣ ራያ፣ ቴምቤን፣ ሙሉ ወልቃይትና ሽሬ እነዚህ በሙሉ በቀዳማይ ወያኔ ተካፍለዋል። ፀረ ቀዳማይ ወያኔ የነበሩት ደግሞ አድዋና አክሱም የነበሩ መሳፍንቶች እንደነበሩ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል እነ ስሑል ፣ሙሴ እና አጋዚ የያዘ ቡድን የቀዳማይ ወያኔን ዓላማ ለማሳካት የወጣ ነበር። እነዚህ ዳግማዊ ወያኔ ብለው የወጡ ሃይሎች ወይም ህዝባዊ አመለካከት የነበራቸው የህዝብ ልጆች ነበሩ። ሁሉም በሴረኛው ቡድን ለሞት መዳረጋቸውን አመልክተዋል። በዚህም ትግሉ በነስብሀት ቡድን በሴራ ተጠልፎ አላማውን መሳቱን አስታውቀዋል።
የትግራይ ህዝብ ሲታገል የነበረው ለባርነት፣ ፍጹም ጨቋኝ እና ክፉ ስርዓት ለማምጣት አለመሆኑን አመልክተው፣ የትግራይ ህዝብ የማይገባውን ዋጋ እየከፈለ ያለ ህዝብ እንደሆነም በቁጭት ተናግረዋል።
ህወሓት በትግል ወቅት በየምክንያቱ የሚገላቸውን ሰዎች ለራሳቸው መቀበሪያ ጉድጓድ ያስቆፍራቸው እንደነበር አመልክ ተው፣ “ጉድጓድህን ከቆፈርክ ታስረህ ጉድጓዱ ውስጥ ትጣልና በጥይት ተደብድበህ ስትሞት አፈር ትለብሳለህ። አልቆፍርም ካልክ ደግሞ ሌሎች መጥተው ጉድጓዱን እንዲቆፍሩት ይደረግና አንተ እጅህን ታስረህ ጉድጓዱ ውስጥ ትጣልና ሳትገደል ከነህይወትህ አፈር ትለብሳለህ”ብለዋል።
“ይሄ ማንም የሚያውቀው ነው። በዚህ መልኩ ሰው አልተገደለም ከተባለ በወር ውስጥ አምስት መቶ ሰው እንደሚገደል፤ የሚገድሉት ሰዎች የሚናገሩት የአደባባይ እውነታ እንደነበር አመልክተው ፣ይሄም የነበረው ስርዓት ደንበኛ አጋንንታዊ እንደ ነበር በደንብ የሚያሳይ ነው። ቀን በቀን ሰው ሳይገድል አይውልም ነበር” ብለዋል።
በአንድ ወቅት ስብሃት ነጋ ድርጅቱ ውስጥ ፀረ አድዋ እና ፀረ አክሱም እንቅስቃሴ አለ ብሎ በመወንጀል፣ ተደራጅቶ ዝግጁ በነበረ ሀይል ክልተ አውላሎ፣ እንደርታ ራያ ተንቤን ታጋዮችን በተገኘበት እንዲገደሉ ሆኗል።
ከ1969 እስከ 1971 ድረስ የአምስቱን አውራጃ ታጋዮች በሄዱበት በገፍ ታርደዋል። በዚህም ትግራይ የእርድ ቦታ ሆና ነበር። ይሄን የሚመሰክሩ ከዚህ ያመለጡም አሁንም በህይወት ያሉ አሉ። ታስሮ ግን የተፈታ የለም። በሺዎች የሚቆጠር ብዙ ታጋይ ተገድሏል ብለዋል።
https://www.youtube.com/watch?v=Q8pepH7VR7I&t=1578s
“ኢትዮጵያ ውስጥ በ1970 ቀይ ሽብር ይካሄድ ነበር። በዚህም በ1970/71 ላይ በርካታ የትግራይ ልጆች ከአራቱም ማዕዘን ወደ በረሃ ፈሰሱ። ከእነዚህ ውስጥ 90 ከመቶው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ ወይም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ፣ የጤና መኮንን፣ በትልልቅ የመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ቁልፍ ቦታ ላይ የሚሰሩና የመምሪያ ኃላፊ የነበሩ ሁሉ ወደ በረሀ መጥተው ነበር” ሲሉም ትውስታቸውን አጋርተዋል።
“ከኤርትራ ጭምር ቀይ ሽብርን ፈርተው በሺህ የሚቆጠሩ ምሁራን ወደ በረሀ ገብተው ነበር። ከዛ ውስጥ ብዙዎቹ በጣም ብሩህ አዕምሮ ያላቸው የአድዋ ልጆች ነበሩ። ይሄንን ያየ የስብሃት ነጋ ኔትዎርክ ጽዳት በሚል አውራጃ ሳይለይ የመጡትን በሙሉ እስር ቤት አስገብቶ ጨርሷቸዋል። ከዚህም አንድ የወጣ ሰው የለም፤ በሺዎች የሚቆጠሩ እነዚህ ወጣቶች አልቀዋል ። ከእነዚህ ውስጥ የማስታውሰው አስመላሽ የሚባል የአድዋ ልጅ ነበረ፤ ኤርትራ ነበር፣ ወደ አምስትና ስድስት ቋንቋ ይናገር ነበር።
ተጫዋች፣ ተግባቢ፣ ምሑር እንዲሁም ተዋጊ ነበር። ሲናገር እንግሊዘኛም ፈረንሳይኛም የሚቀላቅለው ነገር አለው። ይሄን ሰው ስጋት መስሎ ስለታያቸው ሊያጠፉት ስለፈለጉ በውስጣቸው ያሉ ገበሬ ታጋዮችን በኢምፔሪያሊዝም ቋንቋ እየሰደባችሁ ነው በሚል አስገምግመው እንዲገደል አድርገዋል። እንደሱ አይነት ሰው ግን በዚህ አገር ቢኖር ለዓለም የሚተርፍ አይነት አቅም ያለው ነበር” ብለዋል።
 
https://www.youtube.com/watch?v=cGdIGRuZnWE&t=24s
 
በዚህ መልኩ በ1971/72 የነበረውን ምሑር በመጨረስ፤ በዛን ወቅት ህወሓት ገበሬ ብቻ ይዛ ቀረች። ይሄም ያ ድርጅት በተፈጥሮው ፀረ ምሑር መሆኑን ያሳየበት ተጨባጭ አጋጣሚ እንደሆነ በመግለጽ፣ “አንተ በተፈጥሮ የተሻለ አቅምም ወታደራዊ ቁመናም ካለህ እና የእነርሱ ኔትዎርክ ካልሆንክ እድሜህ አጭር” እንደሚሆን አመልክተዋል
“በ1777 ደግሞ የራሳቸውን የአድዋ ልጆች ማለሊት የሚባል ፓርቲ ሲመሰ ርቱ፤ እነሱንም እነ ተክሉ ሐዋዝን፣ ሸዊት፣ ገብረ ህይወት የሚባሉትን እና ድርጅቱን መጀመሪያ የፈጠሩና ይዘውት የመጡትን ጭምር ገድለዋል።
ከ1977 እስከ 1980 የነበረው ግድያና ጭፍጨፋ በአውራጃ ሳይሆን፤ የእነርሱን አስተሳሰብ የማይቀበለውናን የሚገዳደራቸው መስሎ የተሰማቸውን ፣የእነርሱን መንደር ልጅ ጨምሮ የየትኛውንም አውራጃ ታጋይ ነበር የሚገድሉት። ለምሳሌ፣ ሸዊት ማለት የጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም የስብሃት ነጋ የስጋ ዘመድ ሲሆን፤ ይህ ታጋይ ኔትዎርኩን አይደግፍም ነበር። እናም የቤተሰብ መንግሥት ልታፈርስ ነው ተብሎ ነበር የተገደለው” ብለዋል።
አቶ ሊላይ እንደሚሉት ከ1980 በኋላ 1983 እስኪገቡ ድረስም ግድያው አላቆመም ነበር። በዚህ ጊዜ የተገደሉት የአጋሜ፣ ክልተ አውላሎ፣ እንደርታ እና የራያ ልጆች ናቸው። የእነዚህ አገዳደል ደግሞ ይለያል። ከሃይል አዛዥ እስከ ክፍለ ጦር አዛዥ ነው የተገደሉት።
ዋና ዋና የተባሉ ወታደራዊ አዛዦችን አዲስ አበባ መግባታቸውን ሲያረጋግጡ፤ አዲስ አበባ ከገባን አያስቀምጡንም፤ እነዚህ ሊያምጹም ይችላሉ፣ ተሰሚነት አላቸው የተባሉ በሙሉ በስናይፐር ነው የተገደሉት። ጦርነት በሌለበት ቦታ እንዲሁ ቁጭ ባሉበት ይመታሉ። ከዛም በራሪ ጥይት መታው ይባላል። ዙ-23 ተተኩሶ ተመታ ይባላል። እናም ከ80 እስከ 83 ይሄንን አጽድተው ነው የገቡት ብለዋል።
ከቤተ ክህነት እስከ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት፤ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እስከ መቀሌው አፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት ሀገሪቱን ሲገዙ የነበሩት የአንድ ቤተሰብ አባላት እንደነበሩ ያመለከቱት አቶ ሊላይ፣ ለምሳሌ፣ ስብሃት የመለስ ክርስትና አባት ነው። መለስ እና አቡነ ጳውሎስ የሁለት ወንድማማቾች ወይም አንድ ቤተሰብ ልጆች ናቸው ብለዋል።
አዲስ አበባ ከገቡ በኋላም ኢትዮጵያን ይገዟት የነበሩት የአንድ ቤተሰብ ወይም የዘር ሃረግ አባላት እንደሆኑ ጠቁመዋል። ለምሳሌ፣ መቀሌ አጼ ዮሐንስ ቤተመንግስት ብትሄድ አለቃ ፀጋዬ ነው ያለው። እሱ ደግሞ ሚስቱ ቅዱሳን ነጋ ነች። እሷ ደግሞ የስብሃት ነጋ እህት ናት። እናም የአንድ ቤተሰብ ዳይናስቲ ነው የነበረው እንጂ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራል ስርዓት አልነበረም። ትግራይ ውስጥም በሁሉም ቦታ ብትሄድ የስብሃት ቤተሰብ ካልሆንክ ቦታ የለህም። ከዛ ውጭ ከሆንክ የትምህርት ስኮላር ሺፕ እንኳን አታገኝም ሲሉም የነበረውን አሰቃቂ ሁኔታ አብራርተዋል።
ከአቶ ሊላይ ኃይለማርያም ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ሙሉ ቃል በገጽ13 ይመልከቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2012
ወንድወሰን ሽመልስ

Subscribe to our newsletter!

[newsletter_form type=”minimal” lists=”undefined” button_color=”undefined”]
0Shares
0