ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች ያጋለጡት የግብፆች ሙያን ተገን ያደረገ ሴራ

ሪፖርተር – በብርሃኑ ፈቃደ
ከሰሞኑ የኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችን ቀልብ የሳበ፣ በሙያቸው ከያሉበት እንዲሳሳቡና እውነቱን ለዓለም በማሳወቅ እንዲሞግቱ ያስገደደ አንድ መጽሐፍ በታዋቂ ዓለም አቀፍ ጆርናል አሳታሚ በኩል ይፋ ተደርጓል፡፡

‹‹Integrated Watershed Management of Grand Ethiopian Renaissance Dam via Watershed Modeling System and Remote Sensing›› በሚል ርዕስ ግብፃውያን ያወጡት መጽሐፍ ወይም ሪፖርት የህዳሴው ግድብ የመፍረስ አደጋ እንደሚያሠጋው፣ በኢትዮጵያ ሊያጋጥም በሚችል የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ብሎም በግድቡ ግንባታ በአብዛኛው በኮንክሪት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ለመፍረስ ሊያበቃው እንደሚችል ግብፆቹ ሳይንሳዊ አስመስለው ጽፈዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ሱዳን በተለይም ካርቱም ከተማ በጎርፍ ማዕበል የመጥለቅለቅ ሥጋት እንዳጠላባት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

ሞሐመድ ኢ. ዳንድራዊና አል ሳይድ ኢ. ኦምራን የተባሉ ግብፃውያን በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ በተለይ ምዕራፍ 17 ላይ ያሳረፉት ትንታኔ የሳይንስ መነሻዎችን ሆነ ብለው በማዛባት ሸፍጥ የሠሩበትን መንገድ አጋልጠው፣ እውነታዎችን አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ የመረመሩት ይህ መጽሐፍ ሳይንስን ተገን ባደረጉ ለፍላጎታቸው እንጂ ለሳይንስ እውነታዎች ባልተገዙ ግብፃውያን መጻፉ ብቻም ሳይሆን፣ ሳይንስን ከፖለቲካ ፍላጎታቸው ደባልቀው፣ ሐሰቱን በሳይንስ ግኝት ለውሰው ያቀረቡበት፣ ሐሰተኛ ሪፖርት እንደሆነ በማውገዝ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ በፈጠራ የታጀቡ ትንታኔዎች፣ የሌሎችን ሥራ የራስ በማስመሰል የቀረበበት መጽሐፍ በመሆኑ፣ አሳታሚው መጽሐፉን በተለይም ከፍተኛ የሳይንስ ዓላባውያን ሆን ተብለው የተዛነፉበት የመጽሐፉ ክፍል እንዲወገድ፣ ወይም መጽሐፉን ከሥርጭት እንዲያስወጣው፣ ዕውቅና እንዲነሳውና ጸሐፊዎቹም ይቅርታ እንዲጠይቁ ኢትዮጵያውያኑ ሞግተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በላቀ ስበትና ስሜት ከያሉበት ተሰባስበው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ስላላት ተፈጥሯዊና ሉዓላዊ መብት መከበር ግብፆችን በየዓውዳቸው መግጠም የጀመሩበት ይህ የተለወጠ ወቅት እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መገባደድና የመጀመርያው ዙር የውኃ ሙሌት ሥራ መሳካት ለኢትጵያውያን ትልቅ ትንግርት ሆኗል፡፡

በዚህ ግለታዊ ኃይል የግብፅን ለራስ ያደረ ሙግትና ውገና በአደባባይ ለመታገል በርካታ ኢትዮጵያውያን እያበሩ፣ እየተባበሩ መጥተዋል፡፡ ከሰሞኑም ይኸው ጎልቶ የታየበት የሳይንስ ባለሙያዎች ሠልፍ ይጠቀሳል፡፡ ከፖለቲካ በራቀ መንገድ ሳይንስንና ሳይንሳዊ መረጃዎችን እየተነተኑ ግብፆች ዓለምን እያሳሳቱ ስለሚገኙበት አካሄድ ያጋለጡ፣ ከልዩ ልዩ የሙያ ዘርፍ የተውጣጡ 12 ያህል ባለሙያዎች የተሳተፉበት የተቃውሞ ጽሑፍ በርካታ የስህተት ነጥቦችን ነቅሶ አውጥቷል፡፡

ስፕሪንገር ሐውስ የተሰኘውና ዋና መሥሪያ ቤቱ ስዊዘርላንድ የሆነው አሳታሚ ድርጅት በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪና ወሳኝ የሆኑ የአካዴሚ ሥራዎች በጆርናል የሚወጡበት፣ ስሙ የገዘፈ ተቋም ሲሆን፣ ግብፃውያኑ ይህንን ተቋም በመጠቀም የህዳሴው ግድብ ላይ ያየናቸው ችግሮች በማለት ያወጡት ጽሑፍ ከያዛቸውና ካሰፈራቸው መካከል ከባድ ቅጥፈት የተፈጸመባቸውን ዘጠኝ ያህል ነጥቦች ኢትዮጵያውያኑ ነጥብ በነጥብ ውድቅ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንኳር የሆኑትን እንመለከታለን፡፡

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

የህዳሴው ግድብ የሳይንስና የፖለቲካ ፍላጎቶችን በእጅጉ የሳበ፣ ዓለም አቀፍ ትኩረት ያገኘው ወሳኝ የጂኦ ፖለቲካዊ ፋይዳዎች ያሉበት በመሆኑ እንደሆነ የሚያምኑት 12ቱ ምሁራን፣ የግድቡ ጉዳይ ምን ያህል መነጋገሪያ እየሆነ እንደመጣ ማሳያ ያደረጉትም በድረ ገጽ ‹‹GERD›› የሚለውን ቃል መፈለጊያ ቁልፍ በመጫን በአንድ መጠቆሚያ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የጉግል ፍለጋዎችን የተጫኑ ሰዎች መኖራቸውን የሚያመላክት መረጃ ማየታቸውን በማጣቀስ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ እ.ኤ.አ. ጁን 24 ቀን 2020፣ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ የነበረውን የፍለጋ መጠን የሚያሳይ ነው፡፡ በርካቶች በዚህን ያህል ቁጥር መረጃ በሚፈልጉበትና በሚለዋወጡበት ወቅት ግብፃውያኑ ይህንኑ በመገንዘብ ይመስላል የተዛቡ፣ ከሳይንስ እውነታዎች ያፈነገጡ መረጃዎችን ለአካዴሚው ማኅበረሰብ እንዳሰራጩ ያመላከቱት፡፡

ሳይንሳዊ ዕውነታዎችንና አመክንዮዎችን በመቃረን ሆን ተብለው በተፈጸሙ ማዛባቶች የተሳሳቱ ድምዳሜዎችን ለማስጨበጥ ተሞክሮባቸዋል ከተባሉት ነጥቦች መካከል የህዳሴ ግድቡን እውነታዎችን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያውያኑ ትንታኔዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ግድቡ ሮለር ኮምፓክትድ ኮንክሪት (አርሲሲ) በተሰኘው የግንባታ ደረጃ የታነፀ የመጀመርያው የላይኛው ጥቁር ዓባይ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ሁለት ግድቦችን አካቷል፡፡ አንደኛው ይኸው በአርሲሲ ግንባታ የተሠራው ግድብ ሲሆን 1.8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 145 ሜትር ከፍታ ያለው ነው፡፡ ሁለተኛው ኮርቻ ግድብ የሚባለው፣ የአምስት ኪሎ ሜትር ርዝመትና የ50 ሜትር ከፍታ ያለው በአብዛኛው በዓለት ሙሌት ሥልት የተገነባው ግድብ ነው፡፡ ሦስት ማስተንፈሻዎችም ተገንብተውለታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለውን የኢትዮጵያን አብዛኛውን ኃይል የማመንጨት አቅም የሚሸፍነው የህዳሴው ግድብ፣ ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው የኃይል አቅርቦትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጓዳኝ፣ ለግብፅና ለሱዳን የሚያበረክታቸው አለኝታዎችም ተተንተነው እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም በቅርቡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር የወጣው ጥናት፣ ግድቡ በተቀመጠለት ጊዜ ውስጥ ቢሞላ ለሦስቱም አገሮች ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያጎናጽፋቸዋል፡፡ ይሁንና ግድቡ በአራት ዓመታት ውስጥ መሞላቱ ቀርቶ ለስድስት ዓመታት ቢዘገይ ግን እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚያስከትል ባለሙያዎቹ የጥናት ውጤታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ይህ በሆነበት፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ምኅዳራዊና አካባቢያዊ ጥቅሞቹ በሚገለጹበት ወቅት ግድቡ የፖለቲካ ጡዘትና ቅራኔዎች ማጠንጠኛ በሆነበት ወቅት፣ የሳይንሱ ማኅበረሰብ እውነታዎችን አንጥሮ በማውጣት ትክክለኛ ሳይንሳዊ ብያኔዎችን ማስፈር እንደሚጠበቅበት ያስገነዘቡት የኢትዮጵያ ምሁራን፣ የግብፃውያኑ ሪፖርት አሳስቶና አዛብቶ ያቀረባቸውን ነጥቦች ተንትነዋል፡፡

የውኃ ፍሰትን በሚመለከት የቀረበው ትንታኔ ላይ ግብፆች በዓይን እማኝ የታዘገዘ መረጃን ሁሉ ጨምረው፣ በዝናብ መብዛት ምክንያት ከማጠራቀሚያ የሚለቀቀውን የውኃ መጠን፣ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ የውኃው ግፊት እያየለ እንደሚጓዝ ለማሳየት የሄዱበት መንገድ እስከ ሰባት ሰዓት የሚፈጀው የውኃው ጉዞ በአንድ ተመሳሳይ ጊዜ 176 ካሬ ኪሎ ሜትር በማካለል የማዕበል ያህል በጠነከረ መንገድ መጓዝ መቻሉና ጎርፍ ማስከተሉ የቀረበበት የግብፆች የትንታኔ ይዘት ተብጠልጥሏል፡፡

በዝናብ መብዛት ሳቢያ ተጠራቅሞ ወደ የወንዞቹ የሚገባው ዝናብ በጥቁር ዓባይ ተፋሰስ ውስጥ በሰባት ሰዓት ጉዞ ብቻ መወሰኑ ብቻም ሳይሆን፣ የዓባይ ግድብ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም እንዳለው እየታየወቀ ያለ ምንም ተጨባጭ አኃዝና ማመሳከሪያ የግድቡን የመያዝ አቅም ወደ 17.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ዝቅ ማድረጋቸው፣ የግድቡ ጥልቀትም ወደ 100 ሜትር ብቻ እንደሆነ ማስቀመጣቸው በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ትልቅ ግራ መጋባት ብቻም ሳይሆን፣ የሳይንስን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ይዘት ማሠራጨታቸው ግብፃውያኑን እያስተቻቸው ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ ስህተት በዚህ አላበቃም ያሉት ምሁራኑ፣ የግድቡ ደኅንነት አጠራጣሪ እንደሆነ በመጻፍ፣ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት ግብፃውያኑ መጻፋቸውም ከእስካሁኑ የከፋው ስህተት ተብሏል፡፡ የግድቡ የደኅነት መለኪያ ነጥቦች ዝቅተኛ ውጤት እንዳስቆጠረ ማለትም በመለኪያው ከ1.5 ዲግሪ እስከ ዘጠኝ ባለው ርከን ውስጥ መገኘቱ ዝቅተኛ የደኅንነት አቋም እንዳለው ያረጋግጣል በማለት ለየትኛውም የርዕደ መሬት አደጋ ተጋላጭ እንደሚያደርገው ያቀረቡት መላምታዊ ሥሌት አስተችቷቸዋል፡፡ ግድቡ በአፍሪካ የመሬት መንቀጥቀጥ በብዛት በሚገኝበት አቅራቢያ መገኘቱ፣ ለግድቡ የህልውና ሥጋት ተብሎ ቀርቧል፡፡ የግድቡ የደህንነት ሥጋትና የመፍረስ አደጋ ደግሞ የዓባይ ወንዝና ገባሮቹ የጎርፍ አደጋ እንዲያስከትሉ ያደርጋል ያሉት ግብፆቹ፣ ከኢትዮጵያ በ520 ሜትር ከፍታ ላይ ተንደርድሮ ሱዳን ሲገባ የሚያገኘው ከፍታ 480 ሜትር ቦታ በመሆኑ፣ ግድቡ ተንዶ ካርቱምን በጎርፍ ያጥለቀልቃታል የሚል ድምዳሜ አስቀምጠዋል፡፡

ይህን ይበሉ እንጂ፣ ግድቡ ከፍተኛውን የዲዛይን ቴክኒክ ደረጃ በማሟላት ግንባታው በመገባደድ ላይ የሚገኝ፣ በአሜሪካ የጦር ኃይሎች ኮር የምሕንድስና ዘርፍ (United Army Corps of Engineers) የወጡ ደረጃዎችን በማስጠበቅ ጭምር እንደተገነባ፣ የግድቡ ከፍታም ሆነ የተገነባበት መሠረት የትኛውም የመሬት ንቅናቄና የመንቀጥቀጥ አደጋ ቢፈጠር እንኳ የግድቡን ድኅንነት አደጋ ላይ ሊጥል በማይችልበት ጥናታዊ ሥሌት መገንባቱን በማጣቀስ ግብፃውያኑን የሞገቱት ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ በማስረጃ አጣቅሰው እያንዳንዱን ነጥብ ውድቅ አድርገዋል፡፡

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል

የኃይድሮሎጂ ሞዴል ሥነ ልኬት በምን አግባብ እንደሚወሰድና ልኬቱን የሚወስነው ሞዴል በምን ያህል መጠን ግምቱ መወሰድ እንደሚጠበቅበት በማብራራት ባቀረቡት እውነታ፣ የጥቁር ዓባይ ተፋሰስ በመሬት በከርሰ ምድር የሚጓዝበትን ሥሌት ለመሥራት ግብፃውያን የተጠቀሙበት ሞዴል ሆን ተብሎ እንዲዛባ በመደረጉ የተሳሳተ ትንታኔ ይዞ መውጣቱን አሳይተዋል፡፡

በተጨማሪም ግብፆች ጥቁር ዓባይ ከባህር ዳር፣ ኮምቦልቻና ጎንደር የሚመጣ ዝናብ ተፋሰሱን እንደሚቀላቀለው እንጂ ሌሎች እውነታዎችን ለማስቀመጥ መረጃ እንደቸገራቸው በመጥቅስ ያስቀመጡትን፣ በደብረ ማረቆስ የሚገኘውን አንድ የአየር ንብረት መረጃ መሰብሰቢያ የሚቲዮሮሎጂ ጣቢያን ብቻ ሆነ ብለው በመጠቀም ወደ ጥቁር ዓባይ የሚገባውን የዝናብ ሥርጭትና መጠን አሳስተው ማቅረባቸውና የኃይድሮሎጂ ሞዴላቸውም መሠረታዊ ስህተት ላይ በወደቀ ቀመር ድምዳሜ እንደሰጡ ተንትነዋል፡፡

የዓባይ ተፋሰስ ከ176 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚያካልል፣ እጅግ የተለያዩ የጂኦግራፊያዊና የዝናብ ሥርጭት ልዩነቶች የሚታዩባቸውን አካባቢዎች የሚያካልል ሆኖ ሳለና ከ40 በላይ የሚቲዮሮሎጂ ጣቢያዎች ከደብረ ማርቆስ አቅራቢያ በሚገኙበት ሁኔታ ሆነ ብለው የመረጃ እጥረት እንዳለ በማስመሰል ማቅረባቸው ገሃድ ወጥቷል፡፡

እንዲህ ያሉ በርካታ ነጥቦችን አብጠርጥረው ገሃድ ያወጡት ሳይንቲስቶቹ፣ ጽሑፉን ከሌሎች ጽሑፎች ጋር በጋራ በመጽሐፍ ያወጣው ተቋም ለጽሑፎቹ የሰጠውን ዕውቅና እንዲያነሳ፣ የጻፉትም ሰዎች ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዲያደርግ በማሳበሰብ፣ እንዲህ ያሉ ሥራዎች ሳይንሳዊ ይዘቶቻቸው ሳይፈተሹና ሳይገመገሙ መውጣታቸው ኢትዮጵያን ብቻም ሳይሆን የሳይንሱን ማኅበረሰብም ጭምር የተዓማኒነት ጥያቄ ላይ በመጣል ጉዳት እንደሚያደርስበት አሳስበዋል፡፡

ልዑል ሰገድ ታመነ (ዶ/ር) በተባሉና በኢንተርናሽናል ትሮፒካል አግሪካልቸር በተሰኘ ማዕከል ተመራማዊ በሆኑት ባለሙያ አስተባባሪነት ስለ ወጣው ጽሑፍ ዝርዝር ማብሪያ ለመስጠት ከሪፖርተር ጋር ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ለግብፃውያን በቀረው የተቃውሞ ጽሑፍ ውስጥ እኚህን ጨምሮ 12 ባለሙያዎች ከጃፓን፣ አሜሪካ፣ ከኔዘርላንድስ፣ እንዲሁም ከመቀሌ፣ ከባህር ዳር፣ ከሐዋሳና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመውጣጣት ተሳትፈዋል፡፡