ላለፉት ሁለት ዓመታት አዲስ አበባን ያስተዳደሩት ከንቲባ ታከለ ኡማ ከሃላፊነት መነሳታቸውን በጻፉት የምስጋና ደብዳቤ ይፋ አደረጉ። አቶ ታከለ ከሃላፌታቸው የተነሱት የብልጽግና ፓርቲ ስብሰባ አድርጎ ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጡን ይፋ ማድርጉን ተከትሎ ነው።

በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም ተማሪዎችን መመገብና የዳቦ ቤት ግንባታን ተከታትለው በማስፈጸም ምስጋና የተቸራቸው ታከለ ኡማ ከመሬትና ከኮንዶሚኒየም እደላ ጋር ተያይዞ በስፋት ሲተቹ ነበር። ዛሬ ከሃላፊነታቸው ስለተነሱበት ምክንያት ዝርዝር መረጃ ባይቀርብም ጉዳዩ ከመሬት ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ተገምቷል። ለከተማዋ ነዋሪዎች በከንቲባ ጽህፈት ቤት በኩል የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።
ውድ የከተማችን ነዋሪዎች!
ጊዜ የሚሄደው በራሱ ፍጥነት ነው። ለሰው ብሎ አይዘገይም፤ አይቸኩልም። ሰው ግን ጊዜን ለመለካት፤ ጊዜን በራሱ ልክ ለመስፈር ይተጋል። ስኬቶቹን ቆጥሮ፤ ከፈተናዎቹ ጋር አመሳክሮ ለጊዜው ዋጋ ያወጣለታል።
ይኸው! ሰዓታችን ሁለት አመት ሞላት። ዋጋዋም ውድ ነበር። በራሳቸው እርምጃ የሄዱ ሁለት ውድ አመታት።ከነዋሪዎቻችን ጋር ሆነን ተራምደናቸዋል። አመሰግናችኋለሁ!
ወጣቶችን ልጆችንና ተማሪዎችን ይዘን ተጉዘናል። ነገን ለማለማችን፤ ተስፋን ለመናፈቃችን ምስክሮቻችን እነሱ ናቸው። አቅም ያጡ ወገኖቻችንን ቀርበን ለማዳመጥና ሸክማቸውን ለመጋራት የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። አዳዲስ፣ ግዙፍና የከተማችንን ችግሮች መሰረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን መጀመር፤ መመረቅና ማጋመስ እንዲሁም ማስቀጠል የየእለት ስራችን ነበር። የእነዚህ ስኬቶች አካል በመሆናችንም ደስታችን ወደር የለውም። ሁሉንም አብረናችሁ ከውነናል። አመሰግናለሁ!
አዲስ አበባን መምራት ትልቅ ዕድል ነው። ደጋግመን እንደምንለው፤ “በታሪክ አጋጣሚ ያገኘነውን እድል” ላለማባከን ጥረናል። በሁሉም ውስጥ የነዋሪዎቻችን ብርቱ ድጋፍ አብሮን ነበር። አዲስ አበባን እንደስሟ ለማድረግ በደስታ፤ በፍላጎትና በፍቅር ስንተጋ ምርኩዝ ለሆናችሁን ሁሉ፤ ከልቤ አመሰግናለሁ! በፍጹም ቅንነት ላጎደልናቸው ነገሮችም ይቅርታ እጠይቃለሁ!
የምክር ቤት አባላት፤ የከተማዋ አስተዳደር ሰራተኞች፤ በየደረጃው ለምትገኙ አመራሮች፤ አብሬያችሁ ስለሰራሁ ክብር ይሰማኛል፤ ለነበራችሁ የማይተመን ትጋትም አመሰግናለሁ። ሁሌም እንደምለው አዲስ አበባን የመሰለች ታላቅና ታሪካዊ ከተማ ለመምራት በነበረኝ የሀላፊነት ቆይታ ደስተኛ ነኝ።
ለአዲሱ አመራርና የካቢኔ አባላት መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ።
ታከለ ኡማ በንቲ
12/12/12
አዲስ አበባ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *