ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በአራት ዓመታት ብቻ 23 ጊዜ ደም መለገስ

ደሙን ለሕይወት፣ ሙያውን ለዘርፉ ማዘመኛ የለገሰው ደግ ወጣት።ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የደም ባንክ አገልግሎት ቁሳቁሶችን ጠግኗል፡፡
በአራት ዓመታት ብቻ 23 ጊዜ ደም ለግሷል:: አስቡት አንድ ጊዜ ደም ለመለገስ ያልታደለ ብዙ ነው። 27 ዓመቱ ነው። ድጋፍ የሚፈልጉ፣ የተቸገሩ፣ የታመሙ ሰዎች ባሉባት ዓለም ተስፋውም ሆነ መድሐኒቱ ሌላ ሰው ነው።
የልጁ በጎነት አንዳችን ለሌላችን አስፈላጊ ብቻ ሳንሆን ወሳኝ የመሆናችን ማሳያ መሆኑን ያምናል። የተቸገረ ሲያገኝ፣ የጎደለ ሲሞላለት፣ የታመመ ሲድን ማየት እና ማስቻል የሚሰጠው ስሜት የሰው ልጆች በህይዎት የመኖር ሚስጥር ነው ይላል።
ደም መለገስ ደግሞ ከስጦታዎች ሁሉ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት እንደገና ማስቀጠያ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ በሰዎች ቦታ ራሴን አስገብቼ ስመለከት ለሌሎች እድሜ የሰጠሁ ስለሚመስለኝ ደስ ይለኛል ይላል። በከተሞች እና በሆስፒታሎች በሚስተዋለው የደም እጥረት ምክንያት የሰው ህይወት እንዳይጠፋ በአንድ ደም የሦስት ሰዎችን ህይወት የመታደግ ሥራውን የጀመሩት ከ15 እስከ 20 በመሆን ነው።
ከአራት ዓመታት በፊት የባሕር ዳር ደብረ ሰላም በዓለ እግዜአብሔር የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች ማኀበር የተጀመረው ደግነት በደንበር አልባ የደም ልገሳ የበርካቶችን የደም ፍላጎት እንግልት ጥያቄ እንዳይሆን አድርገዋል።
ለህመምተኞችም ፈጥነው ደርሰው ዕድሜያቸውን ሰጥተው ደግነትን በደማቸው አዋህደዋል። ይህን ተግባር በየሦስት ወሩ እየተከታተሉ ሌሎች ደም ለጋሾችንም እየጋበዙ፣ እያሥተማሩ ማስቀጠል ለእንዳልክ መልካም የሕይወቱ አንድ ተግባር ነው። ለተከታታይ 23 ጊዜ ደም ሲለግስ የሚሰማውን የሰዎች ህይወት መታደግ፣እንግልታቸውን ማስቀረት ዓለምን እንደማበርከት ይሰማዋል።
የሰው ልጅ አቅቶት እንጂ እያለው በንፉግነት፣ በቸልተኝነት ወይም በፍርሀት ህይወትን መታደግ ወይም መርዳት አለመቻል በእጅጉ ያሳዝነዋል። እንዳልክ ደም በመስጠት ብቻ ህይወት መታደጉ ግዴታ እንደመወጣት አድርጎ አያየውም፡፡ ይልቁንም ማዳን የመቻሉን ጸጋ፣ ሰዎችን ማስደሰት የመቻሉ መክሊት እና የእምነቴ አስተምህሮ ግብ ነው ብሎ ያምናል። እንዳልክ በየሦስት ወሩ ወዶት ከሚሰጠው ደም ውጭ የባሕር ዳር ደም ባንክ አገልግሎት ‹‹ለደም ልገሳ ተግባራት እንቅፋት ናቸው›› ያላቸውን ቁሳቁሶችን እየጠገነ ነው።
የጥገና ባለሙያው እንዳልክ የደም ልገሳን ባሕል ከማሳደግ ባሻገር አቅርቦቱ የዘመነ እና ቀልጣፋ እንዲሆን ከወራት በፊት ጀምሮ የደም ባንኩ የተበላሹ ቁሳቁሶችን በመለየት፣ በመጥረግ፣ አስፈላጊ ቁሳቁስ በመግዛትና በመጠገን ሥራ ላይ ነው። አሁንም አልጨረሰም፤ ለበርካታ ዓመታት ተከማችተው የተበላሹት የባሕር ዳር ደም ባንክ አገልግሎት ቁሳቁሶችን እስከ መስከረም 2013 ዓ.ም እንደሚያቆየው ገምቷል።
እንዳልክ አንዳንዴ ኋደኛው ጋር ብዙውን ጊዜ ብቻውን በበጎ ፍቃድ ጥገና ሥራው ሲያሳልፍ በርካታ የግል ሥራዎችን ጊዜ ቢሻማበትም ገንዘብ ከሚያስገኘው የቁስ ስጦታ ይልቅ ገንዘብ የማይገዛው የሰው ህይወት የሚያድን በጎ ተግባር ይቀድምብኛል ብሎ መሆኑን ተናግሯል።
እንዳልክ ከደም ልገሳ ተግባር ጋር በተያያዘ በሙያው የትኛውም ቦታ ሄዶ ለማገዝ ፍቃደኛ መሆኑንም አጫውቶናል። የባሕር ዳር ደም ባንክ አገልግሎት ኃላፊ ምክሩ ሽፈራው እንዳልክ እስከአሁን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶችን መጠገኑን ተናግረዋል። አምስት ደም የሚመዝኑ ማሽኖች፣ ሦስት ደም የሚቆርጥ ማሽን፣ የደም ማቆያ ፍሬጆች፣ የደም አይነትን የሚለይ እና ሌሎች የላቦራቶሪ ማሽኖችን ጠግኗል የሚሉት አቶ ምክሩ የእንዳልክ ተግባር ደም እያለ ይፈጠር የነበረ የመለየት፣ የመቁረጥ፣ የመመዘን እጥረትን አግዟል ብለዋል።
የእንዳልክ ተግባር በርካታ በዘርፉ የተቀጠሩ ባለሙያዎች ያልሠሩት መንግሥትን ከኪሣራና አላስፈላጊ ወጭ ያዳነ፣ ዘርፉን በማዘመን አገልግሎቱ እንዲዘምን ያስቸለ ተግባር መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
አቶ ምክሩ የእንዳልክና መሰል በጎ ፍቃደኛ ተግባሮችን በመጠቀም በ2013 በጀት ዓመት 15 ሺህ ዮኒት ደም ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን ገልጸዋል። ገና ከጅምሩ የሐምሌ ወር እቅድ 179 በመቶ በማሳካታቸው ለ24 ሆስፒታሎች አስፈላጊውን የደም አቅርቦት ጥያቄ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር የደም ባንክ አገልገሎት በ2012 የበጀት ዓመት የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የደም እጥረት እንዳይኖር በዘመቻ ተንቀሳቅሶ 12 ሺሕ የደም ዮኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ 20 ሺሕ ዮኒት ደም ከባሕር ዳር እና አካባቢው ውጭ ተሰብስቧል። ይህም ከእቅዱ 176 በመቶ በመሰብሰብ በኢትዮጵያ ከሚገኙ 40 የደም ባንኮች ቀዳሚው መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
የደም ባንኩ ከተለያዮ አካባቢዎች የሰበሰበውን ደም በክልሉ እጥረት ላለባቸው ጎንደር፣ ፓዌ፣ ሰቆጣ፣ መተማ፣ ወልዲያ እና ደሴ ማዕከላት ድጋፍ አድርጓል። የዘመቻ እንቅስቃሴው የእነእንዳልክ አይነት በጎ አድራጎት ስራ ተጨምሮበት በ2013 በጀት ዓመት ከኮሮናቫይረስ መከላከል የደም ባንኩ እጥረት እንዳይፈጠር እንደሚያግዙ አቶ ምክሩ ተናግረዋል።
እርስዎስ ወዳጅዎ፣ አንዲት ነፍሰጡር እናት ወይም ገና ዘሎ ያልጠገበ ወጣት ድንገት በተፈጠረ የትራፊክ አደጋ ሆስፒታል ገብተው እና በህይዎትና በሞት መካከል ሆነው ለመዳናቸው መላ፤ ለመትረፋቸው ሚስጥር የሚጠቀሙት ደም የእነዚህ በጎ አድራጊዎች ስጦታ መሆኑን ለአፍታ እንኳን አስበውት ያውቃሉ? ወይስ ዛሬም ወገን ያላቸው ህይዎታቸው በደም እጦት ይጥፋ?
ምርጫው በሁለቱ ፅንፎች መካከል የቆመ ነው፡፡
ዘጋቢ:- ግርማ ተጫነ
 (አብመድ)
Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?